የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ማርቆስ 1:1-16:8
  • ማርቆስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማርቆስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ማርቆስ

የማርቆስ ወንጌል

1 የአምላክ ልጅ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸው ምሥራች የሚጀምረው እንደሚከተለው ነው፦ 2 ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “(እነሆ፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ፤ እሱም መንገድህን ያዘጋጃል።)*+ 3 አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን* መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናዎቹንም አቅኑ’ በማለት ይጮኻል።”+ 4 አጥማቂው ዮሐንስ ለኃጢአት ይቅርታ፣ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት በምድረ በዳ እየሰበከ ነበር።+ 5 መላው የይሁዳ ምድር እንዲሁም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሙሉ ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤ ደግሞም ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ* ነበር።+ 6 ዮሐንስ የግመል ፀጉር ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ+ የነበረ ሲሆን አንበጣና የዱር ማር ይበላ ነበር።+ 7 እንዲህ እያለም ይሰብክ ነበር፦ “ከእኔ በኋላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ ጎንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።+ 8 እኔ በውኃ አጠመቅኳችሁ፤ እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።”+

9 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት መጥቶ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በዮሐንስ ተጠመቀ።+ 10 ወዲያው ከውኃው እንደወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ አየ።+ 11 ከዚያም “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።+

12 ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ገፋፋው። 13 በምድረ በዳም 40 ቀን ቆየ። በዚያ ሳለ ሰይጣን ፈተነው፤+ ከአራዊትም ጋር ነበረ። መላእክትም ያገለግሉት ነበር።+

14 ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ ኢየሱስ የአምላክን ምሥራች እየሰበከ+ ወደ ገሊላ ሄደ።+ 15 “የተወሰነው ጊዜ ደርሷል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ንስሐ ግቡ፤+ በምሥራቹም እመኑ” ይል ነበር።

16 በገሊላ ባሕር* አጠገብ እየሄደ ሳለ ዓሣ አጥማጆች የነበሩት+ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ+ መረቦቻቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ አየ።+ 17 ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+ 18 እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+ 19 ትንሽ እልፍ እንዳለ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ጀልባቸው ላይ ሆነው መረቦቻቸውን ሲጠግኑ+ አያቸውና 20 ወዲያውኑ ጠራቸው። እነሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር ጀልባው ላይ ትተው ተከተሉት። 21 ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ።

የሰንበት ቀን እንደደረሰም ወደ ምኩራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ።+ 22 እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበረ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።+ 23 በዚሁ ጊዜ በምኩራባቸው ውስጥ የነበረ፣ ርኩስ መንፈስ የያዘው አንድ ሰው በኃይል ጮኾ እንዲህ አለ፦ 24 “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን?+ የመጣኸው ልታጠፋን ነው? ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ ነህ!”+ 25 ሆኖም ኢየሱስ “ዝም በል፤ ከእሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። 26 ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእሱ ወጣ። 27 ሕዝቡ ሁሉ እጅግ በመገረም እርስ በርሳቸው “ይህ ምንድን ነው? ትምህርቱ ለየት ያለ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ሳይቀር በሥልጣን ያዛል፤ እነሱም ይታዘዙለታል” ተባባሉ። 28 ወዲያውኑም በመላው የገሊላ ግዛት በየአቅጣጫው ስለ እሱ በስፋት ተወራ።

29 በዚህ ጊዜ ከምኩራብ ወጥተው ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ሄዱ።+ 30 የስምዖን አማት+ ትኩሳት ይዟት ተኝታ ነበር፤ ስለ እሷም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። 31 እሱም ወደተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሳት። በዚህ ጊዜ ትኩሳቱ ለቀቃትና ታገለግላቸው ጀመር።

32 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ ሰዎች የታመሙትንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤+ 33 የከተማዋም ሰው ሁሉ በደጅ ተሰብስቦ ነበር። 34 ኢየሱስም በተለያየ በሽታ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ፈወሰ፤+ ብዙ አጋንንትንም አወጣ። ሆኖም አጋንንቱ ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ስለነበር* እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።

35 ኢየሱስ በማለዳ ገና ጎህ ሳይቀድ ተነስቶ ከቤት ወጣና ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ፤ እዚያም መጸለይ ጀመረ።+ 36 ይሁን እንጂ ስምዖንና ከእሱ ጋር የነበሩት አጥብቀው ፈለጉት፤ 37 ባገኙትም ጊዜ “ሰው ሁሉ እየፈለገህ ነው” አሉት። 38 እሱ ግን “በዚያም እንድሰብክ በአቅራቢያ ወዳሉት ከተሞች እንሂድ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው።+ 39 እንዳለውም በምኩራቦቻቸው እየሰበከና አጋንንትን እያወጣ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+

40 በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰውም ወደ እሱ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ተንበርክኮ ተማጸነው።+ 41 በዚህ ጊዜ በጣም አዘነለትና እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ከዚያም “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው።+ 42 ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀውና ነጻ። 43 ከዚያም ኢየሱስ ሰውየውን በጥብቅ አስጠንቅቆ ቶሎ አሰናበተው፤ 44 እንዲህም አለው፦ “ለማንም አንዳች ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዛቸውንም ነገሮች አቅርብ፤+ ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ።”+ 45 ሰውየው ግን ከሄደ በኋላ የሆነውን ነገር በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም በየቦታው አሰራጨ፤ ስለሆነም ኢየሱስ ከዚህ በኋላ በግልጽ ወደ ከተማ መግባት ባለመቻሉ ከከተማ ውጭ ገለል ባሉ ቦታዎች ይኖር ጀመር። ይሁንና ሰዎች ከየአቅጣጫው ወደ እሱ መምጣታቸውን ቀጠሉ።+

2 ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ተመልሶ መጣ፤ ደግሞም ቤት ውስጥ እንዳለ ተወራ።+ 2 በመሆኑም ቤቱ ሞልቶ ደጅ ላይ እንኳ ቦታ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ እሱም የአምላክን ቃል ይነግራቸው ጀመር።+ 3 ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እሱ አመጡ።+ 4 ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ስላልቻሉ ከኢየሱስ በላይ ያለውን ጣሪያ ከነደሉ በኋላ ሽባው የተኛበትን ቃሬዛ ወደ ታች አወረዱት። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት+ ሽባውን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+ 6 በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ግን እንዲህ ሲሉ በልባቸው አሰቡ፦+ 7 “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?”+ 8 ሆኖም ኢየሱስ በልባቸው ይህን እያሰቡ እንዳሉ ወዲያው በመንፈሱ ተረድቶ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?+ 9 ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል? 10 ይሁንና የሰው ልጅ+ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .”+ ካለ በኋላ ሽባውን እንዲህ አለው፦ 11 “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ።” 12 በዚህ ጊዜ ሽባው ብድግ ብሎ ወዲያው ቃሬዛውን በማንሳት በሁሉ ፊት እየተራመደ ወጣ። ይህን ሲያዩ ሁሉም እጅግ ተደነቁ፤ ደግሞም “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም”+ በማለት አምላክን አከበሩ።

13 ኢየሱስ እንደገና ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደ፤ ሕዝቡም ወደ እሱ ጎረፈ፤ እሱም ያስተምራቸው ጀመር። 14 በመንገድ እያለፈ ሳለም የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየውና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው።+ 15 በኋላም በሌዊ ቤት ተቀምጦ እየበላ ነበር፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞችም ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየበሉ ነበር። ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ እሱን መከተል ጀምረው ነበር።+ 16 ሆኖም ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ጸሐፍት ከኃጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲበላ ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “እንዴት ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል?” አሏቸው። 17 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው” አላቸው።+

18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን የመጾም ልማድ ነበራቸው። ስለዚህም ወደ እሱ መጥተው “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ዘወትር ሲጾሙ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።+ 19 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው+ ከእነሱ ጋር እያለ ጓደኞቹ የሚጾሙበት ምን ምክንያት አለ? ሙሽራው አብሯቸው እስካለ ድረስ ሊጾሙ አይችሉም። 20 ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤+ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 21 በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ አሮጌውን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋል።+ 22 እንዲሁም ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ይሁንና አዲስ የወይን ጠጅ የሚቀመጠው በአዲስ አቁማዳ ነው።”

23 በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ አብረውት ይሄዱ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።+ 24 በመሆኑም ፈሪሳውያን “ተመልከት! በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?” አሉት። 25 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት የሚበላው ባጣ ጊዜ እንዲሁም እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?+ 26 ሊቀ ካህናት ስለሆነው ስለ አብያታር+ በሚናገረው ታሪክ ላይ ዳዊት ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ማንም እንዲበላ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩትም እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?” 27 ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሰጠ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም።+ 28 በመሆኑም የሰው ልጅ የሰንበትም እንኳ ጌታ ነው።”+

3 ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ 2 ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 3 እሱም እጁ የሰለለበትን* ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” አለው። 4 ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት* ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።+ እነሱ ግን ዝም አሉ። 5 በልባቸው ደንዳናነት+ በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። 6 ፈሪሳውያኑ ወጥተው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር በመሰብሰብ እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ።

7 ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጣ ብዙ ሕዝብም ተከተለው።+ 8 ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች የሰሙ ብዙ ሰዎች ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስና ከዮርዳኖስ ማዶ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ እንኳ ሳይቀር ወደ እሱ መጡ። 9 ኢየሱስም ሕዝቡ እንዳያጨናንቀው አንዲት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። 10 ብዙ ሰዎችን ፈውሶ ስለነበር ከባድ በሽታ የያዛቸው ሁሉ እሱን ለመንካት በዙሪያው ይጋፉ ነበር።+ 11 ርኩሳን መናፍስት+ እንኳ ሳይቀሩ ባዩት ቁጥር በፊቱ ወድቀው “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር።+ 12 ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በተደጋጋሚ አጥብቆ አዘዛቸው።+

