የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 24:- አሁንም ሆነ ለዘላለም የእውነተኛ ሃይማኖት ዘላለማዊ ጌጦች
“ሃይማኖት መለኮታዊ እውነቶችን ከተጎናጸፈ ገና ሲታይ ይማርካል።”—የ18ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ባለ ቅኔ ዊልያም ካውፐር
የሐሰት ሃይማኖት ለአድናቆት የሚያበቃ አንዳች ነገር የለውም። በሰው ልጆች ላይ የ60 መቶ ዓመታት መከራና ሥቃይ አምጥቷል። ውሸቱ፣ አታላይነቱ፣ አጭበርባሪነቱና ጥላቻ የሞላበት መሆኑ በአምላክና በሰዎች ዓይን አስቀያሚ ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል። የሐሰት ሃይማኖት መለኮታዊ እውነቶችን መጎናጸፉ ቀርቶ የእውነትና የውበት ተጻራሪ ሆኗል።
በቅርቡ የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ሠራዊት የሐሰት ሃይማኖትን ዘላለማዊ ወደ ሆነ የጥፋት አዘቅት አሽቀንጥሮ ይጥላል። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ መላው የሰይጣን ሥርዓት ይወድማል። እውነተኛ ሃይማኖትና የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች ግን በሕይወት መኖራቸውን ይቀጥላሉ። የእውነተኛ ሃይማኖት ዘላለማዊ ጌጦች ዛሬ ልንገምት እንኳን በማንችለው መጠን በዚያን ጊዜ ሲንጸባረቁ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነገር ይሆናል!
ጌጦቹ ምንድን ናቸው?
የእውነተኛ ሃይማኖት ጌጦች ብዙ ሲሆኑ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ግን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አውጥታችሁ እያነበባችሁ እነዚህ ዘላለማዊው ጌጦች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ራሳችሁ ለምን አታረጋግጡም?
እውነተኛ ሃይማኖት ካሉት ብዙ ዘላለማዊ ጌጦች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ:-
▪ ስሙ ይሖዋ በሆነውና ትምክህታችንን ሙሉ በሙሉ ልንጥልበት በምንችለው የማይሳሳተው አምላክ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው።—መዝሙር 83:18 NW፤ ኢሳይያስ 55:10, 11
▪ ልዩ የሆነ የአእምሮ ችሎታ ላላቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ትሁት ልብ ያለው ማንኛውም ሰው ሊያገኘው የሚችል ነው።—ማቴዎስ 11:25፤ 1 ቆሮንቶስ 1:26-28
▪ በዘር፣ በማኅበራዊ ኑሮና በኢኮኖሚ ደረጃ አድልዎ አያደርግም።—ሥራ 10:34, 35፤ 17:24-27
▪ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት፣ ሐዘን፣ በሽታ፣ ጭንቀትና ሞት የሌለበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የጸና መሠረት ያለው ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 32:18፤ ራእይ 21:3, 4
▪ አባሎቹ በመሠረተ ትምህርት፣ በምግባርና በመንፈስ ተሳስረው ዓለም አቀፋዊ በሆነ ወንድማማችነት እንዲኖሩ ያስችላል።—መዝሙር 133:1፤ ዮሐንስ 13:35
▪ እያንዳንዱ ሰው፣ ወንድም ሆነ ሴት ወይም ሕፃን አምላክ በሰጠን ሥራ በንቃት የሚሳተፍበትን አጋጣሚ በመስጠት ትርጉም ያለው ኑሮ እንዲኖር ያስችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ዕብራውያን 13:15, 16
▪ ጥቅም የሚያስገኝልንን የአኗኗር መንገድ በማሳየት ስውር ከሆኑ አደጋዎች እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል።—ምሳሌ 4:10-13፤ ኢሳይያስ 48:17, 18
እነዚህ ጌጦች ዘላለማዊ ናቸው ሊባል የሚችለውስ ለምንድን ነው? ባጭሩ እውነተኛ ሃይማኖት ዘላለማዊ ስለሆነ ነው።
ክፍተቱን መሙላት
ከእውነት ዋነኛ ጠላቶች አንዱ ሞት ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ሰዎች ሲሞቱ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች ፈጽሞ የማያውቋቸውን መረጃዎች እንደያዙ ወደ መቃብር ስለሚወርዱ ነው። በ1963 የደረሰውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የጆን ኤፍ ኬኔዲን አሟሟት የመሰሉትን በቅርብ ጊዜ የተፈጸሙ ሁኔታዎች እንኳን በእርግጠኝነት ማወቅ አልተቻለም። ትክክለኛው ሁኔታ እንዴት ነበር? ማን አስረግጦ ሊያውቅ ይችላል? በትክክል ሊያውቁ የሚችሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሉም። ከ35 ዓመት በፊት ስለተፈጸመ ጉዳይ በእርግጠኝነት ማወቅ ካልተቻለ በመቶዎች፣ እንዲያውም በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተፈጸሙ ሁኔታዎችን እንዴት ሙሉ በሙሉ ማወቅ ይቻላል?
