የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 23:- ከ1945 ወዲህ ብድራቷን የምትቀበልበት ጊዜ ቀርቧል
“ሕዝቦች ደስታ እንዲያገኙ ከተፈለገ መስተካከል ከሚኖርባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የመጀመሪያው ሃይማኖትን ማጥፋት ነው።”
ካርል ማርክስ፣ የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ የኅብረተሰብና የኢኮኖሚ ጥናት ተመራማሪ
ካርል ማርክስ በእናቱም ሆነ በአባቱ በኩል በርካታ አይሁዳውያን ረቢዎች የሆኑ ቅድመ አያቶች ቢኖሩትም በስድስት ዓመቱ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት አባል ሆኖ ተጠመቀ። ይሁን እንጂ በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ቅር የተሰኘው ገና በልጅነቱ ነበር። የሰው ልጅ ደስታ እንዲያገኝ ከተፈለገ በሁለቱም ላይ ሥር ነቀል ለውጥ መካሄድ አለበት ብሎ ይከራከር ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስም ከዚህ ጋር ይስማማል። ይሁን እንጂ ማርክስ የተናገረለት ሥር ነቀል ለውጥ ምንም ዓይነት የተሻለ ሁኔታ ያላመጣ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ በእኛ ትውልድ እንደሚደርስ የተነበየለት ለውጥ ግን ዘላቂ የሆነ የተሳካ ውጤት ያስገኛል። በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖረን አይችልም።
በተለይ ከ1914 ወዲህ የሐሰት ሃይማኖት የደም ዕዳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሐሰት ሃይማኖት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ በሄደ የግድየለሽነት መንፈስና በሕዝባዊ ድጋፍ ማጣት ተወጥሯል። (በዚሁ ተከታታይ ርዕስ ሥር ባለፉት ሁለት እትሞች የወጡትን ጽሑፎች ተመልከት።) በአንጻሩ ግን እውነተኛው ሃይማኖት ከዓመት ወደ ዓመት እያበበና ይበልጥ እየተስፋፋ መጥቷል።
ይሁንና ወደፊትስ? ካለፈው ታሪኩ አንጻር የሃይማኖት የወደፊት ዕጣ ምን ይሆናል? ብሎ መጠየቅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ተገቢ ሆኗል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ሁኔታዎች ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጡን ፍንጭ አለ። እስራኤል የሐሰት ሃይማኖት ተከታይ በመሆኗ ምክንያት የአምላክ የቅጣት ፍርድ እንደሚወርድባት ተተነበየ። በእውነተኛው ሃይማኖት የሚመላለሱ ሰዎች ግን ከአይሁዳውያን ሥርዓት ጋር ከመጥፋት የሚድኑበት ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ” ብሎ ነበር።—ሉቃስ 21:20, 21
በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ። ከተማይቱ ወዲያው የምትወድም መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ ሠራዊቱ በድንገት ሳይታሰብ ወደ ኋላ በማፈግፈጉ ክርስቲያኖች ለመሸሽ የሚያስችላቸው አጋጣሚ አገኙ። ይሁን እንጂ ሮማውያን ከአራት ዓመት በኋላ ተመልሰው ከተማዋን ከከበቡና በውስጧ የነበሩትን ሰዎች በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከጨፈጨፉ በኋላ ግን ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ከመጣባት ቅጣት ድናለች የሚለው አስተሳሰብ ከንቱ ሆነ። ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ ማሳዳ የተባለው የአይሁድ የመጨረሻ ምሽግ በሮማውያን እጅ ወደቀ። ታማኝ ክርስቲያኖች ይከተሉት የነበረው እውነተኛ ሃይማኖት ግን ከጥፋት ተርፏል።
