በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች የሚያስፈልጋቸው ነገር
በዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ጀርሲ ውስጥ የምትኖር አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይ “ተማሪዎች በፈተና ወቅት የሚያጭበረብሩት ለምንድን ነው?” በሚል ጭብጥ አንድ ሪፖርት ማዘጋጀት ነበረባት። ምርምር ለማድረግ እንዲረዳት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፏን ይዛ ወደ ትምህርት ቤት ሄደች። ከክፍል ጓደኞቿ መካከል አንዷ መጽሐፉን አነሳችና “ወሲብና ሥነ ምግባር” እንዲሁም “ተቀጣጥሮ መጫወት፣ ፍቅርና ተቃራኒ ጾታ” የሚሉትን በመሳሰሉ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን ርዕሶች ማንበብ ጀመረች።
“ይህን መጽሐፍ መውሰድ እችላለሁ?” በማለት የክፍል ጓደኛዋ ጠየቀቻት።
“ይኼ የኔ ቅጂ ስለሆነ ሌላ ላመጣላት እንደምችል ነገርኳት” ስትል ተማሪዋ ገልጻለች። “መጽሐፉን አምጥቼ ስሰጣት ያየች ሌላዋ የክፍል ጓደኛዬም መጽሐፉን ተመለከተችና ለእርሷም አንድ ቅጂ እንዳመጣላት ጠየቀችኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ተማሪዎችም መጽሐፉን እንዳመጣላቸው ስለ ጠየቁኝ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የተባለውን መጽሐፍ አሥር ቅጂዎች ወሰድኩላቸው።”
የ14 ዓመቷ ተማሪ መጽሐፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተገንዝባለች። “በአሁኑ ጊዜ በወጣትነት ዕድሜ ላይ መኖር በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ይህ ጽሑፍ በእጅጉ ያስፈልገናል” ብላለች።
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ማግኘት ወይም አንድ ሰው እቤትዎ መጥቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጠውን ጥቅም እንዲያወያይዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው አለዚያም ገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች ወደሚቀርብዎ ይጻፉ።