መስቀል የክርስትና ምልክት ነውን?
ለብዙ መቶ ዘመናት ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች መስቀልን የክርስትና ምልክት እንደሆነ አድርገው ተቀብለውታል። ነገር ግን በእርግጥ የክርስትና ምልክት ነውን? መስቀል የክርስትና ምልክት ነው ብለው ከልባቸው ያምኑ የነበሩ ብዙ ሰዎች መስቀል ፈጽሞ ለሕዝበ ክርስትና ብቻ የተወሰነ ምልክት እንዳልነበረ ሲያውቁ በጣም ተገርመዋል። በተቃራኒው በዓለም ዙሪያ ክርስቲያን ባልሆኑ ሃይማኖቶች በሠፊው ተሠርቶበታል።
ለምሳሌ ያህል በ1500ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሄርናን ኮርቴስና የእርሱ “ክርስቲያን” ሠራዊት የአዝቴክን ግዛት ለማጥቃት ሲዘጋጁ “በዚህ ምልክት እናሸንፋለንና የቅዱስ መስቀልን ምልክት በእውነተኛ እምነት እንከተል” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ነበር። አረማውያን የሆኑ ጠላቶቻቸውም መስቀልን ከእነርሱ ባልተለየ መልኩ እንደሚያከብሩት ሲገነዘቡ ተገርመው መሆን አለባቸው። የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች የተሰኘው መጽሐፍ “ኮርቴስና ተከታዮቹ የአዝቴኮች ሰውን የመሠዋት ልማድና ለነፋስና ለዝናብ አማልክት ለቆሙ መስቀል መሰል ምልክቶች ክርስትና ክብር መስጠቱ . . . ለማሳቅ ተብሎ የሚደረግ ዓይነት ሰይጣናዊ ማስመሰያ መስሎ ስለታያቸው ወደ ኋላ አፈገፈጉ” ይላል።
ጸሐፊ ጆሴ አልቤርቶ ፉርኬ ላ ናሲዮን በተባለ ጋዜጣ ላይ በወጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ እንደገለጹት በ18ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ “በሰው ልጆች ላይ ጥናት በሚያካሂዱ ሰዎችና በመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች መካከል የመስቀል ምልክቶች አመጣጥና ትርጉም ላይ የተጧጧፈና ስሜትን የሚቀሰቅስ ክርክር” ተጀምሮ ነበር። እነዚህም የመስቀል ምልክቶች ያገኟቸው በአመዛኙ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ ክፍሎች ነበር። በግልጽ እንደሚታየው አንዳንዶቹ መስቀል “የክርስትና” ብቸኛ መለያ እንደሆነ አድርገው ክብሩን ለመጠበቅ በጣም ዝግጁዎች ስለነበሩ አሜሪካውያን ከምዕራፍ ከፋቹ የኮለምበስ የባሕር ጉዞ በፊት በሆነ መንገድ ወንጌል ተሰብኮላቸው መሆን አለበት የሚል ንድፈ ሐሳብ አስፋፉ! ይህ የማይመስል አስተሳሰብ መሠረተ ቢስ ነው ተብሎ ተወግዷል።
ከጊዜ በኋላ በዚህ መስክ የተደረጉ ተጨማሪ ምርምሮች ይህን መሳይ ክርክሮችን በሙሉ አሳረፉአቸው። ፉርክ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻሉ፦ “በ1893 በስሚዝሶኒያን ተቋም በተዘጋጀ ጽሑፍ ላይ . . . የመጀመሪያዎቹ አውሮፓውያን ሰሜን አሜሪካን ከመርገጣቸው ከረጅም ጊዜ በፊት መስቀል ይከበር እንደነበረ ተረጋግጧል፤ . . . ይህ ዓይነቱ ምልክት በሁሉም ማኅበረሰቦች ዘንድ ሕይወትን አመንጭተዋል ተብሎ ክብር ይሰጣቸው በነበሩ ኃይሎች አምልኮ ክፍል ውስጥ ተገኝቷል።
ኢየሱስ የተገደለው በዘልማድ በሚከበረው መስቀል ላይ ሳይሆን በእንጨት ላይ ወይም በግሪክኛው ስታውሮስ ላይ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ በማቴዎስ 27:40 ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ በሕንፃ መሠረት ላይ እንደሚደረጉት ወጥ ግንዶች ያለ አንድ ወጥ ጠርብ ወይም ግንድ ነው። ስለዚህ መስቀል እውነተኛ ክርስትናን ወክሎ አያውቅም። ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ባለ ጊዜ የእውነተኛው የክርስትና እምነት “ምልክት” ምን እንደሆነ ገልጿል።—ዮሐንስ 13:35