“የአምላክን ቃል መቀበል፣ በሥራ ላይ ማዋልና ከእርሱ መጠቀም
1 ምንም እንኳን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም ብዙዎች እንደ አምላክ ቃል አድርገው አይቀበሉትም፤ አብዛኞቹም ጥበብ ያለበትን ምክሩን በሥራ ላይ አያውሉትም፤ በዚህም ምክንያት ከእርሱ ጥቅም የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው። የይሖዋ ሕዝቦች ግን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነና ለሁሉም ነገር ጠቃሚ መሆኑን በእውነት ያምናሉ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ስለዚህ በ1993 የአገልግሎት ዓመት የሚደረገው የክልል ስብሰባ አጠቃላይ መልዕክት “የአምላክን ቃል መቀበል፣ በሥራ ላይ ማዋልና መጠቀም” የሚል ነው።
2 የሚያበረታታቱ፣ ለአምላክ ቃል ያለን አድናቆት ጥልቅ እንዲሆን የሚያደርጉና በሁሉም የኑሮአችን ዘርፎች ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንድናደርገው የሚረዱን ንግግሮች፣ ትዕይንቶች፣ አጫጭር ድራማዎች፣ ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች ነበሩ። የቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ከመዝናኛ፣ ከጓደኝነትና ቁሳዊ ነገሮችን ከመውደድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በቤተሰብ ክልል ውስጥ ምክርና ተግሣጽ መስጠትን የሚመለከት ነበር። እንዴት ከዓለም የተለየን ለመሆን እንደምንችልና መጥፎ ምግባሮቹን እንዲሁም አክብሮት የጎደላቸውን ወይም ጸያፍ አነጋገሮቹን ላለመቅሰም እንዴት መጠንቀቅ እንደምንችል አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ነጠላ ወላጆችን ወይም አባት የሌላቸውን ልጆች የሚጠቅም ማበረታቻ ተሰጥቷል።
3 በተጨማሪም ራሳቸውን የወሰኑ አዲሶች ቅዳሜ ዕለት በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ከሰሙ በኋላ የመጠመቅ አጋጣሚ አግኝተዋል።
4 የእሁድ ጠዋቱ ፕሮግራም የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን በማረጋገጥ በኩል ራሳችንን ከዓለም ልንለይ የምንችልባቸውን መንገዶች መርምሯል። አለባበሳችንና አበጣጠራችን ያላቸው አስፈላጊነትና አእምሮአችንን የሚያበላሹ ነገሮችን እንዴት መከላከል እንደምንችል የሚገልጹት ሐሳቦች ከተመረመሩት ርዕሶች መሀል ነበሩ። ከሰዓት በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ እንደሆነ የሚያሳውቀው ነገር ምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለው የሕዝብ ንግግር አቅርቧል።