ተገዶ መደፈርን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
ኤሪክ ሀብታም ቤተሰቦች ያሉት፣ ረጅምና ጥሩ ቁመና ያለው ወጣት ነው። ኤሪክ ሎሪን ቤቱ እንድትመጣ ሲጋብዛት 19 ዓመቷ ነበር። በግብዣው ላይ የኤሪክ የክፍል ጓደኛና የሴት ጓደኛው እንደሚገኙ ነግሯት ነበር። ሎሪም በኤሪክ ቤት ግቢ ሥጋ እየተጠበሰ ሲበላ ደረሰች። ነገር ግን እርሷ ባላወቀችው ምክንያት የኤሪክ ጓደኛና ትመጣለች የተባለችው ሴት ጓደኛው ሳይመጡ ቀሩ። ብዙ ሳይቆይ ሌሎቹ እንግዶችም ግብዣውን ትተዉ ውልቅ ውልቅ እያሉ መውጣት ጀመሩ።
እርሷም “‘አንድ መጥፎ ነገር መኖር አለበት፣ ነገሩ ምን ይሆን?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፤ ሆኖም ችላ አልኩት” ብላለች።
ኤሪክ ሎሪን ብቻዋን እንዳገኛት አስገድዶ ደፈራት። ሎሪ ተገዳ መደፈሯን ለፖሊስ ሪፖርት አላደረገችም። ቆይታም ሁለተኛ የኤሪክን ዓይን ላለማየት ስትል 240 ኪሎ ሜትር ርቃ ሄደች። ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላም እንኳ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመጫወት ቀጠሮ መውሰድ ትፈራ ነበር።
ተገድዶ መደፈር በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት ላይ ያለ አስፈሪ አደጋ ነው። አንዲት ሴት እንዲህ ያለው ጥቃት እንዳይደርስባት የሚረዳት ትልቁ መከላከያ ይህ ጥቃት ሊደርስባት የሚችል መሆኑን መገንዘቧና ለመከላከል ዝግጁ መሆኗ ነው። ሴቶች ተገደው ሊደፍሩ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በሙሉ አስቀድሞ ማወቅ አይቻልም። ሆኖም አስገድደው የሚደፍሩ ሰዎችን አስተሳሰብና ብልሃት ማወቅሽ አስቀድመሽ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን እንድትገነዘቢ ይረዳሻል።a አንድ ጥንታዊ ምሳሌ “ብልኅ ሰው መከራ ሲመጣ አይቶ ይሸሻል፤ ማስተዋል የጎደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ ከገባ በኋላ እንደገና ይጸጸታል” ይላል። — ምሳሌ 27:12 የ1980 ትርጉም።
ራስን ተገዶ ለመደፈር ከሚያጋልጥ ሁኔታ መከላከል የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ አስገድደው ከሚደፍሩ ሰዎች መራቅ ነው። በሚገባ የሚታወቅ ሰው ቢሆንም እንኳ አስገድዶ የመድፈር ዝንባሌና ባሕርይ የሚያሳይ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (በገጽ 7 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከቺ።) አንዳንድ ወንዶች ሴት ለመድፈር ያነሣሣቸው የሴቲቱ አለባበስ ወይም ከእነርሱ ጋር ብቻዋን ለመሆን ፈቃደኛ መሆኗ ነው የሚል ሰበብ ይሰጣሉ። አንዲት ሴት እንዲህ ላለው የተጣመመ አመለካከት ምክንያት ባትሆንም እንዲህ ያለ ዝንባሌ ያለውን ሰው አስቀድማ ለማወቅ ጥረት ብታደርግ ጥበበኛ ትሆናለች።
