የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 7/8 ገጽ 23-27
  • በርካታ ጥቅሞች ያሉት የማሽተት ስሜት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በርካታ ጥቅሞች ያሉት የማሽተት ስሜት
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሽታዎችና በአንተ ላይ የሚያስከትሉት ውጤት
  • ይህን ስጦታ ታደንቃለህን?
  • የውሾች የማሽተት ችሎታ
    ንድፍ አውጪ አለው?
  • ጣዕም የመለየት ችሎታህ
    ንቁ!—2008
  • ልዩ ለሆኑት ስጦታዎችህ አመስጋኝ ሁን
    ንቁ!—2011
ንቁ!—1994
g94 7/8 ገጽ 23-27

በርካታ ጥቅሞች ያሉት የማሽተት ስሜት

ትዝታዎችን ይቀሰቅሳል፣ ጣዕሞችን ያዳብራል

በጣም የምትወደው ሽታ ምንድን ነው? ይህ ጥያቄ ለብዙ የተለያዩ ሰዎች ቀርቦላቸው በጣም የሚያስደንቅ መልስ ሰጥተዋል። የጥብስ ሥጋ ሽታ፣ ከውቅያኖስ የሚመጣ የጨዋማ ባሕር ሽታ፣ ታጥቦ የተሰጣ ልብስ ሽታ፣ አዲስ የታጨደ ድርቆሽ ሽታ፣ የቁንዶ በርበሬ ሽታ፣ የቡችላ ትንፋሽ ሽታ ያሉ ነበሩ። እነዚህን ሽታዎች ለምን እንደወደዷቸው ሲጠየቁ ሁሉም እነዚህን ሽታዎች ሲያሸቱ ትዝ የሚሉአቸው ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል። ብዙውን ጊዜ ትዝ የሚሏቸው ነገሮች በልጅነት ዕድሜያቸው ያጋጠሟቸው ነበሩ።

አንዲት ወጣት ሴት ጠዋት አልጋዋ ላይ እንደተኛች የሚሸታት የጥብስ ሽታ ቁርስ መድረሱን ያሳውቃት እንደነበረ አስታውሳለች።

የ58 ዓመቷ ሉዊስ የባሕር አየር ሽታ፣ ልጅ ሳለች በዩናይትድ ስቴትስ በሜይን የባሕር ዳርቻ ታሳልፍ የነበረውን የበጋ ወራት እንደሚያስታውሳት ተናግራለች። “በአሸዋው ላይ እየተሯሯጥን ስንጫወት፣ ክላም የተባለውን ቀንድ አውጣ መሰል ፍጥረት ከአሸዋው ውስጥ ቆፍረን አውጥተን ከቤት ውጭ ባነደድነው እሳት ላይ ስንጠብስ የነበረን ነፃነት ትዝ ይለኛል” ብላለች።

የ72 ዓመቷ ሚሸል ልጅ ሳሉ በልብስ መስቀያ ሽቦ ላይ የተሰጡትን ልብሶች በክንዳቸው ሙሉ ተሸክመው ወደ ቤት ሲያስገቡ ፊታቸውን ልብሱ ውስጥ ቀብረው ንፁሕ የሆነውን የልብስ ሽታ ያሸቱ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

በ55 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ጀረሚን ደግሞ ባደገበት የአዮዋ ክፍለ ሀገር የእርሻ ቦታ ከአባቱ ጋር ሆኖ አዲስ የታጨደውን ድርቆሽ ከዝናብ ለማሸሽ በጋሪ ጭነው ወደ ቤት ያስገቡ የነበረበትን ዘመን የሚያስታውሰው አዲስ የታጨደ የድርቆሽ ሽታ ነው።

የ76 ዓመቷ ጀሲ በልጅነታቸው የቁንዶ በርበሬ ሽታ ሲሸታቸው አፕል በተር የተባለው በዩናይትድ ስቴትስ የሚሠራ ቅመም የሚበዛበት ማርማላት በብረት ጀበና ከቤት ውጭ በመቀቀል ላይ መሆኑን ያውቁ ነበር። ይህ የሆነው ከ70 ዓመት በፊት ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ትዝታው ከአእምሮአቸው አልጠፋም።

