የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwyp ርዕስ 114
  • መኖር ቢያስጠላኝስ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መኖር ቢያስጠላኝስ?
  • የወጣቶች ጥያቄ
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ራሴን የማጥፋት ሐሳብ ሲመጣብኝ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ሞቼ ብገላገልስ?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • የመንፈስ ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ለምን ሞቼ አልገላገልም?
    ንቁ!—2008
ለተጨማሪ መረጃ
የወጣቶች ጥያቄ
ijwyp ርዕስ 114
በመንፈስ ጭንቀት የተዋጠች አንዲት ወጣት በመስኮት ደጁን ፍዝዝ ብላ እየተመለከተች፤ ውጭ ላይ ዝናብ እየጣለ ነው።

የወጣቶች ጥያቄ

መኖር ቢያስጠላኝስ?

“ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ በጭንቀት ከመወጠሬ የተነሳ ውስጤ በእሳት የሚጋይ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። በዚያ ወቅት ራሴን ስለማጥፋት አስብ ነበር። እውነቱን ለመናገር መሞት ፈልጌ አይደለም። የፈለግኩት ከሥቃዬ መገላገል ነበር።”—ጆናታን፣ 17

በ14,000 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከ5ቱ 1ዱ ባለፈው ዓመት ውስጥ ራሱን ስለማጥፋት አስቦ እንደነበር ተናግሯል።a አንተስ መኖር ቢያስጠላህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

  • ታገሥ። እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲመጣብህ በችኮላ እርምጃ ላለመውሰድ ለራስህ ቃል ግባ። ያጋጠሙህ ችግሮች ምንም መፍትሔ የሌላቸው መስለው ይታዩህ ይሆናል። ሆኖም ችግሮችህን ለመቋቋም የሚረዳህ መላ አይጠፋም።

መውጫው የጠፋባት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት።

መውጫ ቀዳዳ የሌለው ሁኔታ ውስጥ እንደገባህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ስሜት ከእውነታው የራቀ ሊሆን ይችላል። ያጋጠሙህን ችግሮች ለመቋቋም የሚረዱ መፍትሔዎች መኖራቸው አይቀርም። ተገቢውን እርዳታ ማግኘት ብትችል መፍትሔው እጅህ ላይ ሊሆን ይችላል።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8

    እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ራስህን የማጥፋት ሐሳብ በተደጋጋሚ የሚመጣብህ ወይም በጣም የሚያስቸግርህ ከሆነ እርዳታ ለማግኘት ሞክር፤ ምናልባትም ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች የሚረዱ ተቋማትን ማማከር ትችላለህ። እነዚህ ተቋማት እርዳታ ለመስጠት የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሏቸው፤ ደግሞም ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።

  • ስሜትህን ለሌላ ሰው ተናገር። ስለ አንተ በጥልቅ የሚያስቡና ሊረዱህ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ጓደኞችህና የቤተሰብህ አባላት ይገኙበታል። ሆኖም ስሜትህን ካልነገርካቸው ያለህበትን ሁኔታ እንዴት ማወቅ ይችላሉ?

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት መነጽር ስታደርግ።

አንዳንድ ሰዎች አጥርተው ለማየት መነጽር ያስፈልጋቸዋል። ጓደኛም ልክ እንደ መነጽር ሊሆን ይችላል፤ ስላጋጠሙህ ችግሮች ተገቢው እይታ እንዲኖርህና በሕይወት የመቀጠል ፍላጎትህ እንዲቀሰቀስ ሊረዳህ ይችላል።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

    እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለጓደኛህ ጉዳዩን ለማንሳት እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ እየመጣ እያስቸገረኝ ነው። ላዋራህ ፈልጌ ነበር፤ ጊዜ ይኖርሃል?” ወይም ደግሞ “የሆነ ችግር ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል፤ ልትረዳኝ የምትችል ይመስልሃል?” ልትለው ትችላለህ።

  • ሐኪም ጋ ሂድ። እንደ መንፈስ ጭንቀት ያሉ የጤና ችግሮች ሰዎች ሕይወት እንዲያስጠላቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። ጥሩው ነገር ግን እነዚህ የጤና ችግሮች መታከም ይችላሉ።

አንዲት የታመመች ወጣት ፍዝዝ ብላ ተቀምጣለች። ፊቷ የቀረበውን ምግብ እየበላች አይደለችም።

ጉንፋን የምግብ ፍላጎትህን እንደሚያጠፋው ሁሉ የመንፈስ ጭንቀትም የመኖር ፍላጎትህ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ለሁለቱም የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይቻላል።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12

    እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በቂ እንቅልፍ ተኛ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ ጥረት አድርግ። ጤንነትህ ስለ ሕይወት ባለህ አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

  • ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን “ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:20) ታዲያ ለምን አሁኑኑ ወደ እሱ አትጸልይም? ይሖዋ የሚለውን ስሙን ተጠቅመህ የልብህን አውጥተህ ንገረው።