13 ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ጠራ፤+ እነሱም ወደ እሱ መጡ።+ 14 ከዚያም 12 ሰዎች መርጦ ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤* እነዚህ አብረውት የሚሆኑ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ለስብከት ሥራ የሚልካቸውና 15 አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን የሚሰጣቸው ናቸው።+

16 የመረጣቸውም* 12 ሐዋርያት+ እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣+ 17 የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ (እነዚህን ቦአኔርጌስ ብሎ የሰየማቸው ሲሆን ትርጉሙም “የነጎድጓድ ልጆች” ማለት ነው)፣+ 18 እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው* ስምዖን 19 እንዲሁም በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

ከዚያ በኋላ ወደ አንድ ቤት ሄደ፤ 20 ዳግመኛም ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ ከዚህም የተነሳ እህል እንኳ መቅመስ አልቻሉም። 21 ዘመዶቹ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ሊይዙት መጡ።+ 22 ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም “ብዔልዜቡል* አለበት፤ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር።+ 23 በመሆኑም ወደ እሱ ከጠራቸው በኋላ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? 24 አንድ መንግሥት እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ መንግሥት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፤+ 25 አንድ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ጸንቶ ሊቆም አይችልም። 26 በተመሳሳይም ሰይጣን በራሱ ላይ የሚነሳና የሚከፋፈል ከሆነ ያከትምለታል እንጂ ሊጸና አይችልም። 27 ደግሞም ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት የገባ ሰው በቅድሚያ ብርቱውን ሰው ሳያስር ንብረቱን ሊሰርቅ አይችልም። ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። 28 እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠሩ ወይም ምንም ዓይነት የስድብ ቃል ቢናገሩ ሁሉም ይቅር ይባልላቸዋል። 29 ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም፤+ ከዚህ ይልቅ ለዘላለም የሚጠየቅበት ኃጢአት ይሆንበታል።”+ 30 ይህን ያለው “ርኩስ መንፈስ አለበት” ይሉ ስለነበር ነው።+

31 በዚህ ጊዜ እናቱና ወንድሞቹ+ መጡ፤ ውጭ ቆመውም ሰው ልከው አስጠሩት።+ 32 በዙሪያውም ብዙ ሰዎች ተቀምጠው ስለነበር “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ሆነው እየጠሩህ ነው” አሉት።+ 33 እሱ ግን መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ እነማን ናቸው?” አላቸው። 34 ከዚያም ዙሪያውን ከበው ወደተቀመጡት ሰዎች ተመልክቶ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!+ 35 የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው።”+

4 ዳግመኛም በባሕሩ አጠገብ ሆኖ ያስተምር ጀመር፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ወደ እሱ መጥቶ ተሰበሰበ። በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን በባሕሩ ዳርቻ ነበር።+ 2 ከዚያም ብዙ ነገር በምሳሌ ያስተምራቸው ጀመር፤+ እንዲህም አላቸው፦+ 3 “ስሙ። እነሆ፣ ዘሪው ሊዘራ ወጣ።+ 4 በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው። 5 ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።+ 6 ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ። 7 ሌሎቹ ዘሮች ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው፤ ፍሬም አልሰጡም።+ 8 ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወድቀው ከበቀሉና ካደጉ በኋላ ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ ደግሞም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ አፈሩ።”+ 9 ከዚያም “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።+

10 ብቻውን በሆነ ጊዜ አሥራ ሁለቱና በዙሪያው የነበሩት ሌሎች ሰዎች ስለ ምሳሌዎቹ ይጠይቁት ጀመር።+ 11 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር+ የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን የሚሰሙት ነገር ሁሉ እንዲሁ ምሳሌ ብቻ ሆኖ ይቀርባቸዋል፤+ 12 በመሆኑም ማየቱን ያያሉ ግን ልብ አይሉም፤ መስማቱን ይሰማሉ ግን ትርጉሙን አይረዱም፤ ደግሞም ሙሉ በሙሉ ስለማይመለሱ ይቅርታ አያገኙም።”+ 13 በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ምሳሌ ካልተረዳችሁ ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ትረዳላችሁ?

14 “ዘሪው ቃሉን ይዘራል።+ 15 ቃሉ ሲዘራ መንገድ ዳር እንደወደቁት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ ግን ሰይጣን መጥቶ+ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል።+ 16 በተመሳሳይም በድንጋያማ መሬት እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ በደስታ ይቀበሉታል።+ 17 ሆኖም ቃሉ በውስጣቸው ሥር ስለማይሰድ የሚቆዩት ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም በቃሉ የተነሳ መከራ ወይም ስደት ሲደርስባቸው ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። 18 በእሾህ መካከል እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑ ሌሎች ደግሞ አሉ። እነዚህ ቃሉን የሰሙ ናቸው፤+ 19 ይሁንና የዚህ ሥርዓት* ጭንቀትና+ ሀብት ያለው የማታለል ኃይል+ እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት+ ወደ ልባቸው ሰርጎ በመግባት ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል። 20 በመጨረሻም፣ ጥሩ አፈር ላይ እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት ቃሉን የሚሰሙና በደስታ የሚቀበሉ እንዲሁም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ የሚያፈሩ ናቸው።”+

21 ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “መብራት አምጥቶ እንቅብ* የሚደፋበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጠው ይኖራል? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለም?+ 22 ስለዚህ የተሸሸገ መገለጡ፣ የተሰወረም ይፋ መውጣቱ አይቀርም።+ 23 የሚሰማ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ።”+

24 አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “የምትሰሙትን ነገር ልብ በሉ።+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25 ላለው ይጨመርለታልና፤+ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።”+

26 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት መሬት ላይ ዘር የሚዘራን ሰው ይመስላል። 27 ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ማለዳም ይነሳል፤ እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። 28 መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል። 29 ሰብሉ እንደደረሰ ግን የመከር ወቅት በመሆኑ ሰውየው ማጭዱን ይዞ ያጭዳል።”

30 ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የአምላክን መንግሥት ከምን ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን? ወይስ በምን ምሳሌ ልንገልጸው እንችላለን? 31 መሬት ላይ በተዘራች ጊዜ በምድር ላይ ካሉ ዘሮች ሁሉ እጅግ የምታንስን የሰናፍጭ ዘር ይመስላል።+ 32 ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከሌሎች ተክሎች ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ ትላልቅ ቅርንጫፎችም ታወጣለች፤ በመሆኑም የሰማይ ወፎች በጥላዋ ሥር መስፈሪያ ያገኛሉ።”

33 ኢየሱስ እንዲህ የመሳሰሉ በርካታ ምሳሌዎችን+ ተጠቅሞ መረዳት በሚችሉት መጠን ቃሉን ይነግራቸው ነበር። 34 እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም ነገር ያብራራላቸው ነበር።+

35 በዚያ ቀን፣ ምሽት ላይ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው።+ 36 በመሆኑም ሕዝቡን ካሰናበቱ በኋላ እዚያው ጀልባዋ ውስጥ እንዳለ ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ።+ 37 በዚህ ጊዜ እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ፤ ማዕበሉም ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።+ 38 ኢየሱስ ግን በጀልባዋ የኋለኛ ክፍል ትራስ* ተንተርሶ ተኝቶ ነበር። ስለዚህ ቀስቅሰውት “መምህር፣ ስናልቅ ዝም ብለህ ታያለህ?” አሉት። 39 በዚህ ጊዜ ተነስቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው።+ ነፋሱ ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ። 40 ከዚያም “ለምን ትሸበራላችሁ?* አሁንም እምነት የላችሁም?” አላቸው። 41 እነሱ ግን በታላቅ ፍርሃት ተውጠው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ።+

5 ከዚያም ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻግረው ጌርጌሴኖን+ ወደተባለው ክልል ደረሱ። 2 ኢየሱስ ከጀልባ እንደወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ከእሱ ጋር ተገናኘ። 3 ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ይኖር የነበረ ሲሆን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሰንሰለት እንኳ አጥብቆ ሊያስረው የቻለ አንድም ሰው አልነበረም። 4 ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር የነበረ ቢሆንም ሰንሰለቱን ይበጣጥስ፣ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፤ እሱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል ጉልበት ያለው አንድም ሰው አልነበረም። 5 ዘወትር ሌሊትና ቀን በመቃብር ቦታና በተራሮች ላይ ይጮኽ እንዲሁም ሰውነቱን በድንጋይ ይተለትል ነበር። 6 ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ግን ወደ እሱ ሮጦ በመሄድ ሰገደለት።+ 7 ከዚያም በታላቅ ድምፅ እየጮኸ “የልዑል አምላክ ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በአምላክ ስም አስምልሃለሁ” አለው።+ 8 ይህን ያለው ኢየሱስ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ”+ ብሎት ስለነበር ነው። 9 ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “ብዙ ስለሆንን ስሜ ሌጌዎን* ነው” ብሎ መለሰለት። 10 መናፍስቱን ከአገሪቱ እንዳያስወጣቸውም ኢየሱስን ተማጸነው።+