ካሮል በአምስት ዓመት ዕድሜዋ ጭንዋ ላይ ትታቀፋት የነበረችውን ቡችላ ሽታ ታስታውሳለች። አዎን፣ ይህ ሽታ ትንሽ የሕፃን ልብስ ለብሳ በአሮጌው በረንዳ ላይ ፀሐይ ትሞቅ የነበረበትን ጊዜ ያስታውሳታል።

አንተስ? በጣም የሚያስደስትህ፣ ትዝታዎችንና ስሜትህን የሚቀሰቅስብህ ሽታ አለን? ከተራራማ ሥፍራ የሚመጣ የደን ሽታ ወይም ከባሕር የሚመጣ ነፋስ ሽታ መንፈስህን አድሶት ያውቃልን? አለበለዚያም አዲስ የሚጋገር ዳቦ አሽትተህ አፍህ ምራቅ ሞልቶ ይሆናል። ጎርደን ሸፐርድ የተባሉት የነርቭ ሳይንቲስት በናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት ላይ እንዲህ ብለዋል። “ሕይወታችን የሚገዛው በማየት ስሜታችን ይመስለናል። ይሁን እንጂ ወደ ገበታህ በቀረብህ መጠን ከሕይወት የምታገኘው ደስታ ምን ያህል ከማሽተት ስሜት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለመገንዘብ ትችላለህ።”

ሽታ የመቅመስ ችሎታችንን በጣም ያዳብረዋል። ጣዕም የሚለዩት የምላሳችን ሕዋሶች ጨዋማ፣ ጣፋጭ፣ መራራና ኮምጣጣ ጣዕሞችን የመለየት ችሎታ ሲኖራቸው የቀሩትን የተለያዩ ጣዕሞች ለመለየት የሚያስችለን የማሽተት ችሎታችን ነው። ፖምና ሽንኩርት የተለያየ ሽታ ባይኖራቸው ኖሮ አንድ ዓይነት ጣዕም ይኖራቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል አፍንጫህን ይዘህ ቸኮላት ብትበላ ምን ያህል ጣዕም የሌለው እንደሚሆን ልትረዳ ትችላለህ።

አንድ የሚያስጎመጅ ምግብ፣ እንበል ገና ከመጥበሻው የወረደ ትኩስ ጥብስ፣ በዓይን ሕሊናህ ይታይህ። ያን የመሰለ የሚያስጎመጅ ሽታ የወጣው ጥብሱ ሞልኪዩሎችን በዙሪያው ባለው አየር ውስጥ ስለሚረጭ ነው። አፍንጫህ እነዚህን ሞልኪዩሎች በጉጉት ይስባል። አየሩን ይስብና እነዚህ ሞልኪዩሎች አስደናቂ በሆነው የማሽተት መሣሪያ በኩል እንዲያልፉ ያደርጋል።

የማሽተት ስሜት እንዴት እንደሚሠራ ተጨማሪ ማብራራያ ለማግኘት በገጽ 24 እና 25 የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት። የዚህ ስሜት ውስብስብነትና ረቂቅነት በጣም የሚያስደንቅ ነው።

ሽታዎችና በአንተ ላይ የሚያስከትሉት ውጤት

የሽቶ ቀማሚዎች፣ ታላላቅ ወጥ ቤቶችና ወይን ጠጅ ጠማቂዎች ሽታዎች አእምሮን የመማረክና ስሜቶችን የማስደሰት ኃይል እንዳላቸው ከተገነዘቡ በርካታ መቶ ዘመናት አልፈዋል። ዛሬ የሽታ ሳይኮሎጂስቶችና ባዮኬሚስቶች የሽታን ኃይል ጥቅም ላይ የሚያውሉባቸውን አዳዲስ መንገዶች በመሞከር ላይ ናቸው። የሽታ መሐንዲሶች የተለያዩ አበቦችና ቅመማ ቅመሞች የሚሰጡት ሽታ በአእምሮና በሰዎች ጠባይ ላይ የሚኖረውን ውጤት ለማጥናት ትምህርት ቤቶች፣ የቢሮ ሕንፃዎች፣ የማገገሚያ ቤቶችና ከመሬት በታች የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች ሳይቀሩ በተለያዩ መዓዛዎች እንዲታወዱ አድርገዋል። አንዳንድ ሽታዎች የሰዎችን ስሜት በመለወጥ ይበልጥ ተግባቢ እንዲሆኑ፣ በተሻለ መንገድ በቅልጥፍና እንዲሠሩና የአእምሮ ንቃታቸው እንዲጨምር ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።