ከዚህም በላይ ታሪክ ጸሐፊዎች ያላቸው እውቀት ውስን ከመሆኑ በተጨማሪ ጉድለታቸውንና መሠረተ ቢስ ጥላቻቸውን በሚጽፏቸው ታሪኮች ላይ የሚያንጸባርቁ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ናቸው። አንድ ምክንያታዊ አመለካከት ያለው ሰው እርግጠኛ የሆነ፣ በመለኮታዊ መሪነት የተጻፈ መረጃ ካልኖረው ስለማንኛውም ነገር ሐሳበ ግትር ወይም ቀኖናዊ ሆኖ መናገር የማይኖርበት በዚህ ምክንያት ነው።
ስለ ሃይማኖት ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜም ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል። ምክንያቱም ሊቃውንቱ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ስምምነት የላቸውም። ንቁ! “የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ—ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር በበቂ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ሐቅ ለማቅረብ ሞክሯል። ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ጊዜ በእርግጠኝነት የማናውቃቸው ነገሮች እንዳሉ እናምናለን። ለምሳሌ ያህል በጨለማው ዘመንና ከጨለማው ዘመን በኋላ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን ነን ባይ ቡድኖች እውነተኛ ክርስትናን ተከትለው የኖሩት እስከምን ድረስ ነው?
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤ ኤም ሬንዊክ ስለ እነዚህ ቡድኖች “የእነዚህን በርካታ ቡድኖች እውነተኛ ታሪክና ሃይማኖታዊ አቋም ይፋ ለማውጣት አሁንም ብዙ የታሪክ ምርምር ይጠይቃል” ብለዋል። ሬንዊክ እንደሚሉት “ባለፉት ዘመናት ታሪክ ጸሐፊዎች የአፈንጋጮቹን ቡድኖች መሠረተ ትምህርትና ሥነ ምግባር ሲመዝኑ ጠላቶቻቸው የሰጧቸውን ማስረጃዎች ከልክ በላይ ተከትለዋል።” ወዳጆቻቸው የሰጡትንም ማስረጃ ከልክ በላይ ቢከተሉ ኖሮ አመለካከታቸው ወደ አንድ ወገን ያዘመመ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ስለዚህ ብዙ የታሪክ ምርምር ከተደረገም በኋላ ቢሆን መልስ የማይገኝላቸው ጥያቄዎች መኖራቸው አይቀርም።
መጽሐፍ ቅዱስስ? አንዳንድ የሃይማኖት ታሪኮች የሰፈሩበት በመለኮታዊ አመራር የተጻፈ መጽሐፍ በመሆኑ በሚናገራቸው ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ ትምክህት መጣል ይቻላል። ይሁን እንጂ በዘመናት በሙሉ ስለተነሱ የተለያዩ የሐሰት ሃይማኖቶች ብዙ አይናገርም። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ምክንያቱም ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው ስለ እውነተኛ ሃይማኖት ለማስተማር እንጂ ስለ ሐሰት ሃይማኖት ለማስተማር አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነተኛ ሃይማኖት እንኳን ሁሉንም ነገር አይነግረንም። እውነተኛን ሃይማኖት በትክክል ለይተን ለማወቅ የሚያስችል በቂ የሆነ መረጃ ቢሰጠንም ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይገልጽ የሚያልፍባቸው ጊዜያት አሉ። እነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ለማወቅ የሚያጓጉ ቢሆኑም ለጊዜያችን የግድ የሚያስፈልጉን ነገሮች አይደሉም።