11 በዚያም በተራራው ላይ ብዙ የአሳማ+ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።+ 12 ርኩሳን መናፍስቱም “አሳማዎቹ ውስጥ እንድንገባ ወደ እነሱ ስደደን” ብለው ተማጸኑት። 13 እሱም ፈቀደላቸው። በዚህ ጊዜ ርኩሳን መናፍስቱ ወጥተው አሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ወደ 2,000 የሚጠጉ አሳማዎችም ከገደሉ አፋፍ* እየተንደረደሩ በመውረድ ባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ። 14 የአሳማዎቹ እረኞች ግን ሸሽተው በመሄድ ወሬውን በከተማውና በገጠሩ አዳረሱ፤ ሰዎችም የሆነውን ነገር ለማየት መጡ።+ 15 ወደ ኢየሱስም መጥተው ጋኔን ያደረበትን ይኸውም ቀደም ሲል ሌጌዎን የነበረበትን ሰው ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ተቀምጦ አዩት፤ በዚህ ጊዜ ፍርሃት አደረባቸው። 16 የተፈጸመውንም ነገር ያዩ ሰዎች አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለና በአሳማዎቹ ላይ የሆነውን ነገር አወሩላቸው። 17 በመሆኑም አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ኢየሱስን ይማጸኑት ጀመር።+

18 ኢየሱስ ወደ ጀልባው በመውጣት ላይ ሳለ ጋኔን አድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ይሄድ ዘንድ ተማጸነው።+ 19 ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ከዚህ ይልቅ “ወደ ቤት ሄደህ ይሖዋ * ያደረገልህን ነገር ሁሉና ያሳየህን ምሕረት ለዘመዶችህ ንገራቸው” አለው። 20 ሰውየውም ሄዶ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በሙሉ በዲካፖሊስ* ያውጅ ጀመር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተደነቁ።

21 ኢየሱስ በጀልባ ዳግመኛ ወደ ባሕሩ ማዶ ከተሻገረ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ ተሰበሰበ፤ እሱም በባሕሩ አጠገብ ነበር።+ 22 በዚህ ጊዜ ከምኩራብ አለቆች አንዱ የሆነ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው ወደዚያ መጣ፤ ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እግሩ ላይ ወደቀ።+ 23 ከዚያም “ትንሿ ልጄ በጠና ታምማለች።* እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር፣ እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት”+ በማለት ደጋግሞ ተማጸነው። 24 ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከትሎት እየተጋፋው ይሄድ ነበር።

25 በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት+ የኖረች አንዲት ሴት ነበረች።+ 26 ይህች ሴት በርካታ ሐኪሞች ጋር የሄደች ሲሆን ሕክምናው ለብዙ ሥቃይ ዳርጓት ነበር፤ ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም። 27 ስለ ኢየሱስ የተወራውን በሰማች ጊዜ በሰዎች መካከል ከኋላው መጥታ ልብሱን ነካች፤+ 28 ምክንያቱም “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበር።+ 29 ወዲያውም ይፈሳት የነበረው ደም ቆመ፤ ያሠቃያት ከነበረው ሕመም እንደተፈወሰችም ታወቃት።

30 ወዲያውኑ ኢየሱስ ኃይል ከእሱ እንደወጣ ታወቀው፤+ በመሆኑም ወደ ሕዝቡ በመዞር “ልብሴን የነካው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።+ 31 ደቀ መዛሙርቱ ግን “ሕዝቡ እንዲህ ሲጋፋህ እያየህ ‘የነካኝ ማን ነው?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። 32 ይሁንና ኢየሱስ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33 ሴትየዋ በእሷ ላይ የተፈጸመውን ነገር ስላወቀች በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ምንም ሳታስቀር እውነቱን ነገረችው። 34 እሱም “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤+ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” አላት።+

35 ገና እየተናገረ ሳለ ከምኩራብ አለቃው ቤት የመጡ ሰዎች “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት።+ 36 ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ሰምቶ የምኩራብ አለቃውን “አትፍራ፤ ብቻ እመን” አለው።+ 37 ከዚህ በኋላ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በስተቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም።+

38 ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት በደረሱም ጊዜ ትርምሱን እንዲሁም የሚያለቅሱትንና ዋይ ዋይ የሚሉትን ሰዎች ተመለከተ።+ 39 ወደ ውስጥ ከገባም በኋላ “የምታለቅሱትና የምትንጫጩት ለምንድን ነው? ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።+ 40 በዚህ ጊዜ በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። እሱ ግን ሁሉንም ወደ ውጭ ካስወጣ በኋላ የልጅቷን አባትና እናት እንዲሁም ከእሱ ጋር የነበሩትን አስከትሎ ልጅቷ ወዳለችበት ገባ። 41 ከዚያም የልጅቷን እጅ ይዞ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” ማለት ነው።+ 42 ልጅቷም ወዲያው ተነስታ መራመድ ጀመረች። (ዕድሜዋ 12 ዓመት ነበር።) ወዲያውም እጅግ ከመደሰታቸው የተነሳ የሚሆኑት ጠፋቸው። 43 እሱ ግን ይህን ለማንም እንዳይናገሩ ደጋግሞ አስጠነቀቃቸው፤*+ ለልጅቷም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት ነገራቸው።

6 ከዚያ ተነስቶ ወደ ትውልድ አገሩ መጣ፤+ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2 እሱም በሰንበት ቀን በምኩራብ ማስተማር ጀመረ፤ የሰሙትም አብዛኞቹ ሰዎች በመገረም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች የተማረው ከየት ነው?+ ይህን ጥበብ ያገኘውስ እንዴት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን ማከናወን የቻለው እንዴት ነው?+ 3 ይህ አናጺው+ የማርያም ልጅ+ እንዲሁም የያዕቆብ፣+ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም+ አይደለም? እህቶቹስ የሚኖሩት ከእኛው ጋር አይደለም?” ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት። 4 ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ ዘንድና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው።+ 5 ስለሆነም ጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን በመጫን ከመፈወስ በቀር በዚያ ሌላ ተአምር መፈጸም አልቻለም። 6 እንዲያውም ባለማመናቸው እጅግ ተደነቀ። ከዚህ በኋላ በዙሪያው ባሉት መንደሮች እየተዘዋወረ አስተማረ።+

7 አሥራ ሁለቱን ከጠራ በኋላ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤+ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙም ሥልጣን ሰጣቸው።+ 8 ደግሞም ከበትር በስተቀር ለጉዟቸው ዳቦም ሆነ የምግብ ከረጢት እንዲሁም በመቀነታቸው ገንዘብ* እንዳይዙ አዘዛቸው፤+ 9 በተጨማሪም ሁለት ልብስ* እንዳይዙ፣ ጫማ ግን እንዲያደርጉ ነገራቸው። 10 አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ አካባቢውን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ።+ 11 ነገር ግን የሚቀበላችሁ ወይም የሚሰማችሁ ካጣችሁ ከዚያ ቦታ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”*+ 12 እነሱም ከዚያ ወጥተው ሰዎች ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ፤+ 13 ብዙ አጋንንትም አስወጡ፤+ እንዲሁም ብዙ ሕመምተኞችን ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።

14 የኢየሱስ ስም በሰፊው ታውቆ ስለነበር ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሰማ፤ ሰዎችም “አጥማቂው ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል፤ እንዲህ ያሉ ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” ይሉ ነበር።+ 15 ሌሎች ግን “ኤልያስ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎች ደግሞ “እንደቀድሞዎቹ ነቢያት ያለ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።+ 16 ሄሮድስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “እኔ ራሱን የቆረጥኩት ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል” አለ። 17 ሄሮድስ የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ሰዎች ልኮ ዮሐንስን በማስያዝ በሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገብቶት ነበር፤ ይህም የሆነው ሄሮድስ እሷን አግብቶ ስለነበር ነው።+ 18 ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።+ 19 በመሆኑም ሄሮድያዳ በእሱ ላይ ቂም ይዛ ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ ሆኖም ይህን ማድረግ አልቻለችም። 20 ሄሮድስ፣ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው+ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ጉዳት እንዳያገኘው ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ምን እንደሚያደርገው ግራ ይገባው የነበረ ቢሆንም በደስታ ያዳምጠው ነበር።

21 ይሁንና ሄሮድስ በልደት ቀኑ+ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን፣ የጦር አዛዦቹንና በገሊላ ያሉ ታላላቅ ሰዎችን ራት በጋበዘ ጊዜ ሄሮድያዳ ምቹ አጋጣሚ ተፈጠረላት።+ 22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ በመጨፈር ሄሮድስንና ከእሱ ጋር እየበሉ የነበሩትን አስደሰተቻቸው። ንጉሡም ልጅቷን “የፈለግሽውን ሁሉ ጠይቂኝ፣ እሰጥሻለሁ” አላት። 23 ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል ማለላት። 24 እሷም ወደ እናቷ ሄዳ “ምን ብጠይቀው ይሻላል?” አለቻት። እናቷም “የአጥማቂው ዮሐንስን ራስ ጠይቂው” አለቻት። 25 ወዲያውም ወደ ንጉሡ ፈጥና በመግባት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁኑኑ በሳህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” ስትል ጠየቀችው።+ 26 ንጉሡ በዚህ እጅግ ቢያዝንም ስለገባው መሐላና ስለ እንግዶቹ ሲል እንቢ ሊላት አልፈለገም። 27 ከዚያም ንጉሡ ጠባቂውን ወዲያው ልኮ የዮሐንስን ራስ እንዲያመጣ አዘዘው። ጠባቂውም ሄዶ ወህኒ ቤት ውስጥ ራሱን ቆረጠው፤ 28 ራሱንም በሳህን ይዞ መጣ። ከዚያም ለልጅቷ ሰጣት፤ ልጅቷም ለእናቷ ሰጠቻት። 29 ደቀ መዛሙርቱም ይህን በሰሙ ጊዜ መጥተው አስከሬኑን በመውሰድ በመቃብር አኖሩት።

