አገርዎ ዋነኛ ዒላማ ተደርጎ ይሆን?
ዩናይትድ ስቴትስ ከብራዚልና ከዚምባብዌ ትንባሆ በርካሽ ስለምትገዛ ከራስዋ ፍጆታ የሚተርፍ ብዙ ትንባሆ አላት። ታዲያ ቱጃሮቹ የትንባሆ አምራቾች ምርታቸውን የት ሊሸጡ ይችላሉ? በአፍሪካና በእስያ ለሚገኙ አገሮች ነዋ! በዚህም የተነሣ ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት “በአሁኑ ጊዜ ከአሜሪካ የባሕር ማዶ የትንባሆ ሽያጭ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሚሸምቱት የእስያ አገሮች ሲሆኑ ዋነኛ ሸማቾች የነበሩትን ብሪታንያንና ምዕራብ ጀርመንን ተክተዋል” ሲል ዘግቧል።
ከዚህም በላይ የወደፊቱ ሁኔታ የትንባሆ ነጋዴዎች ከፍተኛ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ነው። በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ሁለት ቢልዮን ሕዝብ የሚደርስ ትልቅ ገበያ ይጠብቃቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የቻይናና የሕንድ ሕዝቦች ብዛት ብቻውን 1.8 ቢልዮን ደርሷል! ወርልድ ኸልዝ እንደገለጸው “በምዕራቡ ዓለም የትንባሆ አጫሾች ቁጥር በየዓመቱ አንድ በመቶ እየቀነሰ ቢሄድም በማደግ ላይ ባሉ አዳጊ አገሮች ግን በአማካይ በየዓመቱ ሁለት በመቶ እያደገ ይገኛል።” በተጨማሪም እየቀነሰ የሄደው የምዕራቡ ዓለም ገበያ የሚያቅፋቸው ሰዎች ብዛት በምሥራቅ እየተከፈተ ባለው ገበያ ከሚኖሩት ሰዎች በጣም ያነሰ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የዩናይትድ ስቴትስ የትንባሆ ኢንዱስትሪ የእስያ ሽያጭ እስከ 2000 ዓመት ድረስ በ18 በመቶ እንደሚያድግ ይጠብቃል። ይሁን እንጂ ለዚህ እድገት ቢያንስ አንድ እንቅፋት አለ። እሱም መንግሥታት የሚጥሉት ቀረጥ ነው።
በሽታና ሞት በማስፋፋት ረገድ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሁለት ዓይነት አሠራር
የአሜሪካ የትንባሆ ኩባንያዎች ከአገራቸው ፍጆታ በላይ የሆኑትን ትርፍ ምርቶች ሌሎች አገሮች እንዲቀበሉ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? የራሱን አገር ሕዝቦች ማጨስ አደገኛ መሆኑን እያስጠነቀቀ በሌሎች አገሮች ግን ሕይወት ቀሳፊ የሆነው ትንባሆ እንዲሸጥ የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ አጋር አግኝተዋል። ይህ አጋር ማን ነው? የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ነዋ!
ኤዥያዊክ እንደሚከተለው በማለት ያብራራል:- “በጣም ግዙፍ የሆነው የትንባሆ ላኪዎች ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍና ኃይል ከበስተጀርባው አድርጎ ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው። . . . የዩናይትድ ስቴትስ ንግድ ተወካይ ቢሮ . . . የንግድ መሰናክሎችን ሰባብሮ ለመጣል ተነስቷል። በተጨማሪም የሲጋራ ማስታወቂያዎች ከዩናይትድ ስቴትስ የአየር ስርጭት ፈጽሞ እንዲወገዱ ከተደረገ ብዙ ጊዜ ያለፈ ቢሆንም የአሜሪካ ኩባንያዎች በእስያ መገናኛ ብዙሐን ሊጠቀሙ የሚችሉበትን መንገድ ለመክፈት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።” ወርልድ ኸልዝ መጽሔት “የዩናይትድ ስቴትስ የትንባሆ ኩባንያዎች በቀላሉ የማይገመት ፖለቲካዊ ተደማጭነት አላቸው። ሆንግ ኮንግ፣ ታይዋን፣ ጃፓንና ኮሪያ ገበያቸውንና በራቸውን ለአሜሪካ የትንባሆ ውጤቶችና ማስታወቂያዎች ካልከፈቱ የንግድ ማዕቀብ እንደሚደረግባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።”
የትንባሆ ኩባንያዎቹ ምርታቸውን በእስያ በመሸጥ ብቻ ሳይወሰኑ በጣም ኃይለኛ በሆኑ ማስታወቂያዎች አማካኝነት የሽያጫቸውን መጠን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። እንደ ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ ያሉት አገሮች በደረሰባቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ምክንያት በትንባሆ ማስታወቂያዎች ላይ የጣሉትን እገዳ አንስተዋል! በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ ሲጋራ አምራቾች ዋነኛ ዒላማ የሆነችው ቻይና ነች። የአንድ ትንባሆ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ “ምን እንደምንፈልግ ታውቃላችሁ? መላዋን እስያ እጃችን ውስጥ ለማስገባት ነው” ማለታቸው እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን እነዚህን የአሜሪካ ታክቲኮች እንዴት ይመለከቷቸዋል?
