የጃሹዋ ምኞት
መጋቢት 6, 1992 የውድ ቤተሰብ ከሁሉም በዕድሜ የሚያንሰውና ሰባት ዓመት የሆነው የቤተሰባቸው አባል፣ ጃሹዋ ሉኬሚያ የተባለ በሽታ እንደ ያዘው አወቀ። ይህ በሽታ ለሞት የሚያደርስ በሽታ ነው። 16 ዓመት የሆነው የጃሹዋ ታላቅ ወንድም፣ 19 ዓመት የሆናት ታላቅ እህቱና አባቱ የይሖዋ ምሥክሮችና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ሌላው የጃሹዋ ወንድም አሥር ዓመቱ ነው።
ጃሹዋን ለማከም ከባድ መድኃኒቶች ይሰጠው ጀመር። እነዚህ መድኃኒቶች ከሚያስከትሉት መጥፎ ውጤቶች አንዱ የምግብ ፍላጎት ማጣት ስለነበረ ጃሹዋን ምግብ እንዲበላ ማድረግ ማቆሚያ የሌለው የዘወትር ትግል ሆነ። በሐምሌ ወር መላው ቤተሰብ ዊኒፊልድ ከሚገኘው መኖሪያቸው እምብዛም ሩቅ ባልሆነው በላፋዬት ሉዊዚያና በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ለመገኘት ወሰነ። ጃሹዋ በዚህ ስብሰባ ላይ እንዳለ በሽታው ስለጠናበት ቅዳሜ ጠዋት ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተወሰደ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ወላጆቹ አዘውትሮ ይታከምበት ወደነበረው የኒው ኦርሊየንስ ሆስፒታል ወሰዱት።
ቤተሰቡ በኒው ኦርሊየንስ ሳለ አንድ የማኀበራዊ ኑሮ ሠራተኛ ለጃሹዋ እናት ለኤፕሪል በጣም የታመሙ ልጆች የሚመኙትን ምኞት እንዲፈጸምላቸው የሚያደርግ ፕሮግራም እንዳለ ይነግራታል። በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የሚያመለክቱበት ቅጽ ይሰጣቸውና ኤፕሪልና ባልዋ ቅጹን ይሞላሉ። ጃሹዋ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በየወሩ ለሚያደርገው የክትትል ምርመራ ወደ ኒው ኦርሊየንስ ሲመጣ የዚህ ፕሮግራም ተወካይ የሆነ ጂም የተባለ ሰው ጃሹዋን ስለሚመኘው ነገር ሊጠይቀው ይመጣል።
ጃሹዋ “ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ እፈልጋለሁ” አለ።
ልጆች ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉት ወደ አንድ መጫወቻ ቦታ እንዲወሰዱ ስለሆነ ጃሹዋ ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ የፈለገበት ምክንያት ለጂም እንግዳ ይሆንበታል። “የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ለማየት እፈልጋለሁ” ይለዋል።
“መጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምንድን ነው?” ሲል ጂም ይጠይቀዋል።
“መጽሔቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጽሐፎችና ትራክቶች የሚያዘጋጁበት ቦታ ነው” ብሎ ይመልስለታል።
ኤፕሪል ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤትና በዚያ ስለሚካሄደው ጽሑፍ የማዘጋጀት ሥራ ለጂም ተጨማሪ ማብራሪያ ትሰጠዋለች። “በአሁኑ ጊዜ ወንድሜ ይህን ስፍራ በመጎብኘት ላይ ነው። እኔም ከሁሉም ቤተሰቦቼ ጋር ለመሄድ እፈልጋለሁ” አለ ጃሹዋ።
ጂም የቤተሰቡ አባላት ስድስት እንደሆኑ ሲያውቅ ጃሹዋ በፍሎሪዳ ወደሚገኘው ዲስኒ ወርልድ ወደሚባለው የመዝናኛ ቦታ ቢሄድ እንደሚሻለው ይነግረዋል። ጃሹዋ ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ የነበረውን ፍላጎቱን ለመለወጥ ፈጽሞ አልፈለገም። ጂም ይህ ምኞቱ ሊፈጸምለት ይችል እንደሆነ እርግጠኛ አለመሆኑንና ነገሩን ማጣራት እንደሚያስፈልገው ይነግረዋል። ጂም ሁለተኛ ምኞቱ ምን እንደሚሆን ጃሹዋን ይጠይቀዋል።
“የአይ ቢ ኤም ኮምፒዩተር ነው” ሲል ጃሹዋ ይመልሳል።
“አይ ቢ ኤም የፈለግኸው ለምንድን ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል።
በዲስኬት ላይ የተቀረጸውን መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማግኘት ስለሚፈልግ እንደሆነ ጃሹዋ ይነግረዋል። (ጃሹዋ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዲስኬት የሚሠራው በአይ ቢ ኤም ፕሮግራም ሊሠሩ በሚችሉ ኮምፒዩተሮች እንደሆነ ያውቅ ነበር።) ጂም አሁንም “ወደ ዲስኒ ወርልድ ለመሄድ እንደማትፈልግ እርግጠኛ ነህ?” ብሎ ይጠይቀዋል።
ጃሹዋ “እርግጠኛ ነኝ” ሲል መለሰለት።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ጂም ተመልሶ ጃሹዋ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ኒውዮርክ ለመሄድ የጠየቀው ምኞት ሊፈጸምለት የተፈቀደ መሆኑን ይነግረዋል። የጃሹዋ እናት “ጆሽ አብዛኞቹን ሰዎች በደስታ የሚያስፈነድቃቸው ነገር እምብዛም የማያስደንቀው ልጅ ነው። እኔ ግን በደስታ ፈነጠዝኩ” አለች።
