የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ሚልክያስ 1:1-4:6
  • ሚልክያስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚልክያስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ሚልክያስ

ሚልክያስ

1 የፍርድ መልእክት፦

በሚልክያስ* በኩል ለእስራኤል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦

2 “እኔ ፍቅር አሳይቻችኋለሁ”+ ይላል ይሖዋ።

እናንተ ግን “ፍቅር ያሳየኸን እንዴት ነው?” አላችሁ።

“ኤሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረም?”+ ይላል ይሖዋ። “እኔ ግን ያዕቆብን ወደድኩ፤ 3 ኤሳውንም ጠላሁ፤+ ተራሮቹን ባድማ አደረግኩ፤+ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮዎች ሰጠሁ።”+

4 “ኤዶም* ‘ተደምስሰናል፤ ሆኖም ተመልሰን የፈራረሱትን ዳግመኛ እንገነባለን’ ቢልም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሱ ይገነባሉ፤ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ ቦታዎቹ “የክፋት ምድር፣” እነሱ ደግሞ “ይሖዋ ለዘላለም ያወገዘው ሕዝብ” ተብለው ይጠራሉ።+ 5 የገዛ ዓይናችሁ ይህን ያያል፤ እናንተም “ይሖዋ በእስራኤል ምድር ከፍ ከፍ ይበል” ትላላችሁ።’”

6 “እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፣+ ‘ልጅ አባቱን፣ አገልጋይም ጌታውን ያከብራል።+ እኔ አባት ከሆንኩ+ ለእኔ የሚገባው ክብር የት አለ?+ ጌታስ* ከሆንኩ መፈራቴ* የት አለ?’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

“‘እናንተ ግን “ስምህን ያቃለልነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።’

7 “‘በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ* በማቅረብ ነው።’

“‘ደግሞም “ያረከስንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ።’

“‘“የይሖዋ ገበታ+ የተናቀ ነው” በማለታችሁ ነው። 8 ዕውሩን እንስሳ መሥዋዕት አድርጋችሁ ስታቀርቡ “ምንም ችግር የለውም” ትላላችሁ። ደግሞም አንካሳ ወይም የታመመ እንስሳ ስታቀርቡ “ምንም ችግር የለውም” ትላላችሁ።’”+

“እነዚህን እንስሳት እስቲ ለገዢህ ለማቅረብ ሞክር። በአንተ ደስ ይለዋል? ወይስ በሞገስ ዓይን ይቀበልሃል?” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

9 “አሁንም እባካችሁ፣ ሞገስ እንዲያሳየን አምላክን ተማጸኑ። እንዲህ ያሉ መባዎች በገዛ እጃችሁ ስታቀርቡ ከእናንተ መካከል የእሱን ሞገስ የሚያገኝ ይኖራል?” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

10 “ከእናንተ መካከል በሮቹን ለመዝጋት ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?*+ በመሠዊያዬ ላይ እሳት ለማንደድ እንኳ ክፍያ ትጠይቃላችሁና።+ በእናንተ ፈጽሞ ደስ አልሰኝም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “ስጦታ አድርጋችሁ በምታቀርቡት በየትኛውም መባ አልደሰትም።”+

11 “ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ* ድረስ ስሜ በብሔራት መካከል ታላቅ ይሆናል።+ በየቦታው ለስሜ የሚጨስ መሥዋዕትና መባ ተቀባይነት ያለው ስጦታ ሆኖ ይቀርባል፤ ምክንያቱም ስሜ በብሔራት መካከል ታላቅ ይሆናል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

12 “እናንተ ግን ‘የይሖዋ ገበታ የረከሰ ነው፤ ፍሬው ይኸውም ምግቡ የተናቀ ነው’ በማለት ታረክሱታላችሁ።*+ 13 በተጨማሪም እናንተ ‘እንዴት አድካሚ ነው!’ ትላላችሁ፤ ደግሞም ትጸየፉታላችሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “የተሰረቀን፣ አንካሳውንና የታመመውን እንስሳ ታመጣላችሁ። አዎ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ስጦታ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ! ታዲያ ይህን ከእጃችሁ ልቀበል ይገባል?”+ ይላል ይሖዋ።

