የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ገጽ 193-205
  • ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ትወዳለህ?’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ጋብቻ
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ክርስቲያኖች ትዳራቸውን የሰመረ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ሃይማኖት
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ገጽ 193-205

መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች

ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት

መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምን እንደሆነና የጽድቅ መሥፈርቶቹን እንዴት ማሟላት እንደምትችል ተምረሃል። የተማርከውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ስትል ለሕይወት ያለህን አመለካከትም ሆነ ሥነ ምግባርህን በተወሰነ ደረጃ ማስተካከል አስፈልጎህ ይሆናል። አሁን ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ በማድረግህ የምሥራቹ አገልጋይ ሆነህ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ትገኛለህ።

ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች መከለስህ ይሖዋ ያወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች አእምሮህ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀረጹ ለማድረግ የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ የእሱን ተቀባይነት ካገኙት አገልጋዮቹ አንዱ ለመሆን ልታደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን እንድታስታውስ ይረዳሃል። እዚህ ላይ የቀረበው ሐሳብ ሁሉንም ነገር በንጹሕ ሕሊናና ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ የማድረግን አስፈላጊነት እንድትገነዘብ ያስችልሃል።—2 ቆሮ. 1:12፤ 1 ጢሞ. 1:19፤ 1 ጴጥ. 3:16, 21

በጥናትህ ገፍተህ እዚህ ደረጃ ላይ ስለደረስክ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ለማበርከትና ለይሖዋ አመራር ተገዢ ለመሆን እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ጥያቄዎችና ጥቅሶች ከጉባኤ አደረጃጀት፣ ከቤተሰብ ሕይወትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለሰጠው መመሪያ የምታሳየውን ተገዢነት በተመለከተ ግንዛቤህን እንድትመረምር ይረዱሃል። በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለማስተማርና ለመገንባት ላደረገው ዝግጅት ያለህ አድናቆት እንዲጨምር እንደሚረዳህ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ሕዝቡን ከሚያስተምርባቸው መንገዶች መካከል የጉባኤ ስብሰባዎች የሚገኙበት ሲሆን አንተም በተቻለህ መጠን በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብሃል።

ከዚህም ሌላ ይህ ክፍል በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ቋሚ የሆነ ተሳትፎ በማድረግ ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁና ለሰው ልጆች እያደረገ ያለውን ነገር እንዲገነዘቡ የመርዳትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በመጨረሻም ራስህን ለይሖዋ አምላክ ስትወስንና ስትጠመቅ የገባኸው ቃል ምን ያህል ክብደት እንዳለው እንድትገነዘብ ያስችልሃል። ይሖዋ፣ እሱ ላሳየህ ጸጋ የሰጠኸውን ከልብ የመነጨ ምላሽ እንደሚያደንቅ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

1. ጋብቻን በተመለከተ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው መሥፈርት ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ለመፍታት የሚያስችለው ብቸኛው ምክንያት ምንድን ነው?

• “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው። . . . በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”—ማቴ. 19:4-6, 9

2. አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ከሆነ ሕጋዊ ጋብቻ መፈጸም ያለባቸው ለምንድን ነው? ያገባህ ከሆንክ ጋብቻህ ሕጋዊና በመንግሥት ዘንድ እውቅና ያለው ነው?

• “ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ . . . አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1

• “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋልና።”—ዕብ. 13:4

3. በቤተሰብ ውስጥ ያለህ ድርሻ ምንድን ነው?

• “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ተግሣጽ አዳምጥ፤ የእናትህንም መመሪያ አትተው።”—ምሳሌ 1:8

• “ክርስቶስ [የጉባኤው] ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው። ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ . . . ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።”—ኤፌ. 5:23, 25

• “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።”—ኤፌ. 6:4

• “ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና።”—ቆላ. 3:20

• “እናንተ ሚስቶች፣ . . . ለባሎቻችሁ ተገዙ።”—1 ጴጥ. 3:1

4. ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

• “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው [አምላክ ነው]። . . . ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።”—ሥራ 17:25, 28

5. በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ጨምሮ የማንንም ሰው ሕይወት ማጥፋት የሌለብን ለምንድን ነው?