በደንብ ከማታውቂው ወንድ ጋር ብቻችሁን እንድትሆኑ አትፍቀጂ። (ከምታውቂው ሰው ጋርም ቢሆን ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል።) አንድ የማይታወቅ ሰው የጥገና ሠራተኛ ነኝ ብሎ በመግባት ሊደፍርሽ ይችላል። እንዲህ ብሎ የመጣ ሰው ካለ የመታወቂያ ካርዱን እንዲያሳይሽ በመጠየቅ ሁኔታውን አረጋግጪ። የሚያውቃትን ሴት አስገድዶ የሚደፍር ወንድ ብዙውን ጊዜ ሊደፍራት ያሰባትን ሴት ብቻዋን ለማግኘት ሲል አንድ መልእክት ቤቱ እንድታደርስለት ይጠይቃል ወይም የሚገናኙበት ቦታ ብዙ ሰዎች የሚገኙበት ነው ብሎ ይዋሻል። እንዲህ ባለው ዘዴ መታለል የለብሽም።
ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመጫወት በምትቀጣጠሪበት ጊዜ ቀጠሮውን ብዙ ሰዎች ባሉበት ወይም ከሁለታችሁ ሌላ ተመልካች ሰው ሊገኝ በሚችልበት ቦታ ላይ በማድረግ ችግር እንዳይፈጠር ለመከላከል ይቻላል። አብረሽው ለመጫወት ቀጠሮ የምትሰጭውን ሰው በሚገባ እወቂው፤ እንዲሁም አካላዊ መቀራረብ እንዲኖራችሁ የምትፈቅጅም ከሆነ ገደብ ያለው እንዲሆን ጥብቅ ሁኚ። ማንኛውንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ ስለ መጠጣት ጥንቃቄ አድርጊ! የማሰብ ኃይልሽ ከተዳከመ ሊመጣብሽ የሚችለውን አደጋ በንቃት ልትከታተይ አትችይም። (ከምሳሌ 23:29–35 ጋር አወዳድሪ።) ሰውነትሽ የሚሰጥሽን ማስጠንቀቂያ አዳምጪ። ከአንድ ሰው ጋር ስትሆኚ የሰውዬው ሁኔታ ካላማረሽ ወይም ካጠራጠረሽ ግምቴ የተሳሳተ ይሆናል ብለሽ አታስቢ። በፍጥነት አምልጪ።
በአብዛኛው አስገድደው የሚደፍሩትም ሆነ ተገደው የሚደፈሩት ወጣቶች ናቸው። ስለዚህ በተለይ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ተገዶ ወደ መደፈር የሚያመሩ አደገኛ ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆኑ በግልጽ በማስረዳት ጥቃቱን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ያስፈልጋቸዋል።
ቶሎ እርምጃ ውሰጂ
ተገዶ ወደ መደፈር የሚያመሩትን ሁሉንም ሁኔታዎች አስቀድሞ ለማወቅ አይቻልም። ብቻሽን ሆነሽ እያለ ከአንቺ የበለጠ ኃይል ያለውና በጉልበቱ ተጠቅሞ ከአንቺ ጋር የፆታ ግንኙነት ለማድረግ ያቀደ ሰው በድንገት ያጋጥምሽ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ልታደርጊ ትችያለሽ?
ቶሎ እርምጃ ውሰጂ። ግብሽ ማምለጥ መሆኑን አስታውሽ። አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት የሚደፍሯትን ሴት ሁኔታ ለማወቅ ሙከራ ያደርጋሉ። ስለዚህ በተቻለ መጠን ያቀደውን ጥቃት ለመፈጸም እርምጃ ለመውሰድ በቂ ድፍረት ከማግኘቱ በፊት አሳቡን ማስለወጥ ያስፈልግሻል። አስገድዶ ስለ መድፈር ጥናት ያካሄዱ ሰዎች በሁለት መንገዶች መቃወም ማለትም ሰላማዊ ወይም የኃይል ተቃውሞ ማሳየት እንደሚቻል ሐሳብ ይሰጣሉ። በመጀመሪያ ሰላማዊ ተቃውሞ አሳዪ። ያ ካልሠራ ተቃውሞሽን በኃይል ግለጪ።
ሰላማዊ ተቃውሞ ማሳየት አስገድዶ የመድፈር ሙከራ የሚያደርገውን ሰው በማነጋገር ጊዜ ማባከንን፣ የሚተላለፍ የአባለዘር በሽታ እንዳለብሽ ማስመሰልንና ሊደፍርሽ ባሰበው ሰው ላይ ማስታወክን የመሳሰሉትን ዘዴዎች ሊጨምር ይችላል። (ከ1 ሳሙኤል 21:12, 13 ጋር አወዳድር።) ጀራርድ ዊትሞር የተባሉ ሰው ስትሪት ዊዝደም ፎር ውሜን:- ኤ ሀንድ ቡክ ፎር ኧርባን ሰርቫይቫል በተባለው መጽሐፋቸው “በሚገባ ከታሰበ ለማምለጥ የሚያስችል ብዙ ዓይነት ዘዴ ማግኘት ይቻላል” ሲሉ ጽፈዋል።