30 ሐዋርያቱ በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ነገር ሁሉ ነገሩት።+ 31 እሱም “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው።+ ብዙዎች ይመጡና ይሄዱ ስለነበር ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም። 32 ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ገለል ወዳለ ስፍራ ሄዱ።+ 33 ይሁንና ሰዎች ሲሄዱ አዩአቸው፤ ብዙዎችም መሄዳቸውን አወቁ፤ ስለሆነም ከከተሞች ሁሉ አንድ ላይ በእግር በመሮጥ ቀድመዋቸው ደረሱ። 34 ኢየሱስም ከጀልባዋ ሲወርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች+ ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው።+ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።+

35 ሰዓቱ እየገፋ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ቦታ ራቅ ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል።+ 36 በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው።”+ 37 እሱም መልሶ “እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው። እነሱም “ሄደን በ200 ዲናር* ዳቦ ገዝተን እንዲበሉ እንስጣቸው?” አሉት።+ 38 እሱም “ስንት ዳቦ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ!” አላቸው። ሄደው ካዩ በኋላ “አምስት ዳቦና ሁለት ዓሣ” አሉት።+ 39 ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ በቡድን በቡድን ሆኖ በለመለመው መስክ ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ።+ 40 በመሆኑም ሕዝቡ መቶ መቶና ሃምሳ ሃምሳ እየሆነ በቡድን ተቀመጠ። 41 እሱም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ።+ ከዚያም ዳቦውን ቆርሶ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ሁለቱን ዓሣም ለሁሉም አከፋፈለ። 42 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43 ከዚያም ቁርስራሹን ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ዓሣውን ሳይጨምር 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 44 ዳቦውን የበሉትም 5,000 ወንዶች ነበሩ።

45 ወዲያውም፣ እሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ተሳፍረው በቤተሳይዳ አቅጣጫ ወዳለው የባሕር ዳርቻ ቀድመውት እንዲሻገሩ አደረገ።+ 46 ከተሰናበታቸው በኋላ ግን ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ።+ 47 በመሸም ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ነበረች፤ እሱ ግን ብቻውን የብስ ላይ ነበር።+ 48 ነፋሱ ከፊት ለፊታቸው ይነፍስ ስለነበር ለመቅዘፍ ሲታገሉ ባያቸው ጊዜ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት* ገደማ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ፤ ይሁንና አልፏቸው ሊሄድ ነበር።* 49 እነሱም በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ “ምትሃት ነው!” ብለው ስላሰቡ በኃይል ጮኹ። 50 ሁሉም እሱን ባዩት ጊዜ ተረበሹ። ሆኖም ወዲያውኑ አነጋገራቸው፤ ደግሞም “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።+ 51 ከዚያም ጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሯቸው ሆነ፤ ነፋሱም ቆመ። በዚህ ጊዜ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተዋጡ፤ 52 ይህም የሆነው የዳቦውን ተአምር ትርጉም ባለማስተዋላቸው ነው፤ ልባቸው አሁንም መረዳት ተስኖት ነበር።

53  ወደ የብስ በተሻገሩ ጊዜ ጌንሴሬጥ ደረሱ፤ በአቅራቢያውም ጀልባዋን አቆሙ።+ 54 ሆኖም ከጀልባዋ እንደወረዱ ሰዎች አወቁት። 55 ወደ አካባቢው ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በቃሬዛ እየተሸከሙ እሱ ይገኝበታል ወደተባለው ቦታ ያመጡ ጀመር። 56 በገባበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞቹን በገበያ ስፍራ* ያስቀምጡ ነበር፤ የልብሱንም ዘርፍ እንኳ ለመንካት ይማጸኑት ነበር።+ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።

7 ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና አንዳንድ ጸሐፍት ወደ እሱ ተሰበሰቡ።+ 2 ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ በረከሰ ማለትም ባልታጠበ እጅ* ምግብ ሲበሉ አዩ። 3 (ፈሪሳውያንና አይሁዳውያን ሁሉ የአባቶችን ወግ አጥብቀው ስለሚከተሉ እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤ 4 ከገበያ ሲመለሱም ካልታጠቡ በስተቀር አይበሉም። ጽዋዎችን፣ ገንቦዎችንና የነሐስ ዕቃዎችን ውኃ ውስጥ እንደመንከር* ያሉ ከአባቶቻቸው የወረሷቸውና አጥብቀው የሚከተሏቸው ሌሎች በርካታ ወጎችም አሉ።)+ 5 በመሆኑም እነዚህ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።+ 7 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’+ 8 የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”+

9 ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ በዘዴ ገሸሽ ታደርጋላችሁ።+ 10 ለምሳሌ ሙሴ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’+ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ* ይገደል’+ ብሏል። 11 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ቁርባን (ማለትም ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ) ነው” ቢል’ 12 ከዚያ በኋላ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም።+ 13 በመሆኑም ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የአምላክን ቃል ትሽራላችሁ።+ እንዲህ ያለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”+ 14 ከዚያም ሕዝቡን እንደገና ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሁላችሁም ስሙኝ፤ የምናገረውንም አስተውሉ።+ 15 ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰውን የሚያረክሰው ከውስጡ የሚወጣው ነው።”+ 16 *——

17 ከሕዝቡ ተለይቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ይጠይቁት ጀመር።+ 18 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም እንደ እነሱ ማስተዋል ተሳናችሁ? ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ አታውቁም? 19 ምክንያቱም የሚገባው ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ነው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ ይገባል።” እንዲህ በማለት ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን አመለከተ። 20 አክሎም እንዲህ አለ፦ “ሰውን የሚያረክሰው ከውስጡ የሚወጣው ነው።+ 21 ከውስጥ ይኸውም ከሰው ልብ+ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦ የፆታ ብልግና፣* ሌብነት፣ ግድያ፣ 22 ምንዝር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ማንአለብኝነት፣* ምቀኝነት፣* ስድብ፣ ትዕቢትና ሞኝነት። 23 እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ልብ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሳሉ።”

24 ከዚያም ተነስቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና ክልል ሄደ።+ ወደ አንድ ቤትም ገባ፤ እዚያ መኖሩንም ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ይሁንና ከሰዎች ሊሰወር አልቻለም። 25 ወዲያውም፣ ትንሽ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እሱ ሰምታ መጣችና እግሩ ላይ ወደቀች።+ 26 ሴትየዋ ግሪካዊት፣ በዜግነት* ደግሞ ሲሮፊንቃዊት ነበረች፤ እሷም ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ወተወተችው። 27 እሱ ግን “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ ስላልሆነ መጀመሪያ ልጆቹ ይጥገቡ” አላት።+ 28 ሆኖም ሴትየዋ መልሳ “አዎ ጌታዬ፣ ቡችሎችም እኮ ከገበታ በታች ሆነው ከልጆች የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። 29 በዚህ ጊዜ “ሂጂ፤ እንዲህ ስላልሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት።+ 30 እሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ አልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ወጥቶላት አገኘቻት።+

31 ኢየሱስ ከጢሮስ ክልል ሲመለስ በሲዶና በኩል አድርጎ ዲካፖሊስ በተባለው ክልል* በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ።+ 32 በዚያም* ሰዎች መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት+ አንድ ሰው ወደ እሱ አምጥተው እጁን እንዲጭንበት ተማጸኑት። 33 እሱም ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደው። ከዚያም ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አስገባ፤ እንትፍ ካለ በኋላም የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ።+ 34 ወደ ሰማይ እየተመለከተም በረጅሙ ተንፍሶ “ኤፈታ” አለው፤ ይህም “ተከፈት” ማለት ነው። 35 በዚህ ጊዜ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤+ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። 36 ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤+ እነሱ ግን ይበልጥ ባስጠነቀቃቸው መጠን የዚያኑ ያህል ነገሩን በስፋት ያወሩ ነበር።+ 37 እንዲያውም ከመጠን በላይ ከመደነቃቸው የተነሳ+ “ያደረገው ነገር ሁሉ መልካም ነው። ሌላው ቀርቶ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዲሰሙ፣ ዱዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል” አሉ።+

8 በዚያን ወቅት፣ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ 2 “እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው+ አዝንላቸዋለሁ።+ 3 እንዲሁ ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው መንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ፤ ደግሞም አንዳንዶቹ የመጡት ከሩቅ ነው።” 4 ደቀ መዛሙርቱ ግን “በዚህ ገለልተኛ ስፍራ እነዚህን ሰዎች የሚያጠግብ በቂ ዳቦ ከየት ማግኘት ይቻላል?” ሲሉ መለሱለት። 5 በዚህ ጊዜ “ስንት ዳቦ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “ሰባት” አሉት።+ 6 እሱም ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ። ከዚያም ሰባቱን ዳቦ ይዞ አምላክን አመሰገነ፤ ቆርሶም እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነሱም ለሕዝቡ አደሉ።+ 7 ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሯቸው፤ እነዚህንም ከባረከ በኋላ እንዲያድሉ ነገራቸው። 8 ሕዝቡም በልቶ ጠገበ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ሰባት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 9 በዚያም 4,000 ገደማ ወንዶች ነበሩ። በመጨረሻም አሰናበታቸው።

10 ወዲያውኑ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፍሮ ዳልማኑታ ወደተባለ ክልል መጣ።+ 11 እዚያም ፈሪሳውያን መጥተው እሱን ለመፈተን ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቅ ይከራከሩት ጀመር።+ 12 እሱም እጅግ አዝኖ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው?+ እውነት እላችኋለሁ፣ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ።+ 13 ከዚያም ትቷቸው ሄደ፤ እንደገና ጀልባ ተሳፍሮም ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገረ።

