‘የምታመሰግኑ ሁኑ’
1 አብዛኞቻችን አንድ ሰው መልካም ነገር ሲያደርግልን ወይም ደግነት ሲያሳየን “እባክህ” እና “አመሰግናለሁ” እንድንል ገና በልጅነታችን ስልጠና አግኝተናል። ጳውሎስ ዘወትር ‘አመስጋኞች’ እንድንሆንና በተለይ ደግሞ ይሖዋ ባለውለታችን መሆኑን መዘንጋት እንደሌለብን አጥብቆ መክሮናል። (ቆላ. 3:15, 16) ይሁን እንጂ ለታላቁ ፈጣሪያችን አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እርሱንስ ለማመስገን የሚያበቁን ምን የተለዩ ምክንያቶች አሉን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 15:57) በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ አምላክና ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንድናገኝ ቤዛ በማቅረብ ያሳዩንን ወሰን የለሽ ፍቅር እናስባለን። (ዮሐ. 3:16) ሁላችንም ማለት ይቻላል የምናፈቅራቸውን ሰዎች በሞት ያጣን በመሆናችን ኢየሱስ ትንሣኤን አስመልክቶ ለሰጠው ተስፋ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ጭራሽ ሳይሞቱ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የማለፍን የወደፊት ተስፋ ስናስብ ልባችን በምስጋና ስሜት ይሞላል። (ዮሐ. 11:25, 26) በሚመጣው ምድራዊ ገነት ውስጥ ከይሖዋ እጅ ለምናገኛቸው የተትረፈረፉ አስደናቂ በረከቶች ሁሉ ምስጋናችንን የምንገልጽበት ቃላት ያጥረናል። (ራእይ 21:4) አንድ ሰው ለአምላክ ‘ምስጋናውን’ እንዲያቀርብ የሚገፋፋው ከዚህ የተሻለ ምን ምክንያት ሊኖረው ይችላል?
3 ለአምላክ ምስጋና ማቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሚያሳየን ደግነት ዘወትር ምስጋናችንን በጸሎት ማቅረብ ተገቢ ነው። (መዝ. 136:1-3) በሌሎች መንገዶችም ለእርሱ ያለንን ምስጋና ለመግለጽ እንገፋፋለን። ለምሳሌ ያህል እሑድ መጋቢት 23 በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንደምንገኝ የታወቀ ነው። ላለንበት ጉባኤና ለዓለም አቀፉ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ እርዳታዎችን በማሟላት ረገድ አስተዋጽኦ በማድረግ ይሖዋን በሃብታችን በደስታ እናከብረዋለን። (ምሳሌ 3:9) ይሖዋ በሽማግሌዎች በኩል ለሚያቀርብልን እርዳታ ምስጋናችንን ለመግለጽ ሽማግሌዎችን ሙሉ በሙሉ እንረዳቸዋለን እንዲሁም እንተባበራቸዋለን። (1 ተሰ. 5:12, 13) በየዕለቱ የአምላክን ስም የሚያስከብር ትክክለኛ ጠባይ ለማሳየት እንጣጣራለን። (1 ጴጥ. 2:12) አመስጋኝ መሆናችንን የሚያሳዩት እነዚህ ሁሉ ማረጋገጫዎች ይሖዋን ያስደስቱታል።— 1 ተሰ. 5:18
4 ከሁሉም የሚበልጠው የምስጋና መግለጫችን:- በመንግሥቱ የስብከት ሥራ በሙሉ ነፍስ መካፈል፣ የይሖዋን ስም ማክበር፣ በጸሎት ምስጋና ማቅረብና በታማኝነት ለእውነት ጠበቃ ሆኖ መቆም ፈጣሪያችን ለእኛ ላደረጋቸው ነገሮች ከሁሉ የበለጠ ልባዊ ምስጋናችንን ከምንገልጽበት መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ይሖዋ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ” ካለው ፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ ሲመለከት ይደሰታል። (1 ጢሞ. 2:3, 4 NW ) በየካቲት የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በቀረበው ጥሪ መሠረት ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ብዙ አስፋፊዎች ከመጋቢት፣ ከሚያዝያ ወይም ከግንቦት ወራት በአንዱ ወይም ከዚያ በላይ ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ነው። በአገልግሎቱ የበለጠ ለመሳተፍ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ለአምላክ ያለንን አመስጋኝነት የምናሳይበት ጥሩ መንገድ ነው። በሚያዝያ ወይም በግንቦት ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህ?
5 ለዘላለም የመኖር እርግጠኛ ተስፋ ተሰጥቶናል። ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ በየዕለቱ ለይሖዋ የደስታ ምስጋና እያቀረብን እንድንቀጥል የሚያደርጉን ተጨማሪ ምክንያቶች ይኖሩናል።— መዝ. 79:13