ሰሚ ጆሮ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
1 በፊልጵስዩስ ከተማ የምትኖር “ቀይ ሐር ሻጭ . . . ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።” (ሥራ 16:14) ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል? አንድ ሰው እውነትን ማወቅ የሚችለው የሚሰማ ከሆነ ነው። ሰሚ ጆሮ ካገኘን መልእክታችንን ለማቅረብ አንቸገርም። ሰሚ ጆሮ ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
2 ወደ መስክ አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት ስለ ቁመናችንና ስለምንገለገልባቸው ነገሮች ማሰብ አለብን። ለምን? ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያስከብር አቋም ይዘው የሚቀርቧቸውን ሰዎች ለመስማት ፈቃደኞች ይሆናሉ። አለባበሳችን ልከኛና የሚማርክ ነውን? ምንም እንኳ በዓለም ውስጥ ዝርክርክ አለባበስ ተወዳጅ ቢሆንም የአምላክን መንግሥት የምንወክል አገልጋዮች ስለሆንን እንዲህ ያለውን ግዴለሽነት ማስወገድ አለብን። ንጹሕና ሥርዓታማ የሆነው አለባበሳችን ለመንግሥቱ መልእክት ተጨማሪ ምሥክርነት ይሰጣል።
3 ወዳጃዊ አክብሮት የተሞላበት አቀራረብ ይኑርህ፦ ሞቅ ያለ ልባዊ ፈገግታ የቤቱን ባለቤት እንዲረጋጋ ከማድረጉም በላይ አስደሳች ውይይት ለማድረግ በር ይከፍታል። ቅንነታችንና መልካም ጠባዮቻችን በንግግራችንና በምግባራችንም ሊንጸባረቁ ይገባል። ይህም የቤቱ ባለቤት የሚሰጠውን ሐሳብ በአክብሮት ማዳመጥን ያካትታል።
4 ዓላማችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ለሰዎች ማካፈል ነው። ስለዚህ ውይይታችን ሌሎችን ፈተና ውስጥ የሚከት ሳይሆን የሚማርክ መሆን አለበት። ከተቃዋሚ ሰው ጋር በመከራከር ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም። (2 ጢሞ. 2:23-25) ከመንግሥት አገልግሎታችን እና ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ መግቢያዎች መምረጥ እንችላለን።
5 ከውይይቱ በኋላ የነገርናቸውን ነገር በደንብ የሚያስታውሱ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ሆኖም ሁሉም ሰዎች ለማለት ይቻላል በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳነጋገርናቸው ያስታውሳሉ። ጥሩነትና ደግነት የሚያሳድሩትን በጎ ተጽዕኖ አቅልለን መመልከት የለብንም። ሞቅ ባለና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለመናገር እንድንችል ጥሩ አድርገን ከተዘጋጀን በክልላችን ውስጥ ጆሯቸውን ለእውነት የሚሰጡ ብዙ በግ መሰል ሰዎች አሉ።— ማር. 4:20፤ 1 ጴጥ. 3:15