14 ይሁንና ዳቦ መያዝ ረስተው ስለነበር በጀልባው ውስጥ ከአንድ ዳቦ በስተቀር ምንም አልነበራቸውም።+ 15 ኢየሱስም “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ሲል በግልጽ አስጠነቀቃቸው።+ 16 እነሱም ዳቦ ባለመያዛቸው እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። 17 ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ዳቦ ባለመያዛችሁ ለምን ትከራከራላችሁ? አሁንም አልገባችሁም? ደግሞስ አላስተዋላችሁም? ልባችሁ መረዳት እንደተሳነው ነው? 18 ‘ዓይን እያላችሁ አታዩም? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙም?’ ደግሞስ አታስታውሱም? 19 አምስቱን ዳቦ ለ5,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ+ ጊዜ ስንት ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ ሰበሰባችሁ?” እነሱም “አሥራ ሁለት”+ አሉት። 20 “ሰባቱን ዳቦ ለ4,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ ጊዜ ስንት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ አነሳችሁ?” እነሱም “ሰባት” አሉት።+ 21 እሱም “ታዲያ አሁንም አልገባችሁም?” አላቸው።

22 ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ። በዚያም ሰዎች አንድ ዓይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ተማጸኑት።+ 23 እሱም ዓይነ ስውሩን፣ እጁን ይዞ ከመንደሩ ውጭ ወሰደው። በዓይኖቹ ላይ እንትፍ ካለ በኋላ+ እጆቹን ጫነበትና “የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። 24 ሰውየውም ቀና ብሎ በማየት “ሰዎች ይታዩኛል፤ ሆኖም የሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ” አለ። 25 ኢየሱስ እንደገና እጆቹን ሰውየው ዓይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው አጥርቶ አየ። ዓይኖቹም በሩ፤ ሁሉንም ነገር በደንብ ለይቶ ማየት ቻለ። 26 በመጨረሻም “ወደ መንደሩ አትግባ” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

27 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው።+ 28 እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣+ ሌሎች ኤልያስ፣+ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” አሉት። 29 ከዚያም እነሱን “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ ነህ”+ ብሎ መለሰለት። 30 በዚህ ጊዜ ስለ እሱ ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው።+ 31 በተጨማሪም የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበሉ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ተቀባይነት ማጣቱ ብሎም መገደሉና+ ከሦስት ቀን በኋላ መነሳቱ+ እንደማይቀር ያስተምራቸው ጀመር። 32 ደግሞም ይህን በግልጽ ነገራቸው። ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ ይገሥጸው ጀመር።+ 33 በዚህ ጊዜ ዞር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን!* የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ አታስብም” ሲል ገሠጸው።+

34 ከዚህ በኋላ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት* ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።+ 35 ሕይወቱን* ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔና ለምሥራቹ ሲል ሕይወቱን* የሚያጣ ሁሉ ግን ያድናታል።+ 36 ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ሕይወቱን* ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?+ 37 ሰው ለሕይወቱ* ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?+ 38 በዚህ አመንዝራና* ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ+ ያፍርበታል።”+

9 ቀጥሎም “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት በታላቅ ኃይል መምጣቱን እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም” አላቸው።+ 2 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤+ 3 ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር። 4 ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር። 5 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው። 6 እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር። 7 ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+ 8 ከዚያም ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።

9 ከተራራው እየወረዱ ሳሉ የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ+ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አዘዛቸው።+ 10 እነሱም ቃሉን በልባቸው አኖሩ፤* ነገር ግን ከሞት መነሳት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 11 ከዚያም “ጸሐፍት፣ ኤልያስ+ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 12 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጀመሪያ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል፤+ ይሁንና የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና+ መናቅ+ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? 13 ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ+ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት በእርግጥ መጥቷል፤ እነሱም የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።”+

14 ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት በመጡም ጊዜ ብዙ ሕዝብ ከቧቸው አዩ፤ ጸሐፍትም ከእነሱ ጋር እየተከራከሩ ነበር።+ 15 ሆኖም የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን እንዳዩት በጣም ተገረሙ፤ ከዚያም ሰላም ሊሉት ወደ እሱ ሮጡ። 16 እሱም “ከእነሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። 17 ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መምህር፣ ልጄ ዱዳ የሚያደርግ መንፈስ ስላደረበት ወደ አንተ አመጣሁት።+ 18 በያዘው ስፍራ ሁሉ መሬት ላይ ይጥለዋል፤ ከዚያም አፉ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱን ያፋጫል እንዲሁም ይዝለፈለፋል። ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ጠየቅኳቸው፤ እነሱ ግን ሊያስወጡት አልቻሉም።” 19 እሱም መልሶ “እምነት የለሽ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።+ 20 ልጁንም ወደ እሱ አመጡት፤ ልጁን የያዘው መንፈስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ልጁን አንዘፈዘፈው። ልጁም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር። 21 ከዚያም ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለው፦ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል። ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን።” 23 ኢየሱስም “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለው።+ 24 ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!”+ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።

25 ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲያይ ርኩሱን መንፈስ “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው።+ 26 ርኩሱ መንፈስ በኃይል ከጮኸና ብዙ ካንዘፈዘፈው በኋላ ወጣ፤ ልጁም የሞተ ያህል ሆነ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞቷል!” ይሉ ጀመር። 27 ይሁን እንጂ ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ልጁም ተነስቶ ቆመ። 28 ከዚያም ወደ ቤት ከገባ በኋላ ብቻውን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 29 እሱም “እንዲህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው።

30 ከዚያ ተነስተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ሆኖም ይህን ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም። 31 ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱን እያስተማራቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነሱም ይገድሉታል፤+ ይሁንና ቢገደልም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል”+ በማለት እየነገራቸው ነበር። 32 ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

33 ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ “በመንገድ ላይ ስትከራከሩ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?”+ ሲል ጠየቃቸው። 34 በመንገድ ላይ እርስ በርስ የተከራከሩት “ከሁላችን የሚበልጠው ማን ነው?” በሚል ስለነበረ ዝም አሉ። 35 ስለዚህ ከተቀመጠ በኋላ አሥራ ሁለቱን ጠርቶ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉም መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት” አላቸው።+ 36 ከዚያም አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም እንዲህ አላቸው፦ 37 “እንዲህ ካሉት ልጆች+ አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ብቻ ሳይሆን የላከኝንም ይቀበላል።”+

38 ዮሐንስ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ሆኖም እኛን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን።”+ 39 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር ሠርቶ ወዲያውኑ ስለ እኔ ክፉ ነገር ሊናገር የሚችል ስለሌለ አትከልክሉት። 40 እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና።+ 41 ደግሞም የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ጽዋ የሚጠጣ ውኃ የሚሰጣችሁ ሁሉ፣+ እውነት እላችኋለሁ፣ በምንም መንገድ ብድራቱን አያጣም።+ 42 ሆኖም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ* በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።+

43 “እጅህ ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ሊጠፋ ወደማይችልበት ወደ ገሃነም* ከምትሄድ ጉንድሽ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 44 *—— 45 እግርህም ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም* ከምትጣል አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 46 *—— 47 ዓይንህም ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም* ከምትጣል አንድ ዓይን ኖሮህ ወደ አምላክ መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፤+ 48 በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም።+

49 “ሰው ጨው እንደሚነሰንስ ሁሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎችም እሳት ሊወርድባቸው ይገባል።+ 50 ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ትችላላችሁ?+ በሕይወታችሁ ውስጥ ጨው ይኑራችሁ፤+ እርስ በርሳችሁም ሰላም ይኑራችሁ።”+

10 ከዚያም ተነስቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ፤ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እሱ ተሰበሰቡ። አሁንም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ጀመር።+ 2 ፈሪሳውያንም ቀርበው እሱን ለመፈተን በማሰብ አንድ ሰው ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለት እንደሆነ ጠየቁት።+ 3 እሱም መልሶ “ሙሴ ምን ብሎ ነው ያዘዛችሁ?” አላቸው። 4 እነሱም “ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉት።+ 5 ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና+ መሆኑን አይቶ ነው።+ 6 ይሁን እንጂ በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።+ 7 ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤+ 8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤+ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። 9 ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን* ማንም ሰው አይለያየው።”+ 10 እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ ይጠይቁት ጀመር። 11 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በማመንዘር+ ሚስቱን ይበድላል፤ 12 አንዲት ሴትም ብትሆን ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።”+

13 ሰዎችም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።+ 14 ኢየሱስ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና።+ 15 እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”+ 16 ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።+

17 ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው።+ 18 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።+ 19 ‘አትግደል፣+ አታመንዝር፣+ አትስረቅ፣+ በሐሰት አትመሥክር፣+ አታታል፣+ አባትህንና እናትህን አክብር’+ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።” 20 ሰውየውም “መምህር፣ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬአለሁ” አለው። 21 ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ ከዚያም “አንድ ነገር ይጎድልሃል፤ ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።+ 22 ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ።+

23 ኢየሱስ ዙሪያውን ከተመለከተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!” አላቸው።+ 24 ደቀ መዛሙርቱ ግን በንግግሩ ተገረሙ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቼ ሆይ፣ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! 25 ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”+ 26 ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ በመገረም “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉት።*+ 27 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ትኩር ብሎ በመመልከት “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለ።+ 28 ጴጥሮስም “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል” አለው።+ 29 ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣+ 30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት+ ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት* ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል። 31 ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።”+

32 ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ እያቀኑ ሳሉ ኢየሱስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤ እነሱም ተደነቁ፤ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ግን ፍርሃት አደረባቸው። እሱም እንደገና አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ የሚደርስበትን ነገር ይነግራቸው ጀመር፦+ 33 “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ 34 ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል።”+