ዛሬም በዚህ በእኛ ትውልድ መላው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከታላቅ ጥፋት ጋር ፊት ለፊት ተፋጧል። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ መለኮታዊ ፍርድ ሊያወርድ በመዘጋጀት ላይ የሚገኝ “ጭፍራ” አለ። የዛሬው ወራሪ ጭፍራ ፓክስ ሮማናን (የሮማን ሰላም) እንዲያስከብር እንደተቋቋመው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማውያን ሠራዊት ሰላም እንዲያስጠብቅ የተቋቋመ ነው። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ብሔራት የሚውጣጡ ወታደራዊ ኃይሎች ዘመናዊት ኢየሩሳሌም በሆነችው በሕዝበ ክርስትናና የቀረው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል በመጨረሻ ብድራታቸውን እንዲቀበሉ በማድረግ የይሖዋ መሣሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያመለክታል።—ራእይ 17:7, 16
ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? አንደኛ ተሰሎንቄ 5:3 እንደሚከተለው በማለት ይመልስልናል:- “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።”
“የሰላም ወረርሽኝ”
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ጆርጅ ሹልዝ በ1988 “ሰላም በሁሉ ቦታ እየሰፈነ ነው” ብለው ነበር። አንድ የውጭ ግንኙነት ጠቢብ “የሰላም ወረርሽኝ” በመስፋፋት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ዲ ሳይት የተባለ የጀርመን ሳምንታዊ ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት ጠይቋል:- “በብዙ እልቂቶች ሲታመስ የኖረው ይህ መቶ ዘመን በመጨረሻዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ መጠፋፋት ተወግዶ፣ ሰላማዊ ግንባታ የሚጀምርበትን ዘመን ይመለከት ይሆን?” ታይም መጽሔት ደግሞ “በኢራን እና ኢራቅ፣ በካምቦዲያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በደቡብ አፍሪካና በማዕከላዊ አሜሪካ ሳይቀር የሰላም ፍንጭ እየታየ ነው” ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ ስለ ሰላም ብዙ ይነገራል። በየካቲት ወር 1989 ዙድዶቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከ1985 ወዲህ ልዕለ ኃያላን መንግሥታት አደብ ገዝተው ከመቀመጥ የበለጠ ነገር በሚያደርጉበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን። . . . በዛሬው ጊዜ ሁለቱ ልዕለ ኃያላን መንግሥታት ወደ እርቅና ስምምነት ያልተጠጋጉበት የምድር ክፍል አይገኝም። . . . ያም ሆነ ይህ ከአሁኑ ይበልጥ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ የሚጠቁሙ ምልክቶች የታዩበት፣ ሁለቱም ወገኖች ቁርጠኛ አቋም የወሰዱበትና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚመሩ ብዙ እርምጃዎች የተወሰዱበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም።”
ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህን የሚመስል ብሩሕ ሁኔታ አይታይም ነበር። ጆይ ላርሰን የተባሉ ጋዜጠኛ “በ1983 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ‘ሰላም፣ ሰላም’ እያሉ ይጮሁ ነበር። ሰላም ግን አልነበረም” ብለዋል። ታዲያ ከዚያ ወዲህ የሚታዩት አስደናቂ የሆኑ የዓለም ሁኔታዎች በ1 ተሰሎንቄ 5:3 መሠረት የተፈጸሙ ናቸውን? በእርግጠኝነት ለመናገር አንችልም። ቢሆንም ዛሬ፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ “ሰላምና ደህንነት” ወደሚባልበት ዘመን እንደተቃረብን ግልጽ ነው።
የሃይማኖት መሪዎች የሚሯሯጡት ምን ለማምጣት ነው?