የሰላማዊ ተቃውሞ ዘዴዎች የመድፈር ሙከራ ከሚያደርገው ሰው ጋር አካላዊ ግብ ግብ መጀመርን አይጨምሩ እንጂ በጣም ብዙ ናቸው። ረጋ ብሎ ማሰብና የሰውዬውን ሐሳብ ለመከፋፈል ወይም ለማረጋጋት የሚያስችል ዘዴ መጠቀም ያስፈልጋል። የተጠቀምሽበት ዘዴ ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጀውን ሰው ይበልጥ የሚያስቆጣውና በኃይል እንዲጠቀም የሚገፋፋው ከሆነ ሌላ ዘዴ ፈልጊ። ሆኖም ሊሠራ የሚችል ሌላ ዘዴ ለመፈለግ እስክታስቢ ይበልጥ ሰዋራ ወደ ሆነ ሥፍራ እንዳትወሰጂ መጠንቀቅ አለብሽ። ከሁሉም የበለጠ ውጤት ያለው የሰላማዊ ተቃውሞ ዘዴ መጮህ መሆኑን አስታውሽ። — ከዘዳግም 22:23–27 ጋር አወዳድር።
ሌላው አማራጭ ደግሞ ኃይል በመጠቀም የተቃውሞ እርምጃ መውሰድ ነው። ጥቃት ለሰነዘረብሽ ሰው በምንም ዓይነት መንገድ ምኞቱን የማትፈጽሚለት መሆንሽን በግልጽ ንገሪው። የመድፈር ሙከራ የተደረገብሽ ለጨዋታ ቀጠሮ ባደረግሽበት ወቅት ከሆነ ሊያደርግ የፈለገው ነገር ምን መሆኑን በግልጽ በመናገር ልታስደነግጪው ትችያለሽ። “አስገድደህ ልደፍረኝ አትችልም! ፖሊስ እጠራለሁ!” ብለሽ ብትጮሂ አስገድዶ ለመድፈር እየሞከረ ያለው ሰው በድርጊቱ ልቀጥል ወይስ ላቁም እያለ እንዲያመነታ ሊያደርገው ይችላል።
በጉልበት ተቃወሚ
በቃል የገለጽሽው ተቃውሞ ካልሠራ በኃይል ከመ ጠቀም ወደኋላ አትበይ። ኃይል መጠቀምሽ የበለጠ እን ድትጎጂ ወይም እንድትገደይ ላያደርግሽ ይችላል። ዝም ብለሽ ጥቃቱን መቀበልሽም ቢሆን ከጉዳት ለመጠበቅ ዋስትና አይሆንሽም። ስለሆነም አስገድዶ ስለ መድፈር ጥናት ያካሄዱ አብዛኞቹ ሰዎች ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው ሴቶች የሚያጠቋቸውን ወንዶች እስከ መጨረሻው በኃይል መቃወማቸውን እንዲቀጥሉ ይመክራሉ።
የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመመከት በጉልበት ለመቃወም ለሴቶች ቀላል ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ሴቶች በሕይወታቸው ሁሉ ትሕትናን፣ ሰላማዊ መሆንንና የኃይል ማስፈራሪያ ቢያጋጥማቸው እንኳ ታዛዥነት የማሳየትን ባሕርይ እንዲያሳዩ ሆነው ስላደጉ ነው። ጥቃት ባጋጠመሽ ጊዜ ሳታመነቺ ውድ የሆነው ጊዜሽ እንዳይባክንብሽ የተቃውሞ እርምጃ ለመውሰድ መወሰን ይኖርብሻል።
ማንም በማስፈራራት ወይም ግፊት በማድረግ የማትፈልጊውን ነገር እንድታደርጊ ሲሞከር በጣም መቆጣት ይኖርብሻል። ጥቃቱ ቀደም ብሎ የተውጠነጠነ እንደሆነና አስገድዶ ለመድፈር እቅድ ያወጣው ሰው ፈቃዱን እሺ ብለሽ እንደምትፈጽሚለት ያሰበ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልግሻል። ሳትፈሪ ተቆጪ። “መፍራትሽ ትግል የገጠመሽ ሰው አሳቡን እንዲፈጽም ድፍረት የሚሰጠው ትልቁ መሣሪያው ነው” ሲሉ ተመራማሪዋ ሊንዳ ሌድሬይ ተናግረዋል። ከሥርዓት የወጣ ወይም ትዝብት ላይ የሚጥለኝ ድርጊት መፈጸም ይሆናል ብለሽ ይሉኝታ አይያዝሽ። አንድ ምሁር እንዳስቀመጡት “ጨዋ ልሁን ብሎ ከመደፈር ሌላውን መዳፈር ይሻላል።” በአብዛኛው የተቃጣባቸውን ተገዶ የመደፈር ሙከራ በመከላከል የተሳካላቸው ሳይፈሩ በሙሉ ልብ እርምጃ የወሰዱና መናከስ፣ መማታትንና መጮህን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን የተጠቀሙ ሴቶች ናቸው።