• “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና . . . ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት . . . እንዲመለስ ማድረግ አለብህ።”—ዘፀ. 21:22, 23, 25

• “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ፤ አንዳቸውም ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት፣ የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ በዝርዝር ተጻፈ።”—መዝ. 139:16

• “ይሖዋ . . . ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች [ይጠላል]።”—ምሳሌ 6:16, 17

6. አምላክ ደምን በተመለከተ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል?

• “ከደም [እና] ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ . . . ራቁ።”—ሥራ 15:29

7. ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

• “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:34, 35

8. ተላላፊ በሆነና ለሞት ሊዳርግ በሚችል በሽታ የተያዘ ሰው በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳያስተላልፍ (ሀ) ሌሎችን ማቀፍና መሳም የሌለበት ለምንድን ነው? (ለ) አንዳንዶች ቤታቸው ሳይጋብዙት ቢቀሩ ቅር መሰኘት የሌለበት ለምንድን ነው? (ሐ) ተላላፊ ለሆነ በሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሰው ለጋብቻ መጠናናት ከመጀመሩ በፊት በራሱ ፈቃድ የደም ምርመራ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው? (መ) ተላላፊ በሽታ የያዘው ሰው ከመጠመቁ በፊት ሁኔታውን ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ማሳወቅ ያለበት ለምንድን ነው?

• “እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ . . . ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። . . . ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።”—ሮም 13:8-10

• “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵ. 2:4

9. ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድንል የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?

• “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላ. 3:13

10. አንድ ወንድም ስምህን ቢያጠፋ ወይም ቢያጭበረብርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

• “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ። የማይሰማህ ከሆነ ግን ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ። እነሱንም ካልሰማ ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ አድርገህ ቁጠረው።”—ማቴ. 18:15-17

11. ይሖዋ ለሚከተሉት የኃጢአት ድርጊቶች ምን አመለካከት አለው?

▪ የፆታ ብልግና

▪ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም

▪ ግብረ ሰዶም

▪ ስርቆት

▪ ቁማር

▪ ስካር

• “አትታለሉ፤ ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮ. 6:9, 10

12. ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸሙ የተለያዩ ፆታዊ ድርጊቶችን የሚጨምረውን የፆታ ብልግናን በተመለከተ ቁርጥ አቋምህ ምንድን ነው?

• “ከፆታ ብልግና ሽሹ!”—1 ቆሮ. 6:18

13. ለሕክምና ካልሆነ በቀር ሱስ የሚያስይዙ ወይም አስተሳሰብን የሚያዛቡ ተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮችን ከመውሰድ መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

• “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው። በተጨማሪም ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:1, 2

14. አምላክ ከሚከለክላቸው አጋንንታዊ ድርጊቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

• “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።”—ዘዳ. 18:10, 11

15. አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢሠራና የይሖዋን ሞገስ መልሶ ማግኘት ቢፈልግ ወዲያውኑ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

• “ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ ስህተቴን አልሸፋፈንኩም። ‘የፈጸምኳቸውን በደሎች ለይሖዋ እናዘዛለሁ’ አልኩ።”—መዝ. 32:5

• “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል።”—ያዕ. 5:14, 15

16. አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

• “አንድ ሰው ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።”—ዘሌ. 5:1

17. አንድ ሰው ከእንግዲህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ ማስታወቂያ ቢነገር ከዚህ ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ምን ማስተካከያ ማድረግ አለብን?

• “ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን [ተዉ]።”—1 ቆሮ. 5:11

• “ማንም ሰው ወደ እናንተ ቢመጣና ይህን ትምህርት ይዞ ባይመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ወይም ሰላም አትበሉት።”—2 ዮሐ. 10

18. ጓደኛ የምታደርጋቸው ሰዎች ይሖዋን የሚወዱ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

• “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።”—ምሳሌ 13:20

• “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮ. 15:33

19. የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

• “እኔ [ኢየሱስ] የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።”—ዮሐ. 17:16

20. የመንግሥት ባለሥልጣናትን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው?

