1 ይሖዋ ዓመፀኛ የሆኑትን እስራኤላውያን ለማስረዳት እንዲህ ሲል ጠይቋቸዋል:- “አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው።” (ኢሳ. 40:28) እኛ ታላቁን ፈጣሪያችንን እናውቃለን፤ የሚያደርግልንንም ፍቅራዊ እንክብካቤ እናስተውላለን። ይሁን እንጂ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የእርሱን ሕልውና ይጠራጠራሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ከሚናገረው ነገር ጋር የማይስማማ አመለካከት አላቸው። እነዚህን ሰዎች ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
2 ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው አዲሱ መጽሐፍ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። መጽሐፉ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ እንዲያስቡ ይጋብዛል። በአማርኛና በትግርኛ ደግሞ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለው ብሮሹር ተመሳሳይ የሆኑ ነጥቦችን በአጭሩ ያቀርባል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው የሚመስጥ ትምህርትና አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥብ አንባቢዎቹን የሚማርክ ነው።
3 ፈጣሪ ከተባለው መጽሐፍ ጋር ተዋወቁ፦ የማውጫውን አጠቃላይ ይዘት በአእምሮህ አስቀምጥ። ከምዕራፍ 2 እስከ 5 ጽንፈ ዓለሙ፣ ሕይወት እንዲሁም የሰው ልጆች እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡና ምንጫቸው ምን እንደሆነ ይገልጻል። ከምዕራፍ 6 እስከ 9 ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ደራሲው የሚገልጽ ሲሆን በተለይ የዘፍጥረት መጽሐፍ የያዘው የፍጥረት ዘገባ ተአማኒነት ያለው መሆን አለመሆኑን ይመረምራል። ምዕራፍ 10 ሰዎች ከሚጠይቋቸው እረፍት ከሚነሱ ጥያቄዎች ለአንዱ ማለትም “ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚያስብ ከሆነ ይህን ያህል ስቃይ የበዛው ለምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
4 ተጠራጣሪ የሆኑትን ለማስረዳት ሞክሩ፦ ፈጣሪ የተባለው መጽሐፍ ከገጽ 78-9 ላይ ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቅሟችሁ የሚችሉ አሳማኝ ነጥቦች ያቀርባል። “ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ ነበረው?” ብላችሁ ጠይቋቸው። አብዛኞቹ መጀመሪያ እንደነበረው ይስማማሉ። ከሆነ እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ:- “ጽንፈ ዓለምን ያስጀመረ አለ ወይስ ራሱ በራሱ ጀመረ?” ብዙዎች ያስጀመረው እንዳለ ይስማማሉ። ይህ ደግሞ ወደ መጨረሻው ጥያቄ ይመራናል “ጽንፈ ዓለምን ያስጀመረው ዘላለማዊ የሆነ አንድ ነገር ነው ወይስ አንድ አካል?” ይህ አቀራረብ ብዙዎችን ፈጣሪ መኖር አለበት ወደሚለው መደምደሚያ ሊመራቸው ይችላል።
5 አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ፈጣሪ የተባለው መጽሐፍ ወይም አምላክ ስለ እኛ ያስባል? የተባለው ብሮሹር ነው። መጽሐፉን ለዘመዶቻችሁ፣ ለሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ ለትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁና ለምታውቋቸው ሌሎች ሰዎች አበርክቱ። የአምላክን ሕልውና የሚጠራጠሩ ሰዎች ሲያጋጥሟችሁ መጽሐፉን ማበርከት እንድትችሉ ወደ አገልግሎት ስትወጡ አይለያችሁ። ከመጽሐፉ ጋር ይበልጥ በተዋወቅን መጠን ለፈጣሪያችን ያለን ፍቅር ይበልጥ ይጠነክራል ይህም ከፍተኛ ከሆኑት የሥነ ምግባር ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን መመላለሳችንን እንድንቀጥል ያንቀሳቅሰናል።—ኤፌ. 5:1፤ ራእይ 4:11