በጣም ከባድ ካርቶን ለመሸከም የምትታገል ወጣት።

አንዳንድ ሸክሞችን ብቻህን ልትሸከማቸው አትችልም። ፈጣሪህ ይሖዋ ሊረዳህ ፈቃደኛ ነው።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

    እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለይሖዋ ስለ ችግሮችህ ከመናገር ባለፈ በዛሬው ዕለት ያደረገልህን ቢያንስ አንድ ነገር አንስተህ አመስግነው። (ቆላስይስ 3:15) አመስጋኝነት ለሕይወት ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል።

በሕይወት መኖር ዋጋ እንደሌለው የሚሰማህ ከሆነ የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆናታን ያደረገው ልክ እንደዚህ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ከወላጆቼ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ማውራትና የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈልጎኝ ነበር። አሁን በጣም ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። ችግሮች አሁንም ያጋጥሙኛል፤ ራሴን ለማጥፋት ግን አላስብም።”

a ይህን ጥናት በ2019 ያካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ነው።

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

አሌክሳንድራ።

“አእምሯዊ ጤንነት የአካላዊ ጤንነትን ያህል አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው አካሉ ላይ ጉዳት ቢደርስበት ለምሳሌ እጁ ቢሰበር በቀላሉ ይታያል፤ ውስጡ የተጎዳን ሰው ግን በቀላሉ አይቶ ማወቅ አይቻልም። የሚረብሽህ ነገር ካለ ከመናገር ወደኋላ አትበል። እርዳታ መጠየቅ ምንም ችግር የለውም።”—አሌክሳንድራ

Ian.

“ልጅ እያለሁ ወላጆቼ መፍትሔ የሌለው ምንም ችግር እንደሌለ ይነግሩኝ ነበር፤ ሌላው ቢቀር ችግሩን መቋቋም እንደሚቻል አስተምረውኛል። የውስጣችሁን አውጥታችሁ የምትነግሩት ሰው ማግኘት በጣም ጠቃሚ ነው፤ እኔ ለወላጆቼ ስሜቴን አውጥቼ መናገሬ ስለ ችግሮቼ ሚዛናዊ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል።”—ኢየን

ሊጠቅሙህ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

በጭንቀት ስትዋጥ ልታነባቸው የምትችላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ዝርዝር ለምን አታዘጋጅም? ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥቅሶች መያዝ ትችላለህ፦

መዝሙር 34:18፦ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”

ትርጉሙ፦ ይሖዋ ችግራቸው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ለሚሰማቸው ሰዎች ያዝናል። ሊረዳቸውም ይፈልጋል።

መዝሙር 46:1፦ “አምላክ መጠጊያችንና ብርታታችን፣ በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን ነው።”

ትርጉሙ፦ ጭንቅ በሚልህ ሰዓት ሁሉ ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። ይሖዋ ችግርህን እንድትቋቋም ለመርዳት ፈቃደኛ ነው።

መዝሙር 94:18, 19፦ “‘እግሬ አዳለጠኝ’ ባልኩ ጊዜ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ደገፈኝ። በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”

ትርጉሙ፦ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሊያጽናናህ ይችላል። ቃሉን ሳታነብ አንድም ቀን አይለፍብህ።

መዝሙር 139:23, 24፦ “አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ . . . የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ። በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።”

ትርጉሙ፦ ይሖዋ አንተ ራስህን ከምታውቀው በላይ ያውቅሃል። ጎጂ ሐሳቦችን አስወግደህ እንደ ድሮው ደስተኛ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።

ኢሳይያስ 41:10፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።”

ትርጉሙ፦ የትኛውም ዓይነት ከባድ ችግር ቢያጋጥመን ለመቋቋም የሚረዳ ኃይል ይሖዋ ይሰጠናል።

ክለሳ፦ መኖር ቢያስጠላኝስ?

  • ታገሥ። እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲመጣብህ በችኮላ እርምጃ ላለመውሰድ ለራስህ ቃል ግባ። ችግርህን ለመቋቋም የሚረዳህ መላ አይጠፋም።

  • ስሜትህን ለሌላ ሰው ተናገር። ጓደኞችህና ቤተሰብህ ስለ ችግርህ ካልነገርካቸው ያለህበትን ሁኔታ ማወቅ አይችሉም።

  • ሐኪም ጋ ሂድ። ራስህን የማጥፋት ሐሳብ የመንፈስ ጭንቀት ምልክት ሊሆን ይችላል፤ የመንፈስ ጭንቀት ደግሞ በሕክምና ሊስተካከል የሚችል ችግር ነው።

  • ስሜትህን አውጥተህ ለአምላክ በጸሎት ንገረው። አምላክ አንተ ራስህን ከምታውቀው በላይ ያውቅሃል፤ ሊረዳህም ይፈልጋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