አምላክ ሙታንን የሚመለከታቸው እንዴት ነው?
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ልብን በሐዘን ያደማል። በዚህ ወቅት የሚሰማውን የባዶነት ስሜት፣ ብቸኝነትና ከንቱነት በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ማናችንም ብንሆን የቱንም ያህል ሀብት፣ ሥልጣን ወይም ተሰሚነት ቢኖረን በሞት የተለዩንን ሰዎች እንደገና ማስነሳት ስለማንችል የከንቱነት ስሜት ይሰማናል።
ለአምላክ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። የመጀመሪያውን ሰው የፈጠረው ከምድር አፈር እስከሆነ ድረስ የሞተን ሰው በድጋሚ መፍጠር አያቅተውም። በዚህም ምክንያት አምላክ ሙታንን የሚመለከታቸው በሕይወት እንዳሉ አድርጎ ነው። ኢየሱስ በጥንት ጊዜ የሞቱ ታማኝ አገልጋዮችን በሚመለከት ‘ለእርሱ ሕያዋን ናቸው’ በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 20:38
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን ነበረው። (ዮሐንስ 5:21) በመሆኑም በታማኝነት የሞቱ የይሖዋ አገልጋዮችን በሚመለከት ከአባቱ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ነበረው። ለምሳሌ ያህል ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ “ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 11:11) አልዓዛር በሰዎች ዓይን የሞተ ቢሆንም ለይሖዋና ለኢየሱስ ግን እንቅልፍ የተኛ ያህል ነበር።
በኢየሱስ መንግሥት አገዛዝ ሥር ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሣሉ።’ (ሥራ 24:15) ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች መለኮታዊ ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋም ይኖራቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29
አዎን፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ለዓመታት የሚዘልቅ ከባድ ሐዘን ላይ ይጥላል። ሆኖም የሞቱ ሰዎችን በአምላክ ዓይን የምንመለከት ከሆነ ልንጽናና ብሎም ሐዘናችንን ልንረሳ እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4