በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?
“ቤት የውጭው ኅብረተሰብ ከሚያመጣው ውጥረት፣ ጭንቀትና ምክንያተ ቢስነት መጠለያ ከመሆን ይልቅ እነዚህኑ ውጥረቶች የሚያስተላልፍ እንዲያውም ይበልጥ የሚያባብስ ይመስላል።”
—ዚ ኢንቲሜት ኢንቫይሮንመንት፣ ኤክስፕሎሪንግ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ
በቤተሰብ ውስጥ ስለሚነሳ ጠብ ጥናት ማድረግ ከተጀመረ ገና ብዙም አልቆየም። ሰፋ ያለ ጥናት የተደረገው ባለፉት አሥርተ ዓመታት ነው። ከእነዚህ ጥናቶች የተገኙት ውጤቶች ሁልጊዜ ተመሳሳይ ሆነው ባይገኙም በቤተሰብ ውስጥ ለሚነሱ ጠቦች አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች ሊታወቁ ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
አስተዳደግ ምን አስተዋጽኦ አለው?
በርካታ ተመራማሪዎች ስለደረሱበት ግኝት ሲናገሩ “ቃለ መጠይቅ ያደረግንላቸው ባልና ሚስት ይበልጥ ጠበኛ በሆኑ መጠን ልጆቻቸውም እርስ በርሳቸውም ሆነ ከወላጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ይበልጥ ጠበኞች ሆነው ተገኝተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣት ልጆች በቤት ውስጥ ያለውን ጠብ መመልከታቸው ብቻውን በባሕርያቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያሳድራል። ጆን ብራድሾው የተባሉት ቴራፒስት “እናቱ ስትደበደብ የሚመለከት ልጅ ራሱ እንደተደበደበ ያህል ሆኖ ይሰማዋል” ብለዋል። ኤድ የተባለ አንድ ወጣት አባቱ እናቱን ሲመታት ማየት በጣም ያስጠላው ነበር። ይሁን እንጂ በጊዜው ላይገነዘበው ቢችልም አእምሮው ወንዶች ሴቶችን መቆጣጠር እንደሚኖርባቸውና ይህንንም ለማድረግ ማስፈራራት፣ ማሳመምና ማመናጨቅ እንዳለባቸው እንዲያምን እየተደረገ ነበር። ኤድ ካደገ በኋላ ሚስቱን በተመሳሳይ ሁኔታ መሳደብና መደብደብ ጀመረ።
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ጥልና ድብድብ ያለባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዳይመለከቱ ይከለክላሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ያየውን ሁሉ አትሞ የሚያስቀር ለጋ አእምሮ ላላቸው ልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን ይኖርባቸዋል።
ውጥረት ምን አስተዋጽኦ አለው?
እርግዝና፣ ሥራ ማጣት፣ የወላጅ ሞት፣ መኖሪያ መለወጥ፣ በሽታ፣ የገንዘብ ችግርና የመሳሰሉት ሌሎች ነገሮች ውጥረት ያመጣሉ። አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ጠብ ሳይደርሱ ውጥረቶችን ይቆጣጠራሉ። አንዳንዶች ግን ውጥረት ካጋጠማቸው፣ በተለይ ሌሎች ችግሮች ከተጨመሩባቸው ወደ ጠብ ያመራቸዋል። ለምሳሌ ያህል በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦር በተለይ ደግሞ በሽተኛ ከሆነና ጧሪው ደግሞ ሌሎች የቤተሰብ ኃላፊነቶች ከተደራረቡበት የኃይል ድርጊት ለመፈጸም ይገፋፋል።
