የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ማቴዎስ 1:1-28:20
  • ማቴዎስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማቴዎስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ማቴዎስ

የማቴዎስ ወንጌል

1 የዳዊት ልጅ፣+ የአብርሃም ልጅ+ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን* ታሪክ* የያዘ መጽሐፍ፦

 2 አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤+

ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤+

ያዕቆብ ይሁዳንና+ ወንድሞቹን ወለደ፤

 3 ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን+ ወለደ፤

ፋሬስ ኤስሮንን ወለደ፤+

ኤስሮን ራምን ወለደ፤+

 4 ራም አሚናዳብን ወለደ፤

አሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤+

ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤

 5 ሰልሞን ከረዓብ+ ቦዔዝን ወለደ፤

ቦዔዝ ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤+

ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤+

 6 እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ።+

ዳዊት ከኦርዮ ሚስት ሰለሞንን ወለደ፤+

 7 ሰለሞን ሮብዓምን ወለደ፤+

ሮብዓም አቢያህን ወለደ፤

አቢያህ አሳን ወለደ፤+

 8 አሳ ኢዮሳፍጥን ወለደ፤+

ኢዮሳፍጥ ኢዮራምን ወለደ፤+

ኢዮራም ዖዝያን ወለደ፤

 9 ዖዝያ ኢዮዓታምን ወለደ፤+

ኢዮዓታም አካዝን ወለደ፤+

አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤+

10 ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤+

ምናሴ አምዖንን ወለደ፤+

አምዖን ኢዮስያስን ወለደ፤+

11 ኢዮስያስ+ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በተጋዙበት ዘመን+ ኢኮንያንን+ እና ወንድሞቹን ወለደ።

12 ወደ ባቢሎን ከተጋዙ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤

ሰላትያል ዘሩባቤልን ወለደ፤+

13 ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤

አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤

ኤልያቄም አዞርን ወለደ፤

14 አዞር ሳዶቅን ወለደ፤

ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤

አኪም ኤልዩድን ወለደ፤

15 ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤

አልዓዛር ማታንን ወለደ፤

ማታን ያዕቆብን ወለደ፤

16 ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ፤ ዮሴፍም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደችው የማርያም ባል ነበር።+

17 ስለዚህ ጠቅላላው ትውልድ፣ ከአብርሃም እስከ ዳዊት 14 ትውልድ፣ ከዳዊት አንስቶ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን እስከተጋዙበት ጊዜ ድረስ 14 ትውልድ እንዲሁም ወደ ባቢሎን ከተጋዙበት ዘመን እስከ ክርስቶስ ድረስ 14 ትውልድ ነው።

18 ይሁንና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንደሚከተለው ነው፦ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ በነበረበት ጊዜ፣ አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት በመንፈስ ቅዱስ* ፀንሳ ተገኘች።+ 19 ይሁን እንጂ ባሏ* ዮሴፍ ጻድቅ ስለሆነና በይፋ ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊፈታት አሰበ።+ 20 ሆኖም ይህን ለማድረግ አስቦ ሳለ የይሖዋ* መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፣ ሚስትህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ+ እሷን ወደ ቤት ለመውሰድ አትፍራ። 21 ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እሱንም ኢየሱስ* ብለህ ትጠራዋለህ፤+ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና።”+ 22 ይህ ሁሉ የሆነው ይሖዋ* በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 23 “እነሆ! ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል+ ይሉታል”፤ ትርጉሙም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው”+ ማለት ነው።

24 ከዚያም ዮሴፍ ከእንቅልፉ ነቃ፤ የይሖዋ* መልአክ ባዘዘውም መሠረት ሚስቱን ወደ ቤቱ ወሰዳት። 25 ሆኖም ልጁን እስክትወልድ ድረስ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም፤+ ልጁንም ኢየሱስ ብሎ ጠራው።+

2 በንጉሥ ሄሮድስ* ዘመን+ ኢየሱስ በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም+ ከተወለደ በኋላ ኮከብ ቆጣሪዎች* ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ 2 “የተወለደው የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚገኘው የት ነው?+ በምሥራቅ ሳለን ኮከቡን በማየታችን ልንሰግድለት* መጥተናል” አሉ። 3 ንጉሥ ሄሮድስና መላው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ይህን ሲሰሙ ተሸበሩ። 4 ንጉሡም የሕዝቡን የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በሙሉ ሰብስቦ ክርስቶስ* የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 5 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም+ ነው፤ ምክንያቱም ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ 6 ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተልሔም ሆይ፣ ለሕዝቤ ለእስራኤል እረኛ የሚሆን ገዢ ከአንቺ ስለሚወጣ በይሁዳ ገዢዎች ዘንድ ከሁሉ የተናቅሽ ከተማ አትሆኚም።’”+

7 ከዚያም ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹን በድብቅ ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ጊዜ በትክክል አረጋገጠ። 8 ኮከብ ቆጣሪዎቹንም “ሄዳችሁ ሕፃኑን በደንብ ፈልጉ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም ሄጄ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ” ብሎ ወደ ቤተልሔም ላካቸው። 9 እነሱም ንጉሡ የነገራቸውን ከሰሙ በኋላ ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ እነሆም፣ በምሥራቅ ሳሉ ያዩት ኮከብ+ ሕፃኑ ባለበት ቦታ እስከቆመበት ጊዜ ድረስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር። 10 ኮከቡ መቆሙን ሲያዩ በጣም ተደሰቱ። 11 ወደ ቤት ሲገቡም ልጁን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት።* ዕቃ መያዣቸውንም ከፍተው ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ በስጦታ መልክ አቀረቡለት። 12 ይሁንና ወደ ሄሮድስ ተመልሰው እንዳይሄዱ በሕልም መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው+ በሌላ መንገድ አድርገው ወደ አገራቸው ሄዱ።

13 እነሱ ከሄዱ በኋላ የይሖዋ* መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ+ “ሄሮድስ ሕፃኑን አፈላልጎ ሊገድለው ስላሰበ ተነስ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እኔ እስካሳውቅህም ድረስ እዚያው ቆይ” አለው። 14 ስለዚህ ዮሴፍ ተነሳ፤ ሕፃኑንና የሕፃኑን እናት ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ሄደ። 15 ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ እዚያው ቆየ። በመሆኑም ይሖዋ* “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት”+ ብሎ በነቢዩ አማካኝነት የተናገረው ቃል ተፈጸመ።

16 ከዚያም ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹ እንዳታለሉት ሲያውቅ በጣም ተናደደ፤ ኮከቡ የታየበትን ጊዜ በተመለከተ ከኮከብ ቆጣሪዎቹ ባገኘው መረጃ መሠረት+ ሰዎች ልኮ በቤተልሔምና በአካባቢዋ ሁሉ የሚገኙትን ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑትን ወንዶች ልጆች በሙሉ አስገደለ። 17 በዚህ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው የሚከተለው ቃል ተፈጸመ፦ 18 “የለቅሶና የዋይታ ድምፅ በራማ ተሰማ። ራሔል+ ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ ልጆቿ ስለሌሉ ልትጽናና አልቻለችም።”+

19 ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የይሖዋ* መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ+ 20 “ተነስ፣ የሕፃኑን ሕይወት* ለማጥፋት የሚፈልጉት ሰዎች ስለሞቱ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ” አለው። 21 ዮሴፍም ተነሳ፤ ሕፃኑንና የሕፃኑን እናት ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ። 22 ሆኖም አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፋንታ ይሁዳን እየገዛ እንዳለ በመስማቱ ወደዚያ መሄድ ፈራ። በተጨማሪም በሕልም መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጠው+ ወደ ገሊላ+ ምድር ሄደ። 23 ደግሞም “የናዝሬት ሰው* ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው+ ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት+ ወደምትባል ከተማ መጥቶ መኖር ጀመረ።

3 በዚያ ወቅት መጥምቁ ዮሐንስ+ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ፤+ 2 “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” ይል ነበር።+ 3 “አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን* መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናዎቹንም አቅኑ’+ በማለት ይጮኻል” ተብሎ በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረለት እሱ ነው።+ 4 ዮሐንስ ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ ነበር።+ ምግቡ አንበጣና የዱር ማር ነበር።+ 5 በኢየሩሳሌምና በመላዋ ይሁዳ እንዲሁም በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው ክልል ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤+ 6 ደግሞም ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ* ነበር።+

7 ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን+ ወደሚያጠምቅበት ቦታ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣+ ከሚመጣው ቁጣ+ እንድትሸሹ ያስጠነቀቃችሁ ማን ነው? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ። 9 ‘እኛ እኮ አባታችን አብርሃም ነው’ ብላችሁ አታስቡ።+ አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ሊያስነሳለት እንደሚችል ልነግራችሁ እወዳለሁ። 10 መጥረቢያው ዛፎቹ ሥር ተቀምጧል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ እሳት ውስጥ ይጣላል።+ 11 እኔ በበኩሌ ንስሐ በመግባታችሁ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤+ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ ብቁ አይደለሁም።+ እሱ በመንፈስ ቅዱስና+ በእሳት+ ያጠምቃችኋል። 12 ላይዳውን* በእጁ ይዟል፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጸዳል፤ ስንዴውንም ወደ ጎተራ ያስገባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”+

13 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።+ 14 ዮሐንስ ግን “በአንተ መጠመቅ የሚያስፈልገኝ እኔ ሆኜ ሳለ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ሊከለክለው ሞከረ። 15 ኢየሱስም መልሶ “ግድ የለም እሺ በለኝ፤ በዚህ መንገድ ጽድቅ የሆነውን ሁሉ መፈጸማችን ተገቢ ነው” አለው። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ፈቀደለት። 16 ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤+ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ።+ 17 ደግሞም “በጣም የምደሰትበት+ የምወደው ልጄ ይህ ነው”+ የሚል ድምፅ ከሰማያት ተሰማ።+

4 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ+ ይፈትነው+ ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው። 2 እሱም 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። 3 ፈታኙም+ ቀርቦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። 4 እሱ ግን “‘ሰው ከይሖዋ* አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰ።+

5 ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ+ ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት* ላይ አቁሞ+ 6 እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’”+ 7 ኢየሱስም “‘አምላክህን ይሖዋን* አትፈታተነው’ ተብሎም ተጽፏል” አለው።+

8 እንደገናም ዲያብሎስ በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።+ 9 ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። 10 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ* አምላክህን ብቻ አምልክ፤+ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’+ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። 11 ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤+ እነሆም፣ መላእክት መጥተው ያገለግሉት ጀመር።+

12 ኢየሱስ፣ ዮሐንስ እንደታሰረ+ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ።+ 13 ከዚያም ከናዝሬት ወጥቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃዎች፣ በባሕሩ* አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም+ መጥቶ መኖር ጀመረ፤ 14 ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው የሚከተለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 15 “ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ወደ ባሕሩ* በሚወስደው መንገድ አጠገብ ያላችሁ የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድርና የአሕዛብ ገሊላ ሆይ! 16 በጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ታላቅ ብርሃን አዩ፤ ሞት በሰዎች ላይ ባጠላበት ምድር ላሉም ብርሃን+ ወጣላቸው።”+ 17 ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ ይሰብክ ጀመር።+

18 በገሊላ ባሕር* አጠገብ ሲሄድ ሁለቱን ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን+ እና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው፤ እነሱም ዓሣ አጥማጆች+ ስለነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕሩ እየጣሉ ነበር። 19 እሱም “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+ 20 እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+ 21 ከዚያ እልፍ እንዳለ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾችን ማለትም የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አያቸው።+ እነሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረቦቻቸውን እየጠገኑ ነበር፤ ኢየሱስም ጠራቸው።+ 22 እነሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

23 ከዚያም በምኩራቦቻቸው+ እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ+ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+ 24 ስለ እሱም የተወራው ወሬ በመላዋ ሶርያ ተዳረሰ፤ ሰዎችም በተለያየ በሽታና ከባድ ሕመም የሚሠቃዩትን፣+ ጋኔን የያዛቸውን፣+ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና+ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። 25 ከዚህም የተነሳ ከገሊላ፣ ከዲካፖሊስ፣* ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።

5 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ። 2 ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦

3 “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ* ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።

4 “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።+

5 “ገሮች*+ ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።+

6 “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤+ ይጠግባሉና።*+

7 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤+ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።

8 “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤+ አምላክን ያያሉና።

9 “ሰላም ፈጣሪዎች* ደስተኞች ናቸው፤+ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።

10 “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።

11 “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣+ ስደት ሲያደርሱባችሁና+ ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።+ 12 በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ+ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤+ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።+

13 “እናንተ የምድር ጨው+ ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ+ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።

14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ።+ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። 15 ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ* አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል።+ 16 በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን+ አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ+ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።+

17 “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም።+ 18 እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።+ 19 በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ* ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ* ይባላል። 20 ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ+ ልነግራችሁ እወዳለሁ።

21 “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤+ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት+ ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት* ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም* ሊዳረግ ይችላል።+

23 “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ+ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ 24 መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።+

25 “ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ።+ 26 እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን* ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም።

27 “‘አታመንዝር’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 28 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት+ ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።+ 29 ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+ 30 እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+

31 “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’+ ተብሏል። 32 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።+

33 “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤+ ይልቁንም ለይሖዋ* የተሳልከውን ፈጽም’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ።+ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤ 35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤+ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና።+ 36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና። 37 ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤+ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው+ ነው።

38 “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 39 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።+ 40 አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤+ 41 እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር* እንድትሄድ ቢያስገድድህ* ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው* ፊት አትንሳው።+

43 “‘ባልንጀራህን ውደድ፤+ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 44 እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ+ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤+ 45 ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤+ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።+ 46 የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?+ ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 47 ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 48 በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም* እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።+

6 “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ+ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም። 2 በመሆኑም ምጽዋት* በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 3 አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤ 4 ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ያስችላል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።+

5 “በተጨማሪም በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤+ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው+ በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 6 አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ።+ በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል። 7 በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል። 8 ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።+

9 “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦+

“‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ+ ይቀደስ።*+ 10 መንግሥትህ+ ይምጣ። ፈቃድህ+ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።*+ 11 የዕለቱን ምግባችንን* ዛሬ ስጠን፤+ 12 የበደሉንን* ይቅር እንዳልን በደላችንን* ይቅር በለን።+ 13 ከክፉው+ አድነን* እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’+

14 “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤+ 15 እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።+

16 “በምትጾሙበት+ ጊዜ እንደ ግብዞች ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነሱ መጾማቸው በሰው ዘንድ እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን ያጠወልጋሉ።*+ እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 17 አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ፤ 18 እንዲህ ካደረግክ የምትጾመው በሰው ለመታየት ሳይሆን በስውር ላለው አባትህ ስትል ብቻ ይሆናል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።

19 “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።*+ 20 ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና+ ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።+ 21 ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና።

22 “የሰውነት መብራት ዓይን ነው።+ ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ* ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ* ይሆናል። 23 ይሁን እንጂ ዓይንህ ምቀኛ*+ ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን!