14 “በመንጎቹ መካከል ተባዕት እንስሳ እያለው፣ ስእለት ተስሎ እንከን ያለበትን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሚያታልል የተረገመ ነው። እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “ስሜም በብሔራት መካከል የተፈራ ይሆናል።”+

2 “አሁንም ካህናት ሆይ፣ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።+ 2 ለመስማት አሻፈረኝ ብትሉና ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ በልባችሁ ባታኖሩት” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “በእናንተ ላይ እርግማን እሰዳለሁ፤+ በረከታችሁንም ወደ እርግማን እለውጣለሁ።+ አዎ፣ በልባችሁ ስላላኖራችሁት እያንዳንዱን በረከት ወደ እርግማን ለውጫለሁ።”

3 “እነሆ፣ በእናንተ የተነሳ የዘራችሁትን ዘር አጠፋለሁ፤*+ ፈርሱንም ይኸውም በበዓሎቻችሁ ላይ የምትሠዉአቸውን እንስሳት ፈርስ ፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተንም ወደዚያ* ወስደው ይጥሏችኋል። 4 ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ ከሌዊ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ጸንቶ እንዲኖር መሆኑን ታውቃላችሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

5 “ከእሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እነዚህን በረከቶች በማግኘቱ እኔን ለመፍራት* ተነሳሳ። አዎ፣ ለስሜ ታላቅ አክብሮት አሳየ። 6 የእውነት ሕግ* በአፉ ውስጥ ነበር፤+ በከንፈሮቹም ክፋት አልተገኘም። ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፤+ ብዙዎቹንም ከስህተት ጎዳና መለሰ። 7 ካህኑ ምንጊዜም በከንፈሮቹ ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ ሰዎችም ሕጉን* ከአፉ ሊሹ ይገባል፤+ ምክንያቱም እሱ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ መልእክተኛ ነው።

8 “እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል። ብዙዎች ከሕጉ ጋር በተያያዘ* እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል።+ የሌዊን ቃል ኪዳን አርክሳችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 9 “ስለዚህ በሰዎች ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ እንድትሆኑ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም መንገዶቼን አልጠበቃችሁም፤ ከዚህ ይልቅ ሕጉን ተግባራዊ ስታደርጉ አድልዎ ፈጽማችኋል።”+

10 “የሁላችንም አባት አንድ አይደለም?+ የፈጠረንስ አምላክ አንድ አይደለም? ታዲያ የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማርከስ አንዳችን በሌላው ላይ ክህደት የምንፈጽመው ለምንድን ነው?+ 11 ይሁዳ ክህደት ፈጽሟል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ፣ ይሖዋ የሚወደውን ቅድስናውን* አርክሷልና፤+ ደግሞም የባዕድ አምላክ ሴት ልጅን አግብቷል።+ 12 ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ስጦታ አድርጎ መባ ቢያቀርብም እንኳ ይሖዋ ከያዕቆብ ድንኳኖች ያስወግደዋል።”+

13 “ሌላም የምታደርጉት ነገር አለ፤ ይህም የይሖዋ መሠዊያ በእንባ፣ በለቅሶና በሐዘን እንዲሞላ ምክንያት ሆኗል፤ በመሆኑም ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቧቸውን መባዎች ከእንግዲህ አይቀበልም፤ የምታቀርቡትንም ነገር ሁሉ በሞገስ ዓይን አይመለከትም።+ 14 እናንተም ‘ይህ የሆነው ለምንድን ነው?’ ብላችኋል። ይህ የሆነው ይሖዋ በአንተ ላይ ስለመሠከረብህ ነው፤ ምክንያቱም እሷ አጋርህና የቃል ኪዳን ሚስትህ* ሆና ሳለ በወጣትነት ሚስትህ ላይ ክህደት ፈጽመሃል።+ 15 ሆኖም እንዲህ ያላደረገ አለ፤ እሱ በተወሰነ መጠን የአምላክ መንፈስ ነበረው። ፍላጎቱስ ምን ነበር? የአምላክ ዘር ነበር። በመሆኑም መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ በወጣትነት ሚስታችሁም ላይ ክህደት አትፈጽሙ። 16 እኔ ፍቺን እጠላለሁና”*+ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም* እጠላለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ክህደትም አትፈጽሙ።+

17 “ይሖዋን በቃላችሁ አታክታችሁታል።+ እናንተ ግን ‘ያታከትነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። ‘ክፉ ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በይሖዋ ዓይን ጥሩ ነው፤ እሱ እንዲህ ባለ ሰው ደስ ይሰኛል’+ ወይም ‘የፍትሕ አምላክ የት አለ?’ በማለታችሁ ነው።”

3 “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ እሱም በፊቴ መንገድ ይጠርጋል።*+ እናንተ የምትፈልጉት እውነተኛው ጌታ* በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤+ ደስ የምትሰኙበት የቃል ኪዳኑ መልእክተኛም ይመጣል። እነሆ፣ እሱ በእርግጥ ይመጣል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

2 “ይሁንና እሱ የሚመጣበትን ቀን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው? እሱ በሚገለጥበት ጊዜስ ማን ሊቆም ይችላል? እሱ እንደ አንጥረኛ እሳት፣ እንደ ልብስ አጣቢም እንዶድ* ይሆናልና።+ 3 ደግሞም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤+ የሌዊንም ልጆች ያነጻል፤* እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያጠራቸዋል፤ ይሖዋም በጽድቅ መባ የሚያቀርብ ሕዝብ ይኖረዋል። 4 ይሁዳና ኢየሩሳሌም ስጦታ አድርገው የሚያቀርቡት መባ በቀድሞው ጊዜና በጥንት ዘመን እንደነበረው ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል።*+

5 “ለመፍረድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞቹ፣+ በአመንዝሮቹ፣ በሐሰት በሚምሉት ሰዎች+ እንዲሁም ቅጥር ሠራተኛውን፣+ መበለቲቱንና አባት የሌለውን ልጅ* በሚያጭበረብሩትና+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ በማይሆኑት* ላይ ወዲያውኑ እመሠክርባቸዋለሁ።+ እነዚህ ሰዎች እኔን አልፈሩም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

6 “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም።*+ እናንተም የያዕቆብ ልጆች ናችሁ፤ ገና አልጠፋችሁም። 7 ከአባቶቻችሁ ዘመን አንስቶ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ ደግሞም ሥርዓቴን አልጠበቃችሁም።+ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

እናንተ ግን “የምንመለሰው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።

8 “በውኑ ተራ ሰው አምላክን ይሰርቃል? እናንተ ግን እኔን ትሰርቁኛላችሁ።”

እናንተም “የሰረቅንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ።

“በምትሰጡት አሥራትና* መዋጮ ነው። 9 እናንተ በእርግጥ የተረገማችሁ ናችሁ፤* ትሰርቁኛላችሁና፤ አዎ፣ መላው ብሔር እንዲህ ያደርጋል። 10 በቤቴ ውስጥ እህል እንዲኖር አሥራቱን* ሁሉ ወደ ጎተራው አስገቡ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ+ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣*+ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።”

11 “ለእናንተም ስል፣ በላተኛውን* እገሥጻለሁ፤ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ላይ ያለው የወይን ተክልም ፍሬ አልባ አይሆንም”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

12 “እናንተ የደስታ ምድር ስለምትሆኑ ብሔራት ሁሉ ደስተኞች ብለው ይጠሯችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

13 “በእኔ ላይ ኃይለ ቃል ተናግራችኋል” ይላል ይሖዋ።

እናንተም “በአንተ ላይ የተናገርነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።+

14 “እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አምላክን ማገልገል ዋጋ የለውም።+ ለእሱ ያለብንን ግዴታ በመጠበቃችንና በኃጢአታችን የተነሳ ማዘናችንን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ፊት በማሳየታችን ምን ተጠቀምን? 15 አሁን እብሪተኛ የሆኑ ሰዎችን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ደግሞም ክፉ አድራጊዎች ስኬታማ ሆነዋል።+ እነሱ በድፍረት አምላክን ይፈታተናሉ፤ ከቅጣትም ያመልጣሉ።’”

