በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
1. በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለውን ብሮሹር ማጥናት የምንጀምረው መቼ ነው? ብሮሹሩን ማጥናታችን የሚጠቅመንስ እንዴት ነው?
1 የካቲት 17 ቀን 2014 ከሚጀምረው ሳምንት አንስቶ በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለውን ብሮሹር በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እናጠናለን። “ልብህን ጠብቅ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጣው ይህ ብሮሹር የተዘጋጀበት ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ወደ ድርጅቱ ለመምራት ነው። ይህን ብሮሹር ማጥናታችን የይሖዋ ድርጅት አባል መሆናችንን ይበልጥ እንድናደንቅ የሚያነሳሳን ከመሆኑም በላይ ይህን ግሩም መሣሪያ በአገልግሎታችን ለመጠቀም እንድንችል ከብሮሹሩ ጋር በሚገባ ያስተዋውቀናል።—መዝ. 48:13
2. ብሮሹሩ በጉባኤ ውስጥ የሚጠናው እንዴት ነው?
2 ብሮሹሩ የሚጠናበት መንገድ፦ ጥናቱን የሚመራው ወንድም እያንዳንዱ ትምህርት እኩል ሽፋን እንዲያገኝ ጊዜውን ማመጣጠን ይጠበቅበታል። የጥናቱ መሪ እያንዳንዱን ትምህርት የሚጀምረው በጥያቄ መልክ የቀረበውን የትምህርቱን ርዕስ በማንበብ ነው። ከዚያም አንባቢው የመጀመሪያውን አንቀጽ እንዲያነብብ ይጋብዘዋል። በመቀጠል የጥናቱ መሪ ለመጀመሪያው አንቀጽ ያዘጋጀውን ጥያቄ ይጠይቃል። ከዚያ በኋላ ደመቅ ብሎ በተጻፈ ዓረፍተ ነገር የሚጀምሩት ክፍሎች በተናጠል ተነብበው ለየብቻ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል። እነዚህ ክፍሎች ከተነበቡ በኋላ የጥናቱ መሪ፣ በዋና ርዕስ ላይ ለቀረበው ጥያቄ የያዙትን መልስ እንዲናገሩ አድማጮችን ይጋብዛል። በተጨማሪም ብሮሹሩ ሐሳብ ሊሰጥባቸው የሚችል በርካታ ፎቶግራፎችንና ሥዕላዊ መግለጫዎችን ይዟል። ቁልፍ ጥቅሶች ጊዜ በፈቀደ መጠን መነበብ ይኖርባቸዋል። የጥናቱ መሪ ወደሚቀጥለው ትምህርት ከመሄዱ በፊት በእያንዳንዱ ትምህርት ግርጌ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ትምህርቱን ይከልሳል። ትምህርቱ “ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት” የሚል ሣጥን ካለው ደግሞ አንባቢው ሣጥኑ ውስጥ ያለውን ሐሳብ እንዲያነብበው ማድረግ አለበት፤ ከዚያም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በሣጥኑ ውስጥ የቀረበውን ምክር ሥራ ላይ የሚያውል ከሆነ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ ሐሳብ እንዲሰጡ አድማጮችን ይጋብዛቸዋል። ጊዜ ከፈቀደ በጥናቱ መደምደሚያ ላይ የጥናቱ መሪ የትምህርቶቹን ዋና ርዕሶች እንደ ክለሳ ጥያቄዎች ሊጠቀምባቸው ይችላል። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ የግድ ይህን መመሪያ መከተል አለብን ማለት እንዳልሆነ አትዘንጉ።
3. ይህ ብሮሹር በሚጠናበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 ከትምህርቱ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንድትችሉ በደንብ ተዘጋጅታችሁ መምጣት ይኖርባችኋል። ሐሳብ ለመስጠትም ጥረት አድርጉ። እየተጠና ያለው ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሰላስሉ። ይህን አዲስ ብሮሹር ማጥናታችን ሌሎችም ከእኛ ጋር በመሆን የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርጉ ለመርዳት ብቁ እንደሚያደርገን እንተማመናለን፤ ይህ ደግሞ እነሱም የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በር ይከፍታል።—1 ዮሐ. 2:17