24 “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል+ ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።+

25 “ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለ ሕይወታችሁ* ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ+ አትጨነቁ።*+ ሕይወት* ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥም?+ 26 የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤+ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም? 27 ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ* መጨመር የሚችል ይኖራል?+ 28 ስለ ልብስስ ቢሆን ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ 29 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን+ እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። 30 አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? 31 ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’+ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ።+ 32 እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።

33 “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤* እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።+ 34 ስለዚህ ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤+ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።

7 “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤*+ 2 በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል።+ 3 ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?+ 4 ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? 5 አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።

6 “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ።+ አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።

7 “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤+ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።+ 8 የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤+ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል። 9 ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? 10 ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? 11 ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት+ መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!+

12 “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።+ ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።+

13 “በጠባቡ በር ግቡ፤+ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ 14 ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።+

15 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች+ ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው+ ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።+ 16 ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?+ 17 በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።+ 18 ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።+ 19 መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል።+ 20 በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።+

21 “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።+ 22 በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣+ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’+ 23 እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።+

24 “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል።+ 25 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም። 26 ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።+ 27 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤+ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”

28 ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤+ 29 የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።+

8 ከተራራው ከወረደ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2 በዚህ ጊዜ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ* “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።+ 3 ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው።+ ወዲያውኑ ከሥጋ ደዌው ነጻ።+ 4 ከዚያም ኢየሱስ “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤+ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤+ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ።+ ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ” አለው።

5 ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የጦር መኮንን ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ ሲል ተማጸነው፦+ 6 “ጌታዬ፣ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ ቤት ተኝቷል፤ በጣም እየተሠቃየ ነው።” 7 እሱም “መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። 8 መኮንኑም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ፣ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፣ አገልጋዬም ይፈወሳል። 9 እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 10 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት+ ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም። 11 ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማያትም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በማዕድ ይቀመጣሉ።+ 12 የመንግሥተ ሰማያት ልጆች ግን ውጭ ወዳለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።”+ 13 ከዚያም ኢየሱስ መኮንኑን “ሂድ። እንደ እምነትህ ይሁንልህ”+ አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።+

14 ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ሲመጣ የጴጥሮስ አማት+ ትኩሳት ይዟት ተኝታ አገኛት።+ 15 እጇንም ሲዳስሳት+ ትኩሳቱ ለቀቃት፤ ተነስታም ታገለግለው ጀመር። 16 ከመሸ በኋላ ሰዎች አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙ ሰዎች ወደ እሱ አመጡ፤ መናፍስቱንም በአንድ ቃል አስወጣ፤ እየተሠቃዩ የነበሩትንም ሁሉ ፈወሰ፤ 17 ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ “እሱ ሕመማችንን ተቀበለ፤ ደዌያችንንም ተሸከመ” ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።+

18 ኢየሱስ በዙሪያው ብዙ ሰዎች እንደተሰበሰቡ ባየ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው።+ 19 ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።+ 20 ኢየሱስ ግን “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” አለው።+ 21 ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።+ 22 ኢየሱስም “አንተ እኔን መከተልህን ቀጥል፤ ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው” አለው።+

23 ከዚያም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ላይ ተሳፈሩ።+ 24 እነሆ፣ በጉዞ ላይ ሳሉ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ስለተነሳ ጀልባዋ በውኃ ተሞልታ ልትሰጥም ተቃረበች፤ ኢየሱስ ግን ተኝቶ ነበር።+ 25 እነሱም ወደ እሱ ቀርበው ቀሰቀሱትና “ጌታ ሆይ፣ ማለቃችን እኮ ነው፤ አድነን!” አሉት። 26 እሱ ግን “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?”* አላቸው።+ ከዚያም ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።+ 27 ሰዎቹም ተደንቀው “ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” አሉ።

28 ባሕሩን ተሻግሮ ገዳሬኖስ* ወደተባለው ክልል በደረሰ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው ከእሱ ጋር ተገናኙ።+ ሰዎቹ በጣም ኃይለኛ ከመሆናቸው የተነሳ ማንም ሰው በዚያ ለማለፍ አይደፍርም ነበር። 29 እነሱም “የአምላክ ልጅ ሆይ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን?+ የመጣኸው ጊዜው ሳይደርስ+ ልታሠቃየን ነው?”+ ብለው ጮኹ። 30 ከእነሱ ራቅ ብሎ ብዙ የአሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።+ 31 አጋንንቱም “የምታስወጣን ከሆነ ወደ አሳማው መንጋ ስደደን” ብለው ይማጸኑት ጀመር።+ 32 እሱም “ሂዱ!” አላቸው። እነሱም ወጥተው ወደ አሳማዎቹ ሄዱ፤ የአሳማውም መንጋ በሙሉ ከገደሉ አፋፍ* እየተንደረደረ በመውረድ ባሕሩ ውስጥ ሰጥሞ አለቀ። 33 እረኞቹ ግን ሸሽተው ወደ ከተማው በመሄድ አጋንንት ባደሩባቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጨምሮ የሆነውን ነገር ሁሉ አወሩ። 34 ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ለማግኘት ወጣ፤ ሰዎቹም ባዩት ጊዜ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ለመኑት።+

9 ከዚህ በኋላ ጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ* መጣ።+ 2 በዚያም ሰዎች ቃሬዛ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ሰው ወደ እሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ ሽባውን “ልጄ ሆይ አይዞህ! ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+ 3 በዚህ ጊዜ አንዳንድ ጸሐፍት በልባቸው “ይህ ሰው እኮ አምላክን እየተዳፈረ ነው” አሉ። 4 ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ፦ “በልባችሁ ክፉ ነገር የምታስቡት ለምንድን ነው?+ 5 ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነስተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?+ 6 ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” አላቸውና ሽባውን “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።+ 7 እሱም ተነስቶ ወደ ቤቱ ሄደ። 8 ሕዝቡም ይህን ሲያዩ በፍርሃት ተዋጡ፤ እንዲህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውንም አምላክ አከበሩ።

9 ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ እየሄደ ሳለ ማቴዎስ የሚባል ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው።+ 10 በኋላም በማቴዎስ ቤት እየበላ ሳለ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይበሉ ጀመር።+ 11 ፈሪሳውያን ግን ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው ለምንድን ነው?” አሏቸው።+ 12 ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።+ 13 እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’+ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነውና።”

14 ከዚያም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እሱ መጥተው “እኛና ፈሪሳውያን ዘወትር ስንጾም የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።+ 15 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሙሽራው ጓደኞች ሙሽራው ከእነሱ ጋር እስካለ ድረስ የሚያዝኑበት ምን ምክንያት አለ?+ ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤+ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 16 በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ ልብሱን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋልና።+ 17 ደግሞም ሰዎች ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አያስቀምጡም። እንዲህ ቢያደርጉ አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን ሰዎች አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጡት በአዲስ አቁማዳ ነው፤ በመሆኑም ሁለቱም ሳይበላሹ ይቆያሉ።”

18 ይህን እየነገራቸው ሳለ አንድ የምኩራብ አለቃ ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ* “እስካሁን ልጄ ሳትሞት አትቀርም፤ ቢሆንም መጥተህ እጅህን ጫንባት፤ ዳግመኛም ሕያው ትሆናለች”+ አለው።

19 ኢየሱስም ተነስቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። 20 እነሆም፣ ለ12 ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች አንዲት ሴት+ ከኋላ መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤+ 21 “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበርና። 22 ኢየሱስ ወደ ኋላ ዞር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ አይዞሽ! እምነትሽ አድኖሻል” አላት።+ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ሴትየዋ ዳነች።+

23 ኢየሱስ ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት ሲደርስ ዋሽንት ነፊዎቹን እንዲሁም የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ+ 24 “እስቲ አንዴ ውጡ፤ ልጅቷ ተኝታለች+ እንጂ አልሞተችም” አለ። በዚህ ጊዜ በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። 25 ሕዝቡ ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዛት፤+ ልጅቷም ተነሳች።+ 26 ይህም ነገር በዚያ አገር ሁሉ በሰፊው ተወራ።

27 ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች+ “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልን” ብለው እየጮኹ ተከተሉት። 28 ወደ ቤት ከገባ በኋላ ዓይነ ስውሮቹ ወደ እሱ መጡ፤ ኢየሱስም “ዓይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።+ እነሱም “አዎ ጌታ ሆይ” ብለው መለሱለት። 29 ከዚያም ዓይናቸውን ዳስሶ+ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። 30 ዓይናቸውም በራ። ኢየሱስም “ማንም ሰው ስለዚህ ጉዳይ እንዳያውቅ ተጠንቀቁ” ሲል አጥብቆ አሳሰባቸው።+ 31 እነሱ ግን ከወጡ በኋላ በዚያ አካባቢ ሁሉ ስለ እሱ በይፋ አወሩ።

32 እነሱም ሲወጡ፣ ሰዎች ጋኔን ያደረበት ዱዳ ሰው ወደ እሱ አመጡ፤+ 33 ጋኔኑን ካስወጣለት በኋላ ዱዳው ተናገረ።+ ሕዝቡም እጅግ ተደንቀው “በእስራኤል ምድር እንዲህ ያለ ነገር ታይቶ አያውቅም” አሉ።+ 34 ፈሪሳውያን ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር።+

35 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ይዞር ጀመር።+ 36 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች+ ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።+ 37 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው።+ 38 ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”+

10 ከዚያም ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙ ሥልጣን ሰጣቸው፤+ ይህን ያደረገውም ርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጡ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እንዲፈውሱ ነው።

2 የ12ቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦+ በመጀመሪያ፣ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና+ ወንድሙ እንድርያስ፣+ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣+ 3 ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፣+ ቶማስና+ ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣+ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፣ 4 ቀነናዊው* ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን የከዳው የአስቆሮቱ ይሁዳ።+

5 ኢየሱስ እነዚህን 12ቱን የሚከተለውን መመሪያ በመስጠት ላካቸው፦+ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ማንኛውም የሳምራውያን ከተማም+ አትግቡ፤ 6 ከዚህ ይልቅ ከእስራኤል ቤት ወደጠፉት በጎች ብቻ ሂዱ።+ 7 በምትሄዱበት ጊዜም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ።+ 8 የታመሙትን ፈውሱ፤+ የሞቱትን አስነሱ፤ የሥጋ ደዌ ያለባቸውን አንጹ፤ አጋንንትንም አስወጡ። በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ። 9 ወርቅ ወይም ብር አሊያም መዳብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤+ 10 ወይም ለጉዞ የምግብ ከረጢት ወይም ሁለት ልብስ* ወይም ትርፍ ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤+ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።+

11 “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ፤ እስክትወጡም ድረስ እዚያው ቆዩ።+ 12 ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ። 13 ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤+ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። 14 የሚቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የሚሰማ ሰው ካጣችሁ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ፣ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።*+ 15 እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ+ ይቀልላቸዋል።

16 “እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።+ 17 ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራቦቻቸውም+ ይገርፏችኋል፤+ ስለዚህ ራሳችሁን ከእነሱ ጠብቁ። 18 ደግሞም በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤+ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 19 ይሁን እንጂ አሳልፈው ሲሰጧችሁ እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤+ 20 በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።+ 21 በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 22 በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤+ እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 23 በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ፤+ እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች ፈጽሞ አታዳርሱም።

