የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በናሚቢያ የተገኘ ቲኦክራሲያዊ እድገት
የአምላክ መንግሥት ምሥራች መጀመሪያ ወደ ናሚቢያ የደረሰው በ1920ዎቹ መገባደጃ ላይ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለአምላክ የደኅንነት መልእክት ምላሽ ሰጥተዋል። ቀጥሎ የቀረቡት ተሞክሮዎች ይሖዋ እነዚህን የተመረጡ ዕቃዎች እንዴት አድርጎ ወደ በረቱ እየሰበሰበ እንዳለ ያሳያሉ።—ሐጌ 2:7
ጳውሎስ በስተ ሰሜን ምሥራቅ ናሚቢያ የሚኖር ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ኑሮ የሚተዳደር ገበሬ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘው ወደ ዋና ከተማው ወደ ዊንድሆክ በሄደበት ወቅት ነበር። ወዲያውኑ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ሆነ። ወደ ቤቱ የተመለሰው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ይዞ ነበር። ከዚያም ጳውሎስ የመንግሥት አዳራሽ ወደሚገኝበት በቅርብ ወዳለው ከተማ ወደ ሩንዱ ባደረገው ጉዞ ከምሥክሮቹ ጋር ተገናኘና መጥተው እንዲጠይቁት ለመናቸው።
ሆኖም ምሥክሮቹ ጳውሎስ ወዳለበት ሄደው ከእርሱ ጋር ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ቦታው በጣም ራቀባቸው። ጳውሎስ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በተጨማሪም ስለ ተማራቸው ነገሮች ለሌሎች በቅንዓት ይሰብክ ነበር። ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ተመሠረተ። በዚህች ትንሽ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች በሩንዱ አንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ እንደሚደረግ ሲሰሙ ስብሰባው ላይ ለመገኘት የሚያገኟትን ጥቂት ገንዘብ አጠረቃቅመው የመጓጓዣ ዝግጅት አደረጉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰባቸው ምንኛ አስደሳች ተሞክሮ ሆኖላቸው ነበር! ወዲያውኑም ብቃት ያላቸው ወንድሞች ይህን ቡድን በቋሚነት እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደረገ። ዛሬ ጳውሎስ በሚኖርበት መንደር ውስጥ ስድስት አስፋፊዎች አሉ።
ዮሐና ስለ አምላክ ስም ለማወቅ ጉጉት ያደረባት አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክሮችን ስም በመጥፎ ሲያነሳ በሰማችበት ጊዜ ነበር። እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “ለመጀመሪያ ጊዜ ይሖዋ የሚለውን ስም ስሰማ ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ አእምሮዬ ውስጥ ተቀረጸ፤ እንዲሁም ይሖዋ ማን ይሆን እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። የምኖረው በናሚቢያ የባሕር ዳርቻ ዋልቪስ ቤይ አቅራቢያ ከባለቤቴ ጋር ነበር። በአንድ ወቅት ወደ ከተማ ሄደን ሳለ ጥቂት ምሥክሮች መንገድ ላይ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሲያበረክቱ አየሁ። አንድ ቅጂ ወሰድኩና ብዙ ጥያቄዎች ስለነበሩኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉልኝ ጠየቅኋቸው። መኪናቸው በመበላሸቱ ምክንያት እኔ ወዳለሁበት መምጣት እንደማይችሉ ሲነግሩኝ በጣም አዘንኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴ ስለሞተ የመኖሪያ ቦታ ቀይሬ ወደ ኬትማንሹፕ ሄድኩ። በዚያ እንዲያገለግል የተመደበ አንድ ልዩ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ) ስለነበር ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። ገና ከጅምሩ ነገሩ እውነት መሆኑን ተገነዘብኩ።
“በመጨረሻ በስብከቱ ሥራ እንድካፈል ግብዣ የቀረበልኝ ቢሆንም እንኳ ሰውን የመፍራት ስሜት አሸነፈኝ። ከቤት ወደ ቤት በምሄድበት ጊዜ ይሖዋ እንድሰብክ ከሚያደርገኝ ይልቅ ቢገድለኝ ይሻላል እያልኩ ጸልያለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንገድ ወደ መንገድ በሚደረገው ምሥክርነት ስካፈል ያገለገልኩት ማንም ሰው እንደማያየኝ ተስፋ በማድረግ ግራና ቀኝ አትክልት ባለበት ጠባብ መንገድ ላይ ነበር። በመጨረሻም መንገድ ላይ ለሚያልፍ ሰው መጽሔት ለማሳየት በቂ ድፍረት ያገኘሁ ሲሆን ጥቂት ነገር መናገር የቻልኩትም ከዚህ በኋላ ነበር። የዚያን ዕለት በይሖዋ እርዳታ ለብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋዬን ማካፈል ችዬ ነበር።
“ምንም እንኳ ከ12 ዓመት በኋላ ዛሬ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሃ ብሆንም አሁንም የአቅኚነት አገልግሎትን መብት ከፍ አድርጌ የምመለከተው ሲሆን ለሌሎች የመንግሥቱን እውነት በማካፈል ይህ ነው የማይባል ደስታ እያገኘሁ ነው።”