የኒውዮርክ ታይምስ ወኪል እንዳለው አንድ የኮሪያ ነጋዴ “አሜሪካ የራስዋን ሲጋራዎች የኮሪያ ሕዝብ እንዲገዛ የምታደርገው ጥረት ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት መሆኑን በመግለጽ አምርሮ ዘልፏል።” ለዚህም አባባሉ በቂ ምክንያት አለው። አሜሪካ ለአንዳንድ አገሮች የኢኮኖሚ መሠረት የሆኑት ኮኬንና ሄሮይን ወደ አገርዋ እንዳይገቡ አጥብቃ እየተከላከለች የራስዋን መርዘኛ ተክል በሌሎች አገሮች ላይ ለማራገፍ ትፈልጋለች። አሜሪካ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም ያለኝ አገር ነኝ እያለች አደገኛ የሆኑትን የትንባሆ ምርቶችዋን በአብዛኛው በከባድ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ያሉት አገሮች እንዲገዙዋት መደለልዋ ተገቢ ነውን?
አንዳንድ አገሮች ለመከላከል ያደረጉት ሙከራ
እንደ ጋምቢያ፣ ሞዛምቢክና ሴኔጋል ያሉት አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሲጋራ ማስታወቂያዎችን አግደዋል። የናይጄሪያ መንግሥት “በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በሰሌዳዎች ላይ የሚወጡትን ማስታወቂያዎች ሊያግድ ነው። በሁሉም የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችና መጓጓዣዎች ሲጋራ እንዳይጨስ እንከለክላለን” ሲሉ በ1988 የናይጄሪያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ገልጸው ነበር። ይህ ጉዳይ (እስከ ጥር 1989 ድረስ) ገና እልባት ሳያገኝ ክርክር እየተደረገበት እንደነበረ አንድ የናይጄሪያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለንቁ! ዘጋቢ አስታውቀዋል።
ቻይና 240 ሚልዮን አጫሾች ያሉባት አገር ነች። የሕክምና ባለ ሥልጣኖች 2025 ከመድረሱ በፊት በየዓመቱ ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ትንባሆ ከማጨስ ጋር ዝምድና ባላቸው በሽታዎች እንደሚሞቱ ገምተዋል። ቻይና ሪኮንስትራክትስ የተባለው መጽሔት እንዳረጋገጠው ቻይና ከባድ ችግር ተደቅኖባታል። “የቻይና መንግሥት የትንባሆ ማስታወቂያዎችን ያገደ፣ ማጨስ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶች የሚያስጠነቅቁ ዘገባዎች በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በተደጋጋሚ የወጡና የሲጋራ ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ የወጣ ቢሆንም በቻይና የአጫሾች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።” ታዲያ በዚህ ምክንያት እንዴት ያሉ ጉዳቶች ደርሰዋል? “በአሁኑ ጊዜ በቻይና ካንሰር፣ የልብና የደም ዝውውር በሽታዎች፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ዋነኞቹ የሞት ምክንያቶች ሆነዋል።”
በአንዳንዶቹ የቻይና አካባቢዎች እንግዳ ሲመጣ ሲጋራ መስጠት እንደ ጥሩ መስተንግዶ ይቆጠራል። ይሁን እንጂ ቻይናውያን ለዚህ የሚከፍሉት ዋጋ ምን ያህል ከፍተኛ ነው! ቻይና ሪኮንስትራክትስ እንደዘገበው “የሳንባ ካንሰር በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን በመጨመር ላይ እንዳለ የሕክምና ጠበብት አስጠንቅቀዋል።” አንድ የቻይና የሕክምና ጠበብት “ከፍተኛ ዋጋ እየከፈልን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የትንባሆ አስተዋዋቂዎች የሚጠቀሙበት ሌላ አደገኛ መሣሪያ አላቸው። እርሱም በመገናኛ ብዙሐን ላይ ያላቸው ስውር ተጽዕኖ ነው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲጋራ ማጨስን የሚቃወም የሆንግ ኮንግ ማስታወቂያ