ዘ ፊውቸሪስት መጽሔት እንዳለው በቶክዮ፣ ጃፓን በሚገኝ አንድ ዘመናዊ የጤና ክበብ በርካታ ሰዎች የከተማ ኑሮ የሚያስከትለውን ውጥረት ያረግባል የሚባለውን “የሽታ ኮክቴል” ለ30 ደቂቃ ያህል አሽትቶ ለመውጣት ይሰለፋሉ። በተጨማሪም የጃፓን ሳይንቲስቶች የነርቭ መታወክ ያለባቸው ሰዎች በጫካ ውስጥ በእግር እንዲንሸራሸሩ ይመክራሉ። ከዛፎች የሚወጣው ተርፒንስ የተባለ መዓዛ ሰውነትን ብቻ ሳይሆን አእምሮን ጭምር እንደሚያዝናና ተደርሶበታል።

ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ሽታዎች ጤና የሚሰጡ አይደሉም። አንድን ሰው የሚያስደስተው ሽታ ሌላውን ሰው በጣም ሊያስጨንቀው ይችላል። ጠንከር ያሉ ሽታዎች፣ በተለይ ጠንከር ያሉ የሽቶ ሽታዎች በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአስም ወይም የአለርጂ ሕመም እንደሚቀሰቅሱ የታወቀ ነው። ከዚህም በላይ ማንም ሰው የማይወዳቸው መጥፎ ጠረኖች አሉ። ከኢንዱስትሪና ከመኪኖች ጭስ መውጫዎች የሚወጣው መርዛማ ጭስ፣ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታዎችና ገንዳዎች የሚወጣው የቆሻሻ ሽታ፣ በርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚገለገሉባቸው ተናኝ ኬሚካሎች ለጤና የማይበጁ ሽታዎች ያሰራጫሉ።

በተፈጥሮም ቢሆን በአካባቢያችን አደገኛ ኬሚካሎች መኖራቸው አይካድም። ይሁን እንጂ እነኚህ ኬሚካሎች በጣም ተሰራጭተውና ተበርዘው የሚገኙ ስለሆኑ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትሉም። እነዚህ ኬሚካሎች በአንድ ቦታ ተከማችተው በሚገኙበት ጊዜ ግን በጣም ጠንካራ በሆኑት የሽታ ነርቭ ሕዋሳት ላይ እንኳን ጉዳት ያስከትላሉ። ለምሳሌ ያህል ለቀለም መበጥበጫና ለሌላ አገልግሎት ከሚውሉት የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች መካከል ብዙዎቹ ሽታ ለሚለዩት ሕዋሶች አደገኛ መሆናቸውን ሊቃውንት አስጠንቅቀዋል። በተጨማሪም የማሽተትን ስሜት ሊያግዱ ወይም ሊያጠፉ የሚችሉ የአካል ጉድለቶች አሉ።

ይህን ስጦታ ታደንቃለህን?

በእርግጥም ሽታ የመለየት ችሎታ በሚቻልበት ቦታ ሁሉ እንዲህ ካለው አደጋ ሊጠበቅ የሚገባው ውድ ስጦታ ነው። ስለዚህ በሥራህ አጋጣሚ የምታገኛቸው ኬሚካሎች ሊያስከትሉ ስለሚችሉት አደጋ ማወቅና በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉትን የሽታ ሕዋሳት ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያስችልህን ማንኛውም ዓይነት ጥንቃቄ መውሰድ ይኖርብሃል። (ከ2 ቆሮንቶስ 7:​1 ጋር አወዳድር።) በሌላው በኩል ደግሞ ስለሌሎች ስሜትም ማሰብ ጥሩ ነው። በዚህ ረገድ ቤታችንንና ገላችንን በንጽሕና መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም አንዳንዶች በተለይ እንደ ስብሰባ አዳራሽና ቲያትር ቤት ባሉት ረዘም ላለ ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተቀራርበው በሚቆዩባቸው ቦታዎች ስለሚጠቀሙት ሽቶ ጥንቃቄ ለማድረግ መርጠዋል። — ከማቴዎስ 7:​12 ጋር አወዳድር።

