እንዲሰብኩ አነሣሣቸው
በሩሲያ ሩቅ ምሥራቅ በምትገኘውና 700,000 ሰዎች በሚኖሩባት በካባሮቭስክ ከተማ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። ከዚያች ከተማ ብዙም በማይርቅ አንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሴቶች በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ አገኙ። ይሁን እንጂ በካባሮቭስክ የሚኖሩ ምሥክሮች እነዚህን ሴቶች መንደራቸው ድረስ በመሄድ ሊጠይቋቸው አልቻሉም ነበር።
ስለዚህ ሴቶቹ የተሻለ ነው ብለው ባሰቡበት መንገድ አንድ ላይ በመሆን መጽሐፉን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማጥናት ጀመሩ። መጽሐፉን አጥንተው ከጨረሱ በኋላ ልክ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ያደርጉ እንደነበረው የተማርነውን ነገር ለሌሎች መናገራችን በጣም አስፈላጊ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ።—ማቴዎስ 10:7፤ ሥራ 20:20
የመጀመሪያውን በር ሲያንኳኩ ካገኙት አንድ ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ጀመሩ። ከዚያም የሰውየው ሚስትና ሴት ልጁ በመደበኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ተካፋይ ሆኑ። ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ከተገናኙ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አምስቱም ተጠመቁ። ሌሎችን ለማነጋገር የተነሣሡት እነዚያ ሴቶች በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው።
እርስዎም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ በማንበብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን ለሌሎች ለማካፈል ሊነሳሱ ይችላሉ። የመጽሐፉን አንድ ቅጂ ለማግኘት ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎትና መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎት የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።