የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 11:- ከ2 ከዘአበ—100 እዘአ—የእምነት፣ የተስፋና የፍቅር መንገድ
“እንደ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ታላላቅ እውነቶችም ያልተወሳሰቡ ናቸው።”—ጁሊየስና አውጉስቶስ ሄር የተባሉት የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛውያን ደራሲዎች
የመቄዶንያ ንጉሥ የነበረው ታላቁ እስክንድር ከሞተ 320 ዓመታት በኋላ ታላቅ የዓለም ድል አድራጊ ተወልዶ ነበር። በሉቃስ 1:32, 33 ላይ ‘የልዑል ልጅ ይባላል እንዲሁም ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም’ በማለት አስቀድሞ እንደተነገረው ይህ ሰው ከታላቁ እስክንድር በሁለት አበይት መንገዶች ይለያል። ይህ ገዥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን አቧራ በለበሱት የታሪክ መጻሕፍት ገጾች ውስጥ ከመመዘገብ የበለጠ ሕይወት እንዲኖር የታቀደለት ሰው ነበር።
ኢየሱስ ያልተወሳሰበ ሕይወት የሚኖር ተራ ሰው ነበር። ልክ እንደ ቤተ መንግሥት ሰፊና የተንቆጠቆጠ ቤት አልነበረውም። ራሱን በጣም ከፍተኛ ሀብትና ሥልጣን ከነበራቸው ሰዎች መካከል እንዲቆጠር አላደረገም። ኢየሱስ በቤተ ልሔም በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ዝቅተኛ ኑሮ ከነበረው አንድ አይሁድ ቤተሰብ ጥቅምት 2 ከዘአበ ገደማ በጣም ቀላል በሆነ ሁኔታ ተወለደ። የመጀመሪያዎቹ የሕይወቱ ጊዜያት ይህ ነው ተብሎ የሚወራላቸው አልነበሩም። በአናጢነት ሙያ ሰልጥኖ ስለነበር ሰዎች “የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር።”—ሉቃስ 3:23 የ1980 ትርጉም ፤ ማርቆስ 6:3
ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ ሐሳብ የማይዋጥላቸው ሰዎች እንኳ የኢየሱስ ልደት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደ ከፈተ ሊያስተባብሉም ሆነ “ክርስትና በታሪክ ውስጥ በሰፊው የተሰራጨና ለሁሉም የተዳረሰ ሃይማኖት ሆኗል” የሚለውን የወርልድ ክርስቺያን ኢንሳይክሎፔድያ አባባል ትክክል አይደለም ብለው ሊከራከሩ አይችሉም።
ልዩ እንጂ አዲስ አይደለም
ክርስትና ፍጹም አዲስ የሆነ ሃይማኖት አልነበረም። ክርስትና የተመሠረተው በተጻፈው የይሖዋ አምላክ ሕግ በዳበረው የእስራኤላውያን ሃይማኖት ላይ ነው። እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ የይሖዋ አምላኪዎች ከመሆናቸው በፊት እንኳ ቀደምት አባቶቻቸው ኖኅ፣ አብርሃም እና ሙሴ ይከተሉት የነበረ ሲሆን በኤደን በመጀመሪያው ከነበረ አንጋፋ የፈጣሪ አምልኮ የቀጠለ ነው። ነገር ግን የእስራኤል ብሔራዊና ሃይማኖታዊ መሪዎች የሐሰት ሃይማኖት ባቢሎናዊ ከሆኑት ትምህርቶቹ ጋር ሰርጎ እንዲገባና አምልኮታቸውን እንዲበክል ፈቅደዋል። ወርልድ ባይብል እንደሚያስገነዝበው:- “ኢየሱስ በተወለደበት ዘመን የአይሁድ ጉባኤ በግብዝነትና ጥብቅ ገደብ በማበጀት ተበክሎ ስለነበር በታላላቅ ዕብራውያን ነቢያት የተነገሯቸው ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች ደብዝዘው ነበር።”
ውስብስብ የሰው ትምህርት ከታከለበት የአይሁድ እምነት ጋር ሲወዳደሩ የኢየሱስ ትምህርቶች ቀናነት ጉልህ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ታታሪ ክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነው ጳውሎስ ስለ ክርስቲያኖች ዋና ጠባይ በተናገረ ጊዜ ይህንን አሳይቷል:- “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” (1 ቆሮንቶስ 13:13) ሌሎች ሃይማኖቶችም ስለ “እምነት፣ ተስፋና ፍቅር” ይናገራሉ፤ ቢሆንም ክርስትና ከዚህ የተለየ ነው። እንዴት?