ልጆችን ማሳደግ ውጥረት ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት የልጆች ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ልጆችን ማንገላታትም በዚያው መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በተጨማሪም “በባልና ሚስት መካከል ለዱላ የሚያደርስ ግጭት የሚፈጠረው አብዛኛውን ጊዜ በልጆች ምክንያት ስለሆነ” ልጆች ለጠበኝነት መጨመር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል።
ስለ ወንድነትና ስለ ሴትነት የተዛባ አመለካከት መያዝ
በካናዳ አንድ የአማካሪዎች ቡድን የሚመሩ ዳን ባጆሬክ የተባሉ ሰው ዱለኛ ወንዶች ስለ ሴቶች የተዛባ አመለካከት እንዳላቸውና “ከየትኛውም ባሕል የመጡ ቢሆኑ ወንዶች ምንጊዜም የተሻሉ እንደሆኑ እንዲያምኑ ተደርገው ያደጉ” መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዱለኛ ወንዶች የሚደረግ የተሐድሶ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ሃሚሽ ሲንክሌር ወንዶች የሴቶች የበላይ እንደሆኑና እነርሱን “የመቅጣት፣ የመገሰጽና የማሸማቀቅ” መብት እንዳላቸው እንዲያምኑ ተደርገው ያድጋሉ ብለዋል።
በብዙ አገሮች አንድ ወንድ ሚስቱን በቤቱ ውስጥ ከሚገኙት የመገልገያ ዕቃዎች እንደ አንዱ አድርጎ የመቁጠር መብት እንዳለው ይታመናል። ሚስቱን በኃይል መግዛቱና መቆጣጠሩ የወንድነቱና የክብሩ መለኪያ እንደሆነ ይታሰባል። ሴቶች ብዙ ጊዜ በአሰቃቂ ሁኔታ ይደበደባሉ፣ ወይም በሌላ መንገድ በደል ይፈጸምባቸዋል፣ የአገሮቹም ሕግ ይህንኑ የሚፈቅድ በመሆኑ ከሕጉ ምንም ዓይነት ጥበቃ አያገኙም። ወንዱ የበላይ፣ ሴቷ የበታች በመሆኗ ወንዱ ምንም ያህል ባለጌ፣ ጠበኛ፣ ወራዳ ወይም ራስ ወዳድ ቢሆን ሙሉ በሙሉ ልትታዘዘው ይገባል።
የሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ሪፖርተር የሆነው ሞርሊ ሴፈር ስለ አንድ የደቡብ አሜሪካ አገር የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቧል:- “የወንድ ትምክህተኝነት እንደዚህ ገኖ የሚታይበት ሌላ የላቲን አሜሪካ አገር የለም። . . . በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተንሰራፍቶ የሚታይ ባሕርይ ነው። በፍርድ ቤት እንኳን አንድ ወንድ ነፍስ የገደለው ክብሩ ስለተነካበት ከሆነ፣ በተለይም የተገደለችው ሚስቱ ወይም ፍቅረኛው ከሆነች በነጻ ይለቀቃል።” የዚህችን አገር ያህል “ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት አገር በምድር ገጽ ላይ አይገኝም” በማለት በአፅንዖት ተናግረዋል። በዚህ አገር ያለው ሁኔታ የከፋ ይሁን እንጂ የወንድ ትምክህተኝነትም ሆነ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ መመልከት በአንድ አገር ብቻ የተወሰነ አይደለም።
የአንድ በኒው ዮርክ የሚገኝ በቤተሰብ መሃል የሚፈጠር ጠብ አስወጋጅና ሕግ አስከባሪ መሥሪያ ቤት ዲሬክተር የሆኑት ሚና ሹልማን “ዱለኝነት ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ለማስከበርና ያላቸውን ኃይልና መብት ለማሳየት የሚጠቀሙበት መሣሪያ ነው።” አክለውም “በሥልጣንና በመብት መባለግ በቤተሰብ መሃል ጠብ እንዲነሳ ያደርጋል” ብለዋል።
