“የወዳጅ ማቁሰል”
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች እርማት መስጠቱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶት ነበር። ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳይፈጠር በማሰብ ሳይሆን አይቀርም “እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?” ሲል ጠይቋቸዋል።—ገላትያ 4:16
ጳውሎስ ‘እውነቱን ስለ ነገራቸው’ ጠላት አልሆነባቸውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ያደረገው ነገር “የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 27:6) ጳውሎስ አንድ ጥፋተኛ እርማት ሲሰጠው ለራሱ ያለው ግምት ሊነካ እንደሚችል ያውቃል። ሆኖም ኃጢአት ለሠራ ሰው ተግሳጽ ከመስጠት መቆጠብ ሰውዬው የይሖዋ አምላክን የፍቅር መግለጫ እንዳያገኝ ከማድረግ ተለይቶ እንደማይታይ ያውቅ ነበር። (ዕብራውያን 12:5-7) በመሆኑም ጳውሎስ ለጉባኤው ዘላቂ ጥቅም ከልብ የሚያስብ ታማኝ ወዳጅ ስለነበረ እርማት ከመስጠት ወደኋላ አላለም።
በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች “አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈጸም ላይ ናቸው። እነዚህ ቅን ክርስቲያኖች ይህን ተልዕኮ ሲፈጽሙ የመሠረተ ትምህርት ግድፈቶችንና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶችን የሚያጋልጡና የሚያወግዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ወደ ጎን ገሸሽ አያደርጉም። (ማቴዎስ 15:9፤ 23:9፤ 28:19, 20፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ወዳጆችን ለይቶ የሚያሳውቀውን ልባዊ አሳቢነት ስለሚያሳዩ እንደ ጠላት ታይተው ሊርቋቸው የሚገቡ ሰዎች አይደሉም።
መዝሙራዊው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ባገኘው ማስተዋል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፣ ይዝለፈኝም፣ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ።”—መዝሙር 141:5