የአምላክን ቃል በትክክል የምትጠቀም ነህን?
1 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ ነው። የሰዎችን ልብ በሚነካ፣ ስሜታቸውን በሚያነሳሳና ጥሩ ሥራዎች የመሥራት ልማድ እንዲያዳብሩ በሚገፋፋ መንገድ አስተምሯል። (ማቴ. 7:28, 29) የአምላክን ቃል የትምህርቱ መሠረት አድርጎ ዘወትር ይጠቀም ነበር። (ሉቃስ 24:44, 45) ስላወቃቸው ነገሮችና ላለው የማስተማር ችሎታ ክብር የሚሰጠው ለይሖዋ አምላክ ነበር። (ዮሐ. 7:16) ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትክክል በመጠቀም በኩል ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል።— 2 ጢሞ. 2:15
2 ሐዋርያው ጳውሎስም የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ጉልህ ሆኖ የሚታይ ምሳሌ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ለሌሎች ከማንበብ የበለጠ ነገር ያደርግ ነበር። ኢየሱስ በአምላክ የተቀባ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ ከአምላክ ቃል ማስረጃ በማቅረብ ባነበባቸው ነገሮች ላይ የሚያመራምሩ ሐሳቦችን በማከል ያስረዳ ነበር። (ሥራ 17:2-4) በተመሳሳይም አንደበተ ርቱዕ የነበረው ደቀ መዝሙሩ አጵሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረ” ነበረ። የእውነትን መልዕክት በሚያቀርብበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፉን በትክክል ይጠቀም ነበር።— ሥራ 18:24, 28 የ1980 ትርጉም
3 የአምላክ ቃል አስተማሪ ሁን፦ በዚህ ዘመን የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስና በማብራራት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን በማስተማር ግሩም የሆነ ውጤት አግኝተዋል። በአንድ ወቅት አንድ ወንድም የዓመፀኞችና የጻድቃን የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነ ለአንድ ቄስና ለሦስት ጓደኞቹ ለማስረዳት ሕዝቅኤል 18:4ንና ሌሎች ድጋፍ የሚሆኑ ተጨማሪ ጥቅሶችን መጠቀም ችሎ ነበር። በውጤቱም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት ማጥናት ሲጀምሩ አንደኛው ደግሞ ውሎ አድሮ እውነትን ተቀብሏል። (የዓመት መጽሐፍ 94 ገጽ 134) በሌላም ጊዜ አንዲት ፍላጎት ያላት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ገናንና የልደት ቀንን ለምን እንደማያከብሩ ለባሏ እንድታብራራለት አንዲትን እህት ጠየቀቻት። ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ማመራመር ከተሰኘው መጽሐፍ በቀጥታ ባነበበች ጊዜ ሰውየው አመነ። ሚስቱ መልሶቹ ስላሳመኑት በጣም ተደስታ “ወደ ስብሰባዎቻችሁ እንመጣለን” ብላ ተናገረች። ባልየውም ተስማማ!— የዓመት መጽሐፍ 87 ገጽ 28-29
4 ያሉትን የመርጃ መሣሪያዎች ተጠቀሙባቸው፦ የመንግሥት አገልግሎታችን እና የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም የአምላክን ቃል በትክክል እንድንጠቀም የሚረዱንን ጥሩ ጥሩ መመሪያዎች ያቀርቡልናል። ብዙ አስፋፊዎች ለእኛ ጥቅም ተብሎ ወቅታዊና ውጤታማ ሆነው ተዘጋጅተው ለሚታተሙት የተለያዩ የአቀራረብ ዘዴዎችና ሠርቶ ማሳያዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተሰኘው መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዙ ከ70 የሚበልጡ ዋና ዋና ርዕሶችን እንዴት በትክክል ማብራራት እንደሚቻል ብዙ ሐሳቦች ይዟል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተሰኘው መጽሐፍ አዳዲስ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባቸውን ጠቅላላ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶችን እጥር ምጥን አድርጎ ያቀርባል። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ በጥናት 24 እና 25 ላይ ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዴት አድርገው እንደሚያስተዋውቁ፣ እንደሚያነቡና በሥራ ላይ የሚውልበትን መንገድ እንዴት እንደሚገልጹ ያሳየናል። ለእኛ ተብለው የተዘጋጁትን እንደነዚህ ያሉትን እርዳታዎች ጥሩ አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገባል።
5 የአምላክን ቃል በትክክል በምንጠቀምበት ጊዜ የአምላክ ቃል ‘ሕያው እንደሆነ፣ የሚሠራና’ የሰበክንላቸውን ሰዎች ‘ልብ፣ ስሜትና አሳብ የሚመረምር’ ሆኖ እናገኘዋለን። (ዕብ. 4:12) የአምላክን ቃል በመጠቀም የምናገኘው ስኬት እውነትን ከቀድሞው በበለጠ ድፍረት እንድንናገር ያንቀሳቅሰናል!— ሥራ 4:31