ላርሰን እንዳመለከቱት የሃይማኖት መሪዎች ሰላምን ከመከታተል ወደ ኋላ አላሉም። በ1983 በተደረገው የሰላም ጥረት ላይ ያደረጉትን ግምገማ በመቀጠል ጆን ፖል ዳግማዊ በማዕከላዊ አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች ስላደረጉት “የሰላም ጉዞ” ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም በዚያው ዓመት የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ብሔራዊ ጉባኤ “የሰላም ፈተና” የተባለ ግልጽ ደብዳቤ አጽድቋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከ100 አገሮች የተውጣጡ ከ300 የሚበልጡ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ስድስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ውሳኔ አጽድቀዋል። በተጨማሪም ብዙ የፕሮቴስታንት ወንጌላውያን ላርሰን “ዓለም አቀፍ የሰላም ጥረት” ብለው በጠሩት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል።
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በተመሠረተበት ዓመት በ1948 እና በ1966 ባካሄደው ጉባኤ ዘመናዊ የሆኑ አጥፊ መሣሪያዎችን መጠቀምን የሚቃወም ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ መሠረት ሄልሙት ጎልቪዘር የተባሉትን ጀርመናዊ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪ የመሰሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ቀሳውስትና የሃይማኖት ምሁራን ለሰላም ክንዳቸውን አንስተዋል። የእኚህ ሰው 80ኛ የልደት በዓል በተከበረበት ጊዜ አንድ የስዊስ ፕሮቴስታንት ሳምንታዊ ጋዜጣ “ሁልጊዜ ለሰላም የሚጣጣሩና በፖለቲካ ጉዳዮች የሚሳተፉ የሃይማኖት ሰው፣ በትምህርታቸውና በፖለቲካ ቆራጥነታቸው በብዙ ሃይማኖታዊ ምሁራንና ለሰላም በሚደረገው የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደሩ ሰው ናቸው” በማለት አወድሷቸዋል።
በዚህ ምክንያት ታላቂቱ ባቢሎን በቻርተሩ “ዓለም አቀፍ ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ” ኃላፊነት የተጣለበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ዓመት ብሎ ለሰየመው ለ1986 ከፍተኛ ድጋፍ መስጠቷ ያልተጠበቀ ነገር አልሆነም። በዚህ ዓመት የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳሳት፣ የአንግሊካኑ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ፣ እንዲሁም ክርስቲያን ነን ባዮችን፣ ቡድሂስቶችን፣ ሂንዱዎችን፣ ሙስሊሞችን፣ አፍሪካውያን የባሕላዊ እምነት ተከታዮችን፣ የአሜሪካ ሕንዶችን፣ አይሁዶችን፣ ሲኮችን፣ ዞሮአስትራውያንን፣ ሺንቶዎችንና ጄይኖችን ጨምሮ 700 የሚያክሉ ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ሮም አቅራቢያ በምትገኘው በአሲሲ ተሰብስበው ስለ ሰላም ጸልየዋል።
በጥር ወር 1989 ደግሞ በአውስትራሊያ ሲድኒ ሰንደይ ቴሌግራፍ እንደጻፈው “የቡድሂስት እምነት፣ የክርስትና፣ የሂንዱ፣ የአይሁድ፣ የሙስሊም፣ የሲክ፣ የዩኒተርያን፣ የባሃኢ፣ የኮንፍሽያን፣ የጄይን፣ የሺንቶ፣ የታኦ፣ የራጃ ዮጋ እና የዞሮአስትራውያን ሃይማኖት አባሎች” በሜልቦርን ለአምስተኛው የዓለም ሃይማኖቶች እና የሰላም ጉባኤ ተሰብስበዋል። “ከ85 አገሮች የተውጣጡት ከ600 የሚበልጡ ተወካዮች . . . በሃይማኖታዊ ልዩነቶች ምክንያት የሚፈጠሩ ውጥረቶች ዋነኞቹ የጦርነት ምክንያቶች ሆነው መቆየታቸውን ማመናቸው” ትኩረት የሚስብ ነው።
ሃይማኖት ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ መሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ዳግ ሐመርሾልድ በአንድ ወቅት የተናገሩትን ያረጋግጣል:- “በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የእምነትና የአምልኮ ልዩነት ሳያግዳቸው በመላው ምድር ሰላም ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አብያተ ክርስቲያናት ተሳታፊዎች በመሆን ተባብረው ይሠራሉ።”
ይሁን እንጂ ታላቂቱ ባቢሎን በምታደርጋቸው የተቃውሞ ሰልፎች፣ ትዕይንተ ሕዝቦችና በሌሎች ረቂቅ መንገዶች የምትፈጽመው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በመጨረሻ ለጥፋትዋ ምክንያት ይሆናል።a አሁንም እንኳን ቢሆን የዶሚኒካን መነኩሴ የሆኑት አልበርት ኖላን ከደቡብ አፍሪካ እንደተናገሩት ይህ ጉዳይ በቀላሉ የማይገመት ግጭት አስከትሏል። “ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሰላም ለማግኘት የሚያስችለው ብቸኛ መንገድ በውጊያው ውስጥ መግባት ነው። . . . የጦር መሣሪያ ቅነሳ ለማድረግ ከተፈለገ ከመንግሥት ጋር መጋጨት የማይቀር ነገር ነው።”
ታላቂቱ ባቢሎን ለሰላም የምታደርገውን ጩኸት ትቀጥል። ሊቀ ጳጳሱም በገናና በፋሲካ በዓላት የተለመደውን የኡርቢ ኤ ት ኦርቢ (ለሮማ ከተማና ለመላው ዓለም) ቃለ ቡራኬ ማሰማት ይቀጥሉ። እርሳቸው በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የፖለቲካ ውጥረቶች መርገብ አምላክ “ለክርስቲያኖች” ጸሎት የሰጠው ምላሽ ነው ብለው ማመናቸውን ይቀጥሉ። ታላቂቱ ባቢሎን የሰላም ቃላትን መናገሯና የአምላክ በረከት አለኝ ማለትዋ በዘመናት በሙሉ ከተጨማለቀችበት የደም ዕዳ ሊያጠራት አይችልም። በሰዎች መካከል፣ እንዲሁም በአምላክና በሰዎች መካከል ሰላም እንዳይኖር ዋነኛ እንቅፋት ሆና መኖሯን ይመሰክርባታል። እስካሁን ድረስ በመላው የሰው ዘር ላይ የደረሱት ችግሮች በሙሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመነጩት ከእርስዋ ነው!
