ለሴቶች በጉባኤ ውስጥ አክብሮት ማሳየት
ክርስቲያኖች ሊጠብቁት የሚገባቸው የቲኦክራሲያዊ ራስነት የሥልጣን ተዋረድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። ክርስቶስ ለአምላክ፣ ወንድ ለክርስቶስ፣ ሴት ደግሞ ለባልዋ ይገዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ይሁን እንጂ ይህ ተገዢነት አምባገነናዊነትን የሚያመለክት አይደለም። የቤተሰብ ራስነት የሚከበረው በአካል፣ በሥነ ልቦና ወይም በቃል በማስፈራራት ወይም በጉልበት አይደለም። ከዚህም በላይ ክርስቲያናዊ ራስነት አንጻራዊ ሲሆን አንድ ባል ራሱን ምንም ዓይነት ስህተት ሊሠራ እንደማይችል የማይከሰስና የማይወቀስ ባለሙሉ ሥልጣን ራስ አድርጎ መመልከት አይኖርበትም።a “በጣም አዝናለሁ፣ አንቺ ልክ ነበርሽ” ማለት መቼና እንዴት ተገቢ እንደሚሆን ማወቅ ብዙ ጋብቻዎች ለባልዬውም ሆነ ለሚስቲቱ የሚያስደስቱና ረዥም ዕድሜ ያላቸው እንዲሆኑ ሊረዳ ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙ ባሎች እንደዚህ ያሉትን የትህትና ቃላት ከአፋቸው ለማውጣት ይተናነቃቸዋል!— ቆላስይስ 3:12–14, 18
ክርስቲያኖቹ ሐዋርያት ጳውሎስና ጴጥሮስ ስለ ጋብቻ በሰጧቸው ምክሮች የክርስቶስን አርዓያነት በመደጋገም ያሳስቡናል። አንድ ባል አክብሮት የሚያገኘው ክርስቶስ የተወልንን አርዓያ ሲከተል ነው። ምክንያቱም “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።”— ኤፌሶን 5:23
ጴጥሮስ ለባሎች የሰጠው ምክር በጣም ግልጽ ነው። “እናንተ ባሎች ሆይ፣ . . . ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:7) አንድ ዘመናዊ የስፓንኛ ውርስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “በባሎች ረገድ በምትካፈሉት የጋራ ሕይወት ለሚስቶቻችሁ አሳቢነት እያሳያችሁ ዘዴኞች ሁኑ” በማለት ተርጉሟል። እነዚህ ቃላት በጋብቻ ግንኙነት ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ለትዳር ጓደኛ ስሜትና ፍላጎት አሳቢ የመሆን ባሕርይ ጨምሮ ብዙ ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው። አንድ ባል ሚስቱን የፍትወት ማርኪያ መሣሪያ እንደሆነች ብቻ አድርጎ መመልከት የለበትም። በሕፃንነትዋ ተገድዳ ተደፍራ የነበረች አንዲት ሚስት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “እንዲህ ያለ ተሞክሮ ደርሶባት ለነበረች ሚስት ባልዋ ሊሰጣት ስለሚገባው ድጋፍ ብዙ እንድትሉ እመኛለሁ። እኛ፣ አብዛኞቹ ሚስቶች በእውነት የምንወደድና የሚታሰብልን እንደሆንን፣ ምንም ዓይነት ስሜታዊ ቁርኝት ሳይኖረን የወንዶችን አካላዊ ፍላጎት ለማርካት ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ብቻ የተቀመጥን እንዳልሆንን ለማወቅ እንፈልጋለን።”b አምላክ የጋብቻን ሥርዓት ያቋቋመው ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ባልንጀራና ረዳት እንዲሆኑ ነው። እርስ በርሳቸው መከባበርና ተቀናጅተው መሥራት ይኖርባቸዋል።— ዘፍጥረት 2:18፤ ምሳሌ 31:28, 29
“ደካማ ዕቃ” የሆኑት በምን መንገድ ነው?