ሚስታቸውን የሚደበድቡ አንዳንድ ወንዶች የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሲሆን እንዲህ ያለውን ስሜት በሚስቶቻቸውም ላይ ለማሳደር ይሞክራሉ። ከተሳካላቸው የተመኙትን ስለሚያገኙ በሌላ ሰው ላይ ሥልጣንና የበላይነት እንዳገኙ ይሰማቸዋል። በዚህ መንገድ ወንድነታቸውን ለማረጋገጥ የሚችሉ ይመስላቸዋል። ግን ትክክል ናቸው? ጉልበታቸውን የሚያሳዩት በአቅም በማትተካከላቸው ሴት ላይ በመሆኑ እንዲህ ያለው ድርጊታቸው የሚያረጋግጠው ጠንካራ ሰዎች መሆናቸውን ወይስ ምክንያተ ቢስነታቸውን? ጉልበተኛ የሆነ ወንድ አቅመ ደካማ የሆነችንና ደራሽ የሌላትን ሴት መደብደቡ የወንድነት ምልክት ነው? ጠንካራ ሥነ ምግባር ያለው ሰው ከእሱ ያነሰ አቅም ላላቸውና ረዳት ለሌላቸው ሰዎች አሳቢነትና ርኅራሄ ያሳያል እንጂ በደል አይፈጽምባቸውም።
የዱለኛው ምክንያተ ቢስነት ሌላው ገጽታ ደግሞ እንዲደባደብ የምታደርገው ሚስቱ እንደሆነች መናገሩ ነው። ‘ይህን አጥፍተሻል። የምመታሽ በዚህ ምክንያት ነው።’ ወይም ‘ራት ተዘጋጅቶ ስላልቆየኝ ዋጋሽን ታገኚያለሽ’ ይላታል ወይም ይህንን የመሰለ መልእክት የሚያስተላልፍ ቃል ይናገራታል። በደብዳቢው አእምሮ ስህተቱ የእርሷ ነው። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ስህተት ብትሠራ እሷን ለመደብደብ ሰበብ ሊሆን አይችልም።
መጠጥ መውሰድ ለውጥ ያመጣ ይሆን?
የአልኮል መጠጥ ራስን የመቆጣጠርን ችሎታ ስለሚቀንስና ለግልፍተኝነት ስለሚያጋልጥ አንዳንዶች ለዱለኝነት እንደሚያነሳሳ መገንዘባቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ምንም መጠጥ ባልወሰደበት ወቅት ለጠብ የመነሳሳት ስሜቱን መቆጣጠር ቢችልም ጥቂት ከጠጣ በኋላ ግን ለጠብ መጋበዝ ይጀምራል። መጠጡ የማመዛዘን ችሎታውን ያደነዝዝበትና ንዴቱን መቆጣጠር ያቅተዋል።
ይሁን እንጂ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የአልኮል መጠጡ ራሱ ሳይሆን ውጥረት ነው የሚሉ አሉ። ያለባቸውን ውጥረት ለማርገብ ሲሉ የአልኮል መጠጦችን የሚወስዱና ንዴታቸውን ለማብረድ ሲሉ መጣላት የሚቀናቸው ሰዎች በባሕርያቸው አንድ ዓይነት ናቸው በማለት ይናገራሉ። ይህ ማለት ደግሞ ጠጪው ሰው ይስከርም አይስከር የጠበኝነት ዝንባሌ አለው ማለት ነው። ይህ ጉዳይ አከራካሪ ቢሆንም አልኮል ግልፍተኛ ያደርጋል እንጂ አንድ ሰው ስሜቱን እንዲቆጣጠር እንደማያደርግ የተረጋገጠ ነው።
መገናኛ ብዙሐን የሰዎችን ባሕርይ የሚቀርጹበት መንገድ
አንዳንዶች እንደሚሉት የቴሌቪዥንና የሲኒማ ፕሮግራሞች ወንዶች የጉልበተኝነት ባሕርይ እንዲያሳዩ ከማበረታታቸውም በላይ በኃይል ተጠቅሞ ንዴት መወጣት ወይም ግጭቶችን ማስወገድ ተገቢ እንደሆነ ያስተምራሉ። አንድ የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ “እኔ ራሴ ራምቦ የተባለው ፊልም ያሳደረብኝ ስሜት በጣም ይደንቀኛል። ሕግ አክባሪ የሆነው ባሕርዬና [ውስጣዊ] ስሜቴ ራምቦ በፈጸማቸው አሰቃቂ የጅምላ ግድያዎች ሲሰቀቅ ውስጣዊ የሆነው የልጅነት ባሕርዬ ደግሞ ይደሰትበት ነበር” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ብዙ ልጆች በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዓታት ለሚተላለፉ ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው የኃይል፣ አስገድዶ የማስነወር፣ ሌሎች ሰዎችን በተለይም ሴቶችን የሚያዋርዱ ድርጊቶችን ለሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መጋለጣቸው ብዙዎቹ ካደጉ በኋላ እነዚህኑ ፀረ ኅብረተሰብ የሆኑ ድርጊቶች የሚፈጽሙ መሆናቸው አያስደንቅም። በእነዚህ ፕሮግራሞች የሚነኩት ትላልቅ ሰዎችም ጭምር ናቸው እንጂ ልጆች ብቻ አይደሉም።