የሐሰት ሃይማኖት ለራስዋ ጥፋት መቅድም የሚሆነውን “ሰላምና ደህንነት” ለማምጣት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ተቀናጅታ ጥረት ማድረግ መቀጠሏ በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው! የሐሰት ሃይማኖት ፍጻሜ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ሲል የተናገረውን የእውነተኛው ሃይማኖት አምላክ ትክክለኛነት የሚያረጋገጥ ይሆናል።—ገላትያ 6:7
ጊዜ ሳታባክን በፍጥነት ሸሽተህ ሕይወትህን አድን
የሐሰት ሃይማኖት ብድራቷን የምታገኝበት ጊዜ ቀርቧል! ሕይወት ለማዳን የሚያስችለው ብቸኛ መንገድ አለምንም ማመንታት እርሷን ጥሎ መውጣት ነው። (ራእይ 18:4) ወደ ጥፋትዋ የሚያደርሰው የመጨረሻ ቆጠራ ተጀምሯል።
የአምላክ ንብረት የሆነችው ውብ ምድር ከማንኛውም አስመሳይ ሃይማኖትና ሃይማኖታዊ ሽፋን ካለው ብሔረተኝነት ከጸዳች በኋላ በመለኮታዊ አገዛዝ የሚተዳደር እውነተኛ ሃይማኖት ብቻ ይኖራል። ከእነዚህ ሥር ነቀል ለውጦች ተርፈው በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ያለ አስደናቂ ሕይወት ይጠብቃቸዋል! ከእነዚህ ሰዎች መካከል ትገኝ ይሆን? “እውነተኛው ሃይማኖት ባለው ዘላለማዊ ውበት” ለዘላለም ለመደሰት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ይህን ተስፋ እንዴት ልታገኝ እንደምትችል ለማወቅ የዚህን ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻ ክፍል በሚቀጥለው የንቁ! እትም በማንበብ ተረዳ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሰላምና ደህንነት የሚደረገው ጥረት
አብዛኞቹ ሰዎች ሰላምና የተረጋጋ ሕይወት አግኝተው የመኖር የተፈጥሮ ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት በሰው ልጅ ታሪክ ዘመናት በሙሉ በአብዛኛው ሳይሟላ ቆይቷል። የሚከተለው ዝርዝር እንደሚያመለክተው የሰው ልጅ ሰላም ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት አንዳንድ አስደናቂ ውጤቶች ተገኝተዋል።
1985:- (ጥቅምት) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 40ኛ የልደት በዓሉን አክብሮ 1986 የሰላም ዓመት እንዲሆን ወሰነ።
(ኅዳር) በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የልዕለ ኃያላን መንግሥታት መሪዎች ስብሰባ ተደርጎ ጎርባቾቭና ሬገን ያደረጉትን ስብሰባ ሬገን “አዲስ ጅምር” ሲሉ አወደሱ።
1986:- ጎርባቾቭ በ2000 ዓመት የኑክሊየር መሣሪያዎች በሙሉ እንዲታገዱ ጥሪ አደረጉ።
(መስከረም) በአውሮፓ መተማመንና ደህንነት ስለማስፈን እንዲሁም የጦር መሣሪያ ለመቀነስ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች የሚነጋገር ጉባኤ ተካሂዶ (ዩናይትድ ስቴትስን፣ ካናዳንና ሶቪዬት ኅብረትን ጨምሮ፣ ከአልባኒያ በስተቀር የአውሮፓ አገሮች በሙሉ፣ በጠቅላላው 35 አገሮች) ድንገተኛ ጦርነት እንዳይነሳ የሚከላከል ስምምነት ፈረሙ።
(ጥቅምት) ሬገንና ጎርባቾቭ በአይስላንድ ያደረጉት የመሪዎች ስብሰባ ውጤት ሳያስገኝ የቀረ ቢሆንም ጎርባቾቭ “አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍቱ ታላላቅ ውሳኔዎች” ለማድረግ ተቃርበው እንደነበረ ተናገሩ።
1987:- (ጥር) የግላስኖስት ፖሊሲ (ግልጽነት) በሶቪዬት ኅብረት አዲስ ዓይነት ሥርዓት ሊጀመር የተቃረበ መሆኑን ጠቆመ።