መስከረም 30 ቀን የውድ ቤተሰብ በአውሮፕላን ከኒው ኦርልየንስ ወደ ኒው ዮርክ መጣ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት መጥቶ ኒው ዮርክ ይገኝ ከነበረው ከትልቁ ልጅ ከበዲ በስተቀር ሁሉም የመጠበቂያ ግንብን ዋና መሥሪያ ቤት አይተው አያውቁም። ስድስቱም በማንሃታን ኒው ዮርክ በሚገኘው በራማዳ ሞቴል እንዲያርፉ ተደረገ። ከኢስት ሪቨር ባሻገር በብሩክሊን ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የጽሑፍ መላኪያ፣ የማተሚያ፣ የቢሮና የመኖሪያ ሕንፃዎች የሚያደርሳቸው በሾፌር የሚነዳ ለታላላቅ ባለ ሥልጣናት የሚዘጋጅ ምቹ መኪና ተዘጋጅቶላቸዋል።
ቤተሰቡ በኒው ዮርክ በቆየባቸው ሁለት ቀናት ዋናውን መሥሪያ ቤት በአስጎብኚዎች አማካኝነት ተዘዋውረው ተመለከቱ። በአንደኛው ቀን የቢሮ ሕንፃዎቹንና ባለ አምስት ሕንፃ የሆነውን ፋብሪካ ጎበኙ። በሚቀጥለው ቀን 90,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ለጽሑፍ መላኪያ፣ ለቴፕ ማባዣና ለተለያዩ ሌሎች ሥራዎች የሚያገለግል ሕንፃ ጎበኙ። በተጨማሪም ሦስት ሺህ ለሚያክሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች መኖሪያነት ከሚያገለግሉት 21 ሕንፃዎች አንዳንዶቹን ጎበኙ። ቤተሰቡ በዚያ በቆየበት ጊዜ ከዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር ከአሥር የመመገቢያ አዳራሾች መካከል በአንዱ ሦስት ጊዜ ምግብ እንዲጋበዙ ልዩ ዝግጅት ተደርጓል።
ጥቅምት 3 ቀን ቤተሰቡ መኪና ተከራይቶ 160 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ሰሜን ከተጓዘ በኋላ የመጠበቂያ ግንብን እርሻ ጎብኝቷል። በዚያ የሚገኘውን ግዙፍ የማተሚያ ሕንፃና የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከሚመገቡት ምግብ አብዛኛው የሚመረትበትን ቦታ ተመልክቷል። ከሰዓት በኋላ ደግሞ ገና ግንባታው ያላለቀለትን ከመጠበቂያ ግንብ እርሻ የአንድ ሰዓት ያህል መንገድ ርቆ ፓተርሰን ኒው ዮርክ አጠገብ የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ጎበኙ። መሽቶ ፀሐይ ከጠለቀ በኋላ ወደ ኒው ዮርክ ተመለሱ።
በማግስቱ በተዘጋጀላቸው በጣም ምቹ የሆነ ትልቅ መኪና ወደ ኒው ዮርክ ኬኔዲ አውሮፕላን ማረፊያ ተወስደው ወደ ኒው ኦርሊየንስ በአውሮፕላን ተመለሱ። ጃሹዋ “መጽሔቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጻሕፍትና ትራክቶች የሚዘጋጁበትን” ቦታ ለማየት የተመኘው ምኞት ተፈጸመለት። የውድ ቤተሰብ የምኞት መፈጸሚያው ፕሮግራም ወጪያቸውን በሙሉ ከፍሎ ይህን በመንፈሳዊ የሚያንጽ ፕሮግራም ስላዘጋጀላቸው በጣም አመስግነዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ጃሹዋ በየወሩ ለሚያደርገው የክትትል ምርመራ ሆስፒታል ገብቶ እንዳለ ዝነኛ የሆነው ጋርት ብሩክስ የተባለ የካንትሪና ዌስተርን ሙዚቃ ዘፋኝ በሞንሮ ሉዊዝያና ትርዒት በሚያሳይበት ጊዜ ጃሹዋ በእንግድነት እንዲገኝ ተጋበዘ። ትርዒቱ ሲያልቅ ሚስተር ብሩክስ ጃሹዋና አባቱን ከመድረኩ ጀርባ መጥተው እንዲያነጋግሩት ጋበዛቸውና ጃሹዋ “በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር ትችላለህ ” የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ ለሚስተር ብሩክስ ሰጠው። ጃሹዋ ሚስተር ብሩክስን ስለ ሴት ልጁ ጤንነት በጠየቀው ጊዜ (ሚስተር ብሩክስ ትንሽ ልጅ አለችው) የሚስተር ብሩክስ ልብ በጃሹዋ አሳቢነት በጣም ተነካ።
አንድ ትንሽ ልጅ ስለ ሌሎች ደህንነት ሲያስብ፣ በተለይ ደግሞ የሚያደርጋቸው ምርጫዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለውን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሲሆን በእርግጥም በጣም ያስደስታል። እናንተስ የተመኛችሁት ነገር እንደሚፈጸምላችሁ ቢነገራችሁ ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን በመንፈሳዊ የሚጠቅም ነገር ትመርጣላችሁን?
[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጃሹዋና ቤተሰቡ የጎበኟቸው ቦታዎች
በስተ ቀኝ:- የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል
ከታች:- የመጠበቂያ ግንብ ቢሮ ሕንፃ
በስተ ግራ:- 360 ፉርማን ሕንፃ የጽሑፍ መላኪያ ክፈሉ የሚገኝበት ሕንፃ
ከታች:- የፋብሪካ ሕንፃ
በስተ ግራ:- የመጠበቂያ ግንብ እርሻና የማተሚያ ሕንፃ