• “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።”—ሮም 13:1

21. አንድ ሰብዓዊ ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ?

• “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።”—ሥራ 5:29

22. የምትመርጠው ሥራ ከዚህ ዓለም ጋር የሚያነካካህ እንዳይሆን የሚረዱህ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው?

• “አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።”—ሚክ. 4:3

• “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ [ከታላቂቱ ባቢሎን] ውጡ።”—ራእይ 18:4

23. የምትመርጠው መዝናኛ ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? ከየትኞቹ መዝናኛዎችስ ልትርቅ ይገባል?

• “ይሖዋ . . . ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል።”—መዝ. 11:5

• “ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።”—ሮም 12:9

• “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵ. 4:8

24. የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች ጋር በአምልኮ ሥርዓት መካፈላቸው ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?

• “‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።”—1 ቆሮ. 10:21

• “‘ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ’፤ ‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”—2 ቆሮ. 6:17

25. አንድን በዓል ማክበር ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዱህ የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

• “በዚያ ከነበሩት ብሔራት ጋር ተቀላቀሉ፤ የእነሱንም መንገድ ተከተሉ። ጣዖቶቻቸውን አመለኩ፤ እነሱም ወጥመድ ሆኑባቸው።”—መዝ. 106:35, 36

• “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።”—መክ. 9:5

• “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።”—ዮሐ. 17:16

• “ዓይን ባወጣ ምግባር፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።”—1 ጴጥ. 4:3

26. የልደት በዓልን ማክበር ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዱህ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

• “ሦስተኛው ቀን ደግሞ ፈርዖን የልደት በዓሉን የሚያከብርበት ዕለት ነበር፤ እሱም ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አዘጋጀ። አገልጋዮቹ ባሉበትም የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ከእስር ቤት አስወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹንም አለቃ ወደ መጠጥ አሳላፊነት ሹመቱ መለሰው። . . . የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ግን . . . ሰቀለው።”—ዘፍ. 40:20-22

• “የሄሮድስ ልደት በተከበረበት ዕለት የሄሮድያዳ ልጅ በግብዣው ላይ በመጨፈር ሄሮድስን እጅግ ደስ አሰኘችው፤ በመሆኑም የጠየቀችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። ከዚያም እናቷ በሰጠቻት ምክር መሠረት ‘የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ ሳህን ስጠኝ’ አለችው። ሰው ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቆረጠ።”—ማቴ. 14:6-8, 10

27. ሽማግሌዎች የሚሰጡትን አመራር እንድትከተል የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

• “ተግተው ስለሚጠብቋችሁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህን የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያከናውኑ ነው፤ አለዚያ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሐዘን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።”—ዕብ. 13:17

28. አንተም ሆንክ ቤተሰብህ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራችሁ የምታነብቡበትና የምታጠኑበት ጊዜ መመደባችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• “በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል። በጅረቶች ዳር እንደተተከለ፣ ፍሬውን በወቅቱ እንደሚሰጥ፣ ቅጠሉም እንደማይጠወልግ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል።”—መዝ. 1:2, 3

29. በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ የሚያስደስትህ ለምንድን ነው?

• “ስምህን ለወንድሞቼ አሳውቃለሁ፤ በጉባኤ መካከልም አወድስሃለሁ።”—መዝ. 22:22

• “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።”—ዕብ. 10:24, 25

30. ኢየሱስ የሰጠን ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ ምንድን ነው?

• “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20

31. የመንግሥቱን ሥራ ወይም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመደገፍ መዋጮ ስናደርግ የትኛውን ዝንባሌ ማሳየታችን ይሖዋን ያስደስተዋል?

• “ባሉህ ውድ ነገሮች . . . ይሖዋን አክብር።”—ምሳሌ 3:9

• “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።”—2 ቆሮ. 9:7

32. ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ይጠብቃሉ?

• “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና። በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።”—ማቴ. 5:10-12

33. ተጠምቆ ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ መቆጠር ልዩ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

• “ይሖዋ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሴት፣ ለልቤም ደስታ ሆነልኝ።”—ኤር. 15:16

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