(መጋቢት) የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር በ12 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮን ጎበኙ።
(ታኅሣሥ) ጎርባቾቭና ሬገን ባለ መካከለኛ ርቀት የኑክሊየር ሚሳይሎችን ለማስወገድ ስምምነት ፈረሙ።
1988:- (መጋቢት) ኒካራጉዋና ፀረ ኮምኒስት የሆኑት ኮንትራዎች የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመው ዘላቂ የሆነ እርቅ ላይ ለመድረስ ድርድር ጀመሩ።
(ሚያዝያ) ሶቭዬት ኅብረት ወታደሮችዋን እስከ የካቲት 1989 ከአፍጋኒስታን እንደምታስወጣ አስታወቀች፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ግጭታቸውን ለማቆም ተስማሙ።
(ግንቦት) ቪዬትናም 50,000 የሚያክሉ ወታደሮችዋን እስከ ዓመቱ መጨረሻ፣ የቀሩትን ደግሞ እስከ 1990 ድረስ ከካምፑቺያ እንደምታስወጣ አስታወቀች።
(ሰኔ) የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቦብ ሆክ ጎርባቾቭና ሬገን በሞስኮ ስላደረጉት ስብሰባ ሲናገሩ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም እርስ በርስዋ ተስማምታ ለመኖር እንደምትችል የሚያሳይ ጭላንጭል ታየ” ብለዋል።
(ሐምሌ) ኢራን በእርሷና በኢራቅ መካከል ለስምንት ዓመት የቆየው ጦርነት እንዲቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደምትቀበል አስታወቀች።
(ነሐሴ) ዩናይትድ ስቴትስ አግዳ የቆየችውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምትሰጠውን መዋጮ ለመክፈል ተስማማች። ሶቭየቶች ቀደም ሲሉ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው ነበር። ይህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከገባበት የገንዘብ ችግር እንዲወጣና አዲስ አቅምና ችሎታ እንዲያገኝ አስቻለ።
(መስከረም) ሞሮኮና የፖሊሳርዮ ደፈጣ ተዋጊዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምዕራብ ሰሃራ ለ13 ዓመታት የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ያወጣውን እቅድ ተቀበሉ።
(ጥቅምት) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስጠባቂ ጦር የኖቤልን የሰላም ሽልማት አገኘ፤ ሊቢያና ቻድ ለብዙ ዓመታት በመካከላቸው የቆየውን ጦርነት ማቆማቸውን በይፋ አስታወቁ።
(ታኅሣሥ) ጎርባቾቭ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሶቭየት የጦር ኃይል ላይ ከፍተኛ ቅነሳ ለማድረግ የተናጠል እርምጃ እንደሚወስዱ እንዲሁም ጦራቸውና ታንኮቻቸው ከቼኮዝሎቫኪያ፣ ከሃንጋሪና ከጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ እንደሚወጡ አስታወቁ። ደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያና ኩባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሚያዝያ 1, 1989 ያወጣውን ውሳኔ ሥራ ላይ ለማዋል በመስማማታቸው ለ22 ዓመታት የቆየው ጦርነት አቁሞ ናሚቢያ ነፃነቷን አገኘች። እስከ ኅዳር 1 ድረስ በአንጎላ ሰፍረው ከነበሩት 50,000 የኩባ ወታደሮች መካከል ግማሽ የሚያክሉት እንደሚወጡና የቀሩት ደግሞ እስከ ሐምሌ 1, 1991 ድረስ እንደሚወጡ ስምምነት ላይ ተደረሰ። ያሲር አራፋት የእስራኤልን “በሰላምና በፀጥታ የመኖር” መብት እንደሚቀበሉ ከተናገሩ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት ጋር ለመነጋገር ተስማማች።
