የሐኪም ሙያ
ከሰባት ዓመት በፊት ገደማ ዳይ ሱዙኪ የተባለ የአሥር ዓመት ልጅ በደረሰበት የመኪና አደጋ ሕይወቱን አጣ። ለዳይ መሞት ምክንያት የሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ለመታዘዝ ሲሉ ደም እንዲሰጠው ያልፈቀዱት ወላጆቹ ያሳዩት ቸልተኝነት ነው በማለት መገናኛ ብዙኃኑ ወቀሳ አቀረበ። የዳይ ወላጆች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ከፖሊሶች የምርመራ ውጤት በኋላ ግን በወላጆቹ በኩል የታየ ምንም ቸልተኝነት አለመኖሩ ታወቀ።
በጃፓን የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች አገሮች እንዳሉት ምሥክሮች ሁሉ ሐኪሞች ሕይወትን ለማዳን የሚያደርጉትን ጥረት ያደንቃሉ፤ ከሕክምና ሠራተኞች ጋርም ለመተባበር ፈቃደኞች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በዘመናዊ ሕክምና ይጠቀማሉ። እንዲሁም ደም መውሰድን ሳይጨምር በሚሰጣቸው ሕክምና ይስማማሉ። አንድ የሕክምና ውሳኔ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ባላቸው የታማኝነት አቋም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ ግን አምላክን መስማት ይመርጣሉ። (ሥራ 4:19) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም . . . ራቁ’ የሚል ግልጽ ትእዛዝ ይሰጣል።—ሥራ 15:29
ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ትእዛዝ ላይ ያላቸውን እምነት ከማላላት ይልቅ ደም መውሰድን የማይጨምር ሕክምና እንዲደረግላቸው ይመርጣሉ። እንዲህ ያሉትን አማራጭ የሕክምና ዓይነቶች የመስጠት አስፈላጊነት ለሕክምና ባለሞያዎች ፈታኝ ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ዶክተሮችና የሆስፒታል አስተዳዳሪዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ምርጫ ጋር በመስማማት ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሏቸውን መንገዶች በመፈለግ ላይ ናቸው። ለምሳሌ በቅርቡ ማይኒቺ ሹምቡን የተባለ በጃፓን የሚታተም አንድ ጋዜጣ “አንዳንድ ሆስፒታሎች ብዙ ደም እንዳይፈስ በሚቻለው መንገድ ሁሉ በመከላከል ደም አልባ የሆነ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል” በማለት ጽፏል።
ጋዜጣው በኤጂኦ ኮሴይ ሆስፒታል ከ1989 እስከ ጥር 1992 ባለው ጊዜ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያለ ደም 14 ቀዶ ሕክምናዎች ተደርገው መሳካታቸውን ጠቅሷል። ሆስፒታሉ በሚቀርቡት መረጃዎች መሠረት ስምምነት የማድረግን አስፈላጊነት አጥብቆ ገልጿል። የሆስፒታሉ መመሪያ ይፈሳል ተብሎ የሚጠበቀውን የደም መጠንና ደም አልባ የሆነ ቀዶ ሕክምና የሚያስከትለውን አደጋ የይሖዋ ምሥክር ከሆኑት በሽተኞች ጋር መወያየት ነው። በሽተኛው የሕክምና ባለሙያዎችን ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ በጽሑፍ የቀረበ ሰነድ ከሰጣቸው ሐኪሞቹ ያለ ደም ቀዶ ሕክምናውን ያከናውናሉ።
በሌሎች ሆስፒታሎች ተቀባይነት ባያገኙም እንኳ ይህ ሆስፒታል ምሥክር የሆኑ በሽተኞችን ተቀብሎ የሕክምና ምርጫቸውን እንዲያከብር የገፋፋው ምንድን ነው? በማይኒቺ ሽምቡን ዘገባ መሠረት የሆስፒታሉ ዲሬክተር የሆኑት ቶሺሂኮ ኦጄን እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል:- “የአንድ ሐኪም ሙያ በሽተኛው የመጨረሻውን ውሳኔ ለማድረግ ያለውን መብት እንዲያከብርና በሽታውን ለማከም ሙያው እስከፈቀደለት ድረስ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እንዲተባበር ያስገድደዋል። ከዚህ አቋም አንጻር ሲታይ ከበሽተኛው ጋር በመረጃ የተደገፈ ስምምነት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።”
“የይሖዋ ምሥክሮችም በበኩላቸው” ይላል ጋዜጣው በማከል “በአገሪቱ ውስጥ ባሉ 53 ከተሞች ለአማኞቻቸው አገልግሎት የሚሰጡ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችን አቋቁመዋል። የእነዚህ ኮሚቴዎች ዓላማም ደም አልባ የሆኑ ቀዶ ሕክምናዎችን ስለማድረግ ከሆስፒታሎች ጋር ተወያይቶ ስምምነት ላይ መድረስ ነው።” በዚህ ምክንያት አሁን ብዙ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችና የሕክምና ተቋሞች ምሥክሮቹ የመረጡትን ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነዋል።
በአሁኑ ጊዜ በጃፓን ከ1,800፣ በዓለም ዙሪያ ደግሞ ከ24,000 የሚበልጡ ሐኪሞች ደም በመስጠት ፋንታ ሌሎች ደም የሚተኩ ፈሳሾችን በመስጠት ምሥክሮቹን ለመርዳት ፈቃደኞች ሆነዋል። ከ800 በላይ የሚሆኑ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች “የአንድ ሐኪም ሙያ” በሽተኛው ለመምረጥ ያለውን መብት ማክበርን የሚጨምር እንደሆነ የሚሰማቸውን ሐኪሞች አነጋግረዋል።