‘እርስዎ በዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ የሚችሉት እንዴት ነው?’
◼ መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም መጨረሻ ወይም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ አባባል የሚያመለክተው የሰውን ዘር ከምድር ገጽ ሊያጠፋ የሚችለውን ዓለም አቀፋዊ የኑክሌር እልቂት ነው? ወይስ አንድ የሰማይ አካል ከምድር ጋር በመላተሙ ምክንያት ይከሰታል ተብሎ እንደሚገመተው ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን? ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት እንደሚተርፍ ይናገራል። (ራእይ 7:9, 10, 14) ይሁንና የሚተርፉት እነማን ናቸው? እርስዎም ከሚተርፉት መካከል ሊሆኑ ይችላሉ?
“በዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚለው ንግግር ለእነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ይህ ንግግር የሚቀርበው የይሖዋ ምሥክሮች “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” በሚል ርዕስ በሚያደርጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ነው፤ ስብሰባው ግንቦት ወር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የሚጀመር ሲሆን ከዚያ በኋላ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ላይም ይካሄዳል። እርስዎም በአቅራቢያዎ በሚደረገው አውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ በአክብሮት እንጋብዝዎታለን። ስብሰባው የሚደረግበትን ቀንና ቦታ ለማወቅ በአካባቢዎ የሚኖሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገር ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ይችላሉ። በተጨማሪም የመጋቢት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ኢትዮጵያ ውስጥ ስብሰባው መቼና የት እንደሚካሄድ የሚገልጽ ፕሮግራም ይዞ ይወጣል።