ትርጉም የለሽ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነውን?
ካቶሊኮች ለብዙ መቶ ዘመናት ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓቶች ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ለብዙዎች እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት ባዶ ድግግሞሽ ነው። ቦብ የተባለ የአንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁም እንኳ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓት ከቁም ነገር አልቆጥረውም ነበር” በማለት በወጣትነቱ ጊዜ ይሰማው የነበረውን ተናግሯል። ለምን? ለእርሱ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓት ትርጉም የለሽ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሆኖበታል። እንዲህ በማለት ያብራራል፦ “ኃጢአትን መናዘዝ ማለት ኃጢአት የተሞሉ ሻንጣዎችህን በሙሉ ይዘህ በአውሮፕላን ማረፊያ ወደሚገኝ የጉምሩክ ሠራተኛ እንደመሄድ ያክል ነው። እርሱም ስለ ኃጢአቶችህ ይጠይቅህና ውጪ አገር በነበርክበት ጊዜ ለገዛሃቸው የቅንጦት እቃዎች ቀረጥ ካስከፈለህ በኋላ እንድትሄድ ይፈቅድልሃል።”
በተመሳሳይም ፍራንክ ዊስሊን ዩ ኤስ ካቶሊክ በተባለው መጽሔት ላይ ባቀረቡት መጣጥፍ ኃጢአትን ስለ መናዘዝ ሲገልጹ “አንድ ግለሰብ ለሠራቸው የተለመዱ ኃጢአቶች ምሕረት የሚያገኝበት፣ ቀጥሎም በቃል የተሸመደደ የንስሐ ጸሎት የሚያቀርብበትና በኃጢአቱ መጸጸቱን የሚያሳይ አነስተኛ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚያከናውንበት ደረጃ በደረጃ የሚፈጸም በጣም ቀላል የሆነ ሥርዓት ነው” ብለዋል። ታዲያ ዊስሊን ምን በማለት ደምድመዋል? “ኃጢአትን መናዘዝ ለአንድ ሰው መንፈሳዊ ደህንነት ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል። “ይሁን እንጂ ካቶሊኮች ይህንን የሚያከናውኑት በተሳሳተ መንገድ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን ስለ መናዘዝ የሚናገረው ሐሳብ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ከሁሉ በላይ ኑዛዜ መቅረብ ያለበት ለአምላክ ነው። (መዝሙር 32:1–5) እንዲሁም ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ” በማለት ጽፎአል።—ያዕቆብ 5:14, 16
በኃጢአት የተደቆሰ አንድ ክርስቲያን የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችን ሊጠራ ይችላል። እነርሱም መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው የኃጢአት አካሄዱን እንዲተው ለመርዳት ሊሠሩ የሚችሉ ምክሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ ይለግሱታል። የበላይ ተመልካቾች በመንፈሳዊ የታመመው ሰው የሚያሳየውን እድገት እየተከታተሉ አስፈላጊ የሆኑ ማበረታቻዎችን ሊሰጡት ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ከሚደረጉት ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓቶች ምንኛ የተለየ ነው! በጉባኤ ሽማግሌዎች አማካኝነት ባገኙት እርዳታ ንስሐ የገቡ መጥፎ ድርጊት ፈጻሚዎች ዳዊት በመዝሙሩ ውስጥ እንደገለጸው ዓይነት የእፎይታ ስሜት ሊያገኙ ይችላሉ፦ “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።”—መዝሙር 32:5