24 “ተማሪ* ከአስተማሪው፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።+ 25 ተማሪ እንደ አስተማሪው፣ ባሪያም እንደ ጌታው ከሆነ በቂ ነው።+ ሰዎች የቤቱን ጌታ ብዔልዜቡል*+ ካሉት ቤተሰቦቹንማ እንዴት ከዚህ የከፋ አይሏቸው! 26 ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ ሁሉ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም ሁሉ መታወቁ አይቀርም።+ 27 በጨለማ የነገርኳችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በይፋ ስበኩ።+ 28 ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን* ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤+ ከዚህ ይልቅ ነፍስንም ሆነ ሥጋን በገሃነም* ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።+ 29 ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም* አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም።+ 30 የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። 31 ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።+

32 “እንግዲያው በሰዎች ፊት ለሚመሠክርልኝ+ ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሠክርለታለሁ።+ 33 በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።+ 34 በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።+ 35 እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ምራትን ከአማቷ ለመለያየት ነው።+ 36 በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ። 37 ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።+ 38 የመከራውን እንጨት* የማይቀበልና የማይከተለኝ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።+ 39 ነፍሱን* ለማዳን የሚሞክር ሁሉ ያጣታል፤ ነፍሱን* ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ግን ያገኛታል።+

40 “እናንተን የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ሁሉ ደግሞ የላከኝን ይቀበላል።+ 41 ነቢይን ስለ ነቢይነቱ የሚቀበል ሁሉ የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤+ ጻድቅን ስለ ጻድቅነቱ የሚቀበል ሁሉ የጻድቅን ዋጋ ያገኛል። 42 እውነት እላችኋለሁ፣ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ምክንያት ከእነዚህ ከትናንሾቹ ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ የሚሰጥ ሁሉ በምንም ዓይነት ዋጋውን አያጣም።”+

11 ኢየሱስ ለ12 ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ።+

2 ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ+ ክርስቶስ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲሰማ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ+ 3 “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀው።+ 4 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፤+ 5 ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤+ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤+ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።+ 6 በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”+

7 መልእክተኞቹ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር?+ ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?+ 8 ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ* የለበሰ ሰው ለማየት? ምርጥ ልብስ የለበሱማ የሚገኙት በነገሥታት ቤት ነው። 9 ታዲያ ለምን ሄዳችሁ? ነቢይ ለማየት? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።+ 10 ‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ!’+ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው። 11 እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።+ 12 መንግሥተ ሰማያት ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰዎች የሚጋደሉለት ግብ ሆኗል፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ያገኙታል።+ 13 ነቢያትና ሕጉ በሙሉ እስከ ዮሐንስ ዘመን ድረስ ተንብየዋልና፤+ 14 እንግዲህ ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆናችሁ ‘ይመጣል የተባለው ኤልያስ’ እሱ ነው።+ 15 ጆሮ ያለው ይስማ።

16 “ይህን ትውልድ ከማን ጋር ላመሳስለው?+ በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ 17 ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’ 18 በተመሳሳይም ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። 19 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤+ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ።+ የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ* በሥራዋ* ተረጋግጧል።”+

20 ከዚያም ብዙ ተአምራት የፈጸመባቸውን ከተሞች ንስሐ ባለመግባታቸው የተነሳ እንዲህ ሲል ይነቅፋቸው ጀመር፦ 21 “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና* ተደርገው ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ማቅ ለብሰውና አመድ ላይ ተቀምጠው ንስሐ በገቡ ነበር።+ 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።+ 23 አንቺም ቅፍርናሆም+ ወደ ሰማይ ከፍ የምትዪ ይመስልሻል? በፍጹም! ወደ መቃብር* ትወርጃለሽ፤+ ምክንያቱም በአንቺ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። 24 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ምድር ይቀልላታል።”+

25 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለትናንሽ ልጆች ስለገለጥክላቸው በይፋ አወድስሃለሁ።+ 26 አዎ፣ አባት ሆይ፣ ይህ የአንተ ፈቃድ ነውና። 27 አባቴ ሁሉንም ነገር ለእኔ ሰጥቶኛል፤+ ከአብ በስተቀር ወልድን በሚገባ የሚያውቅ የለም፤+ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብን በሚገባ የሚያውቅ ማንም የለም።+ 28 እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። 29 ቀንበሬን ተሸከሙ፤* ከእኔም ተማሩ፤* እኔ ገርና* በልቤ ትሑት ነኝ፤+ ለራሳችሁም* እረፍት ታገኛላችሁ። 30 ቀንበሬ ልዝብ፣* ሸክሜም ቀላል ነውና።”

12 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል አለፈ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ።+ 2 ፈሪሳውያን ይህን ባዩ ጊዜ “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት።+ 3 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁም?+ 4 ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር+ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እንዲበሉ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ አልበሉም? 5 ደግሞስ ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም?+ 6 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 7 ይሁንና ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን+ እንጂ መሥዋዕትን+ አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። 8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”+

9 ከዚያ ስፍራ ከሄደ በኋላ ወደ ምኩራባቸው ገባ፤ 10 በዚያም እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ እነሱም ኢየሱስን መክሰስ ፈልገው “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” ሲሉ ጠየቁት።+ 11 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል?+ 12 ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” 13 ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም እንደ ሌላኛው እጁ ደህና ሆነለት። 14 ፈሪሳውያኑ ግን ወጥተው እሱን ለመግደል አሴሩ። 15 ኢየሱስም ይህን ሲያውቅ አካባቢውን ለቆ ሄደ። ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤+ እሱም የታመሙትን ሁሉ ፈወሳቸው፤ 16 ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በጥብቅ አዘዛቸው፤+ 17 ይህን ያደረገው በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦

18 “እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት*+ የመረጥኩት አገልጋዬ!+ መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤+ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል። 19 አይጨቃጨቅም+ ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም። 20 ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።+ 21 በእርግጥም ብሔራት በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”+

22 ከጊዜ በኋላም፣ ጋኔን የያዘው ዓይነ ስውርና ዱዳ ሰው ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሰው፤ ዱዳውም መናገርና ማየት ቻለ። 23 ሕዝቡም ሁሉ በጣም ተደንቀው “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆን እንዴ?” ይሉ ጀመር። 24 ፈሪሳውያን ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል* ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” አሉ።+ 25 ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። 26 በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? 27 በተጨማሪም እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ* የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው? ልጆቻችሁ ፈራጆች የሚሆኑባችሁ* ለዚህ ነው። 28 ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ መንፈስ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው።+ 29 ደግሞስ አንድ ሰው በቅድሚያ ሰውየውን ሳያስር ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት ገብቶ እንዴት ንብረቱን ሊወስድ ይችላል? ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። 30 ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል።+

31 “ስለሆነም እላችኋለሁ፣ ሰዎች የሚሠሩት ኃጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ግን ይቅር አይባልለትም።+ 32 ለምሳሌ በሰው ልጅ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ይቅርታ ይደረግለታል፤+ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህም ሆነ በሚመጣው ሥርዓት* ይቅርታ አይደረግለትም።+

33 “መልካም ዛፍ ካላችሁ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ካላችሁ ደግሞ የበሰበሰ ፍሬ ያፈራል፤ ዛፍ የሚታወቀው በፍሬው ነውና።+ 34 እናንተ የእፉኝት ልጆች፣+ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ እንዴት መልካም ነገር ልትናገሩ ትችላላችሁ? አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና።+ 35 ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰው ደግሞ በልቡ ካከማቸው መጥፎ ነገር ክፉ ነገር ያወጣል።+ 36 ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰዎች ለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል፤+ 37 ከቃልህ የተነሳ ጻድቅ ትባላለህና፤ ከቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ።”

38 ከዚያም ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር፣ ምልክት እንድታሳየን እንፈልጋለን” አሉት።+ 39 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ* ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።+ 40 ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ+ ሁሉ የሰው ልጅም በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል።+ 41 የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሐ ስለገቡ+ በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይኮንኑታል። ነገር ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 42 የደቡብ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለመጣች+ በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትኮንነዋለች። ነገር ግን ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።+

43 “ርኩስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ የሚያርፍበት ቦታ ፍለጋ ውኃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሆኖም የሚያርፍበት ቦታ አያገኝም።+ 44 ከዚያም ‘ወደለቀቅኩት ቤቴ ተመልሼ እሄዳለሁ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና አጊጦ ያገኘዋል። 45 ከዚያም ሄዶ ከእሱ የከፉ ሌሎች ሰባት መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም ይኖሩበታል፤ የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከቀድሞው የከፋ ይሆንበታል።+ ይህ ክፉ ትውልድም ተመሳሳይ ነገር ይደርስበታል።”

46 ኢየሱስ ለሕዝቡ እየተናገረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ+ ሊያነጋግሩት ፈልገው ውጭ ቆመው ነበር።+ 47 ስለሆነም አንድ ሰው “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” አለው። 48 ኢየሱስም መልሶ ሰውየውን “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። 49 እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!+ 50 በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነውና።”+

13 በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር ተቀመጠ። 2 እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው ተሰበሰቡ፤ በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር።+ 3 ከዚያም ብዙ ነገሮችን እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፦+ “እነሆ፣ አንድ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።+ 4 በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።+ 5 ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።+ 6 ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ። 7 ሌሎቹ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው።+ 8 ሌሎቹ ደግሞ ጥሩ አፈር ላይ ወድቀው ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ አንዱ 100፣ አንዱ 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ አፈራ።+ 9 ጆሮ ያለው ይስማ።”+

10 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ መጥተው “በምሳሌ የምትነግራቸው ለምንድን ነው?” አሉት።+ 11 እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤+ ለእነሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12 ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።+ 13 በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ ቢያዩም የሚያዩት እንዲያው በከንቱ ነውና፤ ቢሰሙም የሚሰሙት እንዲያው በከንቱ ነው፤ ትርጉሙንም አያስተውሉም።+ 14 ደግሞም የኢሳይያስ ትንቢት በእነሱ ላይ እየተፈጸመ ነው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ ‘መስማቱን ትሰማላችሁ ግን በፍጹም ትርጉሙን አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ ግን በፍጹም ልብ አትሉም።+ 15 ምክንያቱም በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው እንዲሁም በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል፤ በጆሯቸው ሰምተው ምላሽ አልሰጡም፤ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።’+

16 “እናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ደስተኞች ናችሁ።+ 17 እውነት እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤+ አሁን የምትሰሙትን ነገር ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም።

18 “እንግዲህ እናንተ ዘር የዘራውን ሰው ምሳሌ ስሙ።+ 19 አንድ ሰው የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ከሆነ ክፉው+ መጥቶ በልቡ ውስጥ የተዘራውን ዘር ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ይህ ነው።+ 20 በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሲሰማ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበል ሰው ነው።+ 21 ሆኖም ቃሉ በውስጡ ሥር ስለማይሰድ የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ በቃሉ የተነሳም መከራ ወይም ስደት ሲደርስበት ወዲያው ይሰናከላል። 22 በእሾህ መካከል የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ይሁንና የዚህ ሥርዓት* ጭንቀት+ እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።+ 23 በጥሩ አፈር ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማና የሚያስተውል ነው፤ ፍሬም ያፈራል፤ አንዱ 100፣ አንዱም 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ ይሰጣል።”+

24 ደግሞም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 25 ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26 እህሉ አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ። 27 ስለሆነም የቤቱ ጌታ ባሪያዎች፣ ወደ እሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፣ በእርሻህ ላይ የዘራኸው ጥሩ ዘር አልነበረም እንዴ? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። 28 እሱም ‘ይህን ያደረገው ጠላት ነው’ አላቸው።+ ባሪያዎቹም ‘ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ አሉት። 29 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ስለምትችሉ ተዉት። 30 እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብረው ይደጉ፤ በመከር ወቅት አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።’”+

31 ደግሞም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ እርሻው ውስጥ ከተከላት አንዲት የሰናፍጭ ዘር ጋር ይመሳሰላል፤+ 32 የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም ስታድግ ግን ከተክሎች ሁሉ በልጣ ዛፍ ስለምትሆን የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ መስፈሪያ ያገኛሉ።”

33 አሁንም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ከሦስት ትላልቅ መስፈሪያ* ዱቄት ጋር ከደባለቀችው እርሾ ጋር ይመሳሰላል።”+

34 ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤+ 35 ይህም የሆነው “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከምሥረታው* ጊዜ አንስቶ የተሰወሩትን ነገሮች አውጃለሁ” ተብሎ በነቢዩ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።+

36 ከዚያም ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው “በእርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርከውን ምሳሌ አብራራልን” አሉት። 37 እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ 38 እርሻው ዓለም ነው።+ ጥሩው ዘር ደግሞ የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ግን የክፉው ልጆች ናቸው፤+ 39 እንክርዳዱን የዘራው ጠላት፣ ዲያብሎስ ነው። መከሩ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ ሲሆን አጫጆቹ ደግሞ መላእክት ናቸው። 40 በመሆኑም እንክርዳዱ ተሰብስቦ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዚህ ሥርዓት* መደምደሚያም እንዲሁ ይሆናል።+ 41 የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነሱም እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች ሁሉና ዓመፅ የሚፈጽሙትን ሰዎች ከመንግሥቱ ይለቅማሉ፤ 42 ወደ እሳታማ እቶንም ይጥሏቸዋል።+ በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ። 43 በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ።+ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ።

