መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው ይመለከቱታልን?
ከ200 ዓመታት በፊት ሜሪ ጆንስ ከአትላንቲክ የባህር ዳርቻ ብዙም በማይርቅ ሌንፊንሼል በሚባል አንድ ገለልተኛ የዌልስ መንደር ውስጥ ተወለደች። ወላጆቿ ድሃ ሸማኔዎች ነበሩ። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን የመግዛት አቅም አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንና በቃል የሚያስታወሷቸውን ጥቅሶች እየደጋገሙ በመንገር ልጃቸው ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርባት አደረጉ። ሜሪ በዌልስ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ከጎረቤት እየተዋሰች ብዙ ጊዜ ታነብ ነበር። የራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ቆርጣ በመነሣት የምታገኘውን አነስተኛ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረች።
በ1800 ሜሪ 16 ዓመት ሲሞላት 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባላ በተባለች አነስተኛ ከተማ በዌልስ ቋንቋ የተጻፉ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሶች እንደሚሸጡ ሰማች። ተስፋ አልቆረጠችም፤ እዚያ ድረስ በእግሯ ለመሄድ ቆርጣ ተነሣች። ባዶ እግሯን ኮረብታዎቹን አቋርጣ ሄደች። ይሁን እንጂ እሷ እዚያ ስትደርስ መጽሐፎቹ ሁሉ ተሸጠው አልቀው ነበር። ያጠራቀመችው ገንዘብም ቢሆን ከመጽሐፉ ዋጋ ጋር የማይመጣጠን አነስተኛ ገንዘብ እንደሆነ ተገነዘበች።
የአካባቢው ሰባኪ የሆኑት ቄስ በሜሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና ፍቅር በጣም ተነኩ። እንደዚያ ደክማ መጽሐፉን ባለማግኘቷ አዝና ስታለቅስ በማየታቸው የራሳቸውን ቅጂ ሰጧት። እንዲህም አሏት፦ “በጥንቃቄ አንብቢው፤ በትጋት አጥኚው፤ ቅዱስ ቃሎቹን በአእምሮሽ ማኅደር ውስጥ ክተቺያቸው፤ የመጽሐፉን ትምህርቶች ተግባራዊ አድርጊ።”
ከጊዜ በኋላ ይህ ታሪክ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የሃይማኖታዊ ትራክት ማኅበር ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተወሳ። በዚያ ስብሰባ ላይ በዌልስ ለሚኖሩት ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለማቅረብ ውሳኔ ተላለፈ። ከዚህ አነስተኛ ጅምር በመነሳት ብዙ የ19ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሮች ተቋቋሙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ቶሎ ቶሎ መታተም ጀመሩ።
በ1884 ሕጋዊ ኮርፖሬሽን ሆኖ የተቋቋመው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ከ200 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ያትማል። በዓለም ዙሪያ ዘመናዊ በሆነ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም 72 ሚልዮን ቅጂዎች አሰራጭቷል። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥና ከግሪክ ቋንቋዎች የተተረጎመው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ በሙሉም ሆነ በከፊል በ18 ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን በሌሎች 12 ልሳኖችም በመተርጎም ላይ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ በማንኛውም ሰው እጅ ውስጥ ይገኛል ሊባልለት የሚችለውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ይመለከቱታል? መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው ይመለከቱታልን? እንደ ውድ ሀብት አድርገው የሚይዙትና የሚያነቡት የግል ቅጂ አለዎትን?
[ምንጭ]
The Story of Mary Jones and Her Bible ከተባለ መጽሐፍ የተወሰደ