ይሖዋ እስራኤላውያንንና ከነዓናውያንን ከምድሪቱ ያስወጣበት ምክንያት ምንድን ነው?
አንድ ሰው “ሌሎችን መንቀፍ እወዳለሁ፤ ያስደስተኛል” ብለዋል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸውና ይሖዋ አምላክን መንቀፍ የሚወዱ ሰዎች ለየት ያለ የበላይነት ስሜት ይሰማቸዋል! የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኝነት ለመገምገምና ለመንቀፍ የተደረገው ምርምር በተደጋጋሚ ይሖዋን ደም የጠማው የአይሁዳውያን የጐሳ አምላክ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል። አንድ ቄስ መጥፎና ጨካኝ ነው በማለት አውግዘውታል። ስለ እርሱ የተናገሩት ነገር ትክክል እንደሆነ ለማስረዳት እነዚህ ደፋር ተቺዎች ይሖዋ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ለመስጠት ሲል ከነዓናውያንን ማጥፋቱን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ክስ ስለነገሩ ምንም እንደማያውቁ ያሳያል። ሙሴ የይሖዋ አፈቀላጤ እንደመሆኑ ለአይሁዳውያን ምክንያቱን ግልጽ ሲያደርግላቸው። “ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንዓት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢያት ምክንያት . . . ነው” ብሏቸዋል።—ዘዳግም 9:5
ከነዓናውያኑን እንዲጠፉ ያደረጋቸው የራሳቸው ክፋት ነበር። እንደገና የታተመው ሃሌይስ ባይብል ሃንድ ቡክ እንደሚለው በኣልን እንደ ዋነኛ አምላካቸው እንዲሁም ሚስቱን አስታሮትን እንደ ዋነኛ የሴት አምላካቸው አድርገው ማምለክ ከጀመሩ በኋላ “የበኣልና የአስታሮት ቤተ መቅደስ ብዙውን ጊዜ አንድ ላይ ይሠራ ነበር። የሴት ካህናቱ የቤተ መቅደስ አመንዝራዎች ነበሩ። ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙት ደግሞ የቤተ መቅደስ ወንድ አመንዝራዎች ነበሩ። ከልክ ባለፈና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ስሜት የተሞሉት የበኣል፣ የአስታሮትና ሌሎች የከነዓናውያን አማልክት ቤተ መቅደሶች የመጥፎ ምግባር ማዕከሎች ነበሩ።”—ገጽ 166
በከነዓናውያን ዘመን እነዚህ “ከፍተኛ ቦታዎች” ይገኙባቸው ከነበሩባቸው አካባቢዎች በአንዱ ከተገኙት ፍርስራሾች ውስጥ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች “ለበኣል አምልኮ ሲባል መሥዋዕት የተደረጉ ሕጻናትን ቅሪት አካል የያዙ ማሰሮዎች አግኝተዋል። አካባቢው በሙሉ ገና የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት መቃብር ሆኖ ተገኝቷል።” እንዲሁም “ብዙ ቁጥር ያላቸው ምስሎችና የጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ ታስበው የተሠሩ የአስታሮትን ምስል የያዙ የግድግዳ ላይ ቅርጻ ቅርጾች በጣም ተጋነው ከሚታዩ የጾታ ብልት ሥዕሎች ጋር ተገኝተዋል። ስለዚህ ከነዓናውያን አምልኳቸውን ያካሂዱ የነበረው እንደ አንድ የአምልኮ ሥርዓት አምላካቸው በተገኘበት ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት በመፈጸምና የበኩር ልጆቻቸውን ለአምላካቸው መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ ነበር።”—ገጽ 166, 167
ከዚያም በመቀጠል ሃሌይስ እንዲህ ይላል:- “ታዲያ አምላክ ከነዓናውያንን እንዲያጠፏቸው ለእስራኤላውያን ትዕዛዝ መስጠቱ ሊያስገርመን ይገባልን? እንዲህ ዓይነቱ አስከፊና ቆሻሻ ሥልጣኔ የመቆየት መብት ነበረውን? . . . የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ የቆፈሩ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች አምላክ ከዚያ ቀደም ብሎ እንዴት ሳያጠፋቸው እንደቀረ ገርሟቸዋል።”—ገጽ 167
በጄ ቢ ሮተርሃም የተተረጎመው ዘ ኢምፋሳይዝድ ባይብል በገጽ 259 ላይ እንዲህ ይላል:- “ልዑሉ ምድርን የሚያረክሱትንና የሰው ዘርን የሚበክሉትን እንደዚህ ያሉ ሰዎች ለማጥፋት መብት የለውም ብሎ ሊናገር የሚችል ማን ነው?”
