የዓለም ፍጻሜ ምን ያህል ቀርቧል?
አዲስ ዓለም ይህን ያህል በጉጉት የሚጠበቀው ለምንድን ነው?
የዓለም ፍጻሜ ይሆናል ሲባል ምን ማለት ነው? አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት ምድር በእሳት ተቃጥላ ትጠፋለች ማለት ነውን? ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም መዝሙር 104:5 “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት” ይላል።
በርከት ያሉ መቶ ዘመናት ወደኋላ ተመልሰን ከመጪው የዓለም ፍጻሜ በፊት የነበረውን የዓለም ፍጻሜ ብንመለከት የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንችላለን። “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም” በጣም ተበላሽቶና በአምላክ ላይ ዓምፆ ስለ ነበረ “በውኃ ሰጥሞ ጠፋ።” ይሁን እንጂ ያ ሰማያትና ምድር የነበሩት ዓለም በኖኅ ዘመን ደርሶ በነበረው የጥፋት ውኃ በጠፋ ጊዜ ግዑዞቹ ሰማያትና ምድር አልጠፉም። የሚመጣው የዓለም ጥፋትም ቢሆን በከዋክብት የደመቁትን ሰማያትም ሆነ ፕላኔቷን ምድር አያጠፋም።2 ጴጥሮስ 3:5, 6፤ ዘፍጥረት 6:1–8
መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማያት” እና “ምድር” የሚሉትን ቃላት በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚጠቀምባቸው ጊዜያት አሉ። “ሰማያት” የዚህ ዓለም አምላክ የሆነውን ሰይጣንን፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉትን የዓለም ገዥዎችና በሰማይ ያሉትን ክፉ መንፈሳውያን ኃይሎች ሊያመለክት ይችላል። እነዚህ ሁሉ የሰው ልጆችን በአጋንንታዊ ኃይል የሚቆጣጠሩ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 6:12) “ምድር” ብዙ ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ለማመልከት አገልግሏል። (ዘፍጥረት 11:1፤ 1 ነገሥት 2:1, 2፤ 1 ዜና መዋዕል 16:31፤ መዝሙር 96:1) 2 ጴጥሮስ 3:7 በእሳት ይጠፋሉ ያለው እነዚህን የዚህ ክፉ ዓለም ምሳሌያዊ ሰማያትና ምድር ነው።ገላትያ 1:4
ከዚያም አስከትሎ ጴጥሮስ ይህ አሮጌ ዓለም በአዲስ ዓለም እንደሚተካ አስደሳች ዜና ይነግረናል:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”2 ጴጥሮስ 3:13
ለቅሶና ሞት የሌለበት አዲስ ዓለም
ጴጥሮስ በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ጽድቅ እንደሚኖር የተናገረው ቃል በጣም የሚያስደስት ዜና ነው። ዮሐንስ ስለዚህ ዓለም የሚሰጠው ተጨማሪ መግለጫ ግን ያስፈነድቃል። በራእይ 21:3, 4 ላይ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፣ ከእነርሱም ጋር ያድራል። እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል። እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”
ይሖዋ ምድርን በእሳት ከማጥፋት ይልቅ ለዘላለም መኖሪያ እንድትሆን ለማድረግ ዓላማው ነው። “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ እንዲህ ይላል።”ኢሳይያስ 45:18
በዚህች ዓለም ውስጥ ጻድቅ ያልሆነ ሰው ስለማይኖር ጽድቅ የሚኖርባት ዓለም ትሆናለች። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና። ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” ምሳሌ 2:21, 22
መዝሙራዊው ዳዊትም በመንፈስ ተነድቶ ይህንኑ አረጋግጧል:- “ገና ጥቂት ኃጢአተኛም አይኖርም። ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”መዝሙር 37:10, 11
ኢየሱስም ቢሆን በተራራ ስብከቱ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ይህንን አረጋግጧል። እነዚህ ቅን ሰዎች “መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” እያሉ የሚጸልዩለት አዲስ የጽድቅ ሰማይ መንግሥታቸው ስለሚሆን ይባረካሉ።ማቴዎስ 5:5፤ 6:10
የዚህ አዲስ ዓለም ነዋሪዎች የሚያገኙት አስደሳች ሰላም ወደ እንስሳት እንኳን ይዳረሳል:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፣ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፣ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። . . . በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም። ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”ኢሳይያስ 11:6–9
ምን ያህል ቀርቧል?
ይህ ሁሉ ‘ላም አለኝ በሰማይ ነው’፣ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ብለህ የምታስብ ከሆነ ቆም በልና አስብ። ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ መገኘት የተነገረው ጥምር ምልክት ክፍል ከሆኑት ክስተቶች በተጨማሪ 1914 ክርስቶስ መገኘት የጀመረበት ዓመት መሆኑን ያመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት አለ። የይሖዋ ምሥክሮች 1914 ይሖዋ ምድርን እንዲያስተዳድር በሚያዘጋጀው መንግሥት ረገድ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ነገር የሚፈጸምበት ዓመት እንደሚሆን ሐምሌ 1879 ታትሞ በወጣው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ አስታውቀው ነበር። ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎችና የዓለምን ሁኔታ የሚከታተሉ ሰዎች 1914 በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ልዩ የሆነ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት መሆኑን ተገንዝበዋል። ይህንንም በሚቀጥለው ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ከሰፈረው መረዳት ይቻላል።
ኢየሱስ የተናገረው ሌላ ሁኔታ ደግሞ በማቴዎስ 24:21, 22 ላይ ይገኛል። “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።”
በተጨማሪም ኢየሱስ ይህ ጥምር ምልክት ምልክቱ በ1914 መታየት ሲጀምር በተመለከተው ትውልድ ዘመን ውስጥ ተፈጽሞ እንደሚያልቅ ተናግሯል። ማቴዎስ 24:32–34 ላይ እንዲህ ብሏል:- “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ። ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”
ይህ አሮጌ ዓለም ከጦርነቶቹ፣ ከረሐቡ፣ ከበሽታውና ከሞቱ ጋር ተጠራርጎ ሲጠፋ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነገር ይሆናል። በይሖዋ አምላክ የጽድቅ አዲስ ዓለም ሲተካ፤ ኀዘን፣ ለቅሶ፣ በሽታና ሞት ሲጠፋ መመልከት ፍጻሜ የሌለው ደስታና ተድላ ያስገኛል። ለታላቁ ፈጣሪ፣ ለጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ፣ ለይሖዋ አምላክ ደግሞ ዘላለማዊ ውዳሴ ያተርፍ ለታል።
ይህን የመሰለ አስደሳች የወደፊት ጊዜ ስለሚጠብቀን ብዙዎች የይሖዋ አዲስ የጽድቅ ዓለም ፈጥና ይህን በኀዘን፣ በወንጀል፣ በበሽታና በሞት የተሞላ ዓለም እንድትተካ መናፈቃቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ናፍቆታቸው በጣም ታላቅ በመሆኑ ምክንያት ጊዜው ከመድረሱ በፊት በዚህ ጊዜ ይመጣል ብለው መናገራቸው አያስገርምም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የምልክቱን አንዳንድ ክፍሎች ብቻ ተመልክተን ይህ አዲስ ዓለም ሊመጣ ነው ብለን የሐሰት ማስጠንቀቂያ በምንሰጥበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። በአሁኑ ጊዜ የተሟላው ጥምር ምልክት በመፈጸም ላይ ስለሆነ ይህ ክፉ ዓለም ጠፍቶ የይሖዋ አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ ቀርቧል ብለን በጉጉት እንድንጠብቅ የሚያስችለን ጠንካራ ማስረጃ አግኝተናል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
1914:- አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እንኳን ብዙ ሰዎች 1914 አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት ነው ይላሉ:-
“በዘመናችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ የሆነው በሂሮሽማ አቶሚክ ቦምብ የፈነዳበት ዓመት ሳይሆን 1914 ነው።”ረኔ አልብሬኽት ካሪዬ፣ ዘ ሳይንቲፊክ መንዝሊ፣ ሐምሌ 1951
“ከ1914 ወዲህ የዓለምን አዝማሚያ የሚከታተል ማንኛውም ሰው ዓለም አስቀድሞ የተወሰነላት በሚመስል ሁኔታ ወደ ባሰ እልቂትና ጥፋት እየገሰገሰች ያለች መሆንዋን በመመልከት መጨነቁ አይቀርም። ብዙ አሳቢ ሰዎች ወደ ጥፋት የምናደርገውን ጉዞ አቅጣጫውን ለማስቀየር ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ይሰማቸዋል።”በርትራንድ ራስል፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን፣ መስከረም 27, 1953
“አዲሱ ዘመን . . . የጀመረው በ1914 ነው። መቼ ወይም እንዴት እንደሚያበቃ ግን የሚያውቅ የለም። . . . መጨረሻው የመላው የሰው ልጅ እልቂት ሊሆን ይችላል።”ዘ ሲያትል ታይምስ፣ ጥር 1, 1959
“አንደኛው የዓለም ጦርነት መላው ዓለም ተናጋ። ለምን እንዲህ እንደሆነ ግን እስከ አሁን አናውቅም። . . . የሰው ልጅ የሚያልማቸውን ነገሮች በሙሉ ሊያገኝ የተቃረበ ይመስል ነበር። ሰላምና ብልጽግና ተስፋፍቶ ነበር። ሁሉ ነገር በድንገት ከመሠረቱ የተናጋው በዚህ ጊዜ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ትንፋሻችን ቀጥ ብሎ የቆመ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን።”ዶክተር ዎከር ፐርሲ፣ አሜሪካን ሜዲካል ኒውስ ኅዳር 21, 1977
“በ1914 ዓለም የነበራትን የእርስ በርስ ስምምነት አጣች። እስካሁን ድረስም ይህን ያጣችውን ስምምነት መልሳ ለማግኘት አልቻለችም። . . . ይህ ዘመን ከብሔራት ድንበሮች ውጭም ሆነ በብሔራት ድንበር ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዓመፅና ብጥብጥ የታየበት ዘመን ነው።”ዚ ኢኮኖሚስት ለንደን፣ ነሐሴ 4, 1979
“ሁሉ ነገር ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ይሄድ ነበር። የተወለድኩበት ዓለም ይህን ይመስል ነበር። . . . በአንድ የ1914 ጠዋት ግን ይህ ሁሉ ነገር ሳይታሰብ በድንገት ወደመ።”ሐሮልድ ማክሚላን የተባሉት የእንግሊዝ መራሔ መንግሥት፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ኅዳር 23, 1980
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰው ሁሉ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጹም ሰላም ያገኛል