በአጠቃላይ ግን የሽታ ሕዋሳት ብዙ ጥንቃቄ የማያስፈልጋቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። ብዙ እንክብካቤና ጥበቃ የማያስፈልጋቸው ቢሆኑም በየዕለቱ ብዙ የምንደሰትባቸው ነገሮች ያስገኙልናል። አንድ የሚያስደስትህ ስጦታ ተሰጥቶህ ከሆነ የሰጠህን ሰው ለማመስገን ትፈልግ የለምን? በአሁኑ ጊዜም የሰው አካል ድንቅ ሆኖ ስለተሠራ ፈጣሪን ከልባቸው የሚያመሰግኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። (ከመዝሙር 139:​14 ጋር አወዳድር።) ይህ ዓይነቱ ውዳሴና ምስጋና እንዲጨምርና የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያቀርቡት እንደነበረው መሥዋዕት ለሚወደንና ለጋስ ለሆነው ፈጣሪያችን “ጣፋጭ ሽታ” ሆኖ እንዲያርግ እንመኛለን። — ዘኁልቁ 15:​3፤ ዕብራውያን 13:​15

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የማሽተት ስሜት የሚሠራው እንዴት ነው?

መጀመሪያ፤ የሽታው ዓይነት ይለያል

አየር ወደ ውስጥ በምትስብበት ጊዜ ሽታውም አብሮ ወደ አፍንጫህ ይገባል። በተጨማሪም ምግብ በምትውጥበት ጊዜ ሞልኪዩሎች በላንቃህ በኩል ተገፍተው ወደ አፍንጫህ ይገባሉ። በመጀመሪያ ግን ሽታ ያዘለው አየር በ“ዘበኞቹ” በኩል ማለፍ ይኖርበታል። በአፍንጫ ቀዳዳ የውስጥ ሽፋን ዙሪያ (1) ትራይጀሚናል የሚባሉት ነርቮች ይገኛሉ። እነዚህ ነርቮች የሚቆጠቁጥ ወይም የሚሰነፍጥ ኬሚካል ሲሰማቸው ሰውዬው እንዲያስነጥስ ያደርጋሉ። በተጨማሪም እነዚህ ነርቮች የሚቆጠቁጥ ጣዕም ያላቸውን ምግቦች በመለየት ከምንመገበው ምግብ ተጨማሪ ደስታ እንድናገኝ ያስችሉናል።

ቀጥሎ፣ ሽታ አዘል ሞልኪዩሎች አየሩ ተርቢነትስ (2) በሚባሉት ሦስት የመጽሐፍ ጥቅልል የሚመስሉ አጥንቶች መካከል ሲያልፍ በሚፈጠረው ግፊት ተገፍተው ወደ ላይ ይሳባሉ። የሚሳበው አየር እግረ መንገዱን ሙቀትና እርጥበት አግኝቶ ሞልኪዩሎቹን የመጀመሪያ ሽታ ተቀባይ ሕዋስ ወደሆነው ወደ ኤፒተልየም (3) ያደርሳል። ይህ የአውራ ጣት ጥፍር የሚያክለው የሕዋሳት ጥርቅም አሥር ሚልዮን የሚያክሉ ስሜት አስተላላፊ ኒውሮኖች (4) አሉት። በእያንዳንዱ ኒውሮን ጫፍ ሲልያ የሚባሉ በቀጭን ንፍጥ የራሱ ፀጉር መሰል ሕዋሳት አሉ። ኤፕተልየም ሽታ የመለየት ችሎታው በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ በአንድ ጊዜ ትንፋሽ ውስጥ የሚገኘውን 1/460, 000,000 ሚሊ ግራም ሽታ መለየት ይች⁠ላል።

ሽታውን እንዴት እንደሚለይ ግን እስከ አሁን ድረስ ያልታወቀ ምሥጢር ነው። የሰው ልጅ 10,000 የሚያክሉ ሽታዎችን መለየት ይችላል። በአካባቢያችን 400,000 የሚያክሉ ሽታ አዘል ነገሮች ሲኖሩ የኬሚስትሪ ሊቃውንት ሌሎች አዳዲስ ሽታ አዘል ነገሮችን በመሥራት ላይ ናቸው። ታዲያ አፍንጫችን እነዚህን ሁሉ ሽታዎች ለመለየት የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ምሥጢር ይፈታሉ ተብለው የቀረቡ ከ20 የሚበልጡ መላ ምቶች አሉ።

አሁን በቅርቡ ሳይንቲስቶች ይህን እንቆቅልሽ በከፊል ለመፍታት የሚያስችል እውቀት አግኝተዋል። በ1991 በሲልያ ውስጥ በሚገኙት የሴል ሽፋኖች ዙሪያ የተጠመጠሙ ኦልፋክተሪ ሪሰፕተርስ የተባሉ ጥቃቅን ፕሮቲኖች እንዳሉ የሚያሳይ ማስረጃ ተገኝቷል። እነዚህ ሽታ ተቀባይ ፕሮቲኖች የተለያዩትን የሽታ ሞልኪዩሎች በተለያየ ዓይነት ሁኔታ ይቀበላሉ። በዚህ መንገድ እያንዳንዱ ሽታ የራሱ አሻራ ይኖረዋል።

ሁለተኛ፣ ሽታው ይተላለፋል

ይህንን መረጃ ወደ አንጎል ለማስተላለፍ የራሳቸው ኮድ ያላቸው ኤሌክቶሮ ኬሚካላዊ መልእክቶች በኦልፋክተሪ ኒውሮኖች (4) አማካኝነት በፍጥነት ይላካሉ። የሳይንሳዊ ጽሑፎች አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ለዊስ ቶማስ እነዚህን ኒውሮኖች ‘የዘመናዊው ዓለም አምስተኛ ድንቅ’ ሲሉ ጠርተዋል። ከመሠረታዊ ነርቭ ሴሎች መካከል ራሳቸውን በየሳምንታቱ በአዳዲስ ሴሎች ለመተካት የሚችሉት እነዚህ ኒውሮኖች ብቻ ናቸው። በተጨማሪም በዓይንና በጆሮ ውስጥ ተሸፍነውና ተጠብቀው ሥራቸውን እንደሚያከናውኑት ስሜት አስተላላፊ ነርቮች ከአካባቢያቸው የሚጠብቃቸው ምንም ዓይነት ሽፋን የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ኦልፋክተሪ ነርቮች ከአንጎል ጋር በቀጥታ ተያይዘው ከውጭው ዓለም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያደርጋሉ። ስለዚህ አፍንጫ አንጎልና የውጭው አካባቢ የሚገናኙበት ብልት ነው።

እነዚህ ኒውሮኖች በሙሉ መልእክታቸውን የሚያደርሱት ወደ አንድ ቦታ ነው። ከአንጎል ግርጌ ወደሚገኙት መንትያ ኦልፋክተሪ በልቦች (5) ያደርሳሉ። እነኚህ በልቦች ለተቀሩት የአንጎል ክፍሎች መልእክት የሚያስተላልፉ ዋነኛ የመልእክት ማስተላለፊያ ጣቢያ ናቸው። በመጀመሪያ ግን እንደ ጎርፍ ከሚወርድላቸው የሽታ መልእክት መካከል የማያስፈልገውን መርጠው ማስቀረትና የሚያስፈልገውን ብቻ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።

ሦስተኛ፣ የሽታው ምንነት ይታወቃል

ኦልፋክተሪ በልቦች ሊምቢክ ሲስተም (6) በሚባለው የአእምሮ ክፍል ላይ በተወሳሰበ ሁኔታ የተጠመጠሙ ናቸው። ይህ ሊምቢክ ሲስተም ትዝታዎችን መዝግቦ በማቆየትና ስሜታዊ መግለጫዎችን በመቀስቀስ ረገድ ቁልፍ የሆነ ሚና የሚጫወት የተጠላለፈ ቅርጽ ያለው የአእምሮ ክፍል ነው። ዘ ሂውማን ቦዲ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “የእውኑ ዓለም በራድነት ወደሚፍለቀለቅ ሰብአዊ ስሜት የሚለወጠው” በዚህ ሊምቢክ ሲስተም ውስጥ ነው። ሊምቢክ ሲስተም ከማሽተት ስሜት ጋር በጣም የተሳሰረ ከመሆኑ የተነሣ ሪነንሰፋለን ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህም “የአፍንጫ አንጎል” ማለት ነው። ሽታ ሲሸተን ስሜታችንና ትዝታችን የሚቀሰቀሰው በአፍንጫና በሊምቢክ ሲስተም መካከል ይህን የመሰለ መቀራረብ ስላለ ሳይሆን አይቀርም። የጥብሱ ሽታ፣ ታጥቦ የደረቀው ልብስ፣ አዲስ የታጨደው ድርቆሽና የቡችላዋ ትንፋሽ የቆየ ትዝታ የቀሰቀሱት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይች⁠ላል።

