ገንዘብ ጨካኝ ጌታ ነው
ማስታወቂያዎች ሥውር በሆኑ የሥነ አእምሮ ዘዴዎች በመጠቀም የሸማቹን ኅብረተሰብ ልብ ለማነሳሳት ይጥራሉ። ሰዎች የግድ የማያስፈልጋቸውን ነገር፣ አንዳንዴም የማይወዷቸውን ሰዎች ለማስቀናት ሲሉ በሌላቸው ገንዘብ እንዲገዙ ይገፋፏቸዋል።’
ብዙዎች ኑሯቸውን አስተማማኝና የተደላደለ ለማድረግ በመፈለግ ብዙ ገንዘብ እንዲያካብቱ ይገፋፋሉ። ይሁን እንጂ ያካበቱት ገንዘብ የፈለጉትን ውጤት ያስገኝላቸዋልን?
ቀደም ሲል የጠቀስናት ሊዝ ሀብታም ባል አገባች። እንዲህ ትላለች:- “በተጋባንበት ጊዜ ቆንጆ ቤትና ሁለት መኪና ነበረን። የነበረን ገንዘብ ይህ ዓለም ሊሰጥ የሚችለውን ቁሳዊ ነገር በሙሉ ለማግኘት፣ ወደፈለግነው ቦታ ለመጓጓዝና ለመዝናናት ያስችለን ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ስለ ገንዘብ ከመጨነቅ አለመላቀቄ የሚገርም ነበር።” ይህ የሆነበትን ምክንያት ስታስረዳ “ብዙ የምናጣው ነገር ነበረን። ንብረት በበዛ መጠን ያለመረጋጋት ስሜት የሚጨምር ይመስለኛል። ገንዘብ ከሐሳብም ሆነ ከጭንቀት ነጻ አላወጣኝም” ብላለች።
ለገንዘብ መሯሯጥ ዘመናችን ተለይቶ የሚታወቅበት ባሕርይ ቢሆንም እውነተኛ እርካታ ግን ሊያስገኝ አልቻለም። ዴቪድ ሲልቨስተር በደትሮይት ፍሪ ፕሬስ ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የፍቅረ ንዋይ ዘመን በሆነው በዚህ በ19 80ዎቹ ዓመታት ስለ ገንዘብ ብቻ ማሰብ እንግዳ ነገር ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ፍቅረ ንዋይ በውስጣችን ያለውን አለመረጋጋት የሚያሳይ ምልክት ይመስለኛል።”
ባለ ዕዳ ወይስ ባለ ገንዘብ
የምታገኘው ገቢ አንዳንድ የቅንጦት ዕቃዎችን ለመግዛት የማያስችልህ ቢሆንም ይህ ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ማኅበረሰብ እነዚህን ነገሮች የማግኘት መብት እንዳለህ ሊያሳምንህ ይፈልጋል። ሰዎች ንብረት ለመሰብሰብ ያላቸው ፍላጎት በጣም በመጨመሩና የገንዘብ ዋጋ በመጋሸቡ ምክንያት የዱቤ ካርድ ወይም የፕላስቲክ ገንዘብ ንግድ በእጅጉ ተስፋፍቷል። ሰዎች ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ‘ገንዘብ እስክታገኝ ድረስ ሳትገዛ ብትቆይ የዕቃው ዋጋ መናሩ ስለማይቀር አሁኑኑ እንጂ በኋላ መግዛት አይበጅም’ የሚል ነው።
ፈረንሳይ ካላት 6.9 ሚልዮን ካርድ ጋር ሲወዳደር 22.6 ሚልዮን የሚያክሉ የዱቤና የመገበያያ ካርዶች ያሏት ብሪታንያ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ትልቋ የእንደዚህ ዓይነት ካርድ ተጠቃሚ አገር ናት። እንዲህም ሆኖ አሁንም ገበያው እየጨመረ መሄዱን አላቆመም። ዘመኑ በጣም ተለውጧል። ዘ ሊስነር መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ከዚህ በፊት ሰዎች ከዕዳ ይሸሹ ነበር። አሁን ግን ሸማቾች ባለ ዕዳ እንዲሆኑ ከሁሉም አቅጣጫ ይወተወታሉ።”
በዚህ ምክንያት የዓለማችን ዕዳ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ የበለጸጉትን አገሮች አደጋ ላይ ጥሏቸዋል። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ግለሰቦች የሚያገኙት ገቢ ካለባቸው ዕዳ ጋር ሲነጻጸር ዕዳቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ሁኔታ በአንድ አገር ወይም በአንድ አህጉር ብቻ የተወሰነ አይደለም። አንድ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ እንደተናገረው “በቀደሙት ዘመናት ጥቁሮች በዱቤ ካርዶች በፍጹም አይጠቀሙም ነበር። አሁን ግን እንደ ቤት ቁሳቁስ ሱቆች ያሉ የንግድ ድርጅቶች ሊንቀሳቀሱ የቻሉት ጥቁሮች በሚወስዱት ዱቤ ነው።”
ስለ ንግድ ጉዳዮች የሚጽፉት ዴቪድ ሲልቨስተር እንዳሉት “የባለ ዕዳዎች ትውልድ ሆነናል። ከአቅማችን በላይ ገንዘብ እናጠፋለን፣ ገንዘባችንን ትርፍ በሚያስገኝ ሥራ ላይ አናውልም፣ ነገ ፈጽሞ የሚመጣ አይመስለንም፣ ቢመጣም ጡረታ አለልን ብለን እናስባለን።” ታዲያ እንዲህ ያለው ቁሳዊ ነገሮችን የማጋበስ ዝንባሌ ደስታ አስገኝቷልን?
