ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ አበርክቱ
1 በዛሬው ጊዜ ወጣቶችን ግራ ስላጋቧቸው ችግሮች የተጨነቁ ወላጆችንና ወጣቶችን ካነጋገራችሁ ወጣትነትህ የተባለው መጽሐፍ እንደደረሳችሁ ልታበረክቱላቸው ትፈልጉ ይሆናል።
2 እንደሚከተለው ማለቱን ተስማሚ ሆኖ ልታገኙት ትችሉ ይሆናል፦
◼ “በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ውስጥ ማደግ ቀላል አይደለም። ወጣቶች ከባድ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚጠይቁባቸው አዳዲስ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ‘መጠጥ መጠጣት ይኖርብኛልን? ዕፅ ብወስድስ? ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለኝ ግንኙነት ማሳየት የሚገባኝ ተገቢ ጠባይ ምንድን ነው?’ ብዙውን ጊዜ ወጣቶች እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሲያነሱ እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መልሶች ይዥጎደጎዱባቸዋል። ታዲያ ብዙዎቹ ምክር ለማግኘት ወዴት ዘወር የሚሉ ይመስልሃል? [አስተያየቱን እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለው ይህ መጽሐፍ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ይሰጣል። [ወደ ርዕስ ማውጫው ውሰደውና ያሉትን የተለያዩ ርዕሶች አሳየው።] ወጣቶች ቀጥተኛና ከእውነታው ያልራቀ መልስ ይፈልጋሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መልሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመረኮዙ ናቸው።”
3 ልትጠቀሙበት የምትችሉት ሌላ ዓይነት አቀራረብ፦
◼ “ዛሬ ወጣቶች ብዙ ግፊቶች ይደርሱባቸዋል። እነዚህን ግፊቶች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንዲችሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እነርሱን ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ተግባራዊ የሆነ መመሪያ ሊሰጥ የሚችል ነገር ለማግኘት አንፈልግም? [አስተያየቱን እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በጣም ከፍተኛ ግፊት የሚደርስባቸው እኩዮቻቸው ከሆኑ ወጣቶች ነው። እስቲ ምዕራፍ ስምንትን ተመልከተው። [በገጽ 64 ላይ በሚገኙት አንቀጾች ላይ እንዲያተኩር አድርግ።] በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሉት የሚቀጥሉት ገጾች ሊሠሩ የሚችሉ ግልጽ መልሶችን ይዘዋል።”
4 ያለንበት ጊዜ በተለይ ለወጣቶች “የሚያስጨነቅ ዘመን” ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ወጣትነትህ የተባለው መጽሐፍ አንድ ወጣት ዛሬ የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ በእርግጥ ይረዳዋል። የመጽሐፉ 24 ምዕራፎች ከእውነታው ያልወጡና ተግባራዊ ሐሳቦችን የያዙ ናቸው። እንግዲያው አጋጣሚውን ባገኛችሁ ጊዜ ሁሉ በዚህ ግሩም መጽሐፍ ለመጠቀም ንቁ ሁኑ።