የይሖዋ ምሥክሮች—እውነተኞቹ ወንጌላውያን
1 ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የመስበኩን ኃላፊነት ለሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷል። በተለይ ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩ አዟቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 10:42) የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያለ ማሰለስ ስለ መንግሥቱ በመስበክ ረገድ ምሳሌ ትተውልናል። እነርሱ የሰበኩት በአምልኮ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በአደባባይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ሰዎችን ባገኙበት ቦታ ሁሉ ነበር። (ሥራ 5:42፤ 20:20) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የመንግሥቱን መልእክት በ232 አገሮች በመስበክና ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከአንድ ሚልዮን በላይ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በማጥመቅ እውነተኛዎቹ ክርስቲያን ወንጌላውያን መሆናችንን አስመስክረናል! የወንጌላዊነት ሥራችን ይሄን ያህል ስኬታማ የሆነው ለምንድን ነው?
ምሥራቹ ያስደስተናል፦ ወንጌላውያን የምሥራች ሰባኪዎች ወይም መልእክተኞች ናቸው። በመሆኑም የይሖዋን መንግሥት የማስታወቅ አስደሳች መብት አለን። ይህ ለተጨነቁ የሰው ልጆች የሚነገር ብቸኛው ትክክለኛ ምሥራች ነው። በሚመጣው ገነት ውስጥ ታማኝ ከሆኑ የሰው ዘሮች የተውጣጣውን አዲሱን ምድር በጽድቅ ስለሚገዛው አዲስ ሰማይ ያገኘነው የላቀ እውቀት እንድንደሰት አድርጎናል። (2 ጴጥ. 3:13, 17) ይህን ተስፋ ያገኘነው እኛ ብቻ ነን። ለሌሎች ለማካፈልም እንጓጓለን።
3 እውነተኛ ፍቅር ያነሳሳናል፦ ወንጌላዊነት ሕይወት አድን ሥራ ነው። (ሮሜ 1:16) የመንግሥቱን መልእክት ስናሰራጭ ታላቅ ደስታ የሚሰማን በዚህ ምክንያት ነው። እውነተኛ ወንጌላውያን እንደመሆናችን መጠን ለሰዎች ፍቅር አለን። ይህ ደግሞ ለቤተሰቦቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለጓደኞቻችንና በተቻለን መጠን ለሌሎች ብዙ ሰዎች ምሥራቹን እንድናካፍል ይገፋፋናል። ይህን ሥራ በሙሉ ነፍስ ማከናወን ለሌሎች ያለንን እውነተኛ ፍቅር መግለጽ የምንችልበት ጥሩ መንገድ ነው።—1 ተሰ. 2:8
4 የአምላክ መንፈስ ይደግፈናል፦ የአምላክ ቃል የመንግሥቱን ዘር የመትከልና የማጠጣት ሥራችንን ስናከናውን ተክሉን ‘የሚያሳድገው’ ይሖዋ መሆኑን ያረጋግጥልናል። ዛሬ በድርጅታችን ውስጥ የምናየው ነገር ይኸው ነው። (1 ቆሮ. 3:5-7) በወንጌላዊነት ሥራችን የሚደግፈንና ከፍተኛ ስኬት እንድናገኝ የሚያስችለን የአምላክ መንፈስ ነው።—ኢዩኤል 2:28, 29
5 ይሖዋ ሥራችንን መባረኩን እንደሚቀጥል በመተማመን በ2 ጢሞቴዎስ 4:5 ላይ “የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ” የሚለውን ማበረታቻ እያስታወስን ለሰዎች ሁሉ ያለን ፍቅር ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ አስደሳቹን የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል ያነሳሳን።