“ይሖዋ ጸሎቴን ሰማልኝ!”
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክና ለሰው ዘር ስላለው አስደናቂ ዓላማ ትክክለኛ እውቀት የማግኘት ፍላጎት ካላቸው ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እያካሄዱ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ በዚህ ሥራ እየተካፈሉ ነው። ለምሳሌ ያህል ጆኤል የተባለውን ልጅ እንውሰድ። ራሱን ለይሖዋ በመወሰን በዘጠኝ ዓመቱ ተጠመቀ። ከተጠመቀ ከአንድ ዓመት በኋላ የሚከተለው ተሞክሮ አጋጠመው፦
“በአገልግሎት ላይ ሳለሁ ካንዲ የተባለች አንዲት ሴት አገኘሁ። ‘እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ ’ የተባለውን ብሮሹር እንድትወስድ ጋበዝኳት። ብሮሹሩ ያላት በመሆኑ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ እንድትወስድ ሐሳብ አቀረብኩላት። ይኼኛውም መጽሐፍ አላት። ስለዚህ ‘ይህችን ሴት ለምን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድትጀምር አልጠይቃትም’ የሚል ሐሳብ መጣልኝ። ፈቃደኛ ሆነች!
“በካንሰር በሽታ በመሠቃየት ላይ የነበረችው የካንዲ እህት ከእሷ ጋር ለመኖር መጣች። ከዚህም በተጨማሪ ካንዲ የነርስነት ትምህርት በመከታተል ላይ ነበረች። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ለተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ። ሆኖም ወላጆቼና እኔ ከእሷ ጋር የነበረንን ግንኙነት አላቋረጥንም፤ ዘወትር እየሄድን ለእሷ ወይም ዲክ ለተባለው ባሏ መጽሔቶች እንሰጣቸው ነበር። ባልዋ መጽሔቶቹን አልጋዋ አጠገብ እያስቀመጠች ማታ ማታ እንደምታነባቸው ነገረን።
“በመጨረሻ የካንዲ እህት ሞተች። አባቴ፣ እናቴና እኔ አንድ ላይ ሆነን ካንዲን ሙታን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አነጋገርናት። ካንዲ ጥናቷን እንደገና ለመጀመር ወሰነች። ሌላ ቀን ስንሄድ ዲክ ከካንዲ ጋር አብሮ እንዲያጠናና ጥናቱን በቤተሰብ መልክ እንድናደርገው ሐሳብ አቀረብንለት። ዲክ በሐሳቡ ተስማማ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ከአባቴ ጋር ሆነን ዲክንና ካንዲን እያስጠናናቸው ነው። ጥሩ እድገት እያደረጉ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ያላቸውን አድናቆት በየጊዜው ይገልጹልናል።
“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዳገኝ ስጸልይ ነበር፤ ይሖዋ ጸሎቴን ሰማልኝ!”