በተጨማሪም በቴሌቪዥንና በፊልም የሚታዩት የድብደባ፣ የብልግና እና ሴቶችን የሚያዋርዱ ድርጊቶች በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእጅጉ ጨምረዋል። ይህም በቤተሰብ ውስጥ ጠብ እንዲጨምር ማድረጉ የማይቀር ነው። አንድ የምርመራ ቡድን እንዳረጋገጠው “ጠብን በመመልከትና በጠበኝነት ባሕርይ መካከል የቅርብ ዝምድና አለ።”
ራስን ማግለል የሚያስከትለው ተጽእኖ
በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ሕይወት በብቸኝነት የተዋጠ ነው። ሰዎች እንደ ልብ የሚጨዋወቱባቸው ትናንሽ ሱቆች በትላልቅ የገበያ አዳራሾች ተተክተዋል። ብዙ ቤተሰቦች የከተሞች መስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ሥራ አጥነት ከለመዷቸው አካባቢዎች እንዲፈናቀሉ ያደርጋቸዋል። ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር በሌለባቸው አካባቢዎች በቤተሰብ ውስጥ ጠብ በዝቶ ተገኝቷል።
ጄምስ ሲ ኮልማን ኢንቲሜት ሪሌሽንሺፕስ፣ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ በተባለው መጽሐፋቸው ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞክረዋል። አንድ ሰው ብቸኛ ሲሆን ትርጉም ያለው ጭውውት የሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች በጣም አነስተኛ ስለሚሆኑ የጠበኝነት ዝንባሌ ያለው ከሆነ የሚያጋጥመውን ሁኔታ በሚዛናዊነት መመልከትና ምሥጢረኛው ከሆነ ሰው እርዳታ ማግኘት ያቅተዋል። ባሕርዩን የሚያለዝብለት ጓደኛ ወይም የቅርብ ዘመድ የሌለው በመሆኑና በየዕለቱ የተሳሳተ አስተሳሰቡን የሚያርምለት የቅርብ ሰው ባለመኖሩ ስሜቱ ያዘዘውን በቀላሉ እንዲፈጽም ያደርገዋል። ምሳሌ 18:1 እንደሚለው ነው:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”
ለጠበኛ ቤተሰቦች የሚሆን እርዳታ
በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች በከፊል ተመልክተናል። ሌሎች መንስዔዎችም አሉ። አንዳንዶቹን ምክንያቶች ለይተን ካወቅን አሁን የሚያስፈልገን መፍትሔዎቹን መመርመር ነው። አንድ ሰው ዘወትር ጠብ ባለበት ቤት ውስጥ የሚኖር ከሆነ ሁኔታው ተባብሶ አምባጓሮ ከመነሳቱ በፊት ግጭቱን እንዴት በአጭር ለመቅጨት ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው? በቤተሰብ መሃል ጠብ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ገጽ 10 ላይ የሚጀምረው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የስሜት ዱላ፣ በቃላት መደባደብ
አካላዊ ምት በእጅ የሚሰነዘር ሲሆን ስሜታዊ ምት ግን በቃላት የሚሰነዘር ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የመሣሪያው አይነት ብቻ ነው። ምሳሌ 12:18 እንደሚለው ነው:- “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፣ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።”