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምንም መግለጫ ሳይሰጥ የሚዘልላቸው ዘመናት አሉ። ለምሳሌ ያህል በተለምዶ ብሉይ ኪዳን የሚባሉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው ባለቁበትና ኢየሱስ በተገለጠበት ዘመን መካከል ባሉት ከ400 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ምን ነገሮች እንደተከናወኑ አይነግረንም። መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ በኋላ ደግሞ 1,900 የሚያክሉ ዓመታት አልፈዋል።
ስለዚህ ከ18 መቶ ዓመታት ለሚበልጡ ዘመናት ስለ ክርስትና የሚገልጽ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ታሪክ አላገኘንም። ደራሲው ሬንዊክ በጠቀሷቸው ክርስቲያን ነን ባይ ቡድኖች ረገድ እርግጠኛ የሆነ ነገር መጨበጥ ያልተቻለው በዚህ ምክንያት ነው። ቢሆንም ባለፉት ዘመናት በሙሉ ቢያንስ ጥቂት ግለሰቦች የመጀመሪያውን ክርስትና ይከተሉ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በቀደሙት ዘመናት የተነሱ አንዳንድ ግለሰቦች ስለነበራቸው ዓላማና ሐቀኝነት መልስ ሊገኝላቸው የማይችሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም። ስለ አንዳንዶቹ የተሐድሶ መሪዎች ምን ለማለት ይቻላል? እንደ ኮንፍዩሺየስና መሐመድ ያሉት ግለሰቦችስ? በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሃይማኖቶች በሚያፈሯቸው ፍሬዎች መሠረት በትክክል መመዘን ቢቻልም ግለሰቦችን ግን፣ በተለይ ከሞቱ ብዙ ዘመን የሆናቸውን በትክክል መመዘን አይቻልም።
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ፣ የሃይማኖት ታሪክን ጨምሮ የታሪክ መጻሕፍት እንደገና እንዲጻፉ የፈጣሪ ፈቃድ ቢሆን ማወቅ ይቻላል። እንዲህ ማድረግ የሚቻለው አንደኛው የእውነተኛ ሃይማኖት ጌጥ በሆነው የሙታን የትንሣኤ ተስፋ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ያነበብናቸውን ነገሮች ያከናወኑትን ሰዎች በግንባር አግኝተን በማነጋገር ለጥያቄዎቻችን ትክክለኛ መልስ ማግኘት ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስቡ። በቀይ ባሕር ሰምጦ የሞተውና በግብጽ ላይ የወረዱትን መቅሰፍቶች የተመለከተው ፈርዖን ስም ማን እንደሆነና እነዚህን የመሰሉትን እስካሁን ያልታወቁ ዝርዝር መረጃዎች ለማግኘት መቻል ምን ያህል ያስደስት ይሆን።
ይህን የመሰለ የታሪክ መዝገብ የሚጻፍ ከሆነ፣ የሚጻፈው የእውነተኛ ሃይማኖት መስራች የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለማስከበርና ማንነቱን ለዘላለም ለማስመስከር ይሆናል። በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት ጥያቄ ሊኖር አይችልም። የሚኖረው ጥያቄ በሕይወት ኖረህ ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ትችል ይሆን? የሚል ነው።
አድናቆት ብቻ አይበቃም