ይሖዋ ከነዓናውያን ለምን እንደጠፉ ለእስራኤላውያን “በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርሷ ላይ እመልሳለሁ፣ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች” በማለት ነግሯቸው ነበር። ከዚያም ለእስራኤላውያን ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው “እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባቸሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፣ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፣ አድርጉትም” አላቸው።—ዘሌዋውያን 18:24–26፤ 20:22
መልእክቱ ግልጽ ነው። ከነዓናውያን የጠፉበት ምክንያት በዝሙታቸው፣ በግብረ ሰዶም ድርጊታቸውና የሕጻናትን ደም በማፍሰስ በፈጸሙት ከፍተኛ ነውር ምድሪቱን ስለበከሉ ነው። እስራኤላውያን የበኣል አምልኮ የሆነውን ይህንን የከነዓናውያን ሃይማኖት ቢከተሉ እነርሱም ጭምር ይጠፋሉ።
እስራኤላውያንም ያንኑ ዓይነት ድርጊት ፈጸሙ። እስራኤላውያን ምድሪቱን ከያዙ በኋላ አካባቢውን በሸፈነው አለት ሥር የነበረውን የአስታሮት ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ቆፍረውት ነበር፤ “ከዚህ ከቤተ መቅደስ ትንሽ እርምጃዎች ራቅ ብሎ የሚገኝ ቦታ ላይ መሥዋዕት የተደረጉ ሕጻናትን ቅሪት የያዙ ገንቦዎች የተገኙበት የመቃብር ቦታ ነበር . . . የበኣልና የአስታሮት ነቢያት የታወቁ የሕጻናት ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ።”—ሃሌይስ ባይብል ሃንድ ቡክ ገጽ 198
በሙሴ አማካኝነት የተሰጠው የይሖዋ ሕግ እንዲህ ዓይነቱን ብልሹ የጾታ ሥነ ምግባር ይከለክል ነበር። ዘሌዋውያን 20:13 “ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽሞ ይገደሉ” ይላል።
እንዲሁም የሙሴ ሕግ በዘዳግም 23: 17, 18 ላይ እንዲህ ይላል:- “ከእስራኤል ሴቶች ልጆች [የቤተ መቅደስ አዓት] ሴት ጋለሞታ አትገኝ፣ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች [የቤተ መቅደስ አዓት] ወንድ ጋለሞታ አይገኝ። ስለተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ [ማጣቀሻ ያለው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “በተለይ ከወንድ ልጆች ጋር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንዶችን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም”] ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።”
ይሖዋ እስራኤልን ለማስጠንቀቅ ነቢያትን ልኳል። “እግዚአብሔርም ማልዶ ተነሥቶ ባሪያዎቹን ነቢያትን ወደ እናንተ ላከ፤ እናንተም አላደመጣችሁም ጆሮአችሁንም አላዘነበላችሁም።”(ኤርምያስ 25:4) ከዚህ ይልቅ እስራኤላውያን “ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፣ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችን ለራሳቸው ሠሩ። በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን [የቤተ መቅደስ ወንድ አመንዝሮች አዓት] [የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ “የሴት ባሕርይ ያለው ወንድ” ይለዋል] ነበሩ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኩሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር።”—1 ነገሥት 14:23, 24
ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል:- “ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፣ መሥዋዕትንም ትሰዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን [የጾታ ብልት ምስል] አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፣ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፣ [የወንድ የጾታ ብልት] ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ።”—ኢሳይያስ 57:7, 8 አን አሜሪካን ትራንስሌሽን
ሴቶች የጾታ ብልት ምስሎችን በመሥራት ከእነርሱ ጋር ይገናኙ እንደነበር ሲገልጽ “ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል [ረክሰሽባቸውማል ሮተርሃም ትርጉም]” ይላል።— ሕዝቅኤል 16:17
እስራኤላውያን እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ጋር ቀላቅለዋል። በሲና ተራራ የወርቁን ጥጃ ሲያመልኩ የስነ ምግባር ብልግና ፈጽመዋል፤ “የይሖዋ በዓል” ብለው አክብረዋል። (ዘጸአት 32:5, 6) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላም እንኳ እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ጋር ይቀላቅሉ ነበር። ነቢዩ ኤልያስ ይህንን ድርጊታቸውን በማውገዝ እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም። ” (1 ነገሥት 18:21) ምናሴ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ካደረገ በኋላ የባዕድ አማልክቱን አስወገደና ለይሖዋ የደህንነትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ። ይሁን እንጂ 2 ዜና መዋዕል 33:17 “ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ግን ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር” ይላል።
ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” በማለት በጥያቄ መልክ ያስቀመጠውን መሠረታዊ ሥርዓት በመጣስ የእስራኤል ሕዝብ ለብዙ መቶ ዘመናት የይሖዋን እውነተኛ አምልኮ በበኣል አምልኮ ሲበክል ኖሯል። (2 ቆሮንቶስ 6:16) አሥሩን የእስራኤል ነገዶች አሶራውያን በምርኮ የወሰዷቸው በ740 ከዘአበ ሲሆን የይሁዳ መንግሥት ሁለቱ ነገዶች በባቢሎናውያን በምርኮ የተወሰዱት ደግሞ በ607 ከዘአበ ነበር። ሁለቱም ሕዝቦች ከነዓናውያን እንዳደረጉት ምድሪቷን አርክሰዋል፤ ስለዚህም ከነዓናውያንን እንዳጋጠማቸው ሁሉ ምድሪቱ ሁለቱንም ሕዝቦች ተፍታቸዋለች።
ዛሬ ያሉትስ ሕዝቦች? አብያተ ክርስቲያኖቻቸው በሥነ ምግባር ብልግና የተበከሉ ናቸውን? ምድርን እየበከሉ ነውን? እነሱስ ቢሆኑ ከምድር ላይ ይጠፉ ይሆንን?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የበአልና የአስታሮት ነቢያት የታወቁ የሕፃናት ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕፃናት ቅሪት የተቀበሩባቸው ማሠሮዎች
[ምንጭ]
Lawrence E. Stager/Oriental Institute, University of Chicago