44 “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ ከተደበቀ ውድ ሀብት ጋር ይመሳሰላል፤ አንድ ሰው ባገኘው ጊዜ ሸሸገው፤ ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።+

45 “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት ጥሩ ዕንቁ ከሚፈልግ ተጓዥ ነጋዴ ጋር ይመሳሰላል። 46 ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ወዲያውኑ በመሸጥ ዕንቁውን ገዛው።+

47 “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር ተጥሎ የተለያየ ዓይነት ዓሣ ከሰበሰበ መረብ ጋር ይመሳሰላል። 48 መረቡ በሞላ ጊዜ ወደ ባሕሩ ዳር ጎትተው አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን+ እየለዩ በዕቃ ውስጥ አስቀመጡ፤ መጥፎ መጥፎውን+ ግን ጣሉት። 49 በዚህ ሥርዓት* መደምደሚያም እንደዚሁ ይሆናል። መላእክት ተልከው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለያሉ፤ 50 ወደ እሳታማ እቶንም ይጥሏቸዋል። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።

51 እሱም “የዚህ ሁሉ ትርጉም ገብቷችኋል?” አላቸው። እነሱም “አዎ” አሉት። 52 ከዚያም ኢየሱስ “እንደዚያ ከሆነ፣ ስለ መንግሥተ ሰማያት የተማረ ማንኛውም የሕዝብ አስተማሪ ከከበረ ሀብት ማከማቻው አዲስና አሮጌ ዕቃ ከሚያወጣ የቤት ጌታ ጋር ይመሳሰላል” አላቸው።

53  ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ሲጨርስ ከዚያ ስፍራ ተነስቶ ሄደ። 54 ወደ ትውልድ አገሩ+ ከመጣ በኋላ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ጀመር፤ ሰዎቹም ተገርመው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ተአምራት የማድረግ ችሎታ ከየት አገኘ?+ 55 ይህ የአናጺው ልጅ አይደለም?+ እናቱስ ማርያም አይደለችም? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉም?+ 56 እህቶቹስ ሁሉ የሚኖሩት ከእኛ ጋር አይደለም? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?”+ 57  ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት።+ ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው።+ 58 በእሱ ባለማመናቸው በዚያ ብዙ ተአምራት አልፈጸመም።

14 በዚያን ጊዜ የአውራጃ ገዢ* የነበረው ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ሲሰማ+ 2 አገልጋዮቹን “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። ከሞት ተነስቷል ማለት ነው፤ እነዚህን ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” አላቸው።+ 3 ሄሮድስ* የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን ይዞ በሰንሰለት በማሰር ወህኒ አስገብቶት ነበር።+ 4 ዮሐንስ ሄሮድስን “እሷን እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።+ 5 ሄሮድስ ሊገድለው ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ስለነበር ሕዝቡን ፈራ።+ 6 ሆኖም የሄሮድስ ልደት+ በተከበረበት ዕለት የሄሮድያዳ ልጅ በግብዣው ላይ በመጨፈር ሄሮድስን እጅግ ደስ አሰኘችው፤+ 7 በመሆኑም የጠየቀችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። 8 ከዚያም እናቷ በሰጠቻት ምክር መሠረት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ ሳህን ስጠኝ” አለችው።+ 9 ንጉሡ ቢያዝንም ስለ መሐላዎቹና አብረውት ይበሉ ስለነበሩት ሲል የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። 10 ሰው ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቆረጠ። 11 ራሱን በሳህን አምጥተው ለልጅቷ ሰጧት፤ እሷም ለእናቷ ሰጠቻት። 12 በኋላም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጡና አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። 13 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ብቻውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ። ሕዝቡ ግን መሄዱን ሰምተው ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት።+

14 ኢየሱስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተና በጣም አዘነላቸው፤+ በመካከላቸው የነበሩትንም ሕመምተኞች ፈወሰ።+ 15 በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው “ቦታው ገለል ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።+ 16 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው። 17 እነሱም “ከአምስት ዳቦና ከሁለት ዓሣ በስተቀር እዚህ ምንም ነገር የለንም” አሉት። 18 እሱም “ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። 19 ሕዝቡንም ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ከዚያም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ፤+ ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ። 20 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 21 የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 5,000 ወንዶች ነበሩ።+ 22 ወዲያውም፣ እሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ ደቀ መዛሙርቱን ጀልባ ተሳፍረው ቀድመውት ወደ ማዶ እንዲሻገሩ ነገራቸው።+

23 ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ።+ በመሸም ጊዜ በዚያ ብቻውን ነበር። 24 በዚህ ጊዜ ጀልባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች* ከየብስ ርቆ የነበረ ሲሆን ነፋሱ ወደ እነሱ ይነፍስ ስለነበር ማዕበሉ በጣም አስቸገራቸው። 25 ሆኖም ኢየሱስ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት* በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። 26 ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ደንግጠው “ምትሃት ነው!” አሉ። በፍርሃት ተውጠውም ጮኹ። 27 ሆኖም ኢየሱስ ወዲያውኑ “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።+ 28 ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። 29 እሱም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። 30 ሆኖም አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። 31 ወዲያው ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።+ 32 ጀልባው ላይ ከወጡ በኋላ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ። 33 ከዚያም በጀልባው ውስጥ ያሉት “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።* 34 ባሕሩንም ተሻግረው ጌንሴሬጥ+ ወደተባለ ቦታ ደረሱ።

35 በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቁ በዙሪያው ወዳለው አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ ሰዎችም የታመሙትን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ። 36 የልብሱን ዘርፍ ብቻ እንኳ ለመንካት ይማጸኑት ነበር፤+ የነኩትም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተፈወሱ።

15 ከዚያም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት+ ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ 2 “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚጥሱት ለምንድን ነው? ለምሳሌ፣ ሊበሉ ሲሉ እጃቸውን አይታጠቡም።”*+

3 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው?+ 4 ለምሳሌ አምላክ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’+ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ* ይገደል’ ብሏል።+ 5 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ ነው”+ ካለ 6 አባቱን የማክበር ግዴታ የለበትም።’ በመሆኑም ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል።+ 7 እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፦+ 8 ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። 9 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’”+ 10 ከዚያም ሕዝቡን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ፤ ደግሞም ይህን ቃል አስተውሉ፦+ 11 ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የሚገባው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው ነው።”+

12 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን በተናገርከው ነገር ቅር እንደተሰኙ አውቀሃል?” አሉት።+ 13 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14 ተዉአቸው፤ እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።”+ 15 ጴጥሮስም መልሶ “ምሳሌውን አብራራልን” አለው። 16 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም እስካሁን ማስተዋል ተስኗችኋል?+ 17 ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚዘልቅና ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ እንደሚገባ አታውቁም? 18 ይሁን እንጂ ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው።+ 19 ለምሳሌ ከልብ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦+ ግድያ፣ ምንዝር፣ የፆታ ብልግና፣* ሌብነት፣ በሐሰት መመሥከርና ስድብ። 20 ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ እጅን ሳይታጠቡ* መብላት ግን ሰውን አያረክስም።”

21 ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና አካባቢ ሄደ።+ 22 በዚያ ክልል የምትኖር አንዲት ፊንቄያዊት* ሴት መጥታ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ። ልጄን ጋኔን ስለያዛት ክፉኛ እየተሠቃየች ነው” ብላ ጮኸች።+ 23 እሱ ግን ምንም መልስ አልሰጣትም። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ይህች ሴት ከኋላችን እየተከተለች ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት” እያሉ ይለምኑት ጀመር። 24 እሱም መልሶ “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች እንጂ ለሌላ ለማንም አይደለም” አለ።+ 25 ሴትየዋ ግን ቀርባ “ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ!” እያለች ሰገደችለት።* 26 እሱም መልሶ “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ አይደለም” አለ። 27 እሷም “አዎ ጌታ ሆይ፣ ግን እኮ ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች።+ 28 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ መልሶ “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ በይ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች።

29 ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ ወደ ገሊላ ባሕር+ አቅራቢያ መጣ፤ ወደ ተራራ ወጥቶም ተቀመጠ። 30 በዚህ ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች አንካሶችን፣ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ ዱዳዎችንና ሌሎች በርካታ ሕመምተኞችን ይዘው ወደ እሱ በመምጣት እግሩ ሥር አስቀመጧቸው፤ እሱም ፈወሳቸው።+ 31 ሕዝቡም ዱዳዎች ሲናገሩ፣ ሽባዎች ሲፈወሱ፣ አንካሶች ሲራመዱና ዓይነ ስውሮች ሲያዩ ተመልክተው እጅግ ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።+

32 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ “እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ።+ እንዲሁ ጦማቸውን ልሰዳቸው አልፈልግም፤ መንገድ ላይ ዝለው ሊወድቁ ይችላሉ” አላቸው።+ 33 ደቀ መዛሙርቱ ግን “በዚህ ገለልተኛ ስፍራ ይህን ሁሉ ሕዝብ ሊያጠግብ የሚችል በቂ ዳቦ ከየት እናገኛለን?” አሉት።+ 34 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ስንት ዳቦ አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “ሰባት ዳቦና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት። 35 እሱም ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጥ ካዘዘ በኋላ 36 ሰባቱን ዳቦና ዓሣዎቹን ወሰደ፤ ካመሰገነ በኋላም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ።+ 37 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ሰባት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 38 የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 4,000 ወንዶች ነበሩ። 39 በመጨረሻም ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ጀልባ ተሳፍሮ ወደ መጌዶን ክልል መጣ።+

16 ከዚያም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እሱ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።+ 2 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሲመሽ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ 3 ጠዋት ላይ ደግሞ ‘ሰማዩ ቢቀላም ደመና ስለሆነ ዛሬ ብርድ ይሆናል፣ ዝናብም ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን መልክ በማየት መተርጎም ትችላላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መተርጎም አትችሉም። 4 ክፉና አመንዝራ* ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በስተቀር+ ምንም ምልክት አይሰጠውም።”+ ይህን ከተናገረ በኋላ ትቷቸው ሄደ።

5 ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገሩ፤ በዚህ ጊዜ ዳቦ መያዝ ረስተው ነበር።+ 6 ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።+ 7 እነሱም እርስ በርሳቸው “ዳቦ ስላልያዝን ይሆናል” ይባባሉ ጀመር። 8 ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ዳቦ ስላልያዝን ነው ብላችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? 9 አሁንም ነጥቡ አልገባችሁም? ወይስ አምስቱ ዳቦ ለ5,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን ምን ያህል ቅርጫት እንደሰበሰባችሁ አታስታውሱም?+ 10 ወይስ ሰባቱ ዳቦ ለ4,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን በትላልቅ ቅርጫት ምን ያህል እንደሰበሰባችሁ ትዝ አይላችሁም?+ 11 ታዲያ የነገርኳችሁ ስለ ዳቦ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? እንግዲህ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።”+ 12 በዚህ ጊዜ ተጠንቀቁ ያላቸው ከዳቦ እርሾ ሳይሆን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንደሆነ ገባቸው።

13 ኢየሱስ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አካባቢ በመጣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው።+ 14 እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣+ ሌሎች ኤልያስ፣+ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። 15 እሱም “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” አላቸው። 16 ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ፣+ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ”+ ብሎ መለሰለት። 17 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “የዮናስ ልጅ ስምዖን፣ ይህን የገለጠልህ ሥጋና ደም ሳይሆን* በሰማያት ያለው አባቴ ስለሆነ ደስ ይበልህ።+ 18 ደግሞም እልሃለሁ፦ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤+ በዚህች ዓለት+ ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የመቃብር* በሮችም አያሸንፏትም። 19 የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈታው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” 20 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው።+

21 ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እጅ ከባድ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንደሚገባው ብሎም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።+ 22 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር።+ 23 እሱ ግን ጀርባውን በመስጠት ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን!* የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው።+

24 ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት* ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።+ 25 ሕይወቱን* ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔ ሲል ሕይወቱን* የሚያጣ ሁሉ ግን ያገኛታል።+ 26 ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ሕይወቱን* ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?+ ወይስ ሰው ለሕይወቱ* ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?+ 27 የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣልና፤ ከዚያም ለእያንዳንዱ እንደ ምግባሩ ይከፍለዋል።+ 28 እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።”+

17 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ።+ 2 በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።*+ 3 ከዚያም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 4 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ከፈለግክ በዚህ ስፍራ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እተክላለሁ” አለው። 5 ገና እየተናገረ ሳለም ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ ተሰማ። 6 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ተውጠው በግንባራቸው ተደፉ። 7 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ እነሱ ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሱ። አትፍሩ” አላቸው። 8 ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንንም አላዩም። 9 ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ራእዩን ለማንም እንዳትናገሩ” ሲል አዘዛቸው።+