35 ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች+ ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እሱ ቀርበው “መምህር፣ የምንለምንህን ማንኛውንም ነገር እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።+ 36 እሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 37 እነሱም “በክብር ቦታህ ላይ ስትቀመጥ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን ደግሞ በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” ሲሉ መለሱለት።+ 38 ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ እየጠጣሁት ያለውን ጽዋ ልትጠጡ ወይም እኔ እየተጠመቅኩት ያለውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁ?” አላቸው።+ 39 እነሱም “እንችላለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ እየጠጣሁት ያለውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ እየተጠመቅኩት ያለውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ።+ 40 በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።”

41 የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ ተቆጡ።+ 42 ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ብሔራትን የሚገዙ* ነገሥታት በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቆቻቸውም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ።+ 43 በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤+ 44 እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባል። 45 ምክንያቱም የሰው ልጅ እንኳ የመጣው ለማገልገልና+ በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን* ቤዛ አድርጎ ለመስጠት+ እንጂ እንዲገለገል አይደለም።”

46 ከዚያም ወደ ኢያሪኮ መጡ። እሱና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዓይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።+ 47 እሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን ሲሰማ “የዳዊት ልጅ፣+ ኢየሱስ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!”+ እያለ ይጮኽ ጀመር። 48 በዚህ ጊዜ ብዙዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 49 ኢየሱስም ቆመና “ጥሩት” አለ። እነሱም ዓይነ ስውሩን “አይዞህ! ተነስ፤ እየጠራህ ነው” አሉት። 50 እሱም መደረቢያውን ጥሎ ዘሎ በመነሳት ወደ ኢየሱስ ሄደ። 51 ኢየሱስም “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዓይነ ስውሩም “ራቦኒ፣* የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው። 52 ኢየሱስም “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው።+ ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤+ እሱም ከሕዝቡ ጋር አብሮ ይከተለው ጀመር።

11 ወደ ኢየሩሳሌም፣ በደብረ ዘይት ተራራ ወዳሉት ወደ ቤተፋጌ እና ወደ ቢታንያ+ በተቃረቡ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ላካቸው፤+ 2 እንዲህም አላቸው፦ “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደሩም እንደገባችሁ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ ውርንጭላ ታስሮ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደዚህ አምጡት። 3 ማንም ሰው ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ ‘ጌታ ይፈልገዋል፤ ደግሞም ወዲያውኑ ወደዚህ ይመልሰዋል’ በሉት።” 4 እነሱም ሄዱ፤ ውርንጭላውንም በአንድ ጠባብ መንገድ ዳር፣ ደጃፍ ላይ ታስሮ አገኙት።+ 5 በዚያ ከቆሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ “ውርንጭላውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 6 እነሱም ኢየሱስ ያለውን ነገሯቸው፤ ከዚያም ፈቀዱላቸው።

7 ውርንጭላውንም+ ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ መደረቢያቸውንም በውርንጭላው ጀርባ ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠበት።+ 8 ብዙዎችም መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ በመንገድ ዳር ካሉት ዛፎች ቅርንጫፎች እየቆረጡ አነጠፉ።+ 9 ከፊቱ የሚሄዱትና ከኋላው የሚከተሉት እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር፦ “እንድታድነው እንለምንሃለን!*+ በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!+ 10 የሚመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከ ነው!+ በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እንድታድነው እንለምንሃለን!” 11 ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያውም ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ፤ ሆኖም ሰዓቱ ገፍቶ ስለነበር ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ሄደ።+

12 በማግስቱ ከቢታንያ እየወጡ ሳለ ተራበ።+ 13 ቅጠሏ የለመለመ አንዲት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየና ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ለማየት ሄደ። ወደ እሷ በቀረበ ጊዜ ግን በለስ የሚያፈራበት ወቅት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14 ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏን “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት።+ ይህን ሲናገርም ደቀ መዛሙርቱ ይሰሙት ነበር።

15 ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ፤+ 16 ማንም ሰው ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ አቋርጦ እንዳያልፍም ከለከለ። 17 ሰዎቹንም ያስተምር ነበር፤ ደግሞም “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም?+ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው።+ 18 የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ያደረገውን በሰሙ ጊዜ እሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤+ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ስለሚገረም ኢየሱስን ይፈሩት ነበር።+

19 አመሻሽ ላይ ከከተማዋ ወጡ። 20 ማለዳም ላይ በመንገድ ሲያልፉ የበለስ ዛፏ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።+ 21 ጴጥሮስም ትዝ አለውና “ረቢ፣ ተመልከት! የረገምካት የበለስ ዛፍ ደርቃለች” አለው።+ 22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “በአምላክ ላይ እምነት ይኑራችሁ። 23 እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና በልቡ ሳይጠራጠር የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም ቢያምን ይሆንለታል።+ 24 ስለዚህ እላችኋለሁ፣ በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ።+ 25 በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ እናንተም ለመጸለይ በምትቆሙበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ ያላችሁን ቅሬታ ሁሉ ይቅር በሉ።”+ 26 *——

27 እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በቤተ መቅደሱም ሲዘዋወር የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች መጥተው 28 “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።+ 29 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30 ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን+ ያገኘው ከአምላክ* ነው ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።”+ 31 እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ 32 ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ?” ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።+ 33 ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

12 ከዚያም ምሳሌ በመጠቀም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤+ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤+ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።+ 2 ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። 3 እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። 4 በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት።+ 5 ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ። 6 አሁን የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር።+ ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው። 7 እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው።+ ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። 8 ስለዚህ ይዘው ገደሉት፤ ከወይን እርሻውም አውጥተው ጣሉት።+ 9 እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣና ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል።+ 10 እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ።+ 11 ይህ የይሖዋ* ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’”+

12 በዚህ ጊዜ ምሳሌውን የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ ስለተረዱ ሊይዙት* ፈለጉ። ሆኖም ሕዝቡን ስለፈሩ ትተውት ሄዱ።+

13 ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንን እና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ።+ 14 እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?* 15 እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር* አምጡና አሳዩኝ” አላቸው። 16 እነሱም አመጡለት፤ እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት። 17 ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣+ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ+ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ።

18 በትንሣኤ የማያምኑት+ ሰዱቃውያን ደግሞ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦+ 19 “መምህር፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሚስትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር መተካት እንዳለበት ጽፎልናል።+ 20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አገባና ዘር ሳይተካ ሞተ። 21 ከዚያም ሁለተኛው አገባት፤ ሆኖም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22 ሰባቱም ዘር አልተኩም። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 23 እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” 24 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም?+ 25 ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።+ 26 ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም?+ 27 እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።”+

28 ከጸሐፍት ወገን የሆነ አንድ ሰው መጥቶ ሲከራከሩ ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ ጥሩ አድርጎ እንደመለሰላቸው አስተውሎ “ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው* የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።+ 29 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ* አምላካችን አንድ ይሖዋ* ነው፤ 30 አንተም አምላክህን ይሖዋን* በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣* በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’+ 31 ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው።+ ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” 32 ጸሐፊውም እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤+ 33 እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና* በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።”+ 34 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በማስተዋል እንደመለሰ ተረድቶ “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ግን ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም።+

35 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ እንዲህ አለ፦ “ጸሐፍት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?+ 36 ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ+ ሲናገር ‘ይሖዋ* ጌታዬን “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ብሏል።+ 37 ዳዊት ራሱ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”+

ሕዝቡም በደስታ ያዳምጠው ነበር። 38 ማስተማሩንም በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ፤+ 39 በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣* በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ ይፈልጋሉ።+ 40 የመበለቶችን ቤት* ያራቁታሉ፤ ለታይታ ብለውም* ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ። እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።”

41 ኢየሱስ በመዋጮ ሣጥኖቹ*+ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ ይመለከት ጀመር፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር።+ 42 በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች* ከተተች።+ 43 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ* ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።+ 44 ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።”+

13 ከቤተ መቅደስ እየወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው።+ 2 ኢየሱስ ግን “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አለው።+

3 በቤተ መቅደሱ ትይዩ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ብቻቸውን ሆነው እንዲህ በማለት ጠየቁት፦ 4 “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የእነዚህ ነገሮች ሁሉ መደምደሚያ መቅረቡን የሚያሳየው ምልክትስ ምንድን ነው?”+ 5 ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ።+ 6 ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። 7 ከዚህም ሌላ ጦርነትና የጦርነት ወሬ ስትሰሙ አትደናገጡ፤ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+

8 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥ ይከሰታል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት ይኖራል።+ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።+

9 “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤+ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 10 አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።+ 11 አሳልፈው ለመስጠት በሚወስዷችሁ ጊዜም ምን እንላለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።+ 12 በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 13 በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+ እስከ መጨረሻው የጸና+ ግን* ይድናል።+

14 “ይሁንና ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’+ በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 15 በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው አይውረድ፤ አንዳችም ነገር ለመውሰድ ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16 በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ ወደ ኋላ አይመለስ። 17 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ 18 ይህ በክረምት እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 19 ምክንያቱም በእነዚያ ቀናት ከአምላክ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ መከራ+ ይከሰታል። 20 እንዲያውም ይሖዋ* ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር። ሆኖም እሱ ለመረጣቸው ምርጦች ሲል ቀኖቹን አሳጥሯል።+

21 “በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’ ወይም ‘እነሆ፣ ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 22 ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ። 23 ስለዚህ ተጠንቀቁ።+ ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።

24 “ሆኖም በእነዚያ ቀናት፣ ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤+ 25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማያት ያሉ ኃይላትም ይናወጣሉ። 26 ከዚያም የሰው ልጅ+ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 27 እሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።+

