ይሖዋ ከወትሮው የበለጠ ኃይል ይሰጣል
1 ለሁሉም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ውድ የሆነ ቅዱስ የአገልግሎት መብት በአደራ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ሆኖም ሰብዓዊ አለፍጽምና እና የዚህ የነገሮች ሥርዓት ጭንቀቶች አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ጨርሶ ብቁ እንዳልሆንን አድርገን እንድንቆጥር ያደርጉን ይሆናል።
2 እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሲሰማን ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ልንጽናና እንችላለን። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።” (2 ቆሮ. 4:7) “ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም” በማለት ጳውሎስ በእርግጠኝነት ተናግሯል። (2 ቆሮ. 4:1) ከቅቡዓን ክርስቲያኖችም ክፍል ሆንን ከ“ሌሎች በጎች” ምሥራቹን ‘ሳንታክት’ መስበክ መቀጠል ለሁላችንም ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑ አይካድም። ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ ከሚሰጠው አምላክ ብርታት ማግኘት ያስፈልገናል።—ዮሐ. 10:16፤ 2 ቆሮ. 4:7
3 ብዙ ምሥክሮች የከረረ ተቃውሞ፣ ከባድ የጤና እክል ወይም የገንዘብ ችግር የሚያጋጥማቸው ቢሆንም ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ መሆናቸው የሚያበረታታ ነው። ሁላችንም የተሰጠን የስብከት ሥራ የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው ማስታወስ ይኖርብናል። ተስፋ መቁረጥ ወይም ፍርሃት የስብከት ወኔያችንን እንዲያዳክምብን ከመፍቀድ ይልቅ ‘በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን’ እንሁን።—ኤፌ. 6:10፤ ምሳሌ 24:10
4 የአምላክን ኃይል ማግኘት የሚቻልበት መንገድ፦ አምላክ እንዲረዳችሁና እንዲያበረታችሁ እየጠየቃችሁ በጸሎት ጽኑ። (ሮሜ 12:12፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ከዚያ በኋላ ይሖዋ ከወትሮው የበለጠ ኃይል እንደሚሰጣችሁ በሙሉ ልባችሁ ታመኑ። (ምሳሌ 3:5) በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ በዘመናችን የተፈጸሙ የሕይወት ታሪኮችን አንብቧቸው። እነዚህ ተሞክሮዎች በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በጽናት እንዲቋቋሙ እየረዳቸው መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። በጉባኤያችሁ ካሉ ወንድሞች ጋር ተቀራረቡ፤ እንዲሁም ከጉባኤ ስብሰባዎች አትቅሩ።—ሮሜ 1:11, 12፤ ዕብ. 10:24, 25
5 ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ያለመታከት እንድንሠራ የሚረዳንን ከወትሮው የበለጠ የይሖዋ ኃይል ለማግኘት እንበቃ ዘንድ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።