10 ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ “ታዲያ ጸሐፍት ኤልያስ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 11 እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል።+ 12 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ መምጣቱን መጥቷል፤ እነሱ ግን የፈለጉትን ነገር አደረጉበት+ እንጂ አላወቁትም። የሰው ልጅም እንደዚሁ በእነሱ እጅ ይሠቃያል።”+ 13 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ ገባቸው።

14 ወደ ሕዝቡ በመጡ ጊዜ+ አንድ ሰው ወደ እሱ ቀረበና ተንበርክኮ እንዲህ አለው፦ 15 “ጌታ ሆይ፣ ለልጄ ምሕረት አድርግለት፤ የሚጥል በሽታ ስላለበት በጠና ታሟል። አንዴ እሳት ውስጥ አንዴ ደግሞ ውኃ ውስጥ ይወድቃል።+ 16 ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ እነሱ ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” 17 ኢየሱስም መልሶ “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አለ። 18 ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።+ 19 ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ መጥተው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት። 20 እሱም “እምነታችሁ ስላነሰ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም”+ አላቸው። 21 *——

22 በገሊላ ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤+ 23 እነሱም ይገድሉታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”+ ደቀ መዛሙርቱም በጣም አዘኑ።

24 ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ የቤተ መቅደሱን ግብር* የሚሰበስቡት ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ የቤተ መቅደሱን ግብር አይከፍልም?”+ አሉት። 25 እሱም “ይከፍላል” አላቸው። ይሁን እንጂ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ በቅድሚያ እንዲህ አለው፦ “ስምዖን ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?” 26 እሱም “ከሌሎች” ብሎ ሲመልስለት ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “እንግዲያው ልጆቹ ግብር ከመክፈል ነፃ ናቸው። 27 ሆኖም እንቅፋት እንዳንሆንባቸው+ ወደ ባሕሩ ሄደህ መንጠቆ ጣል፤ ከዚያም መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት አንድ የብር ሳንቲም * ታገኛለህ። ሳንቲሙን ወስደህ ለእኔና ለአንተ ክፈል።”

18 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” አሉት።+ 2 ኢየሱስም አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው በማቆም 3 እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተመለሳችሁና* እንደ ልጆች ካልሆናችሁ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም።+ 4 ስለዚህ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤+ 5 እንዲሁም እንደዚህ ያለውን ትንሽ ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል። 6 ሆኖም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትናንሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ* በአንገቱ ታስሮ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ቢሰጥም ይሻለዋል።+

7 “ይህ ዓለም ሰዎችን የሚያሰናክል ነገር ስለሚያስቀምጥ ወዮለት! እርግጥ ማሰናከያ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን በእሱ ጠንቅ ሌሎች እንዲሰናከሉ ለሚያደርግ ሰው ወዮለት! 8 እንግዲያው እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለማዊ እሳት+ ከምትወረወር ጉንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል። 9 እንዲሁም ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ እሳታማ ገሃነም* ከምትወረወር አንድ ዓይን ኖሮህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 10 በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።+ 11 *——

12 “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው 100 በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ+ 99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም?+ 13 እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋችውን በግ ካገኛት፣ ካልጠፉት ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል። 14 በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ* ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም።+

15 “በተጨማሪም ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው።*+ ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ።+ 16 የማይሰማህ ከሆነ ግን ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል* ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ።+ 17 እነሱንም ካልሰማ ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና+ እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ+ አድርገህ ቁጠረው።

18 “እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈቱት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። 19 ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር ላይ ከእናንተ መካከል ሁለታችሁ አንድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ለመለመን ብትስማሙ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል።+ 20 ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት+ በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና።”

21 ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” አለው። 22 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ* እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም።+

23 “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ከፈለገ አንድ ንጉሥ ጋር ይመሳሰላል። 24 ሒሳቡን መተሳሰብ በጀመረ ጊዜም 10,000 ታላንት* ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው አቀረቡለት። 25 ሆኖም ሰውየው ዕዳውን የሚከፍልበት ምንም መንገድ ስላልነበረው ጌታው እሱም ሆነ ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ያለው ንብረት ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ።+ 26 ባሪያውም ወድቆ በመስገድ* ‘ጌታዬ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። 27 ጌታውም እጅግ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ሰረዘለት።+ 28 ሆኖም ይህ ባሪያ ወጥቶ ከሄደ በኋላ 100 ዲናር* ያበደረውን እንደ እሱ ያለ ባሪያ አግኝቶ ያዘውና አንገቱን አንቆ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ’ አለው። 29 ባልንጀራው የሆነው ያ ባሪያም እግሩ ላይ ወድቆ ‘ወንድሜ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ይለምነው ጀመር። 30 እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ሄዶ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው። 31 ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። 32 በዚህ ጊዜ ጌታው አስጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። 33 ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?’+ 34 ጌታውም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው። 35 እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ+ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”+

19 ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ከገሊላ ወጥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ።+ 2 እጅግ ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ እሱም በዚያ ፈወሳቸው።

3 ፈሪሳውያንም ወደ እሱ መጥተው ሊፈትኑት በማሰብ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለታል?” ሲሉ ጠየቁት።+ 4 እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም?+ 5 ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም?+ 6 በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን* ማንም ሰው አይለያየው።”+ 7 እነሱም “ታዲያ ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ያዘዘው ለምንድን ነው?” አሉት።+ 8 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ የልባችሁን ደንዳናነት አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ+ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም።+ 9 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”+

10 ደቀ መዛሙርቱም “በባልና በሚስት መካከል ያለው ሁኔታ እንዲህ ከሆነስ አለማግባት ይመረጣል” አሉት። 11 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ስጦታው ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ይህን ሁሉም ሰው ሊቀበለው አይችልም።+ 12 ምክንያቱም ጃንደረባ ሆነው የሚወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸው ጃንደረቦችም አሉ፤ እንዲሁም ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ጃንደረቦችም አሉ። ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”+

13 ከዚያም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸውና* እንዲጸልይላቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።+ 14 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ልጆቹን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ እንዳይመጡ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ነውና” አለ።+ 15 እጁንም ከጫነባቸው* በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነስቶ ሄደ።

16 ከዚያም አንድ ወጣት ወደ እሱ መጥቶ “መምህር፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ጥሩ ነገር ማድረግ ይኖርብኛል?” አለው።+ 17 እሱም “ስለ ጥሩ ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? ጥሩ የሆነው አምላክ ብቻ ነው።+ ሆኖም ሕይወት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ዘወትር ትእዛዛቱን ጠብቅ” አለው።+ 18 እሱም “የትኞቹን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “አትግደል፣+ አታመንዝር፣+ አትስረቅ፣+ በሐሰት አትመሥክር፣+ 19 አባትህንና እናትህን አክብር+ እንዲሁም ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ።”+ 20 ወጣቱም “እነዚህን ሁሉ ስጠብቅ ኖሬአለሁ፤ ታዲያ አሁን የሚጎድለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለው። 21 ኢየሱስም “ፍጹም* መሆን ከፈለግክ ሂድና ንብረትህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤+ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።+ 22 ወጣቱም ይህን ሲሰማ ብዙ ንብረት ስለነበረው እያዘነ ሄደ።+ 23 ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል።+ 24 ዳግመኛም እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”+

25 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ተገርመው “በዚህ ዓይነትማ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።+ 26 ኢየሱስም ትኩር ብሎ እያያቸው “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል” አላቸው።+

27 ከዚያም ጴጥሮስ መልሶ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” አለው።+ 28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር አዲስ በሚሆንበት ጊዜ* የሰው ልጅ፣ ክብራማ በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።+ 29 እንዲሁም ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።+

30 “ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።+

20 “መንግሥተ ሰማያት በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ ከወጣ የእርሻ ባለቤት ጋር ይመሳሰላል።+ 2 በቀን አንድ ዲናር* ሊከፍላቸው ከተዋዋለ በኋላ ሠራተኞቹን ወደ ወይን እርሻው ላካቸው። 3 በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤ 4 እነዚህንም ሰዎች ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ፤ ተገቢውንም ክፍያ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። 5 እነሱም ሄዱ። ዳግመኛም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6 በመጨረሻም በ11 ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው። 7 እነሱም ‘የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው’ ሲሉ መለሱለት። እሱም ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሄዳችሁ ሥሩ’ አላቸው።

8 “በመሸም ጊዜ የወይኑ እርሻ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ‘ሠራተኞቹን ጠርተህ በመጨረሻ ከተቀጠሩት አንስቶ በመጀመሪያ እስከተቀጠሩት ድረስ ደሞዛቸውን ክፈላቸው’+ አለው። 9 በ11 ሰዓት የተቀጠሩት ሰዎች መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር* ተቀበሉ። 10 በመሆኑም በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲመጡ እነሱ የበለጠ የሚከፈላቸው መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሱም የተከፈላቸው አንድ አንድ ዲናር* ነበር። 11 ክፍያውን ሲቀበሉ በእርሻው ባለቤት ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ 12 እንዲህም አሉት፦ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት ሰዎች አንድ ሰዓት ብቻ ነው የሠሩት፤ ያም ሆኖ አንተ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንቃጠል ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግካቸው!’ 13 እሱ ግን ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘የኔ ወንድም፣ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር* እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ?+ 14 ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ። በመጨረሻ ለተቀጠሩት ለእነዚህ ሰዎችም ለአንተ የሰጠሁትን ያህል መስጠት ፈለግኩ። 15 በገዛ ገንዘቤ የፈለግኩትን የማድረግ መብት የለኝም? ወይስ እኔ ደግ* በመሆኔ ዓይንህ ተመቀኘ?’*+ 16 ስለሆነም ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ይሆናሉ።”+

17 ወደ ኢየሩሳሌም እየወጡ ሳሉ ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ነጥሎ ወሰዳቸው፤ በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ አላቸው፦+ 18 “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤+ 19 እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና በእንጨት ላይ እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤+ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”+

20 ከዚያም የዘብዴዎስ+ ሚስት ከልጆቿ ጋር ወደ እሱ ቀርባ እየሰገደች* አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።+ 21 እሱም “ምንድን ነው የፈለግሽው?” አላት። እሷም መልሳ “በመንግሥትህ እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን፣ አንዱን በቀኝህ አንዱን ደግሞ በግራህ አስቀምጥልኝ” አለችው።+ 22 ኢየሱስም መልሶ “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ በቅርቡ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁ?” አላቸው።+ እነሱም “እንችላለን” አሉት። 23 እሱም “በእርግጥ የእኔን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤+ በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ግን አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” አላቸው።+

24 የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ተቆጡ።+ 25 ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህ ዓለም ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ።+ 26 በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤+ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤+ 27 እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባል።+ 28 የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና+ በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን* ቤዛ አድርጎ ለመስጠት+ እንጂ እንዲገለገል አይደለም።”

29 ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ ሳሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 30 በዚህ ጊዜ መንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዓይነ ስውሮች ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ጮኹ።+ 31 ሆኖም ሕዝቡ ዝም እንዲሉ ገሠጿቸው፤ እነሱ ግን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ይበልጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። 32 ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33 እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” አሉት። 34 ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤+ ወዲያውኑም ማየት ቻሉ፤ ከዚያም ተከተሉት።

21 ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረቡና በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤተፋጌ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤+ 2 እንዲህም አላቸው፦ “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ እዚያ እንደደረሳችሁም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጭላዋ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው። 3 ማንም ሰው ቢጠይቃችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት። በዚህ ጊዜ ወዲያውኑ ይልካቸዋል።”

4 ይህም የሆነው ነቢዩ እንዲህ ብሎ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 5 “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፦ ‘እነሆ ንጉሥሽ+ ገር+ ሆኖ በአህያ፣ አዎ በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል።’”+

6 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።+ 7 አህያይቱንና ውርንጭላዋን አምጥተው መደረቢያዎቻቸውን በላያቸው ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠባቸው።*+ 8 ከሕዝቡ መካከል አብዛኞቹ መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፤+ ሌሎች ደግሞ ከዛፎች ላይ ቅርንጫፎች እየቆረጡ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር። 9 በተጨማሪም ከፊት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው የሚከተለው ሕዝብ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን!*+ በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!+ በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እንድታድነው እንለምንሃለን!”+ ብሎ ይጮኽ ነበር።

10 ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም “ይህ ሰው ማን ነው?” በማለት መላዋ ከተማ ታወከች። 11 ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው!”+ ይል ነበር።

12 ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ።+ 13 እንዲህም አላቸው፦ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤+ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አድርጋችሁታል።”+ 14 ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንዳለም ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደ እሱ መጡ፤ እሱም ፈወሳቸው።

15 የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ውስጥ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን!”+ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ ተቆጥተው+ 16 “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም “አዎ እሰማለሁ። ‘ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” አላቸው።+ 17 ከዚያም ትቷቸው ከከተማዋ ከወጣ በኋላ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ እዚያም አደረ።+