አሳዛኝ ውጤቶች
ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ “የከተማ ከበርቴዎች ውጥረታቸውን በኮኬይን ያረግባሉ” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። አዎን፣ ቁጥራቸው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የሄደ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ወጣት የንግድ ድርጅት ሠራተኞች ስለ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች በሚደራደሩበት ጊዜ ከፍተኛ ጭንቀት ስለሚሰማቸው በአደንዛኝ ዕፅ ሱሰኝነት በመጠመድ ላይ ናቸው።
ይህ የአደንዛዥ ዕፆች ቸነፈር በዎል ስትሪት በሚገኘው የኒው ዮርክ ገንዘብ ማዕከልም ተስፋፍቷል። አንድ የፌዴራል አደንዛዥ ዕፆች ቁጥጥር አስተዳደር ወኪል እንዲህ ብሏል:- “ዕፅ የሚወስዱት ሰዎች በጣም ጠንቃቆች ናቸው። በግድየለሽነት በየደረሱበት አያጨሱም። ስለሆነም በገንዘብ ማዕከሉ ከሚሠሩ ሰዎች 90 በመቶ የሚያክሉት በዕፅ እንደሚጠቀሙ ይታሰባል። ከፍተኛ ውጥረት የሚጫናቸው ወጣት ሠራተኞች አንድ ዓይነት ዕፅ ወስደው ካልተነቃቁ ጥሩ ድርድር ሊያደርጉ የሚችሉ አይመስላቸውም።”
ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የገንዘብ ገበያዎች የተበከሉት ዕፅ በመውሰድ ወንጀል ብቻ አይደለም። በጣም ብዙ ማጭበርበርና ማታለል እንደሚፈጸም ይዘገባል።
“በዓመት ከአንድ ሚልዮን ዶላር የበለጠ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ሕግ እስከመጣስ የሚደርሱት እንዴት ነው?” በማለት ጄይ ቢ ሮርሊች የተባሉት የዎል ስትሪት የሥነ አእምሮ ሐኪም ጠይቀዋል። ሮርሊች ራሳቸው ላነሡት ጥያቄ መልስ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “አንዳንድ ሰዎች የአልኮል፣ የኮኬንና የሌሎች አደንዛዥ ዕፆች ሱስ እንደሚይዛቸውና ዕፁን ሲወስዱ እንደሚረኩ ሁሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የገንዘብ ሱስ ይይዛቸዋል። ገንዘብ ሲያገኙም ይረካሉ። ለእነርሱ ገንዘብ የሚሰማቸውን ጉድለት የሚያስረሳቸው መድኃኒት ነው።”
በዚህ ፍቅረ ንዋይ በተጠናወተው ዓለማችን ውስጥ ንብረት ማካበት የሚጠላ ነገር መሆኑ ቀርቷል። ሊ ፊጋሮ በተባለው የፈረንሳይኛ መጽሔት ላይ በወጣ ጥናት ላይ እንደተገለጸው ‘አሁን ገንዘብን ያስጠላ የነበረው መጥፎ ጠረን ጠፍቷል።’ ጥናት የተደረገባቸው ፈረንሳዮች ገንዘብ ምን ያስገኛል ተብለው ሲጠየቁ 45 በመቶ የሚያክሉት ደስታ ያስገኛል በማለት መልሰዋል። ይሁን እንጂ የሚያስገኘው የዚህን ተቃራኒ ነው።
ይህን ከፍተኛ ሐዘን ያስከተለውን ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ መጎምጀት ለማስወገድ ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖራልን?
ራስን የመመርመር አስፈላጊነት
የገንዘብ ሱስ የያዘህ መስሎ ላይሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ከሰዎች ጋር የምታደርገው ጭውውት የሚያተኩረው በገንዘብ ወይም ገንዘብ ሊገዛ በሚችላቸው ነገሮች ላይ ነውን? ለገንዘብ ከሚገባ በላይ ትኩረት ትሰጣለህን? እንዲህ ዓይነት ስሜት ያለኝ እኔ ብቻ አይደለሁም ብለህ በማሳበብ ለገንዘብ መጎምጀትህ ተገቢ እንደሆነ ታስባለህን?
በገንዘብ ፍቅር ተጠምዶ የገንዘብ ባሪያ መሆን አደገኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ኖሮ የነበረ አንድ ጠቢብ አስተማሪ ስለ ገንዘብ አታላይነት አስጠንቅቋል። ብዙ ገንዘብ በማግኘት መደሰትን ፍሬ የሚሰጥ ተክልን አንቆ በሚያደርቅ እሾህ መስሏል። (ማቴዎስ 13:22) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት ያስጠነቅቃል።—1ጢሞቴዎስ 6:10
በእውነት ገንዘብ የበላይነት አግኝቶ ሲቆጣጠረን ጨካኝ ጌታ ነው። ይሁን እንጂ አገልጋይ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በዚህ በዛሬው ዓለማችን ጠቃሚ አገልግሎት ሊያበረክት ይችላል።