የእውነተኛ ሃይማኖት ጌጦች በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው የካውፐር ቃል እንደሚያመለክተው ሁልጊዜ በቀላሉ ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም። በዚህ ምክንያት የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የመጀመሪያ እትም የዛሬ 119 ዓመት የሚከተለውን ብሏል:- “እውነት በሕይወት ምድረ በዳ ውስጥ እንደምትገኝ አነስተኛ አበባ እንደ ልባቸው ባደጉ የስህተት አረሞች ተውጣለች። ይህችን አበባ ካገኘህ እንዳትጠፋብህ ዘወትር መጠንቀቅ አለብህ። ውበቷን ለማየት ከቻልክ የስህተትን አረሞችና የሰብዓዊ አስተሳሰቦችን እሾህ መንጥረህ ማስወገድ አለብህ። ንብረትህ ልታደርጋት ከፈለግህ ጎንበስ ብለህ ማንሳት አለብህ።”
“የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ—ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ” የሚለው ተከታታይ ርዕስ አንባቢዎቻችን “የስህተትን አረሞችና የሰብዓዊ አስተሳሰቦችን እሾህ” እንዲያስወግዱና የእውነተኛን ሃይማኖት ዘላለማዊ ጌጦች በይበልጥ እንዲያደንቁ እንደረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን።
ይሁን እንጂ አድናቆት ብቻውን አይበቃም። “ወደ ጆሮ እንጂ ወደ ልብ ዘልቆ የማይገባ ትምህርት በሕልም እንደተበላ እንጀራ ነው” የሚል ጥሩ የቻይናውያን ተረት አለ። ስለ እውነተኛ ሃይማኖት ዘላለማዊ ጌጦች በግላችን ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ከማለም አልፈን ከእነዚህ ነገሮች የምንማራቸው ሁሉ ወደ ጆሮቻችን ዘልቀው በመግባት ልባችንን እንዲነኩ መፍቀድ ያስፈልገናል።
“ሃይማኖትህ እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ለይተህ ማወቅ” የሚለውን ሣጥን በጥንቃቄ አንብብ። ከዚያ በኋላ ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ። ‘በዓለም አቀፉ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ረገድ ቮልቴር፣ ሃይማኖት “የሰው ልጅ ጠላት ነው” ማለቱ ትክክል እንደሆነ እስማማለሁ? ይህ ስለ ሃይማኖት ታሪክ ያደረግኩት ጥናት እውነተኛ ሃይማኖትን ለይቼ እንዳውቅ ረድቶኛልን? በዚህ የሰው ልጆች ታሪክ መደምደሚያ በተቃረበበት ዘመን የት እንደሚገኝ አውቃለሁን? ከሆነስ ዦሴ ዡበ የተባለው የ18ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ ሐያሲ እንዳለው “እርሱን ተድላቸውና ግዴታቸው” ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል መሆን እፈልጋለሁ?’
ለእነዚህ ጥያቄዎች የአዎንታ መልስ የሚሰጡ ሁሉ ንቁ! መጽሔትንና ሌሎቹን ተጓዳኝ ጽሑፎች ማንበባቸውን ይቀጥሉ። ከላይ የጠቀስነው የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እትም የሰጠውን ጥሩ ምክር እንድትከተሉ እንጋብዛችኋለን። “አንድ የእውነት አበባ ብቻ በማግኘታችሁ አትርኩ። አንድ አበባ ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ሌሎች አበባዎች አይኖሩም ነበር። ሁልጊዜ ፈልጉ፣ ብዙ ለመሰብሰብ ጥረት አድርጉ።”
አዎን፣ መሰብሰባችሁን ቀጥሉ። የእውነተኛን ሃይማኖት ዘላለማዊ ጌጦች መፈለጋችሁን ቀጥሉ!