28 “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 29 በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 30 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+ 31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤+ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+

32 “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።+ 33 ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ+ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 34 ይህም ለባሪያዎቹ ሥልጣን ከሰጠና ለእያንዳንዱ የሥራ ድርሻውን ከመደበ በኋላ በር ጠባቂውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማዘዝ+ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው።+ 35 ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት* ይሁን በእኩለ ሌሊት* ወይም ዶሮ ሲጮኽ* ይሁን ከመንጋቱ* በፊት፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ 36 አለዚያ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ ያገኛችኋል።+ 37 ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”+

14 ፋሲካና*+ የቂጣ* በዓል+ ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር።+ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት የተንኮል ዘዴ ተጠቅመው እሱን የሚይዙበትንና* የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤+ 2 ደግሞም “ሕዝቡ ሁከት ሊያስነሳ ስለሚችል በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ይሉ ነበር።

3 በቢታንያ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን ቤት እየበላ ሳለ አንዲት ሴት እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይኸውም ንጹሕ ናርዶስ የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች። ብልቃጡንም ሰብራ በመክፈት ዘይቱን ራሱ ላይ ታፈስ ጀመር።+ 4 በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ተቆጥተው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ዘይት እንዲህ የሚባክነው ለምንድን ነው? 5 ከ300 ዲናር* በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር!” በሴትየዋም እጅግ ተበሳጩ።* 6 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት። ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች።+ 7 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ በፈለጋችሁ ጊዜ ሁሉ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።+ 8 እሷ የምትችለውን አድርጋለች፤ ሰውነቴን ለቀብሬ ለማዘጋጀት ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት አስቀድማ ቀብታዋለች።+ 9 እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ምሥራቹ በሚሰበክበት+ ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”+

10 ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።+ 11 እነሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸውና የብር ገንዘብ* ሊሰጡት ቃል ገቡለት።+ ስለዚህ እሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን አጋጣሚ ይፈልግ ጀመር።

12 የቂጣ በዓል+ በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ እንደተለመደው የፋሲካን መሥዋዕት+ በሚያቀርቡበት ዕለት ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን እንድትበላ የት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።+ 13 እሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፦ “ወደ ከተማው ሂዱ፤ በዚያም የውኃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ። እሱንም ተከተሉት፤+ 14 ወደሚገባበት ቤት ሄዳችሁ የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ “ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የት ነው?” ብሏል’ በሉት። 15 እሱም የተነጠፈና የተሰናዳ ሰፊ ሰገነት ያሳያችኋል። እዚያ አዘጋጁልን።” 16 ደቀ መዛሙርቱም ሄዱ፤ ወደ ከተማውም ገቡ፤ እንዳላቸውም ሆኖ አገኙት፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ።

17 እሱም ከመሸ በኋላ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።+ 18 በማዕድ ተቀምጠው እየበሉ ሳለም ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ፣ ከእኔ ጋር እየበላ ያለ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ።+ 19 እነሱም አዝነው በየተራ “እኔ እሆን?” ይሉት ጀመር። 20 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይኸውም ከእኔ ጋር በሳህኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው።+ 21 የሰው ልጅ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!+ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”+

22 እየበሉም ሳሉ ቂጣ አንስቶ ባረከ፤ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና “እንኩ፣ ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” አለ።+ 23 ጽዋ አንስቶም አምላክን ካመሰገነ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእሱ ጠጡ።+ 24 እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ለብዙዎች የሚፈሰውን+ ‘የቃል ኪዳን+ ደሜን’+ ያመለክታል። 25 እውነት እላችኋለሁ፣ በአምላክ መንግሥት አዲሱን ወይን እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ በኋላ ከዚህ ወይን አልጠጣም።” 26 በመጨረሻ የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።+

27 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “‘እረኛውን እመታለሁ፤+ በጎቹም ይበተናሉ’+ ተብሎ ስለተጻፈ ሁላችሁም ትሰናከላላችሁ። 28 ከተነሳሁ በኋላ ግን ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”+ 29 ይሁንና ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለው።+ 30 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ፦ ዛሬ፣ አዎ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።+ 31 እሱ ግን “አብሬህ መሞት ቢኖርብኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” በማለት አጥብቆ ይናገር ጀመር። የቀሩትም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።+

32 ከዚያም ጌትሴማኒ ወደተባለ ቦታ መጡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “እኔ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።+ 33 ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ከእሱ ጋር ይዟቸው ሄደ፤+ ከዚያም እጅግ ይጨነቅና* ይረበሽ ጀመር። 34 ኢየሱስም “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ።*+ እዚህ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ”+ አላቸው። 35 ትንሽ ወደ ፊት ራቅ በማለት መሬት ላይ ተደፍቶ ቢቻል ሰዓቱ ከእሱ እንዲያልፍ ይጸልይ ጀመር። 36 እንዲህም አለ፦ “አባ፣* አባት ሆይ፣+ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን።”+ 37 ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ስምዖን፣ ተኝተሃል? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አልቻልክም?+ 38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ+ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ። እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ* ነው፤ ሥጋ* ግን ደካማ ነው።”+ 39 እንደገናም ሄዶ ስለዚያው ነገር ጸለየ።+ 40 ዳግመኛም ተመልሶ ሲመጣ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ስለነበር ተኝተው አገኛቸው፤ በመሆኑም የሚሉት ነገር ጠፋቸው። 41 ለሦስተኛ ጊዜም ተመልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? በቃ! ሰዓቱ ደርሷል!+ እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ ሊሰጥ ነው። 42 ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”+

43 ወዲያውም ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።+ 44 አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 45 ይሁዳም በቀጥታ መጥቶ ወደ እሱ በመቅረብ “ረቢ!” ብሎ ሳመው። 46 ሰዎቹም ያዙት፤ ደግሞም አሰሩት። 47 ይሁን እንጂ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።+ 48 ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው?+ 49 በየዕለቱ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ+ ከእናንተ ጋር ነበርኩ፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይሁንና ይህ የሆነው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።”+

50 በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ።+ 51 ሆኖም እርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት በቅርብ ርቀት ይከተለው ጀመር፤ ሊይዙትም ሞከሩ፤ 52 እሱ ግን በፍታውን ትቶ ራቁቱን* አመለጠ።

53  ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤+ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍትም በሙሉ ተሰበሰቡ።+ 54 ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ተከተለው፤ ከዚያም ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ጀመር።+ 55 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የምሥክሮች ቃል እየፈለጉ ነበር፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።+ 56 እርግጥ ብዙዎች በእሱ ላይ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፤+ ሆኖም ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም። 57  አንዳንዶችም ተነስተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት ይመሠክሩበት ነበር፦ 58 “‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”+ 59 በዚህ ጉዳይም ቢሆን የምሥክርነት ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም።

60 ከዚያም ሊቀ ካህናቱ በመካከላቸው ቆሞ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው።+ 61 እሱ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።+ ሊቀ ካህናቱም እንደገና “አንተ ብሩክ የሆነው አምላክ ልጅ ክርስቶስ ነህ?” እያለ ይጠይቀው ጀመር። 62 ኢየሱስም “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ+ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ+ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”+ አለ። 63 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ እንዲህ አለ፦ “ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል?+ 64 አምላክን ሲሳደብ ሰምታችኋል። ታዲያ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው?”* ሁሉም ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።+ 65 አንዳንዶች ይተፉበት ጀመር፤+ ፊቱንም ሸፍነው በቡጢ እየመቱት “ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን!” ይሉት ነበር። የሸንጎው አገልጋዮችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።+

66 ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በታች በኩል ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ሴት አገልጋዮች አንዷ መጣች።+ 67 እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከዚህ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። 68 እሱ ግን “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” ሲል ካደ፤ ከዚያም ወደ መግቢያው* ሄደ። 69 አገልጋይዋም እዚያ አየችውና በአጠገቡ ለቆሙት “ይህ ከእነሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ትናገር ጀመር። 70 አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በዚያ ቆመው የነበሩት ጴጥሮስን እንደገና “የገሊላ ሰው ስለሆንክ፣ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” ይሉት ጀመር። 71 እሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” ሲል ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። 72 ወዲያውኑ ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤+ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።+ ከዚያም እጅግ አዝኖ ያለቅስ ጀመር።

15 ወዲያውኑ በማለዳ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ማለትም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ተሰብስበው ተማከሩ፤ ኢየሱስንም አስረው በመውሰድ ለጲላጦስ አስረከቡት።+ 2 ጲላጦስም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው።+ እሱም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።+ 3 የካህናት አለቆቹ ግን በእሱ ላይ በርካታ ክስ መደርደራቸውን ቀጠሉ። 4 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “ምንም መልስ አትሰጥም?+ በስንት ነገር እየከሰሱህ እንዳሉ ተመልከት” ሲል እንደገና ጠየቀው።+ 5 ሆኖም ኢየሱስ ምንም ተጨማሪ መልስ አልሰጠም፤ በመሆኑም ጲላጦስ ተገረመ።+

6 ጲላጦስ ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ ይፈታልን ብለው የጠየቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።+ 7 በወቅቱ፣ በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ሰው ገድለው ከታሰሩ ዓመፀኞች መካከል በርባን የሚባል ሰው ይገኝ ነበር። 8 ሕዝቡም መጥተው ጲላጦስ እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ ይጠይቁት ጀመር። 9 እሱም መልሶ “የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።+ 10 ጲላጦስ ይህን ያለው የካህናት አለቆች አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው።+ 11 ይሁንና የካህናት አለቆቹ በኢየሱስ ምትክ በርባንን ይፈታላቸው ዘንድ እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሳሱ።+ 12 ጲላጦስም እንደገና መልሶ “እንግዲያው የአይሁዳውያን ንጉሥ የምትሉትን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው።+ 13 እነሱም “ይሰቀል!”* ብለው እንደገና ጮኹ።+ 14 ሆኖም ጲላጦስ “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!”* እያሉ የባሰ ጮኹ።+ 15 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ሕዝቡን ለማስደሰት ስለፈለገ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ካስገረፈው+ በኋላ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።+