በተጨማሪም ጴጥሮስ ባሎች ሚስቶቻቸውን “እንደ ደካማ ዕቃ” (አዓት) እንዲያከብሩ መክሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ጴጥሮስ ሴት “ደካማ ዕቃ” ነች ሲል ምን ማለቱ ነበር? በእርግጥም በአማካይ ሴቶች ከወንዶች ያነሰ አካላዊ ጉልበት አላቸው። ይህም የሆነው የአጥንታቸውና የጡንቻዎቻቸው አሠራር ከወንዶች የተለየ ስለሆነ ነው። ውስጣዊ ስለሆነው የሞራል ጥንካሬ የምንናገር ከሆነ ግን ሴቶች ከወንዶች በምንም ዓይነት መንገድ አያንሱም። ሴቶች ወንዶች ለጥቂት ጊዜ እንኳን ሊቋቋሙ የማይችሏቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለበርካታ ዓመታት ችለው ኖረዋል። ከእነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች መካከል ዱለኛ ወይም ሰካራም ባሎችን ችሎ መኖር ይገኝበታል። አንዲት ሴት ልጅ ስትወልድ እንዴት ያሉ ሁኔታዎችን እንደምታሳልፍና በምጥ ጊዜ እንዴት ያለ ጭንቅ እንደሚደርስባት አስቡ! ልጅ በሚወለድበት ጊዜ የሚፈጸመውን ተአምራዊ ሁኔታ የተመለከተ ስሜት ያለው ማንኛውም ባል ለሚስቱና ሚስቱ ላላት ውስጣዊ ጥንካሬ ያለው አክብሮት እንደሚጨምር የታወቀ ነው።
ሴቶች ስላላቸው ውስጣዊ የሞራል ጥንካሬ በራቨንስብሩክ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ታስረው የነበሩት አይሁዳዊቷ ሐና ሌቪ ሐስ በ1944 በግል ማስታወሻቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እዚህ ላይ አንድ በጣም የሚያናድደኝ ነገር አለ። እርሱም ወንዶች ከሴቶች ይበልጥ በጣም ደካማ መሆናቸውና አካላዊም ሆነ ሞራላዊ ችግሮችን ለመቋቋም የማይችሉ ሆነው መመልከቴ ነው። የሞራል ብርታት አጥተው ራሳቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው የተመለከተ ሰው ከልብ ሊያዝንላቸው ይገደዳል።”— ማዘርስ ኢን ዘ ፋዘርላንድ በክላውዲያ ኩንዝ
ይህ ተሞክሮ ሴቶች ከወንዶች ያነሰ አካላዊ ጥንካሬ ስላላቸው ብቻ ሊናቁ እንደማይገባቸው ያሳያል። ኤድዊን ራይሻወር “በዚህ ዘመን ሴቶች በአጠቃላይ ከወንዶች የበለጠ ቆራጥነትና የሥነ ልቦና ጥንካሬ እንዳላቸው ታውቋል” በማለት ጽፈዋል። (ዘ ጃፓኒዝ) ይህ የሴቶች ጥንካሬ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። የጎለመሱ ሴቶች ከባድ የሆነ የስሜት ጭንቀት ያጋጠማቸውን ሴቶች ሊረዱ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች አንዲት ግፍ የተፈጸመባት ሴት የአእምሮ እረፍት ለማግኘት ከወንድ ይልቅ የጎለመሰች ሴት ማነጋገር ይቀላታል። አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ መመሪያ ለማግኘት ክርስቲያን ሽማግሌ ማማከር ይቻላል።— 1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10፤ ያዕቆብ 5:14, 15
ሴቶች የሚያደርጉትን ሁሉ በጅምላ “በወር አበባዋ ዑደት ምክንያት የተሰማት የስሜት ቀውስ ነው” ብሎ ችላ ማለት ብዙ ሴቶችን ያበሳጫቸዋል። ትጉህ ክርስቲያን የሆነችው ቤቲ “ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደጻፈው በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ‘ደካማ ዕቃ’ እንደሆንና ይበልጥ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንዳለን እናውቃለን። እንዲህ ሲባል ግን አንድ የመሥሪያ ቤት አለቃ ወይም ተቆጣጣሪ እኛ ሴቶች ያደረግነውን ነገር ሁሉ ከወርሐዊ ዑደታችን ጋር አዛምዶ በመመልከት ሊያዝንልን ወይም አባታዊ በሆነ መንገድ ሊያየን ይገባል ማለት አይደለም። የማሰብ ችሎታ ያለን ፍጡሮች በመሆናችን በአክብሮት እንድንደመጥ እንፈልጋለን።”
ሁሉም ወንዶች የስሜት ግንፋሎት የማይታይባቸው እንዳልሆኑ ሁሉ ሁሉም ሴቶችም ስሜታውያን አይደሉም። እያንዳንዷ ሴት በግለሰብ ደረጃ መመዘን ይኖርባታል። ቀደም ሲል የጠቀስናት ሴት ለንቁ! መጽሔት “በጾታዬ ምክንያት የተለየ ባሕርይ እንዳለኝ ሆኜ እንድታይ አልፈልግም። ወንዶችም ቢሆኑ ስሜታዊ ሆነው ሲያለቅሱ ተመልክቻለሁ። የብረት ያህል ጠንካራ የሆኑና ስሜታቸው የማይደፈር ሴቶችም አሉ። ስለዚህ ወንዶች ጾታችንን ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ በሚዛናዊነት ያዳምጡን” ብላለች።
ለውጥ እንዲገኝ የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?
የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ሴቶች ለመብታቸውና ለፍትሕ መታገላቸው ብቻውን ወይም ወንዶችም ለሴቶች የይስሙላ አክብሮት ማሳየታቸው በቂ አይሆንም የሚሉ አሉ። በሁሉም ባሕሎችና የአካባቢ ሁኔታዎች የሚኖሩ ወንዶች በዚህ ረገድ ምን ዓይነት ሚና በመጫወት ላይ እንደሆኑና የሴቶችን ሕይወት ይበልጥ አስደሳችና ጥሩ ለማድረግ ምን ማድረግ እንደሚችሉ መመርመር ይኖርባቸዋል።— ማቴዎስ 11:28, 29
ደራሲና ገጣሚ የሆኑት ካታ ፖሊት በታይም መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አብዛኞቹ ወንዶች ሴቶችን አስገድደው እንደማይደፍሩ ወይም እንደማይደባደቡ ወይም እንደማይገድሉ የታወቀ ነው። ይህ ስለሆነ ግን ብዙዎቹ እንደሚያስቡት በሴቶች ላይ በሚፈጸመው ግፍ ምንም ዓይነት ተካፋይነት የላቸውም ማለት አይደለም። እያንዳንዳችን በዕለታዊ ኑሯችን በምናደርጋቸው ነገሮች በሚፈቀዱና በማይፈቀዱ ድርጊቶች መካከል ድንበር በሚያበጀው ባሕላዊ ግንዛቤና አስተሳሰብ ላይ ለውጥ ለማምጣት መርዳት እንችላለን። . . . ወንዶች ራሳቸውን በጥሞና እንዲመረምሩና ያላቸውን የተሳሳተ አስተሳሰብና መብት አሸንፈው አሁን ለምንኖርበት የዘቀጠ ኑሮ ኃላፊ መሆናቸውን እንዲቀበሉ መናገሬ ነው።”
ይሁን እንጂ በመላው ዓለም የሚኖሩ ወንዶች ለሴቶች ባላቸው አመለካከት ረገድ ሥር ነቀል ለውጥ ቢያደርጉ እንኳን የሰው ልጅ ለሚያጋጥሙት ኢፍትሐዊ ሁኔታ የተሟላ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ለምን? ምክንያቱም ወንዶች ኢፍትሐዊና አረመኔያዊ ድርጊት የሚፈጽሙት በወንዶች ላይ ጭምር እንጂ በሴቶች ላይ ብቻ አይደለም። ጦርነት፣ ጠብ፣ ግድያ፣ የቡድን ግድያና አሸባሪነት በብዙ አገሮች ዕለታዊ ጉዳዮች ሆነዋል። የሚያስፈልገው በመላዋ ምድር የሚሰፍን አዲስ የአገዛዝ ሥርዓት ነው። መላው የሰው ልጅ አዲስ ትምህርት ማግኘት ያስፈልገዋል። አምላክ ሰማይ ሆኖ ምድርን በሚያስተዳድረው ንጉሣዊ አገዛዙ ሊያደርግልን ቃል የገባው ይህንን ነው። ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት እውነተኛ ፍትሕና ሙሉ እኩልነት የሚያገኙት በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። በወንዶችና በሴቶች መካከል እውነተኛ የሆነ የእርስ በርስ መከባበር የሚኖረው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢሳይያስ 54:13 ላይ “[ወንዶችና ሴቶች] ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ይላል። አዎን፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች መማራቸውና ማወቃቸው እርስ በርስ መከባበር የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንዲኖር ያስችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታኅሣሥ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19–21 “በጋብቻ ውስጥ መገዛት ምን ማለት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b የእንግሊዝኛ ንቁ! ጥቅምት 8, 1991 ገጽ 3–11፤ ሚያዝያ 8, 1992 ገጽ 24–7 ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት የጎለመሰች ሴት በብዙ ሁኔታዎች ጠቃሚ ምክር ልትሰጥ ትችላለች
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ባል ለሚስቱ አክብሮት ሊያሳይ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ በቤት ውስጥ ሥራዎች በመካፈል ነው