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃይማኖትህ እውነተኛ ወይም ሐሰተኛ መሆኑን ለይተህ እወቅ
▪ እውነተኛ ሃይማኖት በተከታዮቹ መካከል በብሔራዊ ድንበሮች የማይገደብ የፍቅርና የአንድነት ትስስር እንዲኖር ያደርጋል። (ዮሐንስ 13:35) ሐሰተኛ ሃይማኖት እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖር አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹ የቃየልን አርዓያ በመከተል በብሔራት መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች እርስ በርሳቸው ይገዳደላሉ።—1 ዮሐንስ 3:10-12
▪ እውነተኛ ሃይማኖት ከሰው ልጆች የፖለቲካ ጉዳዮች ነጻ ሆኖ ፈጣሪ ራሱ በንጉሣዊ መንግሥቱ አማካኝነት የዓለምን ችግሮች እንዲፈታ ይጠብቃል። የሐሰት ሃይማኖት ናምሩድ በባቤል ግንብ ያደረገውን ነገር ይከተላል። ራሱን ከፖለቲካ ጋር ያቆራኛል፣ በፖለቲካ አማልክት በመታመን በጉዳዮቻቸው እጁን ያስገባል፣ ይህንንም በማድረግ የገዛ ራሱን መጥፊያ ያዘጋጃል።—ዳንኤል 2:44፤ ዮሐንስ 18:36፤ ያዕቆብ 1:27
▪ እውነተኛ ሃይማኖት እውነተኛ አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነና ከጭቆናም ነጻ ሊያወጣ የሚችል እርሱ ብቻ እንደሆነ ይቀበላል። የሐሰት ሃይማኖት በጥንትዋ ግብጽና ግሪክ እንደነበሩት ሃይማኖቶች ምንም እርባና የሌላቸውና ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው የተረት አማልክት አሉት።—ኢሳይያስ 42:5፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6
▪ እውነተኛ ሃይማኖት ደስታ የሰፈነበት የዘላለም ሕይወት በምድር ላይ እንደሚገኝ ተስፋ ይሰጣል። እንደ ቡድሂዝም ያለው የሐሰት ሃይማኖት ምድራዊ ሕይወት ተፈላጊ እንዳልሆነና ከዚህ ሕይወት ነጻ ወጥቶ እርግጠኛ ወዳልሆነ ሌላ ሕይወት መሻገር አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4
▪ እውነተኛ ሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሰዎች የማይናወጥ እምነትና የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ ለአምላክና ለጎረቤቶቻቸው እውነተኛን ፍቅር በተግባር እንዲያሳዩ ያነሳሳል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የሐሰት ሃይማኖት የራሱ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢኖሩትም በአብዛኛው እነዚህን ባሕርያት ለማስፈጸም ችሎታ የለውም።—1 ዮሐንስ 5:3, 4
▪ እውነተኛ ሃይማኖት ትሁታን የሆኑ የበላይ ተመልካቾች አሉት። የሐሰት ሃይማኖት እውነቱን ለማጣመም ፈቃደኛ በሆኑና ፖለቲካዊ ወይም ዓለማዊ ረብ ለማግኘት በሚፈልጉ ሥልጣን ወዳድ መሪዎች ይታወቃል።—ሥራ 20:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
▪ እውነተኛ ሃይማኖት ለአምላክ በተገቢ ሁኔታ የመገዛት መንገድ ሲሆን መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ ሠይፍ አይመዝም። የሐሰት ሃይማኖት ግን በአንጻሩ እውነተኛን መሠረተ ትምህርት ይበርዛል፣ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን ይጥሳል፣ ከመለኮታዊ ጉዳዮች ይልቅ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ይከታተላል።—2 ቆሮንቶስ 10:3-5
▪ እውነተኛ ሃይማኖት የማያምኑ ሰዎችን ልብ ወደ እውነተኛ አምላክ አምልኮ ይመልሳል። የሐሰት ሃይማኖት ለጥርጥር፣ መጨበጫ ለሌለው ፍልስፍና፣ ለሰብዓዊ አስተሳሰብና ለዓለማዊነት መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ሉቃስ 1:17፤ 1 ቆሮንቶስ 14:24, 25
▪ የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት እውነተኛ ሃይማኖት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እድገትና መስፋፋት እያሳየ ነው። ዘርፎቹ በደም የራሰ መጎናጸፊያ ያጠለቀው የሐሰት ሃይማኖት ግን ያለበት መንፈሳዊ ችጋር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመሄዱም በላይ የደጋፊዎቹ ቁጥር በመመናመን ላይ ይገኛል።—ኢሳይያስ 65:13, 14
ሃይማኖት ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ የወደፊት ዕጣው ምንድን ነው? የሐሰት ሃይማኖት ለወደፊቱ አይቀጥልም። ሳትዘገዩ በአፋጣኝ ሸሽታችሁ ውጡ! (ራእይ 18:4, 5) ወደ እውነተኛ ሃይማኖት ተመለሱ፣ ለዘላለም የሚኖረው እርሱ ነውና።