የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 6/97 ገጽ 4
  • የጥያቄ ሣጥን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጥያቄ ሣጥን
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1997
የመንግሥት አገልግሎታችን—1997
km 6/97 ገጽ 4

የጥያቄ ሣጥን

◼ ዛሬ ክርስቲያኖች ስለግዝረትና በባህላዊ እምነት መሠረት ሊደረጉ አይገባም ተብለው ስለሚታሰቡ ነገሮች ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

ወንዶችን መግረዝ በሙሴ ሕግ ሥር ለነበሩት የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች እንደ “ምልክት” ሆኖ ያገልግል እንጂ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው ከሚገቡት ‘አስፈላጊ ነገሮች’ መካከል አይደለም። (ዘፍ. 17:11፤ ሥራ 15:1, 2, 28, 29፤ ገላ. 5:6) ስለዚህ ዛሬ በአምላክ አመለካከት የተገረዘም ሆነ ያልተገረዘ እኩል ናቸው። (1 ቆሮ. 7:18-20) ወንድ ልጃቸውን ለማስገረዝ የሚያስቡ ወላጆች ይህን ለማድረግ የተነሳሱበትን ዓላማ መመርመር ይኖርባቸዋል። በዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በመቁጠር፣ ወደ ትልቅ ሰውነት መሸጋገሪያ ነው ብለው በማሰብ፣ አንድን ልጅ የአንድ ጎሳ አባል አድርጎ ለመቀበል ወይም ለግል ክብር ሲሉ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች “የዚህ ዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት ትልቅ ትርጉም ያለው ቃል ተናግሯል። (ዮሐ. 17:14) በተጨማሪም ፍላጎታችን ይሖዋን ለማስከበርና ከፍ ከፍ ለማድረግ ሊሆን ስለሚገባው በሌሎች ዘንድ ለመወደስ በመፈለግ ለኩራት በር አንከፍትም። (ዮሐ. 5:44) መገረዝ ለጤንነት ጠቃሚ መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ስለሚያሳዩ በአንዳንድ አገሮች ለጤንነት ሲባል ወንዶችን ማስገረዝ የተለመደ ነው። ይህን በማሰብ ልጁ እንዲገረዝ ከፈለግን ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምሳሌ በመከተል ቀላል በሚሆንበት ጊዜ ማለትም ልጁ ከተወለደ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ማስገረዙ የተሻለ ነው።—ዘሌ. 12:3

ይሁን እንጂ ስለ ሴቶች መገረዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። እንዲሁም የታመኑት የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ዓይነት ልማድ እንደነበራቸው የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለም። የሴቶች ግርዛት በዓይነቱና በመጠኑ እንደየአካባቢው ይለያይ እንጂ ምንጊዜም የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥን የሚጨምር ነው። ይህንን በመፈጸም ገቢ የሚያገኙ አረጋውያን ሴቶች ነገሩን ትክክል አስመስለው ለማቅረብ የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለጤንነት ጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ከባድ የጤንነት እክሎች ያስከትላል። ሰውነት ተፈጥሯዊ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ ዘላቂ የሆነ የሕመም ስሜት እንዲሰማ ማድረግ፣ መካንነት እና አንዳንዴም ወደ ሞት ሊመራ የሚችል ብዛት ያለው ደም መፍሰስ ወይም ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል። በሕይወት ለመትረፍ የቻሉት እንኳ ከጥቂት አመታት በኋላ አንዲት ልጃገረድ “ስለዚህ ጉዳይ በማስብበት ጊዜ በውስጤ የሞትኩ ያህል ሆኖ ይሰማኛል” ስትል የተናገረችው ዓይነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል።

ይህ ልማድ የማያስፈልግ ከመሆኑም ሌላ እነዚህን የመሳሰሉ አደጋዎችና ሥቃይ ስለሚያስከትል በአካል ላይ ከሚደርስ ጥቃት ወይም ስቃይ ጋር ሊወዳደር ይችላል። በፊልጵስዩስ 2:4፤ 4:5 እና ቆላስይስ 3:12 ላይ እንደሚገኙት ካሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ፈጽሞ አይስማማም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሴቶች ግርዛት ክርስቲያናዊ ያልሆነ ልማድ ነው። የሰኔ 22, 1985 የእንግሊዝኛ ንቁ! እና የጥቅምት 1993 የአማርኛ ንቁ! እትሞች በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ይዘዋል።

በተመሳሳይም አንዳንድ ሰዎች ከልጅ መወለድ፣ ከሞት፣ ከመንታዎች መወለድ፣ ከወር አበባ፣ እና ከሌሎችም ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ሊደረጉ አይገባም ብለው የሚያስቧቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሰዎች የተወሰኑ ነገሮች እንዳይነኩ፣ እንዳይበሉ ወይም እንዳይጠጡ፣ አንዳንድ ነገሮችን እንዳያዩ፣ አንዳንድ ልብሶች እንዳይለብሱ፣ በተወሰኑ ቦታዎች እንዳያልፉ ወይም አንዳንድ ነገሮችን በተወሰኑ ጊዜያት እንዲያደርጉ የሚያዙ ልማዶች አሉ። በባህላዊ እምነት መሠረት ሊደረጉ አይገባም ተብለው የሚታሰቡ እንደነዚህ ዓይነት ነገሮች ክርስቲያኖች እንዲያከብሯቸው ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ አልተጠቀሱም። ስለዚህ እነዚህን ባህላዊ እምነቶች ‘ከአባቶቻችሁ የወረሳችሁት ከንቱ ኑሮ’ ወይም ‘እንደሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ያለ ከንቱ መታለል’ ከተባሉት ነገሮች ጋር ልንመድባቸው እንችላለን። (1 ጴጥ. 1:18፤ ቆላ. 2:8) ዛሬ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ በገላትያ 4:9-11 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ ሊያውሉ ይችላሉ። እንግዲያውስ እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ያደገበት ባህል ፍጹም ከሆነው የይሖዋ ምክር ጋር የሚጋጩ ልማዶች ያሉበት መሆን አለመሆኑን መለስ ብሎ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