የቀድሞው ዳኛ ከ45 ዓመት በኋላ ይቅርታ ጠየቁ
ነሐሴ 1995 በርሊን ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ውስጥ አንድ የቀድሞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ከ45 ዓመት በፊት ለፈጸሙት ስሕተት የተሰማቸውን ጸጸት ለአንድ የይሖዋ ምሥክር ገልጸውለታል።
ጥቅምት 1950 የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ (ጂ ዲ አር) ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፀረ መንግሥት ቅስቀሳ አድርገዋል እንዲሁም ምሥጢር አቀብለዋል በማለት በዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በይኖ ነበር። ሁለቱ ዕድሜ ይፍታህ የተፈረደባቸው ሲሆን በፎቶግራፉ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ አራተኛ ላይ የሚገኘውን የ22 ዓመቱን ሎታር ሆርኒክን ጨምሮ የተቀሩት ሰባቱ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው።
ከአርባ ዓመት በኋላ ጂ ዲ አር የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ አካል ሆነች። ባለ ሥልጣኖች በቀድሞዋ ጂ ዲ አር የተፈጸመውን አንዳንድ የፍትሕ መጓደል መርምረው ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት አድርገዋል። እንዲህ ዓይነቱ የፍትሕ መጓደል ከተፈጸመበት ጊዜ አንዱ በ1950 የይሖዋ ምሥክሮችን ጉዳይ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያዋለው ችሎት ነው።
በአሁኑ ጊዜ 80 ዓመት የሆናቸው ኤ ቲ በዘጠኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፈረዱት ሦስት ዳኞች አንዱ ነበሩ። አሁን ግን ፍትሕን በማዛባት ተከሰው ስለሰጡት ፍርድ እንዲያስረዱ በርሊን ውስጥ በሚገኘው የአካባቢ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የቀድሞው ዳኛ ያሳለፉት ቅጣት ከሌሎቹ ያነሰ ቢሆንም ከ45 ዓመት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጥተው እንደነበረ የእምነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል። ሆኖም አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ጉዳዩን እንደገና እንዲያጤኑት አድርጓቸዋል። ለምን? የይሖዋ ምሥክሮች ሂትለርን አንደግፍም ስላሉ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች አሳድደዋቸው ነበር። እንደገናም ከጦርነቱ በኋላ ምሥክሮቹ ከኮሚኒስቱ መንግሥት ስደት ደርሶባቸዋል። ይህም ዳኛውን “በጣም አሳዘናቸው።”
ሎታር ሆርኒክ አምስት ዓመት ተኩል ከሰው ተገልሎ እንደታሰረና ከብራንደንበርግ እስር ቤት የተፈታው በ1959 እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናገረ። የቀድሞው ዳኛ ሆርኒክ የሚናገረውን ሲሰሙ አለቀሱ። ሲቃ እየተናነቃቸው “በጣም አዝናለሁ። ይቅርታ አድርግልኝ” አሉት። ሆርኒክ ይቅር አላቸው።—ከሉቃስ 23:34 ጋር አወዳድር።
[ምንጭ]
Neue Berliner Illustrierte