ይህ “እንደሚዋጋ ሰይፍ” የሆነው የስሜት ዱላ ምን ያህል አደገኛ ነው? ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ሁለቱም የሚያስከትሉት ውጤት አንድ አይነት ነው። ሁለቱም ያሳምማሉ፣ ያስፈራሉ፣ የመጠቃት ስሜት ያሳድራሉ።”
በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም ስሜታዊ ዱላ:- “በባለ ትዳሮች መካከል የሚከሰተው ጠብ የሚያስከትለው ጉዳት በአካል ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በብዛት፣ ምናልባትም አብዛኛውን ጊዜ በቃልና በስሜት የሚሰነዘር ዱላ ነው” በማለት አንዲት ለረዥም ዓመታት ጥቃት የተሰነዘረባት ሴት ተናግራለች። ጥቃቱ በቅጽል ስም በመጥራት፣ በመጮህ፣ ሁልጊዜ በመተቸት፣ አዋራጅ የስድብ ቃላት በማዥጎድጎድና በዛቻ ሊሰነዘር ይችላል።
የሚያዋርዱ፣ የሚያመናጭቁና የሚያስፈራሩ ቃላት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስክትሉ ይችላሉ። መጥፎ ቃላት በመጀመሪያ ላይ በድንጋይ ላይ እንደሚወርድ የውኃ ጠብታ ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙ ሳይቆይ ግለሰቡ ለራሱ ያለው ግምት ይናዳል። አንዲት ሴት “ከአካላዊና ከቃላት ዱላ አንዱን ምረጪ ብባል ወዲያው በዱላ መመታቱን እመርጣለሁ” ብላለች። ምክንያቱን ስታስረዳ “ዱላው የተወው ሰንበር ስለሚታይ ሌላው ቢቀር ሌሎች ሰዎች ያዝኑልኛል። የቃላት ዱላ ግን እኔኑ ብቻ ያሳብደኛል። ቁስሉ አይታይም። ማንም ስለ እኔ አይገደውም” ብላለች።
በልጆች ላይ የሚሰነዘር ስሜታዊ ዱላ:- ይህ ደግሞ አንድን ልጅ ቁመናውን፣ ብልህነቱን፣ ችሎታውን ወይም ጠቃሚነቱን በማጥላላት ደጋግሞ መተቸትን ሊጨምር ይችላል። በተለይ ልጅን በሽሙጥ መናገር በጣም ጎጂ ነው። ልጆች ከምር የተነገረውንና ለቀልድ ብቻ የተነገረውን መለየት ስለማይችሉ የሚሰነዘርባቸውን የሽሙጥ አነጋገር እንደ እውነት ይወስዳሉ። ሲን ሆጋን ዳውኒ የተባሉት የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ “ሁሉ ሰው ሲስቅ ልጁ ግን ከልቡ ይከፋል። በዚህም ምክንያት የራሱን ስሜት አለማመንን እየተማረ ይሄዳል” ብለዋል።
ስለዚህ ቶማስ ካርላይል የተባሉት ስኮትላንዳዊ ታሪክ ጸሐፊና ሐያሲ “የሽሙጥ አነጋገር በአጠቃላይ የዲያብሎስ ቋንቋ እንደሆነ ተረድቼአለሁ፣ በዚህም ምክንያት ፈጽሜ ከተውኩት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል” ሲሉ የተናገሩት ቃል እውነትነት አለው።
ግፍ በተፈጸመባቸው ልጆች ላይ በርካታ ጥናት ያደረጉት ጆይ ባየርስ “አካላዊ ዱላ አንድን ልጅ ሊገድለው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ መንፈሱንም ጭምር መግደል ይቻላል። ወላጆች በተደጋጋሚ ልጃቸውን በሚተቹበት ጊዜ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው” ብለዋል። ፋሚሊ ላይፍ ኤጁኬተር የተባለው መጽሔት “ስሜታዊ ቁስል በግልጽ ከሚታየውና ቀስ በቀስ ሊሽር ከሚችለው አካላዊ ቁስል የተለየ ከመሆኑም በላይ በአንድ ልጅ አእምሮና ስብእና ላይ ሊታይ የማይችል ለውጥ ስለሚያመጣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነትና ገሃዱን ዓለም ያበላሽበታል” ይላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ልጅ በተደጋጋሚ ጊዜ ድብደባ መመልከቱ ወደፊት በሚኖረው ባሕርይ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል