ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ሥራ ፈትቶ ጊዜን ስለማባከን ምን ለማለት ይቻላል?
የሱቅ በረንዳዎች፣ ሻይ ቤቶች፣ የመንገድ ማዕዘኖችና ገበያዎች ሀብታምም ሆኑ ድሃ ወጣቶች ተጎልተው የሚውሉባቸው ቦታዎች ሆነዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ብዙ ወጣቶች በየሱቁ በረንዳ በመቆም ጊዜያቸውን በሥራ ፈትነት ያሳልፋሉ። እንደነዚህ ባሉት ቦታዎች ወጣቶች ለበርካታ ሰዓታት ሲንቀዋለሉ ይታያሉ። አንዲት ወጣት ልጅ “የሱቅ በረንዳዎች ብዙ ነገሮች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች ስለሆኑና ጥሩ ቁመና ያላቸውን ወንዶች የመሳሰሉ ዓይን የሚስቡ ነገሮች ምንጊዜም ስለማይታጣባቸው ሁልጊዜ የምናዘወትራቸው ቦታዎች ናቸው” ብላለች።
በአካባቢህ ትላልቅ የሱቅ በረንዳዎች ባይኖሩስ? የጎዳና ዳርቻ ወይም ባዶ ሜዳ መኖሩ አይቀርም። የ15 ዓመቷ ታሪ እንዲህ ትላለች:- “እኔና ጓደኞቼ አቅራቢያችን ወደሚገኝ መናፈሻ ቦታ በመኪና እንሄድና መኪኖቻችን ኮፈን ላይ ቁጭ ብለን ለብዙ ሰዓታት እናወራለን።”—ቲን መጽሔት፣ መስከረም 1990
እርግጥ ነው፣ ሥራ ፈትቶ ጊዜን ማሳለፍ ዛሬ የተፈጠረ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ነገር በመናገርና በመስማት ብቻ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይወድዱ” ስለነበሩ የጥንት ሰዎች ይናገራል። (ሥራ 17:21 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የጊዜ ማሳለፊያ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ለምንድን ነው?
በኤፍ ፊሊፕ ራይስ የተዘጋጀው ዘ አዶለሰንት የተባለ መጽሐፍ እንደሚለው ጎረምሶች “የአንድ ቡድን አባል መሆን እንደሚያስፈልጋቸው እየተሰማቸው ይሄዳል። እኩዮቻቸው እንዲወዷቸው ይፈልጋሉ።” ስለዚህ ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር ሥራ ፈትተው መዋላቸው ባልንጀራና ድጋፍ የማግኘት ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል።
ሌሎች ወጣቶች ደግሞ የሚያድርባቸውን የመሰልቸት ስሜት የሚያስወግድላቸው ዘዴ ሆኖ ይታያቸዋል። ወጣቷ ሚሸል እንዲህ በማለት ታስረዳለች:- “ማታ እቤት ቁጭ ማለት ይሰለቻል። ወጣ ብሎ ካልተጫወቱ ምሽቱ በጣም አሰልቺ ይሆናል።” የአሥራ ስድስት ዓመቱ ኤድ ያለምንም ሥራ ከጓደኞች ጋር ጊዜን ማሳለፍ “ችግር ውስጥ ከመግባት ያድናል” ብሏል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ችግር ውስጥ ከመግባት ያድናል?
ሰዎች ሥራ ፈትተው ጊዜ የሚያሳልፉት መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ከጓደኛ ጋር መጨዋወትንና መዝናናትን አያወግዝም። ቢሆንም “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ምሳሌ 13:20) ታዲያ ተኮልኩለው ጎዳና ላይ ከሚቆሙ ወጣቶች መካከል ጠቢባን ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የጠለቀ አክብሮት ያላቸው ናቸው ሊባሉ የሚችሉት ስንቶቹ ናቸው? ሁከት ፈጣሪዎች ወይም ረብሸኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጊዜ የተረፋቸውና ኑሮ የሰለቻቸው ወጣቶች በዛ ብለው ከተሰባሰቡና ተቆጣጣሪ ካጡ ችግር መፈጠሩ የማይቀር ነው።
በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ ፈትቶ ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍን አይደግፍም። ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ በተሰሎንቄ ከተማ ሳሉ የሆነውን ነገር እንመልከት። የክርስትናን መልእክት የሚቃወሙ ሰዎች “ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ። ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ።” (ሥራ 17:5) የቫይን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ተስታመንት ወርድስ እንደሚለው ከሆነ እነዚህ በገበያ አካባቢዎች የሚውሉ ሥራ ፈቶች “ከገበያ አካባቢዎች የማይጠፉና አንዳች ጉዳይ ሳይኖራቸው ሲያውደለድሉ የሚውሉ ግለሰቦች ነበሩ።” እንዲህ መሆኑ የሚያስደስት ነው? እነዚህ ሥራ ፈቶች ጳውሎስ ለሚያሰማው መልእክት ምንም ደንታ ወይም የመስማት ፍላጎት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ምንም የሚሠሩት ሥራ ስላልነበራቸው በቀላሉ ተነሳስተው ረብሻ እንዲፈጠር አድርገዋል።
ተንኮልና ሁከት
አሁንም ቢሆን ሥራ ፈት የሆኑ ወጣቶች አንድ ላይ በሚሰባሰቡበት ጊዜ ምን ዓይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አስብ። ሁከት ወይም ረብሻ እንዲፈጠር የሚፈልግ የለም። በአንድ ትምህርት ቤት የመኪና ማቆሚያ መቆም የሚያዘወትረው የ16 ዓመቱ ኬን “የምናደርገው ነገር እምብዛም አይኖርም። መኪናችን ውስጥ ተቀምጠን ለዛ ቢስ ቀልዶችን ወይም ከሴት ጓደኞቻችን ጋር ስላሳለፍነው ጊዜ እናወራለን” ብሏል። አዎን፣ ስለ ስፖርት፣ ስለ ሙዚቃና ስለ ተቃራኒ ጾታ የሚነገሩ ወሬዎች ለጥቂት ጊዜ ሁሉንም ሊያስደስቱ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ማውራት ብቻውን ወጣቶችን የሚያሰለች ይሆናል።
ሚሃሊ ቺክሴንትሚሃሌ እና ሪድ ላርሶን የተባሉት ተመራማሪዎች የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል:- “[ወጣቶች] እነዚህ ሥራ ፈትተው የሚውሉባቸው ወቅቶች ብዙ ብልግና፣ ጩኸት፣ ረብሻና ሁከት የሚታዩባቸው እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። . . . ወጣቶቹ በየግላቸው ብልግና የመፈጸም ዝንባሌ ባይኖራቸውም እኩያሞች አንድ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ሁከት ወይም ረብሻ እንዲያነሱ የሚቀሰቅስ አንድ ነገር የሚኖር ይመስላል። . . . ከሚፈጽሟቸው ግብረገብነት የጎደላቸው ድርጊቶች መካከል በመኪና ሆኖ እየጮሁ መዞር፣ ሰዎች ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር፣ እርስ በርስ መደባደብ ይገኙበታል።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)—ቢይንግ አዶለሰንት
እርግጥ፣ ጓደኞችህ መጥፎ ነገር ስላደረጉ አንተም ታደርጋለህ ማለት ላይሆን ይችላል። ቢሆንም መጥፎ ድርጊት በሚያደርጉ ሰዎች መካከል ስትሆን አንተም መጥፎ ድርጊት እንድትፈጽም ከፍተኛ ግፊት ይደርስብህ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በመጥፎ ድርጊታቸው ባትካፈልም እንኳን በዚያ ቦታ መገኘትህ ብቻውን ሌሎች በአንተ ላይ የተሳሳተ ግምት እንዲያሳድሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። የዕብራውያን አባት የነበረው የያዕቆብ ሴት ልጅ ዲና የደረሰባት እንዲህ ያለ ሁኔታ ነበር።
የዲና ቤተሰቦች ይኖሩ የነበረው የጾታ ብልግናና የጣዖት አምልኮ በጣም በተስፋፋበት የከነዓን ምድር ቢሆንም ዲና የይሖዋ አምላኪ ሆና ያደገች ልጅ ነበረች። አባቷ ያዕቆብ ከሴኬም ከተማ ራቅ ብሎ በመስፈርና የራሱን የውኃ ጉድጓድ በመቆፈር ምግባረ ብልሹ ከሆኑት የከነዓናውያን ሰዎች ጋር የሚገናኙበትን አጋጣሚ በጣም ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ዘፍጥረት 33:18፤ ዮሐንስ 4:12) ይሁን እንጂ ዲና አዘውትራ ሊሆን ይችላል “የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት” ትወጣ ነበር። (ዘፍጥረት 34:1) ዲና ሥራ ፈትታ ከከነዓናውያን ጋር መዋሏ ጉዳት እንደሌለው ጊዜ ማሳለፊያ አድርጋ አስባ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከነዓናውያን ሴቶች በዘማዊነታቸው የታወቁ ነበሩ። ስለዚህም ሴኬም የተባለ አንድ ከነዓናዊ ሰው ከእነዚህ ሴቶች ጋር ሆና ዲናን ሲመለከት “ወሰዳት፣ ከእርስዋም ጋር ተኛ፣ አስነወራትም።”—ዘፍጥረት 34:2
አንተም ከመጥፎ ልጆች ጋር ብትውል በተመሳሳይ ሁኔታ ከባድ ችግር ውስጥ ልትወድቅ ትችላለህ። ሊዎናርድ የተባለ አንድ ወጣት ወላጆቹ በክርስቲያናዊ መንገድ ያሳደጉት ቢሆንም “ከዓመፀኛ ልጆች ጋር መዋል” እንደጀመረ ያስታውሳል። “መጠጥ መጠጣት በሚፈቀድበት ዕድሜ ላይ ገና ያልደረስኩ ብሆንም እየዞርን ቢራ መጠጣት ጀመርን። አሥራ ስምንት ዓመት በሞላኝ ጊዜ ማሪዋና አጨስ ነበር” ይላል።
ጊዜህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም
ጥናት ከተደረገባቸው ወጣቶች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ወደ ትላልቅ ሱቅ በረንዳዎች በመሄድ በየቀኑ ከሦስት እስከ አምስት ሰዓት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ሲያሳልፉ፣ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስድስት ሰዓት ያሳልፋሉ። ጠቢብ የሆነ ወጣት ግን ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ከማባከን ይልቅ ‘ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ዘመኑን ይዋጃል።’—ኤፌሶን 5:15, 16
እንዳተ ካሉ ወጣቶች ጋር ጊዜህን ያለሥራ በማሳለፍህ ምክንያት የትምህርት ቤት ወይም የቤት ውስጥ ሥራህ ተበድሏልን? መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህ፣ ማለትም የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችህና ለሌሎች የመመስከሩ ሥራህስ? እንደዚህ ያሉትን ኃላፊነቶች ችላ እያልክ ነውን? ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልህ ከሆንክ’ በሥራ ፈትነት የምታሳልፈው ጊዜ አይኖርህም።—1 ቆሮንቶስ 15:58