ሊደፍርሽ የተነሣውን ሰው መከላከል የማትችይበት ደረጃ ላይ ከደርስሽ ግን ጥቃቱን የፈጸመብሽን ሰው ለማስያዝ በሚያስችልሽ ነገር ላይ ትኩረት አድርጊ። ከተቻለም ሰውነቱን በመቧጠጥ እንዲደማ አድርጊ ወይም ልብሱን በመቅደድ ለማስረጃ የሚሆን የልብስ ቁራጭ እጅሽ ላይ አስቀሪ። ከዚያ በኋላ እርሱን ለመታገል አቅም ታጪ ይሆናል። በዚህ ጊዜ “‘እንዲደፍርሽ የፈቀድሽው አንቺ እንደሆንሽ በማሰብ’ ራስሽን መውቀስና ማውገዝ የለብሽም። ተገደሽ የተደፈርሽ መሆንሽን ‘ለማረጋገጥ’ ጉዳት ወይም ሞት እንዲደርስብሽም አያስፈልግም” ሲሉ ሮቢን ዋርሻው አይ ኔቨር ኮልድ ኢት ሬፕ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ሁኔታዎች አይገኙም፤ መቶ በመቶ ፍቱን የሆነ የመከላከያ ምክርም የለም። አስገድዶ ስለ መድፈር ምርምር ያደረጉ ሰዎችም እንኳ ጥቃት የሚደርስባት ሴት ምን ያህል መከላከል እንዳለባት ወይም ምን ዓይነት የመከላከያ መንገድ መጠቀም እንደሚገባት የሚስማሙበት አንድ ወጥ የሆነ ምክር የለም።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አስገድዶ የመድፈር ዝንባሌ ያለውን ሰው ለማወቅ የሚያስችል ምልክት
□ በመሳደብ ወይም ለነገሮች ያለሽን አመለካከት ችላ በማለት ወይም ሐሳብ ስታቀርቢ በመቆጣት ወይም በመናደድ ስሜትሽን ያቃልላል።
□ ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንዳለብሽ ወይም ጓደኞችሽ እነማን መሆን እንዳለባቸውና በመሳሰሉት ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር ሕይወትሽን ለመቆጣጠር ይሞክራል። ለመጫወት ቀጠሮ ባደረጋችሁበት ቀን ሁሉንም ውሳኔዎች ማለትም ምግብ መመገብ ያለባችሁ የት መሆን እንዳለበት ወይም ምን ዓይነት ሲኒማ መመልከት እንዳለባችሁ ራሱ መወሰን ይፈልጋል።
□ አለ ምክንያት ይቀናል።
□ በአጠቃላይ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ እንደሚመለከት ይናገራል።
□ የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ ለመስከር ወይም አደንዛዥ ዕፅ ወስዶ “ሞቅ” እንዲለው ይፈልጋል። አንቺም እንዲሁ እንድታደርጊ ይሞክራል።
□ ብቻችሁን እንድትሆኑ ወይም የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ይገፋፋሻል።
□ ለመጫወት ቀጠሮ ባደረጋችሁበት ቀን በምታወጡት ወጪ እንድትካፈይ አይፈልግም። ገንዘብ ልክፈል ካልሽ ይናደዳል።
□ እንቅ አድርጎ እንደ መያዝ ወይም እንደ መግፋት ባሉት ግልጽ ባልሆኑ መንገዶች ጉልበተኝነቱን ለማሳየት ይሞክራል።
□ ማለፊያ መንገድ እንድታጪ በማድረግ ወይም ወደ አንቺ በጣም ተጠግቶ በመቀመጥ፣ አትንካኝ እያልሽው በመነካካት ወይም ሳያውቅሽ አውቅሻለሁ በማለት ያስፈራራሻል።
□ ችግር ሲያጋጥመው ሳይናደድ ማሳለፍ አይችልም።
□ በእኩልነት አይመለከትሽም።
□ የጦር መሣሪያ መያዝ ያስደስተዋል። በእንስሳት፣ በልጆችና በጉልበት በሚበልጣቸው ሰዎች ላይ መጨከን ደስ ይለዋል።
አይ ኔቨር ኮልድ ኢት ሬፕ በሚል ርዕስ በሮቢን ዋርሻው ከተጻፈው መጽሐፍ የተወሰደ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በአብዛኛው የተሰነዘረባቻውን አስገድዶ የመድፈር ጥቃት በመቃወም የተሳካ ውጤት ያገኙት ሳይፈሩ በሙሉ ልብ እርምጃ የወሰዱና ከአንድ በላይ ዘዴዎችን የተጠቀሙ ሴቶች ናቸው