18 በማለዳም ወደ ከተማዋ እየተመለሰ ሳለ ተራበ።+ 19 በመንገድ ዳር አንድ የበለስ ዛፍ አየና ወደ እሷ ሄደ፤ ሆኖም ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት+ “ከእንግዲህ ወዲህ ፍሬ አይገኝብሽ” አላት።+ የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ ደረቀች። 20 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ተገርመው “የበለስ ዛፏ እንዲህ በአንዴ ልትደርቅ የቻለችው እንዴት ነው?” አሉ።+ 21 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግኩትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆንላችኋል።+ 22 እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።”+

23 ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ እያስተማረ ሳለ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” አሉት።+ 24 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ። መልሱን ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፦ 25 ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ሥልጣን የሰጠው ማን ነው? አምላክ* ነው ወይስ ሰው?” እነሱ ግን እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር፦ “‘አምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤+ 26 ‘ሰው’ ብንል ደግሞ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን እንፈራለን።” 27 ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እሱ ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም።

28 “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። 29 ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው፤ በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። 30 ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። 31 ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነሱም “የመጀመሪያው” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ ይቀድሟችኋል። 32 ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አመኑት፤+ እናንተ ይህን አይታችሁም እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም።

33 “ሌላም ምሳሌ ስሙ፦ የወይን እርሻ+ ያለማ አንድ ባለ ርስት ነበር፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ በዚያም የወይን መጭመቂያ ቆፈረ እንዲሁም ማማ ሠራ፤+ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።+ 34 ፍሬው የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ድርሻውን እንዲያመጡለት ባሪያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35 ገበሬዎቹ ግን ባሪያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት።+ 36 ከበፊቶቹ የሚበዙ ሌሎች ባሪያዎች በድጋሚ ላከ፤ ይሁንና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው።+ 37 በመጨረሻም ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከው። 38 ገበሬዎቹ ልጁን ሲያዩት እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው።+ ኑ እንግደለው፤ ርስቱንም እንውረስ!’ ተባባሉ። 39 ስለዚህ ያዙትና ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት።+ 40 እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚህን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” 41 የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎችም “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።

42 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ።+ ይህ የይሖዋ* ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’+ 43 የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው። 44 በተጨማሪም በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል።+ ድንጋዩ የሚወድቅበት ሰው ሁሉ ደግሞ ይደቅቃል።”+

45 የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑ ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነሱ እንደተናገረ ገባቸው።+ 46 ሊይዙት* ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡን ፈሩ፤ ምክንያቱም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ነበር።+

22 በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል በምሳሌ ነገራቸው፦ 2 “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ+ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 3 ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።+ 4 በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። 5 እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤+ 6 ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።

7 “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።+ 8 ከዚያም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም።+ 9 ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’+ 10 በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።

11 “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። 12 በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። 13 ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው።

14 “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

15 ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው በንግግሩ ሊያጠምዱት ሴራ ጠነሰሱ።+ 16 ስለዚህ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር ወደ እሱ በመላክ እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር እንዲሁም ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ እናውቃለን። 17 እስቲ ንገረን፣ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”* 18 ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? 19 እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ።” እነሱም አንድ ዲናር* አመጡለት። 20 እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። 21 እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።+ 22 ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ከዚያም ትተውት ሄዱ።

23 በዚያኑ ዕለት፣ በትንሣኤ የማያምኑት+ ሰዱቃውያን መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦+ 24 “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል።+ 25 በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። 26 ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ። 27 በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 28 እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”

29 ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ተሳስታችኋል፤+ 30 ምክንያቱም በትንሣኤ ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማይ እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።+ 31 የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ አምላክ እንዲህ ሲል ለእናንተ የተናገረውን አላነበባችሁም? 32 ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ብሏል።+ እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”+ 33 ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ በትምህርቱ ተደነቁ።+

34 ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሲሰሙ ተሰብስበው መጡ። 35 ከእነሱም መካከል አንድ ሕግ አዋቂ እሱን ለመፈተን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 36 “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?”+ 37 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “‘አምላክህን ይሖዋን* በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና* በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’+ 38 ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። 39 ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።+ 40 መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።”+

41 ፈሪሳውያን አንድ ላይ ተሰብስበው እንዳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦+ 42 “ስለ መሲሑ* ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” እነሱም “የዳዊት” አሉት።+ 43 እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ+ እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል? 44 ምክንያቱም ዳዊት ‘ይሖዋ* ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ሲል ተናግሯል።+ 45 ታዲያ ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”+ 46 ከዚህ በኋላ አንዲት ቃል ሊመልስለት የቻለም ሆነ ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ አንድም ሰው አልነበረም።

23 ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2 “ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል። 3 ስለዚህ የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ።+ 4 ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤+ እነሱ ግን በጣታቸው እንኳ ለመንካት* ፈቃደኞች አይደሉም።+ 5 ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በሰዎች ለመታየት ብለው ነው፤+ ለምሳሌ ትልቅ ክታብ* ያስራሉ፤+ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ።+ 6 በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ* ይወዳሉ፤+ 7 በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ እንዲሁም ረቢ* ተብለው መጠራት ይሻሉ። 8 እናንተ ግን መምህራችሁ+ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። 9 በተጨማሪም አባታችሁ+ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። 10 እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ። 11 ይልቁንም ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል።+ 12 ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤+ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።+

13 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።+ 14 *——

15 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ አንድን ሰው ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙና ሰውየው በተለወጠ ጊዜ ከእናንተ ይባስ ሁለት እጥፍ ለገሃነም* የተገባ እንዲሆን ስለምታደርጉት ወዮላችሁ!

16 “‘አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’+ የምትሉ እናንተ ዕውር መሪዎች+ ወዮላችሁ! 17 እናንተ ሞኞችና ዕውሮች! ለመሆኑ ከወርቁና ወርቁ እንዲቀደስ ካደረገው ቤተ መቅደስ የትኛው ይበልጣል? 18 ደግሞም ‘አንድ ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ በመሠዊያው ላይ ባለው መባ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’ ትላላችሁ። 19 እናንተ ዕውሮች! ለመሆኑ ከመባውና መባው እንዲቀደስ ካደረገው መሠዊያ የትኛው ይበልጣል? 20 ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል ሁሉ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ነገር ሁሉ ይምላል፤ 21 እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የሚምል ሁሉ በቤተ መቅደሱና በዚያ በሚኖረው+ ይምላል፤ 22 በሰማይ የሚምል ሁሉ ደግሞ በአምላክ ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

23 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ትሰጣላችሁ፤+ ነገር ግን በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣+ ምሕረትና+ ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ። እነዚያን ችላ ማለት ባይኖርባችሁም እነዚህን ነገሮች ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው።+ 24 እናንተ ዕውር መሪዎች!+ ትንኝን+ አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን+ ግን ትውጣላችሁ!

25 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤+ ውስጡ ግን ስግብግብነትና*+ ራስ ወዳድነት የሞላበት ነው።+ 26 አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል።

27 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ከውጭ አምረው የሚታዩ ከውስጥ ግን በሙታን አፅምና በብዙ ዓይነት ርኩሰት የተሞሉ በኖራ የተቀቡ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!+ 28 እናንተም ከውጭ ስትታዩ ጻድቅ ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በዓመፅ የተሞላ ነው።+

29 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ የነቢያትን መቃብር ስለምትገነቡና የጻድቃንን መቃብር ስለምታስጌጡ ወዮላችሁ!+ 30 ደግሞም ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁ። 31 በመሆኑም የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሠክራላችሁ።+ 32 እንግዲያው አባቶቻችሁ የጀመሩትን ተግባር ዳር አድርሱ።

33 “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣+ ከገሃነም* ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?+ 34 ስለዚህ ነቢያትን፣+ ጥበበኞችንና የሕዝብ አስተማሪዎችን+ ወደ እናንተ እልካለሁ። ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ+ እንዲሁም በእንጨት ላይ ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በምኩራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፤+ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዷቸዋላችሁ፤+ 35 በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም+ ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።+ 36 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳሉ።

37 “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር!+ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።+ 38 እነሆ፣ ቤታችሁ* ለእናንተ የተተወ ይሆናል።*+ 39 ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’+ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አታዩኝም።”

24 ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እሱ ቀረቡ። 2 እሱም መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አላቸው።+

3 በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና*+ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ+ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።

4 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤+ 5 ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ።+ 6 ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+

7 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና+ የምድር ነውጥ ይከሰታል።+ 8 እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

9 “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣+ ይገድሏችኋል+ እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።+ 10 በተጨማሪም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። 11 ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤+ 12 ክፋት* እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። 13 እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 14 ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤+ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።

15 “ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’ በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ+ አንባቢው ያስተውል፤ 16 በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 17 በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ፤ 18 በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ አይመለስ። 19 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 20 ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት* ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 21 ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ ታላቅ መከራ+ ይከሰታል። 22 እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ።+

23 “በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’+ ወይም ‘ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 24 ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ።+ 25 እንግዲህ አስቀድሜ አስጠንቅቄያችኋለሁ። 26 ስለዚህ ሰዎች ‘እነሆ፣ በምድረ በዳ ነው’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘እነሆ፣ ቤት ውስጥ በውስጠኛው ክፍል ይገኛል’ ቢሏችሁ አትመኑ።+ 27 መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም* እንዲሁ ይሆናል።+ 28 በድን ባለበት ሁሉ ንስሮች ይሰበሰባሉ።+

29 “በእነዚያ ቀናት ከሚኖረው መከራ በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤+ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ።+ 30 ከዚያም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ወገኖችም ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ፤+ የሰው ልጅም+ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 31 እሱም መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣* ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።+

32 “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 33 በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 34 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም። 35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+

36 “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣+ ማንም አያውቅም።+ 37 በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ+ የሰው ልጅ መገኘትም* እንደዚሁ ይሆናል።+ 38 ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን+ ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ 39 የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤+ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። 40 በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል። 41 ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ እዚያው ትተዋለች።+ 42 ስለዚህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።+

43 “ነገር ግን ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ+ በየትኛው ክፍለ ሌሊት* እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።+ 44 ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።+

45 “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም* ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?+ 46 ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!+ 47 እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።

48 “ነገር ግን ያ ክፉ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብ+ 49 ደግሞም ባልንጀሮቹ የሆኑትን ባሪያዎች መደብደብ ቢጀምር እንዲሁም ከሰካራሞች ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤+ 51 ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤* ዕጣውንም ከግብዞች ጋር ያደርገዋል። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።+

25 “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን+ ይዘው ሙሽራውን+ ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 2 አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች* ነበሩ።+ 3 ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ 4 ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። 5 ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። 6 እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ። 7 በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ።+ 8 ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። 9 ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው። 10 ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤+ በሩም ተዘጋ። 11 በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ።+ 12 እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።

13 “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+

14 “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል።+ 15 ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣* ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ። 16 አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ። 17 በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። 18 አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ* ቀበረ።

19 “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ።+ 20 ስለዚህ አምስት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ ‘ጌታ ሆይ፣ አምስት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ አምስት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።+ 21 ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ።+ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።+ 22 ቀጥሎም ሁለት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ፣ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ ሁለት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።+ 23 ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

24 “በመጨረሻም አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታ ሆይ፣ አንተ ያልዘራኸውን የምታጭድ፣ ያልደከምክበትንም እህል የምትሰበስብ ኃይለኛ ሰው መሆንህን አውቃለሁ።+ 25 ስለዚህ ፈራሁ፤ ሄጄም ታላንትህን መሬት ውስጥ ቀበርኩት። ገንዘብህ ይኸውልህ።’ 26 ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ ባሪያ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ያልደከምኩበትንም እህል የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? 27 ይህን ካወቅክ ገንዘቤን፣* ገንዘብ ለዋጮች ጋ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም ስመጣ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስደው ነበር።

28 “‘ስለዚህ ታላንቱን ውሰዱበትና አሥር ታላንት ላለው ስጡት።+ 29 ምክንያቱም ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል። የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።+ 30 ይህን የማይረባ ባሪያ ውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።’

31 “የሰው ልጅ+ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር+ በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። 32 ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። 33 በጎቹን+ በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።+

34 “ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። 35 ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል። እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፤+ 36 ታርዤ* አልብሳችሁኛል።+ ታምሜ አስታማችሁኛል። ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’+ 37 ከዚያም ጻድቃኑ መልሰው እንዲህ ይሉታል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ተጠምተህ አይተንስ መቼ አጠጣንህ?+ 38 እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ አስተናገድንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? 39 ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ 40 ንጉሡም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።+

41 “ከዚያም በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ የተረገማችሁ፣ ከእኔ ራቁ፤+ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው+ ዘላለማዊ እሳት+ ሂዱ። 42 ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም። 43 እንግዳ ሆኜ አላስተናገዳችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’ 44 እነሱም መልሰው ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን ሳናገለግልህ ቀረን?’ ይሉታል። 45 እሱም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ይህን ሳታደርጉ መቅረታችሁ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።+ 46 እነዚህ ወደ ዘላለም ጥፋት*+ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት+ ይሄዳሉ።”

26 ኢየሱስ ይህን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2 “እንደምታውቁት ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ* ይከበራል፤+ የሰው ልጅም በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አልፎ ይሰጣል።”+