16 በዚያ ጊዜ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ተነጋገሩ፤ ይሖዋም በትኩረት አዳመጠ፤ ደግሞም ሰማ። ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ*+ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።+

17 “የእኔ ልዩ ንብረት*+ በማደርጋቸውም ቀን እነሱ የእኔ ይሆናሉ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “አባት ለሚታዘዝለት ልጁ እንደሚራራ እኔም እራራላቸዋለሁ።+ 18 እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”+

4 “እነሆ፣ ያ ቀን እንደ ምድጃ እየነደደ ይመጣል፤+ በዚያ ጊዜ እብሪተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ እንደ ገለባ ይሆናሉ። የሚመጣው ቀን በእርግጥ ይበላቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አይተውላቸውም። 2 ስሜን ለምታከብሩት* ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሐይ በጨረሮቿ* ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም እንደሰቡ ጥጆች ትቦርቃላችሁ።”

3 “እኔም እርምጃ በምወስድበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ሥር እንዳለ አቧራ ይሆናሉና” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

4 “የአገልጋዬን የሙሴን ሕግ ይኸውም መላው እስራኤል እንዲያከብረው በኮሬብ ያዘዝኩትን ሥርዓትና ድንጋጌ አስታውሱ።+

5 “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት+ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ።+ 6 እሱም መጥቼ ምድርን እንዳልመታና ፈጽሜ እንዳላጠፋ የአባቶችን ልብ እንደ ልጆች ልብ፣+ የልጆችንም ልብ እንደ አባቶች ልብ ያደርጋል።”*

(የዕብራይስጥና የአረማይክ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም እዚህ ላይ ተደመደመ፤ ከዚህ በኋላ ያሉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ናቸው)

“መልእክተኛዬ” የሚል ትርጉም አለው።

ዘፍ 25:30 እና ዘፍ 36:1 ላይ በተገለጸው መሠረት ኤዶም የኤሳው ሁለተኛ ስም ነው።

ወይም “ታላቅ ጌታስ።”

ወይም “መከበሬ።”

ቃል በቃል “ዳቦ።”

ኃላፊነት ወስዶ የቤተ መቅደሱን በሮች ለመዝጋት ፈቃደኛ መሆንን ያመለክታል።

ወይም “ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ።”

“እኔን ታረክሳላችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እገሥጻለሁ።”

የመሥዋዕቶቹ ፈርስ የተጣለበትን ቦታ የሚያመለክት ነው።

ወይም “ለማክበር፤ ለእኔ አምልኮታዊ ክብር ለመስጠት።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”

“በመመሪያችሁ፤ በትምህርታችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“መቅደሱን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ሕጋዊ ሚስትህ።”

ቃል በቃል “እሱ ፍቺን ይጠላልና።”

ወይም “ግፍ የሚፈጽመውንም።”

ወይም “ያዘጋጃል።”

የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ያመለክታል።

ወይም “ሳሙና።”

ወይም “ያነጥራል።”

ወይም “ለይሖዋ እርካታ ያስገኝለታል።”

ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”

ወይም “የባዕዱን መብት በሚነፍጉት።”

ወይም “አልተለወጥኩም።”

ወይም “አንድ አሥረኛና።”

“በእርግማን ትረግሙኛላችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “አንድ አሥረኛውን።”

ቃል በቃል “ባልገለብጥላችሁ።”

ተባይ የሚያስከትለውን መቅሰፍት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “ስሙን ለሚያስቡ።” “ስሙን ከፍ አድርገው ለሚመለከቱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ውድ ንብረት።”

ቃል በቃል “ለምትፈሩት።”

ቃል በቃል “በክንፎቿ።”

ወይም “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