ከበላይ አካሉ የተላከ ደብዳቤ
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል እኛም “ስምህ ይቀደስ” ብለን ወደ አምላክ ከልብ እንጸልያለን። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን በሚያሳይ መንገድ ሕይወታችንን በመምራት ከዚህ ጸሎት ጋር ተስማምተን ለመኖር ጽኑ ፍላጎት እንዳለን እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ የአምላክን ስም ከማወቅ የበለጠ ነገር እንድናደርግ ይጠበቅብናል። ማንኛውንም አጋጣሚ ስሙን ለማወደስ ልንጠቀምበት ይገባል። በእርግጥም፣ ማንኛችንም ልናገኘው ከምንችለው ክብር ሁሉ እጅግ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ተብለን መጠራታችን ነው።—ማቴ. 6:9፤ ኢሳ. 43:10
የይሖዋ ሕዝቦች ከመዝሙር 110:3 ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋ እንዲያከናውኑ ያዘዛቸውን ሥራ በፈቃደኝነት እየፈጸሙ ናቸው። በየትኛውም ዕድሜ የሚገኙና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ለስብከቱ ሥራ ራሳቸውን ያቀረቡት ለምንድን ነው? በቀዳሚነት አምላክን ስለሚወዱና ራሳቸውን ለእርሱ ስለወሰኑ ነው። ዘዳግም 6:5, 6 ይሖዋን ‘በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኃይላችን’ እንድንወድ ያዘናል። እንዲህ ዓይነቱ ከልብ የመነጨ ፍቅር ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ሀብታችንን ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን እንድንጠቀምበት ይገፋፋናል። ይህን የምናደርግበት አንዱ መንገድ ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን በአገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመሳተፍ ነው።
ይሖዋ፣ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንዲታወጅ ያዘዘው ለሰው ልጆች ፍቅር ስላለው ነው። ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰዎች የዓመጽ ጎዳናቸውን ትተው ንስሐ በመግባት ወደ ፈጣሪያቸው እንዲመለሱና ሕይወት እንዲያገኙ ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9) ይሖዋ “ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም” ብሏል። (ሕዝ. 33:11) በአገልግሎት ስንካፈል ይሖዋ ለሰዎች ፍቅር እንዳለው የምናሳይ ሕያው ማስረጃ እንሆናለን። ይህ ሐቅ፣ በዚህ አስፈላጊ ሥራ ስንካፈል ለምናገኘው ደስታና እርካታ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጥርጥር የለውም።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር በመንፈሱ አማካኝነት ላስጻፈው ቃሉ ማለትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ባለን አመለካከትም ይንጸባረቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ ያዕቆብ 4:8 እንደሚያበረታታን አምላክን ማወቅም ሆነ ወደ እርሱ መቅረብ ባልቻልን ነበር። እንዲሁም የተፈጠርነው ለምን እንደሆነና ወደፊት ምን እንደሚከሰት ማወቅ አንችልም። ችግሮች የሚደርሱብን የሁላችንም አባት በሆነው በአዳም የተነሳ መሆኑንም ባልተረዳን ነበር። (ሮሜ 5:12) ከዚህም ባሻገር አምላክ አንድያ ልጁን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በመስጠት ስላሳየን ታላቅ ፍቅር የምናውቀው ነገር አይኖርም። ይሖዋ በተለያዩ ሌሎች መንገዶች በመጠቀም እርሱ ያለውን ከፍተኛ እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል እያካፈለን ነው። በእርግጥም ይሖዋ የሰጠንን ስጦታ ማለትም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንመለከተዋለን! ለዚህ ግሩም ስጦታ ያለን አድናቆት ቃሉን ለማንበብ፣ ለማጥናትና ባነበብነው ላይ ለማሰላሰል ‘ዘመኑን በሚገባ እንድንዋጅ’ ይገፋፋናል። (ኤፌ. 5:15, 16፤ መዝ. 1:1-3) የአምላክን ቃል በየዕለቱ ለማንበብ የምናውለውን ጊዜ እንዳባከንነው ሆኖ ሊሰማን ፈጽሞ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ያለን ፍቅር ቃሉን ይበልጥ እንድናነብ ሊገፋፋን ይገባል፤ ይህም ስለ አምላክ ይበልጥ እንድናውቅ እንዲሁም ለእርሱ የጠለቀ ፍቅር እንዲኖረን ይረዳናል።
አዳም በይሖዋ ላይ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኛን ጨምሮ ዘሮቹን በሙሉ አስከፊና ተስፋ አስቆራጭ ለሆነ ሁኔታ እንደዳረጋቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምረናል። ሆኖም አምላክ የሰው ልጆችን ከዚህ ሁኔታ ማላቀቅ የሚችል ሲሆን ለዚህም ዝግጅት አድርጓል፤ በዚህ መንገድ ለምድር ያለውን ዓላማ ከዳር ለማድረስ የሚያስችሉትን እርምጃዎች ወስዷል።—ዘፍ. 3:15
ሁላችንም የአምላካችንን ድንቅ ስም የማስቀደስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ምን ያህል ድንቅ አምላክ መሆኑን ይበልጥ ባወቅን መጠን ታላቅ ስሙንና ዓላማውን ለሌሎች ለማሳወቅ ከእርሱና ከድርጅቱ ጋር ተባብረን ለመሥራት እንገፋፋለን። ይህንንም ስናደርግ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ሞገስ እንደምናገኝና እርዳታው እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ በመጪው አዲስ ዓለም ዘላለማዊ ሕይወት የመውረስ ተስፋም ተዘርግቶልናል።
እኛ የበላይ አካሉ አባላት ለእናንተ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጥልቅ ፍቅር እንዳለን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። በተጨማሪም “ታላቁ መከራ” ከመምጣቱ በፊት ባለው ቀሪ ጊዜ በተቻለ መጠን ለበርካታ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ የምታደርጉትን ትጋት የተሞላበት ጥረት ከልብ እንደምናደንቅ ልንገልጽላችሁ እንፈልጋለን። (ራእይ 7:14) እንዲህ በማድረግ፣ ሌሎችም ልክ እንደ እናንተ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውቀት የማግኘት አጋጣሚ እንዲኖራቸው ትረዷቸዋላችሁ።—ዮሐ. 17:3
ወንድሞቻችሁ፣
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል