ሕይወትን ትወዳለህ?
“አንድ ጊዜ ብርሃን ልይ።” ኢጣሊያዊው ባለ ቅኔ ጂያኮሞ ሊዮፓርዲ ሞት አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት ያስታምሙት ለነበሩት ሰዎች እነዚህን ቃላት እንደተናገረ ተዘግቧል። አባባሉ የሰው ልጅ በብርሃን ለተመሰለው ሕይወት ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ያመለክታል።
ሕይወትን ማፍቀር ብዙ ግለሰቦች ራሳቸውን ከአደጋ እንዲያርቁና በሕይወት መኖራቸውን ለመቀጠል የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ውድ ባሕርይ ነው። እንስሳትም ተመሳሳይ የሆነ ጠንካራ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ያላቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ ሰው ከእንስሳት ብዙም የሚለይ አይደለም።
ይሁን እንጂ ጥሩና አስደሳች ሊባል የሚችለው ምን ዓይነት ሕይወት ነው? እንዲያው መተንፈስና መንቀሳቀስ ብቻ ጥሩና አስደሳች ሕይወት ሊባል እንደማይችል ግልጽ ነው። ወይም በሕይወት እስካለህ ድረስ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ተደሰት የሚለውን ፈሊጥ በመከተል እርካታ የሞላበት ሕይወት መምራት አይቻልም። “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚለው የኤፊቆሮሳውያን ፍልስፍና ለሰዎች እርካታ የሞላበት ሕይወት አላስገኘም። (1 ቆሮንቶስ 15:32) የሰው ልጅ ካሉት በርካታ መሠረታዊ የሆኑ ቁሳዊ ፍላጎቶች በተጨማሪ ባሕላዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች እንዲሁም የሁሉ የበላይ የሆነ አካል አለ ከሚል እምነት ጋር የተሳሰሩ መንፈሳዊ ፍላጎቶች አሉት። የሚያሳዝነው ግን በአብዛኛው የዓለም ክፍል ያለው ማኅበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባ በመሆኑ በመቶ ሚልዮን ምናልባትም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው። መብላትን፣ መጠጣትን፣ ሃብት ማካበትን ወይም የጾታ ስሜት ማርካትን በመሳሰሉ ሰብዓዊ ፍላጎቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ ሰዎች ሕይወታቸው ብዙም እርካታ የማያገኙበት ከእንስሳ ያልተለየ ሕይወት ይሆንባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር የሰው ልጅ የእውቀት አድማሱን ለማስፋትና ስሜቱን ለማርካት ሕይወት ከሚያቀርብለት ስጦታ ተቋዳሽ እንዳይሆን ያደርገዋል። ከዚህም በላይ የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ብቻ ለማርካት የሚሯሯጡ ሁሉ ሕይወትን በተሻለ መንገድ ለማጣጣም ካለመቻላቸውም በላይ የሚኖሩበትን ኅብረተሰብ ይጎዳሉ እንዲሁም የሌሎችን ሰዎች ጥቅም ሳያስጠብቁ ይቀራሉ።
ከዚህ ጋር በመስማማት የወጣት ጥፋተኞችን ጉዳይ የሚመለከቱ አንድ ዳኛ “በሥነ ምግባር ላይ የደረሰው ቀውስ፣ በመጥፎ ምሳሌነታቸው የሚታወቁ ሰዎች በአደባባይ ሲወደሱ መስማት እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት ላይ መድረስ . . . ከፍተኛ የፉክክር መንፈስ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ” በማለት ተናግረዋል። ይህም ኅብረተሰቡን የሚጎዳና ወጣቶች መጥፎ አኗኗር እንዲከተሉ የሚያበረታታ ባሕርይ እንዲስፋፋ ያደርጋል። በተለይ ደግሞ ወጣቶች ወደ አደንዛዥ ዕፅ ዞር በሚሉበት ጊዜ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል።
እንደምታውቀው ሕይወት ማራኪ መስህብ ባላቸው አካባቢዎች የእረፍት ጊዜ ማሳለፍን፣ ስሜት የሚመስጥ ጽሑፍ ማንበብን ወይም ምርምር ማድረግን፣ ከቅርብ ወዳጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍን፣ ለጆሮ የሚጥም ሙዚቃ ማዳመጥን የመሰሉ የተለያዩ አስደሳች ነገሮች አሉት። እርካታ የሚሰጡ ሌሎች በርካታ እንቅስቃሴዎችም አሉ። በአምላክ ላይ በተለይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በተገለጸው አምላክ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ሕይወትን እንዲወዱ የሚያደርጓቸው ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሏቸው። እውነተኛ እምነት የጥንካሬና የመንፈስ እርጋታ ምንጭ በመሆኑ ሰዎች አስቸጋሪ ወቅቶችን ተቋቁመው እንዲያሸንፉ ሊረዳቸው ይችላል። በእውነተኛው አምላክ ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች “ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” በማለት በልበ ሙሉነት ሊናገሩ ይችላሉ። (ዕብራውያን 13:6) የአምላክን ፍቅር የሚያውቁ ሰዎች እርሱ እንደሚወዳቸው ይሰማቸዋል። ፍቅሩ ጥልቅ ደስታ ስለሚያስገኝላቸው አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። (1 ዮሐንስ 4:7, 8, 16) እርካታ የሚያስገኝ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ጥሩ ሕይወት ሊመሩ ይችላሉ። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ብሎ እንደተናገረው ነው።—ሥራ 20:35
የሚያሳዝነው ግን በአሁኑ ጊዜ ያለው ሕይወት ሌላ ገጽታም አለው። ብዙውን ጊዜ ሕይወትን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት በጣም ተስፋፍተው የሚገኙ ነገሮች መካከል ሥቃይ፣ ግፍ፣ ድህነት፣ በሽታና ሞት ጥቂቶቹ ናቸው። ከፍተኛ ሀብት፣ ሥልጣንና ጥበብ የነበረው የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ንጉሥ ሰሎሞን ለሰዎች ደስታ ያስገኛሉ የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ነበሩት። ሆኖም ‘በጥበቡ፣ በእውቀቱና በብልሃቱ’ ተጠቅሞ ያከማቸውን ሀብት ሲሞት ለሌላ ሰው ጥሎት እንደሚሄድ ስለሚያውቅ ይረበሽ ነበር።—መክብብ 2:17-21
ልክ እንደ ሰሎሞን ሌሎች ብዙ ሰዎችም ሕይወት አሁን ታይቶ በኋላ እንደሚጠፋ ጤዛ እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ። አምላክ ‘በአእምሯችን ውስጥ ዘላለማዊነትን እንዳስቀመጠ’ ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። (መክብብ 3:11 ባይንግተን) እንዲህ ያለው ለዘላለም የመኖር ስሜት የሰው ልጅ ሕይወት አጭር ስለሆነበት ምክንያት እንዲያስብ ያደርገዋል። ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ትርጉም አሳማኝ የሆነ መልስ ሳያገኝ በመጨረሻ አፍራሽና ከንቱ በሆኑ ስሜቶች ይዋጣል። ይህም ሕይወትን በሐዘን የተሞላ ሊያደርግ ይችላል።
የሰውን ልጅ ለሚያስጨንቁት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይቻል ይሆን? ወደፊት ሕይወትን ይበልጥ ማራኪና ዘላቂ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይመጡ ይሆን?