16 ወታደሮቹ ወደ ግቢው ይኸውም ወደ አገረ ገዢው መኖሪያ ቤት ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ አንድ ላይ ሰበሰቡ።+ 17 ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጎንጉነውም በራሱ ላይ ደፉበት፤ 18 ደግሞም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ጀመር።+ 19 ከዚህም ሌላ ራሱን በመቃ ይመቱትና ይተፉበት ነበር፤ ተንበርክከውም እጅ ነሱት።* 20 ሲያፌዙበት ከቆዩ በኋላም ሐምራዊውን ልብስ ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት። ከዚያም በእንጨት ላይ ሊቸነክሩት ይዘውት ሄዱ።+ 21 ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር መጥቶ በዚያ ሲያልፍ አግኝተው ኢየሱስ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት* እንዲሸከም አስገደዱት፤* ይህ ሰው የእስክንድርና የሩፎስ አባት ነበር።+

22 በኋላም ኢየሱስን ጎልጎታ ወደተባለ ቦታ አመጡት፤ ትርጉሙም “የራስ ቅል ቦታ” ማለት ነው።+ 23 እዚያም ከርቤ* የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ ሰጡት፤+ እሱ ግን አልተቀበለም። 24 ከዚያም እንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ማን ምን እንደሚወስድ ለመወሰንም ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።+ 25 እንጨት ላይ ሲቸነክሩትም ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር። 26 የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚገልጽ “የአይሁዳውያን ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር።+ 27 ከእሱም ጋር ሁለት ዘራፊዎችን፣ አንዱን በቀኙ ሌላውን ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ሰቀሉ።+ 28 *—— 29 በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡትና ራሳቸውን እየነቀነቁ+ እንዲህ ይሉት ነበር፦ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ!+ 30 እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት* ላይ ወርደህ ራስህን አድን።” 31 የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍት ጋር ሆነው እርስ በርሳቸው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም!+ 32 አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት* ይውረድ።”+ ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉትም እንኳ ሳይቀሩ ይነቅፉት ነበር።+

33 ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜም አገሩ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነ።+ 34 በዘጠነኛውም ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው።+ 35 በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “አያችሁ! ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር። 36 ከዚያም አንድ ሰው ሮጦ በመሄድ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ሰፍነግ* ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠውና+ “ተዉት! እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደሆነ እንይ” አለ። 37 ሆኖም ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ሞተ።*+ 38 የቤተ መቅደሱ መጋረጃም+ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ።+ 39 ከፊት ለፊቱ ቆሞ የነበረው መኮንንም በዚህ ሁኔታ መሞቱን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አለ።+

40 በተጨማሪም ከሩቅ ሆነው የሚያዩ ሴቶች የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል መግደላዊቷ ማርያም እንዲሁም የትንሹ* ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያምና ሰሎሜ ነበሩ፤+ 41 እነዚህም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤+ ከእሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች በርካታ ሴቶችም ነበሩ።

42 ቀኑ በመገባደዱና የዝግጅት ቀን ማለትም የሰንበት ዋዜማ በመሆኑ 43 የተከበረ የሸንጎ* አባል የሆነውና የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ መጣ። ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።+ 44 ጲላጦስ ግን ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ ለማወቅ የመቶ አለቃውን ጠርቶ በእርግጥ ሞቶ እንደሆነ ጠየቀው። 45 መሞቱን ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላም አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት። 46 እሱም በፍታ ገዝቶ አስከሬኑን ካወረደ በኋላ በበፍታው ገነዘው፤ ከዚያም ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው፤+ ድንጋይ አንከባሎም የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋው።+ 47 በዚህ ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም አስከሬኑ የተቀመጠበትን ቦታ ይመለከቱ ነበር።+

16 ሰንበት+ ካለፈ በኋላም መግደላዊቷ ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና+ ሰሎሜ ሄደው አስከሬኑን ሊቀቡ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞች ገዙ።+ 2 ከዚያም በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ወደ መቃብሩ መጡ።+ 3 እርስ በርሳቸውም “በመቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር። 4 ቀና ብለው ሲመለከቱ ግን በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከቦታው ተንከባሎ አዩ።+ 5 ወደ መቃብሩ ሲገቡ ነጭ ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “አትደንግጡ።+ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ። እሱ ተነስቷል።+ እዚህ የለም። ተመልከቱ፣ እሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውና።+ 7 ይልቁንስ ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።+ እንደነገራችሁም እዚያ ታዩታላችሁ’ በሏቸው።”+ 8 እነሱም ከመቃብሩ ከወጡ በኋላ በአድናቆት ተውጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ሸሽተው ሄዱ። ከፍርሃታቸውም የተነሳ ለማንም ምንም ነገር አልተናገሩም።*+

እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ የተወሰደው ከሚልክያስ 3:1 ነው።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ይነከሩ፤ ይጠልቁ።”

ማቴ 4:18 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

“የእሱን ማንነት አውቀው ስለነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ሽባ የሆነ።”

ወይም “ሽባ የሆነበትን።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ሾማቸው።”

ወይም “የሾማቸውም።”

ወይም “ቀናተኛው።”

ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።

ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።

ወይም “መከዳ።”

ወይም “ትርበተበታላችሁ?”

ማቴ 26:53 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “ገደላማ ከሆነው የባሕሩ ዳርቻ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “አሥሩ ከተሞች በሚገኙበት ክልል።”

ወይም “ልትሞት ተቃርባለች።”

ወይም “አጥብቆ አዘዛቸው።”

ቃል በቃል “መዳብ።”

ወይም “ትርፍ ልብስ።”

የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ 12 ሰዓት ገደማ ላይ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሰዓት ያመለክታል።

ወይም “አልፏቸው ሊሄድ ተቃርቦ ነበር።”

ሰዎች የሚገበያዩበት እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባ የሚካሄድበት ገላጣ ስፍራ።

ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አለመንጻትን ያመለክታል።

ቃል በቃል “እንደማጥመቅ።”

ወይም “የሚያንቋሽሽ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ፖርኒያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ምቀኛ ዓይን።”

ወይም “በትውልድ።”

ወይም “አሥሩ ከተሞች በሚገኙበት ክልል።”

ኢየሱስ በዲካፖሊስ ሳለ ማለት ነው።

“ሰይጣን” የሚለው ቃል ተቃዋሚ የሚል ትርጉም ስላለው ኢየሱስ ጴጥሮስን “ተቃዋሚ” ብሎ መጥራቱ ነበር።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ለነፍሱ።”

ወይም “ለአምላክ ታማኝ ባልሆነና።”

“ጉዳዩን በውስጣቸው ያዙት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በአህያ የሚዞር የወፍጮ ድንጋይ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “በአንድ ቀንበር ያጣመደውን።”

“ተባባሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ብሔራትን እንደሚገዙ ተደርገው የሚታሰቡ።”

ወይም “ነፍሱን።”

“መምህር” የሚል ትርጉም አለው።

ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ከሰማይ።”

ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሊያስሩት።”

ወይም “ትክክል ነው ወይስ አይደለም?”

ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚበልጠው።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ቃል በቃል “በሙሉ የመረዳት ችሎታና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የተሻለውን መቀመጫ መያዝ።”

ወይም “ንብረት።”

ወይም “ማሳበቢያ እንዲሆናቸውም።”

ወይም “በዕቃዎቹ።”

ቃል በቃል “ሁለት ሌፕተን ይኸውም አንድ ኳድራንስ።” ለ14ን ተመልከት።

ወይም “በዕቃዎቹ።”

ወይም “የሚጸና ግን።”

ማቴ 24:17 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።

“ምሽት።” ግሪካውያንና ሮማውያን የሌሊቱን ጊዜ በሚከፋፍሉበት መሠረት የመጀመሪያው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 3 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።

“እኩለ ሌሊት።” ሁለተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ነው።

“ዶሮ ሲጮኽ።” ሦስተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከእኩለ ሌሊት እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።

“ንጋት።” አራተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ነው።

ወይም “የማለፍ በዓልና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የሚያስሩበትንና።”

ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ሴትየዋን ተቆጧት፤ ነቀፏት።”

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።

ወይም “ይደነግጥና።”

ወይም “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች።”

“አባት ሆይ!” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ወይም የአረማይክ ቃል ነው።

ወይም “ፈቃደኛ።”

የሰው ልጅ ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለው መሆኑን ያመለክታል።

ወይም “ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻ።”

ወይም “ምን ይመስላችኋል?”

ወይም “መተላለፊያው።”

ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”

ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”

ወይም “ሰገዱለት።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “በመሸከም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አደረጉት።”

የሚያሰክር ንጥረ ነገር።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።

ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።

ወይም “እስትንፋሱ ቆመ።”

“ትንሹ” የሚለው ቃል ያዕቆብ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ከሆነው ከሐዋርያው ያዕቆብ በዕድሜ ወይም በቁመት እንደሚያንስ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “የሳንሄድሪን።”

ከፍተኛ ተአማኒነት ያላቸው በእጅ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ቅጂዎች እንደሚያመለክቱት የማርቆስ ወንጌል የሚያበቃው ቁጥር 8 ላይ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