ሊምቢክ ሲስተም ተለይቶ በታወቀው ሽታ መሠረት ሃይፖታላመስን (7) ይቀሰቅሳል። ሃይፖታላመስ ደግሞ በተራው የአእምሮ ዋነኛ ሆርሞን አመንጪ የሆነው ፒቱተሪ ግላንድ (8) የተለያዩ ሆርሞኖችን እንዲያመነጭ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ከምግብ ወይም ከወሲብ ተግባራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሰውነት ክፍሎች የሚቆጣጠሩትን ሆርሞኖች እንዲያመነጭ ያደርጋል። ስለዚህ የምግብ ሽታ ሲሸተን መራባችን ወይም ሽቶ ወሲባዊ መፈላለግ እንደሚጨምር ተደርጎ መታየቱ የሚያስደንቅ አይደለም።

በተጨማሪም ሊምቢክ ሲስተም ኒዎኮርቴክስ (9) ወደሚባለው ምሁራዊ ግምገማ ወደ ሚደረግበት የአንጎል ክፍል ይደርሳል። ከአፍንጫ የመጣው ዜና ከሌሎች የስሜት ሕዋሳት ከሚመጣው መረጃ ጋር የሚገናዘበው እዚህ ነው። ወዲያው የጭሱን ሽታ፣ የሚንኮሻኮሸውን ድምፅና ላይና ታች የሚርገበገበውን የአየር ሞገድ አንድ ላይ አዛምደህ በአካባቢው እሳት አለ ከሚል መደምደሚያ ትደርሳለህ።

ታላመስም (10) የራሱ የሆነ የሥራ ድርሻ አለው። በስሜት የሚነዳውን ሊምቢክ ሲስተምና በመረጃ የሚመራውን “ምሁሩን” ኒዎኮርቴክስ የሚያስታርቀው እርሱ ሳይሆን አይቀርም። ኦልፋክተሪ ኮርቴክስ (11) ተመሳሳይነት ያላቸውን ሽታዎች ለመለየት ይረዳል። በተጨማሪም የተለያዩት የአንጎል ክፍሎች የመልእክት ማሰራጫ ጣቢያ ወደሆኑት ወደ ኦልፋክተሪ በልቦች መልእክት ሊልኩ ይችላሉ። የመልስ መልእክት መላክ ለምን ያስፈልጋል? በልቦቹ ለይተው የላኩትን የሽታ መልእክት እንዲያሻሽሉ ማለትም መልእክቱን እንዲቀንሱ ወይም ጨርሰው እንዲያጠፉ ነው።

ከጠገባችሁ በኋላ የምግቡ ሽታ ከመብላታችሁ በፊት እንደነበረው እንደማያስጎመጅ አስተውላችሁ ይሆናል። ወይም አንድ መጥፎ ሽታ እንድታሸቱ በሚያስገድድ ሁኔታ ላይ ትሆኑና መጥፎው ሽታ ከጊዜ በኋላ እየቀነሰ ሲሄድ አላስተዋላችሁም? ይህን ለውጥ ያመጡት ኦልፋክተሪ በልቦች ከአንጎል በደረሳቸው መልእክት መሠረት ነው። በዚህ ረገድ በሲልያ ላይ ያሉት ስሜት ተቀባይ ሴሎች ሊረዷቸው ይችላሉ። እነዚህ ሴሎች በቀላሉ የሚደክሙ እንደሆነ ይነገርላቸዋል። ይህም በተለይ መጥፎ ሽታ በሚኖርበት ጊዜ በጣም ጠቃሚ ነው።