1989:- (ጥር) በፓሪስ የኬሚካል ጦር መሣሪያዎችን አስመልክቶ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙት 149 አገሮች የኬሚካል መሣሪያዎች እንዳይፈለሰፉ፣ እንዳይመረቱ፣ እንዳይከማቹና ሥራ ላይ እንዳይውሉ የሚያግድ ውሳኔ አስተላለፉ።
(የካቲት) ኮስታ ሪካ፣ ሆንዱራስ፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ኒካራጉዋና ጓቲማላ በማዕከላዊ አሜሪካ ሰላም እንዲገኝ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። ከኮሎምቢያ አማጽያን ቡድኖች መካከል ትልቁ የሆነው ኤፍ ኤ አር ሲ (የኮሎምቢያ አብዮታዊ ሠራዊት) የተኩስ አቁም ውሳኔ ማድረጉን በማስታወቁ ለ35 ዓመታት የቆየው የሽምቅ ውጊያ ወደ ፍጻሜ እንደሚመጣ የነበረው ተስፋ ከፍ አለ።
(መጋቢት) ከ35 አገሮች የተውጣጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአውሮፓ ያሉትን ወታደራዊ ኃይሎች ለመቀነስ የሚያስችል ምክክር በቪዬና ማድረግ ጀመሩ።
(ሚያዝያ) ቪዬትናም እስከ መስከረም 30 ወታደሮችዋን ከካምፑቺያ ሙሉ በሙሉ እንደምታስወጣ አስታወቀች።
(ግንቦት) ሃንጋሪ በኦስትርያ ድንበር ላይ የሠራችውን ለ40 ዓመታት የቆየ የሽቦ አጥር ማፍረስ ጀመረች። በ30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የሶቭዬትና የቻይና መሪዎች ስብሰባ ላይ ሶቭዬቶች በእስያ ያላቸውን የጦር ኃይል እንደሚቀንሱ አስታወቁ። ሶቭዬቶች በምሥራቅ አውሮፓ የነበሯቸውን ወታደሮችና የጦር መሣሪያዎች ለመመለስ የተናጠል እርምጃ መውሰድ ጀመሩ።
(ሰኔ) ቡሽ እስከ 1992 ድረስ በአውሮፓ ያሉት ወታደሮች፣ ታንኮች፣ መድፎችና የጦር አውሮፕላኖች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀነሱ ጥሪ በማድረጋቸው አንድ የዜና መጽሔት “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ ለማይታወቅና ከፍተኛ ለሆነ የጦር መሣሪያ ቅነሳ በር ከፋች ሊሆን ይችላል” አለ።
(ነሐሴ) አምስት የማዕከላዊ አሜሪካ አገሮች በኒካራጉዋ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም በሚያስችል እቅድ ላይ ተስማሙ።
እነዚህን የመሰሉ ትላልቅ ድሎች ቢገኙም በርካታ የሆኑ አገሮች ገና ሰላም አላገኙም። ጥቂቶቹን ብቻ ብንጠቅስ እንኳን በሰሜን አየርላንድ፣ በሊባኖስ፣ በሱዳን፣ በስሪላንካና በአፍጋኒስታን በጦርነት ምክንያት በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች ሰላም ይመጣል የሚል ብሩህ አመለካከት ቢኖራቸውም ሁለተኛው የራእይ ፈረስ ጋላቢ ማለትም ጦርነትን የሚያመለክተው ‘ቀይ ፈረስ’ በመላው ምድር ላይ እየጋለበ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።—ራእይ 6:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1988 የታተመው ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለው መጽሐፍ ይህ እንዴት እንደሚከናወን ማብራሪያ ይሰጣል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኒው ዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤትና የዓለም የሰላም ሐውልት—ሰውየው ሠይፉን ማረሻ ለማድረግ ሲቀጠቅጥ