ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች መሆን የነበረበት
ከላይ የሚታየው ጽሑፍ በ2004/2005 በተደረገው “ከአምላክ ጋር መሄድ” በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጣ ቡክሌት ነው። ዘጠና ስድስት ገጾች ያሉት የዚህ ቡክሌት አንደኛው እትም ከአቾሊ እስከ ዙሉ ባሉ 92 ቋንቋዎች የተጻፈ የአንድ ገጽ አጭር መልእክት ይዟል። ቡክሌቱ የመንግሥቱን ወንጌል በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የሚከተሉት ተሞክሮዎች ቡክሌቱን መጠቀም የሚያስገኘውን ውጤት የሚያሳዩ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው።
• በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባው ላይ ቡክሌቱን ከወሰዱ በኋላ ወደ ሦስት ብሔራዊ ፓርኮች ሄደው ነበር። በዚያም ከሕንድ፣ ከኔዘርላንድ፣ ከፓኪስታንና ከፊሊፒንስ የመጡ ሰዎችን አገኙ። ባልየው ስለ ሁኔታው እንዲህ ብሏል:- “ከትውልድ አገራቸው በጣም ርቀው የመጡት እነዚህ ሰዎች በተወሰነ መጠን እንግሊዝኛ መናገር ቢችሉም እንኳ መልእክቱን በራሳቸው ቋንቋ ስናሳያቸው ተደንቀው ነበር። የሥራችን ዓለም አቀፋዊነትና አንድነታችን ግልጽ ሆነላቸው።”
• አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከሕንድ ለመጣ የሥራ ባልደረባዋ ቡክሌቱን አሳየችው። በቡክሌቱ ውስጥ ያሉትን ቋንቋዎች ሁሉ ሲመለከትና በራሱ ቋንቋ የተጻፈውን መልእክት ሲያነብ በጣም ተደሰተ። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ ከፍቶላቸዋል። ከፊሊፒንስ የመጣች ሌላ የሥራ ባልደረባዋ ደግሞ የአገሯ ቋንቋ ቡክሌቱ ውስጥ መኖሩ ስላስደነቃት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ የማወቅ ጉጉት አድሮባታል።
• በካናዳ ከኔፓል የመጣች ሴት ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር በስልክ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ብትስማማም እህትን ወደ ቤቷ ለመጋበዝ አቅማምታ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሯ በኔፓሊ ቋንቋ የተጻፈ መልእክት የያዘ አንድ ቡክሌት እንዳለ ስትነግራት በመደነቅ እህት ወደ ቤቷ እንድትመጣ ጋበዘቻት። በአፍ መፍቻ ቋንቋዋ የተጻፈውን መልእክት በገዛ ዓይኗ ተመለከተች! ከዚያን ዕለት ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ በሴትየዋ ቤት መካሄድ ጀመረ።