የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በጣም አስቸጋሪ በሆነ ወቅትም መስበክ
ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን [እንደሚመጣ]” አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እነዚህ ቃላት ትክክለኛ መሆናቸው ምንኛ ተረጋግጧል! በመካከለኛው አሜሪካ በምትገኘው በኤል ሳልቫዶር የሚኖሩ ሕዝቦች ይህንን መራራ እውነታ ለረዥም ጊዜ ቀምሰዋል። ይህች አገር ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት በብዙ ሺህ ሰዎች ላይ ሥቃይና ሞት ባስከተለ የእርስ በርስ ጦርነት ተውጣ ነበር። ጦርነቱ ቢያልፍም ችግሩ ግን አሁንም አለ። ከጦርነቱ በኋላ ወንጀል በፍጥነት ተስፋፍቷል። በቅርቡ አንድ የአካባቢው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ “አምባጓሮና ዝርፊያ የዕለት ተዕለት ገጠመኛችን ሆኗል” በማለት ገልጿል።
የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ የወንጀል ማዕበል አላመለጡም። ቤት ሰርሳሪ ሌቦች ወደ ብዙ የመንግሥት አዳራሾች በጉልበት ገብተው የድምፅ መሣሪያዎችን ሰርቀዋል። ብዙ ጊዜ በቡድን የተደራጁ የታጠቁ ወጣት ዘራፊዎች ክርስቲያናዊ ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ሳይታሰብ ወደ መንግሥት አዳራሾች በመግባት ከተሰብሳቢዎች ገንዘብ፣ ሰዓቶችንና ሌሎች ውድ ጌጣ ጌጦችን ዘርፈዋል። ሌላው ቀርቶ ብዙ ምሥክሮች በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ላይ ሳሉ በዘራፊዎች ተገድለዋል።
ምንም እንኳ እነዚህ እንቅፋቶች ቢጋረጡባቸውም በኤል ሳልቫዶር የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በርትተው ቀጥለዋል። ይህንንም የሚያደርጉት “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ በመቀበል ነው። (ማርቆስ 13:10) በዚህች አገር መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን የመንግሥቱን ተስፋ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሁንም ያሉ ሲሆን ምሥክሮቹም እያንዳንዳቸውን ለማግኘት እየጣሩ ነው። መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነትም ውጤታማ የመስበኪያ ዘዴ መሆኑ እየታየ ነው።
በአንድ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለ ያለ አንድ ምሥክር ባለው አጋጣሚ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚኙትን አምላክ ስለወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸውን ተስፋዎች ከሌሎች በሽተኞች ጋር ለመነጋገር ይጠቀም ነበር። በጽኑ የታመመ አንድ በሽተኛ “በቅርቡ እሞታለሁ!” በማለት በሐዘን ተውጦ ተናገረ። ነገር ግን የበሽተኛው የጨለመ ተስፋ ምሥክሩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማካፈል ተስፋ አላስቆረጠውም። ከዚህ ይልቅ ድምፁን ከፍ አድርጎ በይሖዋ ምሥክሮች ከታተመው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ ከተባለው መጽሐፍ ለሰውዬው ያነብለት ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ምሥክሩ ከሆስፒታሉ ሲወጣ ሰውዬው በሞት አፋፍ ላይ እንደሆነ በማሰብ አዝኖ ነበር።
ከአራት ዓመታት በኋላ ምሥክሩ በሌላ ሆስፒታል ህክምና መከታተል ነበረበት። እዚያ ሳለ አንድ በሽተኛ ወደ እርሱ መጣና “ታስታውሰኛለህ?” አለው። ከአራት ዓመት በፊት ያገኘው ይሞታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሰውዬ ነበር! ሰውዬው ሲጠመጠምበትና ቀጥሎም “አሁን እኔም ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ሆኛለሁ!” ሲለው እንዴት ያለ ያልታሰበ ደስታ ነበር! ሰውዬው ስለ ወደፊቱ ጊዜ በተነገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት አሳድሯል፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቷል እንዲሁም ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኗል። ምሥክር መሆን ብቻ ሳይሆን ለሁለት ዓመታት ያህል የዘወትር አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈል ነበር።
በዚህ አጋጣሚ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተዘሩት የእውነት ዘሮች አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጥ ልብ አግኝተዋል። ያለንበት ጊዜ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ቢሆንም እንኳ ይህ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ የመርዳት መብት እውነተኛ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ እንዲቀጥሉ ይገፋፋቸዋል።