የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ጽናት የአምላክን በረከት እንደሚያስገኝ በማላዊ ታይቷል
ዮሴፍ የታመነ የይሖዋ አገልጋይ ነበር። (ዕብራውያን 11:22) ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ጽናት ያሳየ ሰው ነበር። ዮሴፍ ምንም እንኳ የገዛ ወንድሞቹ ቢክዱት፣ ሁለት ጊዜ ለባርነት ቢሸጥና ከጊዜ በኋላ በውሸት ተከስሶ ወህኒ ቤት ቢጣልም ተስፋ አልቆረጠም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና የይሖዋን በረከት በመጠባበቅ ለበርካታ ዓመታት የደረሰበትን መከራ በትዕግሥት ጸንቷል።—ዘፍጥረት 37:23-28, 36፤ 39:11-20
ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን በረከት ለማግኘት በትዕግሥት ተጠባብቀዋል። እነዚህ ክርስቲያን ምሥክሮች የመንግሥት እገዳዎችን፣ ከባድ ተቃውሞዎችንና በርካታ የጭካኔ ድርጊቶችን ለ26 ዓመታት ተቋቁመው ኖረዋል። ሆኖም ጽናታቸው ፍሬ አፍርቷል!
በማላዊ በ1967 ማብቂያ ላይ ስደቱ ሲጀምር የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 18,000 የሚጠጋ ነበር። የ1997 የአገልግሎት ዓመት ሲጀምር 38,393 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ማለትም እገዳው ሲጀምር ከነበረው ከእጥፍ የሚበልጥ ቁጥር እንደነበር ሲያውቁ ምሥክሮቹ ምን ያህል እንደሚደሰቱ ገምት! ከዚህም በተጨማሪ በማላዊ በተደረጉት 13 “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የነበረው አጠቃላይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ117,000 በላይ ነበር። በእርግጥም ይሖዋ እምነታቸውንና ጽናታቸውን ባርኮላቸዋል።
ማቻካ የተባለው የ14 ዓመት ልጅ ተሞክሮ ለዚህ በረከት አብነት ይሆናል። ማቻካ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ በሆነ ጊዜ ወላጆቹ በነገሩ በጣም ተበሳጩ። “የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ቤቱን ለቀህ መውጣት አለብህ” አሉት። ሆኖም ይህ ዛቻ ጥናቱን እንዳይቀጥል ተስፋ አላስቆረጠውም። በዚህ ምክንያት የማቻካ ወላጆች ልብሶቹን ሁሉ ወሰዱበት። ወንድሞች ሌላ ልብስ ገዙለት። የማቻካ ወላጆች ይህን ባዩ ጊዜ “ምሥክሮቹ የሚረዱህ ከሆነ ከእነርሱ ጋር ሁን” ብለው ከቤት አስወጡት። ማቻካ ጉዳዩን በጥሞና ካሰበበት በኋላ ቤቱን ለቆ ወጣና በዚያ ጉባኤ ውስጥ ከሚገኝ አንድ የምሥክሮች ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመረ።
የማቻካ ወላጆች በነገሩ በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ ከምሥክሮቹ ጋር ጭራሽ ላለመገናኘት ሲሉ አካባቢውን ለቀው ሄዱ። እርግጥ ነው፣ ይህ ጉዳይ ማቻካን አስጨንቆት ነበር። ሆኖም “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ስለሚለው የመዝሙር 27:10 ጥቅስ ወንድሞች ባወያዩት ጊዜ ከፍተኛ መጽናኛ አግኝቷል።
ከጊዜ በኋላ የወላጆቹ ተቃውሞ ስለረገበ ማቻካ ወደ ቤት ለመመለስ ወሰነ። ልጃቸው ይሖዋን ለማገልገል ባደረገው ቁርጥ ውሳኔ በእጅጉ በመነካታቸው እነርሱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ሆኑ! በተጨማሪም “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ ሦስቱንም ቀን ከተካፈሉ በኋላ “በእውነትም ይህ የአምላክ ድርጅት ነው” ብለው ለመናገር ተገድደዋል።
አዎን፣ ተቃውሞ ፈታኝ ሊሆን ቢችልም የአምላክ ታማኝ መልእክተኞች ተስፋ አይቆርጡም። ‘ከመከራ ጽናት እንደሚገኝ፣ መጽናት ደግሞ ተቀባይነት ያለው አቋም’ እንደሚያስገኝ ስለሚያውቁ በቆራጥነት ወደፊት ይገፋሉ። (ሮሜ 5:3, 4 NW) በማላዊ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ ጽናት የአምላክን በረከት እንደሚያስገኝ በተግባር ያሳየ ነው።