3 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ+ ተብሎ በሚጠራው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው 4 የተንኮል ዘዴ በመጠቀም ኢየሱስን ለመያዝና* ለመግደል ሴራ ጠነሰሱ።+ 5 ይሁን እንጂ “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይፈጠር በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ይሉ ነበር።

6 ኢየሱስ በቢታንያ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን+ ቤት ሳለ 7 አንዲት ሴት በጣም ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እሱ ቀረበች፤ እየበላ ሳለም ዘይቱን ራሱ ላይ ታፈስ ጀመር። 8 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲያዩ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? 9 ይህ ዘይት እኮ በውድ ዋጋ ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር።” 10 ኢየሱስ ስለ ምን እየተነጋገሩ እንዳለ አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። 11 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።+ 12 ይህች ሴት ዘይቱን በሰውነቴ ላይ ስታፈስ እኔን ለቀብር ማዘጋጀቷ ነው።+ 13 እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ይህ ምሥራች በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”+

14 ከዚህ በኋላ፣ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ+ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ+ 15 “እሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው።+ እነሱም 30 የብር ሳንቲሞች* ሊሰጡት ተስማሙ።+ 16 ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር።

17 የቂጣ* በዓል+ በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።+ 18 እሱም “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህሩ “የተወሰነው ጊዜዬ ደርሷል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ” ብሏል’ በሉት” አላቸው። 19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ።

20 በመሸም ጊዜ+ ከ12 ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።+ 21 እየበሉ ሳሉም “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ።+ 22 እነሱም በዚህ እጅግ አዝነው ሁሉም ተራ በተራ “ጌታ ሆይ፣ እኔ እሆን?” ይሉት ጀመር። 23 እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር በሳህኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው።+ 24 እርግጥ፣ የሰው ልጅ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው+ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!+ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”+ 25 አሳልፎ ሊሰጠው የተዘጋጀው ይሁዳም “ረቢ፣ እኔ እሆን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።

26 እየበሉም ሳሉ ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ቆረሰው፤+ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት “እንኩ፣ ብሉ። ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” አለ።+ 27 ጽዋ አንስቶም አምላክን ካመሰገነ በኋላ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፦ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤+ 28 ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ+ የሚፈሰውን+ ‘የቃል ኪዳን+ ደሜን’+ ያመለክታል። 29 ነገር ግን እላችኋለሁ፦ በአባቴ መንግሥት አዲሱን ወይን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከአሁን በኋላ ከዚህ ወይን አልጠጣም።”+ 30 በመጨረሻ የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።+

31 ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’+ ተብሎ ስለተጻፈ በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ላይ በሚደርሰው ነገር የተነሳ ትሰናከላላችሁ። 32 ከተነሳሁ በኋላ ግን ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”+ 33 ይሁንና ጴጥሮስ መልሶ “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” አለው።+ 34 ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፣ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።+ 35 ጴጥሮስም “አብሬህ መሞት ቢያስፈልገኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” አለው።+ የቀሩት ደቀ መዛሙርትም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።

36 ከዚያም ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ጌትሴማኒ ወደተባለ ቦታ መጣ፤+ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።+ 37 ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ከሄደ በኋላ እጅግ ያዝንና ይረበሽ ጀመር።+ 38 ከዚያም “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ።* እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።+ 39 ትንሽ ወደ ፊት ራቅ በማለት በግንባሩ ተደፍቶ “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ+ ከእኔ ይለፍ። ሆኖም እንደ እኔ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አንተ ፈቃድ ይሁን”+ ብሎ ጸለየ።+

40 ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት እንኳ ነቅታችሁ መጠበቅ አልቻላችሁም?+ 41 ወደ ፈተና እንዳትገቡ+ ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ ሳታሰልሱም ጸልዩ።+ እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ* ነው፤ ሥጋ* ግን ደካማ ነው።”+ 42 እንደገናም ሄዶ ለሁለተኛ ጊዜ “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሳልጠጣው ይለፍ። ካልሆነ ግን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም”+ ሲል ጸለየ። 43 ዳግመኛም ተመልሶ ሲመጣ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ስለነበር ተኝተው አገኛቸው። 44 እንደገናም ትቷቸው ሄደና ለሦስተኛ ጊዜ ስለዚያው ነገር ደግሞ ጸለየ። 45 ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል። 46 ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።” 47 ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።+

48 አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙት” በማለት ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 49 ይሁዳም በቀጥታ ወደ ኢየሱስ በመሄድ “ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። 50 ኢየሱስ ግን “ወዳጄ፣ እዚህ የተገኘህበት ዓላማ ምንድን ነው?” አለው።+ በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። 51 ሆኖም ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ሰዶ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።+ 52 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤+ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።+ 53  ለመሆኑ በዚህች ቅጽበት ከ12 ሌጌዎን* የሚበልጡ መላእክት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ የማልችል ይመስልሃል?+ 54 እንዲህ ከሆነ ታዲያ፣ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” 55 በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ አስተምር ነበር፤+ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም።+ 56 ይህ ሁሉ የሆነው ግን በነቢያት መጻሕፍት* የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።”+ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ።+

57  ኢየሱስን ያሰሩት ሰዎች ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ወደተሰበሰቡበት+ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ+ ወሰዱት። 58 ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላም መጨረሻውን ለማየት ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀመጠ።+

59 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል እየፈለጉ ነበር።+ 60 ይሁንና ብዙ የሐሰት ምሥክሮች ቢቀርቡም ምንም ማስረጃ አላገኙም።+ በኋላ ሁለት ሰዎች ቀርበው 61 “ይህ ሰው ‘የአምላክን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” አሉ።+ 62 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ቆሞ “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” አለው።+ 63 ኢየሱስ ግን ዝም አለ።+ ሊቀ ካህናቱም “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” አለው።+ 64 ኢየሱስም “አንተው ራስህ ተናገርከው። ነገር ግን እላችኋለሁ፦ ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ+ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ+ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”+ አለው። 65 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ እንዲህ አለ፦ “አምላክን ተሳድቧል! ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል? ስድቡን እንደሆነ እናንተም ሰምታችኋል። 66 እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” እነሱም “ሞት ይገባዋል”+ ብለው መለሱ። 67 ከዚያም ፊቱ ላይ ተፉበት፤+ በቡጢም መቱት።+ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት+ 68 “ክርስቶስ ሆይ፣ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን?” አሉት።

69 ጴጥሮስ ከቤት ውጭ፣ ግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት አገልጋይ ወደ እሱ መጥታ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው።+ 70 እሱ ግን “ስለ ምን እየተናገርሽ እንዳለ አላውቅም” በማለት በሁሉም ፊት ካደ። 71 ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሲሄድ ሌላ ሴት አየችውና በዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።+ 72 እሱም “ሰውየውን አላውቀውም!” ብሎ በመማል ዳግመኛ ካደ። 73 ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአካባቢው ቆመው የነበሩት መጥተው ጴጥሮስን “አነጋገርህ* ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አሉት። 74 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም!” በማለት ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። 75 ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ”+ ሲል ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

27 በነጋ ጊዜም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል አንድ ላይ ተማከሩ።+ 2 ካሰሩት በኋላ ወስደው ለአገረ ገዢው ለጲላጦስ አስረከቡት።+

3 አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ ጸጸት ተሰምቶት 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች* ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ይዞ በመምጣት+ 4 “ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነሱም “ታዲያ እኛ ምን አገባን? የራስህ ጉዳይ ነው!”* አሉት። 5 ስለዚህ የብር ሳንቲሞቹን ቤተ መቅደሱ ውስጥ በትኖ ወጣ። ከዚያም ሄደና ታንቆ ሞተ።+ 6 የካህናት አለቆቹ ግን የብር ሳንቲሞቹን ወስደው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለሆነ ግምጃ ቤት ውስጥ መግባት የለበትም” አሉ። 7 ከተመካከሩም በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። 8 በመሆኑም ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት”+ ተብሎ ይጠራል። 9 በዚህ ጊዜ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፦ “ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ የገመቱትን፣ ለሰውየው የወጣውን የዋጋ ተመን ይኸውም 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች ወሰዱ፤ 10 ይሖዋ* ባዘዘኝም መሠረት ሳንቲሞቹን ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉ።”+

11 ኢየሱስም አገረ ገዢው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዢውም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።+ 12 የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ በከሰሱት ጊዜ ግን ምንም መልስ አልሰጠም።+ 13 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “በስንት ነገር እየመሠከሩብህ እንዳሉ አትሰማም?” አለው። 14 እሱ ግን አገረ ገዢው እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም።

15 አገረ ገዢው ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚፈልጉትን ማንኛውንም እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።+ 16 በዚያን ጊዜ በዓመፀኝነቱ የታወቀ በርባን የተባለ እስረኛ ነበራቸው። 17 በመሆኑም ሕዝቡ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ወይስ ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። 18 ጲላጦስ ይህን ያለው አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው። 19 በተጨማሪም በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ “በእሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለተሠቃየሁ በዚያ ጻድቅ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት። 20 ይሁንና የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ በርባን እንዲፈታላቸው፣+ ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይጠይቁ ዘንድ ሕዝቡን አግባቡ።+ 21 አገረ ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነሱም “በርባንን” አሉ። 22 ጲላጦስም “እንግዲያው ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!”* አሉ።+ 23 እሱም “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ የባሰ መጮኻቸውን ቀጠሉ።+

24 ጲላጦስ ያደረገው ጥረት ምንም የፈየደው ነገር እንደሌለ ከዚህ ይልቅ ሁከት እያስነሳ መሆኑን በመገንዘብ “ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ። ከዚህ በኋላ ተጠያቂ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ” በማለት ውኃ አምጥቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። 25 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ መልሰው “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።+ 26 ከዚያም በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ+ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።+

27 በዚህ ጊዜ የአገረ ገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው መኖሪያ ቤት ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ።+ 28 ልብሱንም ገፈው ቀይ መጎናጸፊያ አለበሱት፤+ 29 የእሾህ አክሊል ጎንጉነውም በራሱ ላይ ደፉበት፤ በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት። በፊቱ ተንበርክከውም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ አሾፉበት። 30 ደግሞም ተፉበት፤+ መቃውንም ወስደው ራሱን ይመቱት ጀመር። 31 ሲያፌዙበት ከቆዩ በኋላም መጎናጸፊያውን ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት፤ ከዚያም በእንጨት ላይ እንዲቸነከር ይዘውት ሄዱ።+

32 እየሄዱም ሳሉ ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው አገኙ። ሰውየውንም ኢየሱስ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት* እንዲሸከም አስገደዱት።*+ 33 የራስ ቅል ቦታ የሚል ትርጉም ወዳለው ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ+ በደረሱ ጊዜ 34 ሐሞት* የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤+ እሱ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው አልፈለገም። 35 እንጨት ላይ ከቸነከሩት በኋላ ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ፤+ 36 በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37 እንዲሁም “ይህ የአይሁዳውያን ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚገልጽ ጽሑፍ ከራሱ በላይ አንጠልጥለው ነበር።+

38 በዚያን ጊዜ ሁለት ዘራፊዎች ከእሱ ጋር፣ አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ተሰቅለው ነበር።+ 39 በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡት ነበር፤+ ራሳቸውንም እየነቀነቁ+ 40 “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ፣+ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት* ላይ ውረድ!” ይሉት ነበር።+ 41 የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ጀመር፦+ 42 “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ+ ከሆነ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት* ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። 43 በአምላክ ታምኗል፤ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’+ ብሎ የለ፤ አምላክ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው።”+ 44 ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉት ዘራፊዎችም እንኳ ሳይቀሩ ልክ እንደዚሁ ይነቅፉት ነበር።+

45 ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አገሩ በሙሉ በጨለማ ተሸፈነ።+ 46 በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ይህም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው።+ 47 በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር።+ 48 ወዲያውኑም ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ ሰፍነግ* ወስዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው።+ 49 የቀሩት ግን “ተወው! ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። 50 ኢየሱስ ዳግመኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ።*+

51 በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ+ ከላይ እስከ ታች+ ለሁለት ተቀደደ፤+ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጣጠቁ። 52 መቃብሮችም ተከፈቱ፤ በሞት ካንቀላፉት ቅዱሳን ሰዎች መካከልም የብዙዎቹ አስከሬኖች ወጡ፤ 53  ብዙ ሰዎችም አዩአቸው። (ኢየሱስ ከተነሳ በኋላ ሰዎች ከመቃብር ስፍራው ወጥተው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ገቡ።)* 54 ሆኖም መኮንኑና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች የምድር ነውጡንና የተከሰቱትን ነገሮች ሲመለከቱ እጅግ ፈርተው “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አሉ።+

55 ኢየሱስን ለማገልገል ከገሊላ ጀምሮ አብረውት የነበሩ ብዙ ሴቶችም+ እዚያ ሆነው ከሩቅ ይመለከቱ ነበር፤ 56 ከእነሱም መካከል መግደላዊቷ ማርያም፣ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙ ነበር።+

57  ቀኑ በመገባደድ ላይ ሳለ የአርማትያስ ሰው የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሀብታም መጣ፤ እሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር።+ 58 ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጠየቀ።+ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ።+ 59 ከዚያም ዮሴፍ አስከሬኑን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ገነዘው፤+ 60 ከዓለት ፈልፍሎ በሠራው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥም አኖረው።+ ከዚያም አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋውና ሄደ። 61 በዚህ ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም ከመቃብሩ ፊት ለፊት እዚያው ተቀምጠው ነበር።+

62 እነዚህ ነገሮች የተከናወኑት ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ቀን+ ነበር። በማግስቱም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን አንድ ላይ ተሰብስበው ጲላጦስ ፊት ቀረቡና 63 እንዲህ አሉ፦ “ክቡር ሆይ፣ ያ አስመሳይ በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሳለሁ’ ብሎ የተናገረው ትዝ አለን።+ 64 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና+ ለሕዝቡ ‘ከሞት ተነስቷል!’ እንዳይሉ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን። አለዚያ ይህ የኋለኛው ማታለያ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል።” 65 ጲላጦስም “ጠባቂዎች መውሰድ ትችላላችሁ። ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው። 66 ስለዚህ ሄደው ድንጋዩ ላይ ማኅተም በማድረግ መቃብሩን አሸጉ፤ ጠባቂም አቆሙ።

28 ከሰንበት ቀን በኋላ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን* ጎህ ሲቀድ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ለማየት መጡ።+

2 እነሆም የይሖዋ* መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ መልአኩም መጥቶ ድንጋዩን አንከባለለውና በላዩ ተቀመጠ።+ 3 መልኩ እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።+ 4 ጠባቂዎቹ እሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።

5 ሆኖም መልአኩ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ።+ 6 አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም።+ ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ። 7 ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።+ እዚያም ታዩታላችሁ’ በሏቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።”+

8 ስለዚህ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተውጠው ከመታሰቢያ መቃብሩ በፍጥነት በመውጣት ወሬውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።+ 9 ወዲያውም ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡና እግሩን ይዘው ሰገዱለት።* 10 ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው።

11 ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ+ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው። 12 የካህናት አለቆቹም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች* በመስጠት 13 እንዲህ አሏቸው፦ “‘ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት’ በሉ።+ 14 አትጨነቁ፤ ወሬው ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን።”* 15 እነሱም የብር ሳንቲሞቹን ተቀብለው እንደታዘዙት አደረጉ፤ ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዳውያን ዘንድ በስፋት ይወራል።

16 ይሁንና የኢየሱስ 11 ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ለመገናኘት በገሊላ ወደሚገኘው፣ እሱ ወደነገራቸው ተራራ ሄዱ።+ 17 ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤* አንዳንዶች ግን ተጠራጠሩ። 18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።+ 19 ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤+ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣+ 20 ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።+ እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ* መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”+

“ቅቡዕ፤ መሲሕ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የትውልድ ሐረግ።”

በሥራ ላይ ያለን ኃይል ያመለክታል።

በአይሁዳውያን ባሕል መሠረት የተጫጩ ሰዎች እንደተጋቡ ይቆጠራል።

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ “ይሖዋ” የሚለው መለኮታዊ ስም ከሚገኝባቸው 237 ቦታዎች ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።ከተጨማሪው መረጃ ላይ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የሹዋ ወይም ኢያሱ ከተባለው የዕብራይስጥ ስም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሰብአ ሰገል።”

ወይም “እጅ ልንነሳው።”

ወይም “መሲሑ፤ የተቀባው።”

ወይም “እጅ ነሱት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

“ቀንበጥ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሳይሆን አይቀርም።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ይነከሩ፤ ይጠልቁ።”

እህልን ከገለባው ለመለየት የሚያገለግል ከእንጨት የሚሠራ እንደ አካፋ ያለ መሣሪያ ነው።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በቤተ መቅደሱ ጣሪያ ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።

ሜድትራንያን ባሕር ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ግን ገሊላ ባሕር ነው ይላሉ።

በመሠረቱ ባሕር ሳይሆን ሐይቅ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌንሴሬጥ ሐይቅ፣ ገሊላ ባሕር እንዲሁም ጥብርያዶስ ባሕር ተብሎ ተጠርቷል።

ወይም “አሥሩ ከተሞች ከሚገኙበት ክልል።”

ወይም “መንፈስ ለማግኘት የሚለምኑ፤ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ።”

ወይም “የዋሆች።”

ወይም “ይረካሉና።”

ወይም “ሰላማውያን።”

እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።

“መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ ያልሆነ” ማለት ነው።

“መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ የሆነ” ማለት ነው።

የአይሁዳውያንን የሳንሄድሪን ሸንጎ ያመለክታል።

ከኢየሩሳሌም ውጭ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የመጨረሻዋን ትንሽ ሳንቲምህን።” ቃል በቃል “የመጨረሻዋን ኳድራንስ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “አንድ ማይል።” ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የግዳጅ አገልግሎት እንድትፈጽም ቢያስገድድህ።”

ያለወለድ መበደር የሚፈልግን ሰው ያመለክታል።

ወይም “ሙሉ።”

ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የተቀደሰ ይሁን፤ ብሩክ ይሁን።”

ወይም “ፈቃድህ በሰማይ እንዲሁም በምድር ይሁን።”

ቃል በቃል “ዳቧችንን።”

ቃል በቃል “የሌሎችን ዕዳ።”

ቃል በቃል “ዕዳችንን።”

ወይም “ታደገን።”

ወይም “ራሳቸውን ይጥላሉ።”

ወይም “ማከማቸት ተዉ።”

ወይም “አጥርቶ የሚያይ።” ቃል በቃል “ቀላል።”

ወይም “በብርሃን የተሞላ።”

ቃል በቃል “መጥፎ፤ ክፉ።”

ወይም “ነፍሳችሁ።”

ወይም “መጨነቃችሁን ተዉ።”

ወይም “ነፍስ።”

ለ14ን ተመልከት።

ወይም “መፈለጋችሁን ቀጥሉ።”

ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”

ወይም “እሱን እጅ በመንሳት።”

ወይም “ለምን ትርበተበታላችሁ?”

ማር 5:1 እና ሉቃስ 8:26 ላይ ጌርጌሴኖን ተብሎም ተጠርቷል።

ወይም “ገደላማ ከሆነው የባሕሩ ዳርቻ።”

ኢየሱስ በገሊላ ሲያገለግል አብዛኛውን ጊዜ ይቀመጥባት የነበረችውን ቅፍርናሆም የተባለች ከተማ ያመለክታል።

ወይም “እጅ በመንሳት።”

ወይም “ቀናተኛው።”

ወይም “ትርፍ ልብስ።”

የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።

ወይም “የሚጸና።”

ወይም “ደቀ መዝሙር።”

የአጋንንት አለቃ ወይም ገዢ ለሆነው ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።

ወይም “ሕይወትን።” የወደፊት ሕይወት ተስፋን ያመለክታል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “አሳሪዮን።” ለ14ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሕይወቱን።”

ወይም “ሕይወቱን።”

ወይም “ለስላሳ ልብስ።”

ወይም “ትክክል መሆኗ።”

ወይም “በውጤቷ።”

እነዚህ የአይሁዳውያን ከተሞች አልነበሩም።

ወይም “ሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ቀንበሬን አብራችሁኝ ተሸከሙ።”

ወይም “ደቀ መዛሙርቴም ሁኑ።”

“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሻካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ለነፍሳችሁም።”

ወይም “ለመሸከም የማያስቸግር።”

ወይም “ሽባ የሆነ።”

ወይም “የምወደውና ነፍሴ ደስ የምትሰኝበት።”

ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።

ወይም “ተከታዮቻችሁ።”

ወይም “መሳሳታችሁን የሚነግሯችሁ።”

ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ለአምላክ ታማኝ ያልሆነ።”

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

በአጠቃላይ 10 ኪሎ ግራም ገደማ ይሆናል።

“ዓለም ከተመሠረተበት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “የአራተኛው ክፍል ገዢ።”

ሄሮድስ አንቲጳስን ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ብዙ ስታዲዮን።” አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው።

ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ 12 ሰዓት ገደማ ላይ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሰዓት ያመለክታል።

ወይም “እጅ ነሱት።”

ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አለመንጻትን ያመለክታል።

ወይም “የሚያንቋሽሽ።”

ፖርኒያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አለመንጻትን ያመለክታል።

ወይም “ከነአናዊት።”

ወይም “እጅ ነሳችው።”

ወይም “ለአምላክ ታማኝ ያልሆነ።”

ወይም “ይህን የገለጠልህ ሰው ሳይሆን።”

ወይም “የሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ሰይጣን” የሚለው ቃል ተቃዋሚ የሚል ትርጉም ስላለው ኢየሱስ ጴጥሮስን “ተቃዋሚ” ብሎ መጥራቱ ነበር።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ለነፍሱ።”

ወይም “ነጭ ሆነ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ሁለት ድራክማ።” ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ስታቴር ሳንቲም።” ቴትራድራክማ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ካልተለወጣችሁና።”

ወይም “በአህያ የሚዞር የወፍጮ ድንጋይ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

“አባታችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ውቀሰው።”

ቃል በቃል “በሁለት ወይም በሦስት ምሥክሮች አፍ።”

ቃል በቃል “70 ጊዜ 7።”

10,000 የብር ታላንት ከ60,000,000 ዲናር ጋር እኩል ነው። ለ14ን ተመልከት።

ወይም “እጅ በመንሳት።”

ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “በአንድ ቀንበር ያጣመደውን።”

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ኢየሱስ እንዲባርካቸውና።”

ወይም “ከባረካቸው።”

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ሙሉ።”

ወይም “በዳግም ፍጥረት።”

ለ14ን ተመልከት።

ለ14ን ተመልከት።

ለ14ን ተመልከት።

ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ለጋስ።”

ቃል በቃል “መጥፎ ሆነ፤ ክፉ ሆነ።”

ወይም “ወደ እሱ ቀርባ እጅ እየነሳች።”

ወይም “ነፍሱን።”

“ተቀመጠባቸው” የሚለው ቃል በመደረቢያዎቹ ላይ እንደተቀመጠ ያሳያል።

ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ሰማይ።”

ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።” እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል ሁለት የሕንጻ ግድግዳዎች የሚገናኙበት ማዕዘን አናት ላይ የሚቀመጥ ድንጋይን ያመለክታል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሊያስሩት።”

ወይም “ትክክል ነው ወይስ አይደለም?”

ለ14ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ስለ ክርስቶስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የሌሎችን ሸክም ለማቅለል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል።

አይሁዳውያን ወንዶች በግንባራቸውና በግራ ክንዳቸው ላይ የሚያስሩት የሕጉን አራት ክፍሎች የያዘ ማኅደር።

ወይም “የተሻለውን መቀመጫ ማግኘት።”

ወይም “መምህር።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ዝርፊያና።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቤተ መቅደሱን ያመለክታል።

“ወና ሆኖ ይቀርላችኋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ሕገ ወጥነት።”

ወይም “የሚጸና።”

በዚያ ወቅት የሚሠሩት አብዛኞቹ ቤቶች ጠፍጣፋ ጣሪያ የነበራቸው ሲሆን ሰዎች በጣሪያው ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር።

ሥራ 1:12 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከሰሜን፣ ከምሥራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ አቅጣጫ የሚነፍሱ ነፋሳትን ያመለክታል።

በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሌሊት በስንት ሰዓት።”

ወይም “ጥበበኛ።”

ወይም “ለሁለት ይቆርጠዋል።”

ወይም “ጥበበኞች።”

የግሪኩ ታላንት 20.4 ኪሎ ግራም ነው። ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ብር።” ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።

ቃል በቃል “ብሬን።”

ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።

በቂ ልብስ አለመልበስን ያመለክታል።

ቃል በቃል “መቆረጥ፤ መገረዝ።” ከሕይወት መቆረጥን ያመለክታል።

ወይም “የማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ለማሰርና።”

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች።”

ወይም “ፈቃደኛ።”

የሰው ዘር ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለው መሆኑን ያመለክታል።

“ሌጌዎን” በጥንት የሮም ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ አንድን ትልቅ ክፍለ ሠራዊት ያመለክት ነበር። እዚህ ላይ ቃሉ ብዛትን ያመለክታል።

ወይም “ቅዱሳን መጻሕፍት።”

ወይም “አፍህ።”

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።

ወይም “እሱ የአንተ ችግር ነው!”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “በመሸከም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አደረጉት።”

“ከዕፀዋት የሚዘጋጅ የማደንዘዝ ባሕርይ ያለው መራራ ንጥረ ነገር ሳይሆን አይቀርም።”

የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።

ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።

ወይም “ሞተ።”

በቅንፍ ውስጥ ያለው ሐሳብ ከጊዜ በኋላ የተከናወነውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው።

ይህ ቀን በአሁኑ ጊዜ እሁድ ተብሎ የሚጠራው ቀን ነው። ለአይሁዳውያን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ነበር።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እጅ ነሱት።”

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።

ቃል በቃል “እናሳምነዋለን።”

ወይም “እጅ ነሱት።”

ወይም “ዘመኑ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