በጣም የተወሳሰበ ሥርዓት አይደለምን? ይሁን እንጂ የተመለከትነው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው። ውስብስብ ስለሆነው ስለዚህ ሥርዓተ ስሜት ብዙ መጻሕፍት ተጽፈዋል።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(ሥዕሉን ተመልከት)

የማሽተት ስሜት መበላሸት

የማሽተት ስሜታቸው የተበላሸባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ለእነዚህ ሰዎች የፀደይ መዓዛ ወይም የጣፋጭ ምግብ ጣዕም አይታወቃቸውም። አንዲት ሴት የማሽተት ስሜትዋ በድንገት ከጠፋ በኋላ የደረሰባትን ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ሁላችንም ስለ መታወር ወይም ስለ መደንቆር እናውቃለን። በእኔ ላይ የደረሰውም በእነዚህ የአካል ጉድለቶች እንዲለወጥ አልመኝም። የቡናን የሚያውድ ሽታ፣ የብርቱካንን ጣፋጭ ጣዕም በአድናቆት አንመለከትም። የማሽተት ስሜታችንን ስናጣ ግን እንዴት እንደምንተነፍስ እንኳን የዘነጋን መስሎ ይታየናል።” ኒውስ ዊክ መጽሔት።

የማሽተት ስሜት መበላሸት በሕይወት ላይ እንኳን አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ኤቫ የምትባል ሴት እንደሚከተለው በማለት አስረድታለች። “ማሽተት ስለማልችል በጣም መጠንቀቅ ይገባኛል። ክረምት ሲመጣ የቤቴን መስኮቶችና በሮች በሙሉ ለመዝጋት ስለምገደድ በጣም እፈራለሁ። ንፁሕ አየር ለመግባት ካልቻለ በጋዝ ምድጃው ላይ ያለው የማስጠንቀቂያ መብራት ተበላሽቶ ሳላውቀው በሚወጣ ጋዝ ታፍኜ ልሞት እችላለሁ።”

የማሽተት ስሜት የሚበላሸው በምን ምክንያት ነው? ከአሥር የሚበልጡ ምክንያቶች ቢኖሩም በጣም የተለመዱት ሦስት ናቸው። እነርሱም በአናት ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የመተንፈሻ አካላት ላይኛ ክፍል በቫይረስ ሲለከፍ እና የሳይነስ በሽታ ናቸው። የነርቭ መተላለፊያዎች ከተቆረጡ ወይም ኤፒተልየም ደንዝዞ ስሜት ማስተላለፍ ካቆመ ወይም የአፍንጫ ቀዳዳ በመዘጋቱ ወይም በመቆጣቱ ምክንያት አየር ወደ ኤፒተልየም ሊደርስ ካልቻለ የማሽተት ስሜት ይጠፋል። እንደነዚህ ያሉት የአካል እክሎች ዋነኛ የጤና ችግር መሆናቸውን በመገንዘብ በመቅመስና በማሽተት ስሜቶች ላይ ጥናት የሚያደርጉ የምርምር ማዕከሎች ተቋቁመዋል።

በኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሲራከስ የጤንነትና የሳይንስ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማክስዌል ሞዘል በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለዋል:- “[ለእነርሱ ብቻ የሚታወቅ መጥፎ ሽታ የሚያሸቱ] በሽተኞች ነበሩን። በጣም መጥፎ ሽታ ይሸታቸዋል። አንዲት ሴት ሁልጊዜ ዓሣ ይሸታታል። በየቀኑ አንድ ጊዜም ሳያቋርጥ ዓሣ ብቻ ወይም የሚቃጠል ጎማ ብቻ ቢሸታችሁ ሕይወት ምን ያህል አስከፊ እንደሚሆን ልትገምቱ ትችላላችሁ።” አንዲት ሴት ለ11 ዓመታት ያህል መጥፎ ሽታ ሲሸታት ከቆየ በኋላ ከኦልፋክተሪ በልቦቿ አንዱ በቀዶ ሕክምና እንደ ወጣላት ወዲያው ድናለች።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቡችላ ትንፋሽ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥብስ ሥጋ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዲስ የታጨደ ድርቆሽ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