የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 3/11 ገጽ 3-4
  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
km 3/11 ገጽ 3-4

ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

የተወደዳችሁ የይሖዋ አገልጋዮች

የምንኖረው አስደናቂ የሆኑ ነገሮች እየተከናወኑ ባሉበት ዘመን ውስጥ ነው። በእርግጥም ያለንበት ጊዜ በጣም አስደሳች ነው! ውድ ወንድሞችና እህቶች በሰማይ ስለሚኖረው አባታችን ስለ ይሖዋ ከምንጊዜውም የበለጠ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ከእናንተ ጋር “ትከሻ ለትከሻ” ተደጋግፈን መሥራት በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን!​—ሶፎ. 3:9 NW፤ ዮሐ. 14:12

ይሖዋን በማገልገል ደስታ እናገኛለን ሲባል ከባድ የሆኑ ችግሮች አያጋጥሙንም ማለት አይደለም። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት አንዳንዶቻችሁ በመሬት መናወጥ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአውሎ ነፋስና በሌሎች አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ይህ ነው የማይባል ችግር አሳልፋችኋል። (ማቴ. 24:7) ብዙዎች ደግሞ በበሽታና በእርጅና ምክንያት ዕለት ዕለት ይሠቃያሉ። ሁላችንም እየተፋፋመ የመጣውን “የምጥ ጣር” ተቋቁሞ መኖር ግድ ሆኖብናል። (ማቴ. 24:8) በአርሜኒያ፣ በኤርትራና በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩትን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች ያሉ ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል።​—ማቴ. 24:9

እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል የረዳን ምንድን ነው? የ2010 የዓመት ጥቅስ ‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም’ በማለት አንዱን ወሳኝ ምክንያት ይጠቁመናል። (1 ቆሮ. 13:7, 8) አዎን፣ እርስ በርስ ያለን ፍቅር አልፎ ተርፎም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ችግሮችን በተሳካ መንገድ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቶናል።

ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሰዎች የስብከት ሥራችን መጠነ ሰፊ ብሎም የማይቋረጥና ወጥ መሆኑ በጣም ያስገርማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ እምነታችንንና የምናስተምረውን ትምህርት ባይቀበሉም እንኳ “እናንተ የምትሠሩት እኮ እኛ መሥራት ያለብንን ሥራ ነው!” ብለው ለመናገር ተገፋፍተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ነጋ ጠባ እንዲሰብኩ ያስቻላቸው አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? አሁንም መልሱ ፍቅር ነው። በሰማይ እንደሚኖረው አባታችን ሁሉ እኛም ማንም እንዲጠፋ አንፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 7,508,050 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር መመዝገቡ ሁሉም ሰው ወደ ንስሐ እንዲደርስ ያለንን ፍላጎት ያንጸባርቃል። ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረብ ይህን ሥራ ሳያሰልሱ በፍቅር የሚያከናውኑ በርካታ አገልጋዮች ያሉት ሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ማግኘት ይቻላል?

ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት የጻፈው ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ማየታችን ያበረታታናል፦ “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።” (ኢሳ. 2:2-4) ወደ ይሖዋ ቤት ከሚጎርፉት ሕዝቦች መካከል ባለፈው የአገልግሎት ዓመት የተጠመቁት 294,368 ሰዎች ይገኙበታል። ወደ ድርጅታችን የመጡትን እነዚህን ውድ የይሖዋ ንብረቶች በደስታ እንቀበላቸዋለን። ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ የሚሰነዝርባቸውን ጥቃት መመከት እንዲችሉ በክርስቲያናዊ ፍቅር ተነሳስተን እነሱን መርዳታችንን እንቀጥል።​—1 ጴጥ. 5:8, 9

ማክሰኞ፣ መጋቢት 30, 2010 በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ 18,706,895 የሚደርስ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር መገኘቱ ገና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ይሖዋን ለማወደስ ከእኛ ጋር ሊተባበሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል። ይሖዋ የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ እስካሁን እንዲቆይ በማድረጉ ደስተኞች ልንሆን ይገባል! መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ግን ፍቅራችን በጽናት እንድንቀጥል ይረዳናል።​—2 ተሰ. 3:5

በዓለም ዙሪያ በአብዛኛው 2010 ላይ የተደረገው “ከአምላክ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ!” የሚለው የአውራጃ ስብሰባ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና አጠናክሮልናል። ይሖዋ “አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! (መዝ. 144:15) መጪው ጊዜ ይዞ የሚመጣው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ከጎናችን እስከሆነ ድረስ የሚያስፈራን አንዳች ነገር እንደሌለ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 23:4) በቅርቡ ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ‘የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሰዋል።’ (1 ዮሐ. 3:8) በእርግጥም ይህ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን! እስከዚያው ድረስ ግን የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉን።​—1 ቆሮ. 15:58

“ያለማቋረጥ” በጸሎታችን እንደምናስባችሁ እርግጠኞች ሁኑ። (ሮም 1:9) “ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ኑሩ።”​—ይሁዳ 21

ሁላችሁንም እንወዳችኋለን!

ወንድሞቻችሁ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