እምነት በማንና በምን?
ፈጣሪ በሆነው ‘በእግዚአብሔር የማመንን’ አስፈላጊነት ኢየሱስ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:1፤ ማቴዎስ 19:4፤ ማርቆስ 13:19) ስለዚህ ክርስትና ጽንፈ ዓለም ምን ጊዜም የነበረ ነው በማለት ፈጣሪ አለ የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል አሻፈረኝ ከሚሉት ከጄኒዝም ሆነ ከቡድሂዝም የተለየ ነው። ክርስቶስ “ብቻህን እውነተኛ አምላክ” ብሎ ስለተናገረ የጥንቶቹ የባቢሎን፣ የግብፅ፣ የግሪክና የሮም ሃይማኖቶች ያስተምሩ እንደነበረው ወይም የሂንዱይዝም ሃይማኖት አሁንም እንደሚያስተምረው በብዙ ተባዕትና እንስት አማልክት አያምንም ነበር።—ዮሐንስ 17:3 (በአይታሊክ የጻፍነው እኛ ነን።) የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ ያብራራው መለኮታዊ ዓላማ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ በመስጠት’ “የጠፋውን ለማዳን” በዚህም አማካኝነት “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ማድረግ ነበር። (ማርቆስ 10:45፤ ሉቃስ 19:10፤ ዮሐንስ 3:16፤ ከሮሜ 5:17–19 ጋር አወዳድር።) ከኃጢአት ነፃ በሚያወጣው መሥዋዕታዊ ሞት ላይ እምነት ማሳደር ጥንቱን የነበረ ወይም የተወረሰ ኃጢአት አለ የሚለውን ሐሳብ ከሚቃወመው ሺንቶ የተለየ ነው።
ኢየሱስ አንድ እውነተኛ እምነት ብቻ እንዳለ አስተምሯል። “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” በማለት ምክሩን ለግሷል። (ማቴዎስ 7:13, 14) ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ “[የመጀመሪያዎቹ] ክርስቲያኖች እነሱ ብቻ እውነትን እንደያዙ ሌሎች ሃይማኖቶች ግን . . . ሐሰተኞች እንደሆኑ ድርቅ ያለ እምነት ነበራቸው” ብሏል። ይህም ሁሉም ሃይማኖቶች መልካም ተግባር አላቸው ከሚለው ሂንዱ—ቡድሂስት አመለካከት በግልጽ የተለየ ነው።
ምን ዓይነት ተስፋ?
የክርስቲያን ተስፋ ያተኮረው ፈጣሪ መንግሥቱ የዓለምን ችግሮች እንደምታስወግድ በገባው ቃል ላይ ነው። ኢየሱስ በ29 እዘአ ገና አገልግሎቱን ሲጀምር “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” ስለዚህ ‘በወንጌል እመኑ’ እያለ ሰዎችን ያበረታታ የነበረው ለዚህ ነው። (ማርቆስ 1:15) እንደ ቾንዶጊዮ የመሳሰሉት የምሥራቅ ሃይማኖቶች እንደሚያበረታቱት የኢየሱስ ትምህርት ብሔርተኝነት የክርስቲያንን ተስፋ እግቡ የሚያደርስ ጎዳና ነው የሚል አልነበረም። እንዲያውም ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች እንዲገባ የቀረቡለትን ሐሳቦች በሙሉ አልተቀበለም። (ማቴዎስ 4:8–10፤ ዮሐንስ 6:15) አንዳንድ የአይሁድ መሪዎች እንዳደረጉት “የሰው ዘር መሲሕን ለማስገኘት በሙሉ ልብ እግዚአብሔርን መርዳት ይኖርበታል” ብሎ እንዳልደመደመ ግልጽ ነው።
የክርስቲያን ተስፋ ጻድቅ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘትን ያጠቃልላል። (ከማቴዎስ 5:5ና ከራእይ 21:1–4 ጋር አወዳድር።) ይህ ያልተወሳሰበና ለመረዳት የማያስቸግር አይደለምን? ዘ ፌዝስ ኦቭ ማንካይንድ “የአንድ ነገር ማቆሚያ” እንጂ “ሙሉ በሙሉ አለመጥፋት” ብሎ በገለጸው በቡድሂስት ኒርቫና ጽነሰ ሐሳብ አእምሯቸው ለተጋረደ ግን ይህ ቀላል አይደለም። ይህ መጽሐፍ ኒርቫና “ለማስረዳት የማይቻል” መሆኑን አረጋግጧል።
ፍቅር:- ለማንና በምን ዓይነት ሁኔታ?
ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ:- “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የሚለው ነው ብሏል። (ማርቆስ 12:30) ለሰዎች መዳን ቅድሚያ በመስጠት ለመለኮታዊ ዓላማ ግን ትንሽ ቦታ ከሚሰጡት ሃይማኖቶች እንዴት የተለየ ነው። ኢየሱስ በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠው ለባልንጀራ ቀና የሆነ ፍቅር ማሳየትን ነው። “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት መክሯል። (ማቴዎስ 7:12፤ 22:37–39) ነገር ግን ይህ “እንዲያደርጉባችሁ የማትፈልጉትን እናንተም በሌሎች ላይ አታድርጉ” ከሚለው የኮንፊሸስ ግራ የሆነ ትምህርት ጋር እንዴት እንደሚለይ ልብ በሉ። ብልጫ የምትሰጡት ፍቅር ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳያደርጉባችሁ የሚያግዳቸውን ነው ወይስ ጥሩ እንዲያደርጉላችሁ የሚገፋፋቸውን?
ጆን ባስኪን የተባሉ የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ደራሲ “በርግጥም ታላቅ ለሆነ ሰው የመጀመሪያ መለኪያው ትህትና ነው” በማለት ተናግረዋል። ኢየሱስ ለአባቱ ስምና ዝና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለሰዎች ሲል በትህትና ሕይወቱን በመስጠት ለአምላክም ሆነ ለሰው ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ኮሊየርስ ኢንሳይክሎፔድያ “በተደጋጋሚ ጊዜያት አደጋ ላይ ወድቆ በነበረው ሕይወቱ በሙሉ እሱ ከሞተ በኋላ በሕዝቦቹ ላይ ምን ይደርስባቸው ይሆን ለሚለው ጥያቄ አንዲት ሐሳብ እንደተናገረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም” ብሎ ከተናገረለት ከታላቁ እስክንድር በራስ ወዳድነት ምኞት ላይ ከተመሠረተ አምላክ የመሆን ፍላጎት በጣም የተለየ ነው።
ኢየሱስ ይኖርበት በነበረው ዘመን በህንድ እንደነበረው ሂንዱ ለተለየ ኅብረተሰብ ክፍል አድሎ ባለማድረግ ለአምላክና ለሰው ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ሕዝባዊ ድጋፍ በሌላቸው ገዥዎች ላይ አባሎቻቸው ክንዳቸውን እንዲያነሱ ከሚፈቅዱት የአይሁድ ቡድኖች ጋር ከመስማማት ይልቅ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸዋል።—ማቴዎስ 26:52
በሥራ የተገለጸው እምነት
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለእምነት፣ ለተስፋና ለፍቅር ከፍተኛ ግምት ይሰጡ እንደነበረ በአኗኗራቸው ታይቷል። ክርስቲያኖች ለኃጢአተኛው የሰው ዘር የተለመደ የሆነውን ‘አሮጌውን ሰው እንዲያስወግዱና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንዲለብሱ’ ተነግሯቸው ነበር። (ኤፌሶን 4:22–24) እነሱም ይህንኑ አድርገዋል። እንግሊዛዊው የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ሟቹ ሃሮልድ ጄ ላስኪ እንዲህ ሲሉ አስደናቂ ነገር ተናግረዋል:- “የእውነተኛ እምነት መለኪያ እምነቱን የተቀበሉ ሰዎች እምነታቸውን ለሌሎች ለመንገር ያላቸው ችሎታ አይደለም፤ መለኪያው ተራ በሆነው የዕለት ተለት አኗኗር ባሕሪያቸውን ለመለወጥ ያለው ችሎታ ነው።” (በአይታሊክ የጻፍነው እኛ ነን።)—ከ1 ቆሮንቶስ 6:11 ጋር አወዳድር።
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በማይናወጥ እምነት፣ ጥሩ መሠረት ባለው ተስፋና በእውነተኛ ፍቅር በመገፋፋት ኢየሱስ ከማረጉ በፊት “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል የሰጣቸውን የመጨረሻ ትእዛዝ ለመታዘዝ ቆርጠው ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20
በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ፎቅ ውስጥ በተሰበሰቡ 120 ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ ፈሰሰባቸው። በዚህ ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ ተወለደ!a አባሎቹ በዚያ ቀን በተሰጣቸው ተአምራዊ በሆነው በባዕድ አገር ቋንቋዎች የመናገር ስጦታ በመጠቀም በበዓሉ ላይ ለመገኘት በኢየሩሳሌም ከነበሩ ከተለያዩ አገሮች ከመጡ አይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተለወጡ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ችለዋል። (ሥራ 2:5, 6, 41) እንዴት ያለ ውጤት አስከተለ! በአንድ ቀን ብቻ የክርስቲያኖች ቁጥር ከ120 ወደ 3, 000 አሻቀበ!
ኢየሱስ ስብከቱን ባብዛኛው ለአይሁዶች ወስኖት ነበር። ነገር ግን ከጰንጠቆስጤ ዕለት ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ለሚጠብቁ ሳምራውያን በኋላም በ36 እዘአ አይሁድ ላልሆኑትም ሁሉ “መንገዱን” ለመክፈት አገለገለ። ጳውሎስም “የአሕዛብ ሐዋርያ” በመሆን ሦስቱን ሚስዮናዊ ጉዞ ተያያዘው። (ሮሜ 11:13) ጉባኤዎች ተመሠረቱ እንዲሁም ተስፋፉ። ቡክ ፍሮም ክራይስት ቱ ኮንስታንቲን የተባለው መጽሐፍ “እምነታቸውን ለማሰራጨት ያላቸው ቅንዓት ወሰን የለውም ነበር” ይላል፤ አክሎም “የክርስቲያን ምሥክርነት በሰፊው የተሰራጨና ውጤታማ ነበር” ብሏል። የክርስቲያኖች መሰደድ ልክ እሳትን እንደማራገብ ያክል ይበልጥ መልእክቱን ለማሰራጨት ረድቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው የሐዋርያት ሥራ ክርስትና ገና ለጋ በነበረበት ጊዜ የነበረውን ሊገታ ያልቻለ እንቅስቃሴ በተመለከተ የሚያጓጓ ታሪክ ይተርክልናል።
‘ይህ እኔ የማውቀው ክርስትና አይደለም!’
ስለ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የተሰጠውን ይህን መግለጫ ስትሰማ የምታሳየው ቅሬታ ይህ ነውን? ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ጠንካራ እምነት ከመያዝ ይልቅ በሚያምኑባቸው ነገሮች በመዋለል በጥርጣሬ የተሞሉ ሆነው አግኝተሃቸዋልን? አብዛኞቹ ከተስፋ ይልቅ በፍርሃት የተዋጡና የወደፊቱ ጊዜ የማያስተማምን ሆኖባቸው አግኝተሃልን? ጆናታን ስዊፍት የተባሉት እንግሊዛዊ ባለ ቅኔ “እርስ በርሳችን እንድንፋቀር ሳይሆን እንድንጠላላ የሚያደርገን ሃይማኖት አለን” ብለው እንደገለጹት ሆነው አግኝተሃቸዋልን?
ጳውሎስ ስለዚህ አሉታዊ ክስተት አስቀድሞ ተናግሯል። “ጨካኞች ተኩላዎች” ማለት በስም ብቻ የክርስቲያን መሪዎች የሆኑ “ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ” ብሏል። (ሥራ 20:29, 30) ይህ ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ይደርስ ይሆን? የሚቀጥለው እትማችን ይህንን ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በውጪ ባሉ ሰዎች ዘንድ ክርስትና እንደ “መንገድ” ተደርጎ ይታይ ነበር። “ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ [በግምት ከ10 እስከ 20 ከሚሆኑ ዓመታት በኋላ] በአንጾኪያ [“በመለኮታዊ መሪነት” አዓት ] ክርስቲያን ተባሉ።”—ሥራ 9:2፤ 11:26
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን በሕያው አምላክ ላይ እምነት አለው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቲያን ተስፋ ተመልሳ የምትመጣውን ምድራዊ ገነት አሻግሮ ይመለከታል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቲያን ፍቅር ሌሎች ሰዎች አምላክን አንዲያገለግሉ በመርዳት ረገድ አድሎ አያደርግም