ሃይማኖት ሊወያዩበት የማይገባ ርዕስ ነውን?
“በጭራሽ መወያየት የማልፈልጋቸው ሁለት ርዕሶች አሉ—ሃይማኖትና ፖለቲካ!” ይህ የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነጋግሩ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ምላሽ ነው። ሰዎች እንዲህ ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው በቂ ምክንያት አላቸው።
ሰዎች ስለ ፖለቲካ ሲከራከሩ ግልፍ ሊላቸውና ወዲያውኑ ጥል ሊከተል ይችላል። ብዙዎች በባዶ ተስፋዎች አይታለሉም፤ ብዙውን ጊዜ ፖለቲከኞች ሥልጣን፣ ዝናና ገንዘብ እንደሚፈልጉ ይገነዘባሉ። አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ ከፍተኛ ብጥብጦች ማምራታቸው ያሳዝናል።
‘ይሁን እንጂ ሃይማኖትስ እንዲሁ አይደለምን? በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ብዙዎቹን ግጭቶች የቀሰቀሰው የሃይማኖት አክራሪነት አይደለምን?’ ትል ይሆናል። በሰሜን አየርላንድ የሮማ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ለረጅም ጊዜ ሲቀናቀኑ ኖረዋል። በቦልቲክ አገሮች የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሮም ካቶሊኮችና ሌሎች ሃይማኖቶች የመሬት የበላይነትን ለማግኘት ይሻኮታሉ። ይህ ምን ውጤት አስከተለ? ብዙ ግፍ እንዲፈጸምና የማያቋርጥ ጥላቻ እንዲፈጠር አድ ርጓል።
ብዙዎች ለሕይወታቸው በመስጋት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን እምነት ይደብቃሉ። በአፍሪካ ውስጥ በሕዝበ ክርስትና ምእመናን፣ ከውጪ በመጡና በጎሣ ሃይማኖት አክራሪዎች መካከል የሚደረግ ለብዙ መቶ ዘመናት የቆየ ሃይማኖታዊ ግጭት መኖሩ ወላጆች ልጆቻቸውን በመጠኑም ቢሆን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ ሁለት ስሞች እንዲያወጡላቸው አድርጓቸዋል፤ ይህ ልማድ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራበታል። ስለዚህ ልጁ ከሁለቱ በአንደኛው ስም ብቻ በመጠቀም ራሱን የቤተ ክርስቲያን ወይም የሌላ ሃይማኖት አባል እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ይችላል። አንድን ሰው ሃይማኖቱ ሕይወቱን እንዲያጣ የሚያደርገው ከሆነ ስለ ሃይማኖት በግልጽ ለመወያየት ቢያቅማማ ምንም አያስደንቅም።
ሌሎች ሰዎች ለሕይወታቸው የሚያሰጋ ነገር ባይኖርም እንኳ ስለ ሃይማኖት መወያየት አይፈልጉም። የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ከሆነ ሰው ጋር መወያየት እልባት ወደሌለው ክርክር ይመራል ብለው ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ ሁሉም ሃይማኖች ጥሩ ናቸው የሚል እምነት አላቸው። አንድ ሰው የሚያምነው ነገር እስካረካው ድረስ ስላሉት ልዩነቶች መነጋገሩ ፋይዳ አይኖረውም ይላሉ።
ሥራዬ ብለው ስለ ሃይማኖት የሚያጠኑ ሰዎችም እንኳ እርስ በርሳቸው አይስማሙም። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ “የሃይማኖቶች ጥናትና ልዩነቶች” በተባለው ርዕሱ ላይ እንዲህ ይላል፦ “[የሃይማኖትን] ጽንሰ ሐሳብ በተመለከተ በምሁራን መካከል እምብዛምስምምነት የለም። . . . ስለዚህ ይህ ርዕስ በታሪክ ዘመናት ሁሉ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል።”
አንድ መዝገበ ቃላት ለሃይማኖት የሰጠው ፍቺ “የሰው ልጅ እንደ ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለም ገዥ አድርጎ ለሚቀበለው ከሰው በላይ ለሆነ ኃይል ያለው እምነትና አክብሮት መግለጫ” የሚል ነው። ይህ ሁኔታ ሃይማኖት በሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት የሚያደርግ ነው። በእርግጥም ሃይማኖት በሁሉም ቦታ የሰው ልጆችን የታሪክ አቅጣጫ ሲመራ ቆይቷል። ኦክስፎርድ ኢላስትሬትድ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ፒፕልስ ኤንድ ካልቸርስ የተባለው መጽሐፍ “በአንድ ዓይነት ሃይማኖት ተጠቅሞ የሕይወትን ሥርዓትና ትርጉም ለመፈለግ ያልጣረ ኅብረተሰብ የለም” ብሏል። እንደ “ሥርዓት” እና “ትርጉም” ያሉትን የሕይወት መሠረታዊ ነገሮች ስለሚያቅፍ በሃይማኖት መከራከር ወይም መወዛገብ አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን ከሌላ ሰው ጋር መወያየት ማለትም በጥሞና መመርመር ይገባል። ግን ከማን ጋር? ነገሩን በጥሞና ከመመርመርስ ምን ጥቅም ይገኛል?