ጤናማ የሆኑ አማራጮች
መዝናናት አስፈላጊ የሆነ የሕይወት ክፍል ነው። (መክብብ 3:4) ይሁን እንጂ ለመዝናናት ብቸኛው መንገድ በሥራ ፈትነት መንቀዋለል አይደለም። ሉሲ የተባለች አንዲት ወጣት ሴት እንዲህ ትላለች:- “ለብቻዬ ሆኜ የማሳልፈው ጊዜ በጣም ያስደስተኛል። ማንበብ እወዳለሁ። ይህም የሌሎች አገሮችን ታሪክ፣ ባሕልና ቋንቋ የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርብኝ ረድቶኛል። ሙዚየሞችንና የሥነ ጥበብ ማዕከሎችን እጎበኛለሁ። ልብስ እሰፋለሁ፣ ምግብ እሠራለሁ። ሥዕል መሳልና ደብዳቤ መጻፍ ያስደስተኛል። አልፎ አልፎ ደግሞ ግጥም ለመጻፍ እሞካክራለሁ።” ስለሆነም ብቸኛ መሆን የግድ አሰልቺ ነው ማለት አይቻልም።
የገዛ ራስህ ቤተሰብም ጤናማ የሆነ መዝናኛ ሊፈጥርልህ ይችላል። ቸኩለህ ይህን ሐሳብ ከማጣጣልህ በፊት ጃክ የተባለ አንድ ወጣት የተናገረውን አዳምጥ። ያለፈውን በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “ወላጆቼ ሁልጊዜ አንድ ነገር እንድንሠራ እቅድ ያወጡልን ነበር። ኳስ እንጫወታለን፣ መናፈሻዎችን፣ አራዊት የሚታዩባቸውን ቦታዎችና ቤተ መዘክሮች እንጎበኛለን። ሁሉም የቤተሰብ አባል አንድ ላይ ሆኖ የሚሠራ ከሆነ ግቢ ወይም ቤት ማጽዳት እንኳን አስደሳች ሊሆን ይችላል።” ምናልባት ያንተ ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ የመሥራቱን ልማድ ቀስ በቀስ ትቶት ይሆናል። ከሆነ ሁላችሁም ወጣ የምትሉበት አንድ ዝግጅት እንዲደረግ አንተ ራስህ ለምን ሐሳብ አታቀርብም? ከምታስበው በላይ ሊያስደስትህ ይችላል!
ይህ ማለት ግን ከእኩዮችህ ጋር የሚያስደስት ጭውውት ማድረግ ወይም አብረህ እየተዝናናህ የምታሳልፈው ጊዜ ሊኖርህ አይገባም ማለት አይደለም። ጓደኞችህን ግን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል። ኤንሪኬ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ከዓለማዊ ወጣቶች ጋር ያለ ሥራ ጊዜዬን አሳልፍ ነበር። ይሁን እንጂ ሕይወቴን ለይሖዋ አገልግሎት ከወሰንኩ በኋላ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወጣቶች ጋር ብቻ መጎዳኘት ጀመርኩ። አብረን በስብከት ሥራ ተሰማርተን እንውላለን፣ አብረን ኳስ እንጫወታለን። በተቻለ መጠን ብዙውን ነገር ከእነርሱ ጋር ለመሥራት እሞክራለሁ።”
ሽሊስም በተመሳሳይ ከመጥፎ ወጣቶች ጋር ጊዜዋን ታሳልፍ ነበር። ስለ ቀድሞ ጓደኞችዋ እንዲህ ትላለች:- “ሕይወታቸው ዓላማና አቅጣጫ የለውም። ከእነርሱ ለመለየት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል። ከተለየኋቸው በኋላ ግን ራሴን በጥሩ ባልንጀሮች አጠርኩ። በመንፈሳዊ ለማደግ የቻልኩት ከዚያ በኋላ ብቻ ነው።”
ስለዚህ ሥራ ፈት ሆኖ ከሌሎች ጋር ጊዜን ማሳለፍ አስደሳች የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም በመንፈሳዊ ይጎዳህ እንደሆን እንጂ ፈጽሞ አይጠቅምህም። ብልህ ሁን። ጊዜህን በተሻለ መንገድ ልትጠቀም የምትችልበትን መንገድ ፈልግ።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጊዜህን ሥራ ፈት ሆነህ ከማባከን ይልቅ ለተሻለ ተግባር ልትጠቀምበት አትችልም?