የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 10/8 ገጽ 30-31
  • ዓለምን ስንመለከታት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዓለምን ስንመለከታት
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጾታ እክል ሲሆን
  • በበጎ አድራጊ ድርጅቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚውለው ለእነማን ነው?
  • አባቶችም ተጠያቂ ናቸው
  • የሕፃናትን ሕይወት የሚቀጥፉ በሽታዎች
  • “በዓለም ብዙ የግድያ ወንጀል የሚፈጸምባት ዋና ከተማ”
  • ሌላ የፍሉ ወረርሽኝ?
  • የሙዚቃ መዘዝ
  • መንስዔው ካፌን ነው ተባለ
  • በመጨረሻ ይቅርታ ተደረገለት
  • በሰው ልጅ ታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ የከፋው ወረርሽኝ
    ንቁ!—2005
  • በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢንፍሉዌንዛ ምን እናውቃለን?
    ንቁ!—2005
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • የቤተሰብህን አባላት ከኢንፍሉዌንዛ ጠብቅ
    ንቁ!—2010
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1993
g93 10/8 ገጽ 30-31

ዓለምን ስንመለከታት

ጾታ እክል ሲሆን

“በሦስተኛው ዓለም ውስጥ የሴቶች ኑሮ፣ ኑሮ አይደለም” በማለት በቅርቡ ዘ ዋሺንግተን ፖስት በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ ተከታታይ የጥናት ሪፖርት ሐተታውን ይጀምራል። የፖስት ዘጋቢዎች በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ባሉ ድህነት ያጠቃቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ በርካታ ሴቶች ጋር ቃለ ምልልስ ካደረጉ በኋላ “ብዙውን ጊዜ ባሕል፣ ሃይማኖትና የአገሩ ሕግ ሴቶች ሊኖራቸው የሚገባቸውን ሰብዓዊ መብቶች ከመንፈጋቸውም በላይ አንዳንድ ጊዜ ከሰብዓዊ ፍጡርነት ዝቅ ተደርገው” አግኝተዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ በሂማልያ አካባቢ በሚገኝ መንደር ውስጥ 59 በመቶ የሚሆነውን ሥራ የሚሠሩት ሴቶች ሲሆኑ በቀን እስከ 14 ሰዓት ድረስ ሲለፉ ይውላሉ። እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ከራሳቸው የሰውነት ክብደት 1.5 ጊዜ የሚበልጥ ክብደት ይሸከማሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሴቶቹ “ሁለት ሦስት . . . ልጆችን ከወለዱ በኋላ ኃይላቸው ሁሉ ተሟጦ እየደከሙ ስለሚሄዱ በሠላሳዎቹ ዕድሜያቸው መገባደጃ ላይ እያረጁና እየደከሙ በመሄድ በመጨረሻ ይሞታሉ።” አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ልጆች የሚሰጣቸው ምግብ ከወንዶች ያነሰ ሲሆን ከትምህርት ገበታቸው አፈናቅለው ሥራ እንዲሠሩ ያደርጓቸዋል፤ የሚደረግላቸውም ሕክምና ከወንዶች ያነሰ ነው። ብዙ ሴቶች ዕዳውን ማን ይችለዋል በማለት ሴት ሕፃናትን በአራስነታቸው ይገድሏቸዋል። ዘጋቢዎቹ እንዳመለከቱት በገጠራማው ደቡባዊ ህንድ ውስጥ ሕፃናቶቹን ከሚገድሉባቸው የተለመዱ ዘዴዎች አንዱ በሕፃናቱ ጉሮሮ ትኩስ የዶሮ ሾርባ በማንቆርቆር ነው። አንድ የፖሊስ አዛዥ እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ይቀጣሉ ወይ ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ “ከዚህ ይበልጥ የሚያስጨንቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይህን በሚመለከት ወደኛ የሚመጡት ክሶች በጣም ጥቂት ናቸው። ሰዉም ቢሆን ደንታ የለውም” ብለዋል።

በበጎ አድራጊ ድርጅቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚውለው ለእነማን ነው?

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በየዓመቱ የሚሰበስቡት ገንዘብ ሁሉ ምን ይደረግበታል? ከሚሰበሰበው ገንዘብ ከፊሉ የሚውለው ድርጅቶቹን ለሚያስተዳድሩት ሰዎች ነው። በተደረገው ጥናት መሠረት ባለፈው ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ 100 ታላላቅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ዋና ሥራ አስኪያጆች እያንዳንዳቸው ከ200,000 ዶላር በላይ የሚሆን ደሞዝ እና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኙ መሆናቸው ታውቋል። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡንም ተመሳሳይ ሪፖርት ዘግቧል። ከእነዚህ አስተዳዳሪዎች መካከል ሦስቱ ከ500,000 ዶላር በላይ አግኝተዋል። ምርመራው የተደረገው በገንዘብ አያያዝ ጉድለትና በአባካኝነት ምክንያት ተከሶ ከሥራ በወጣ የአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዘዳንት ላይ ነበር። ፕሬዘዳንቱ በየዓመቱ 390,000 ዶላር ያገኝ ነበር። አሁን በእርሱ ምትክ የገባው ፕሬዘዳንት 195,000 ዶላር “ብቻ” ያገኛል።

አባቶችም ተጠያቂ ናቸው

ካሁን በፊት በነበሩት ጊዜያት፣ ጤነኛ ያልሆኑ ሕፃናት እንዳይወለዱ ሲባል ነፍሰ ጡር እናቶች የአልኮል መጠጥ ከመጠጣትና ሲጋራ ማጨስን ከመሳሰሉት ድርጊቶች እንዲርቁ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆቷል። “አሁን ግን ለአባቶችም ጭምር ተመሳሳይ ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው” በማለት ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ያትታል። “በቅርቡ የተደረገው ምርመራ እንደሚያሳየው አንድ ወንድ ለኬሚካሎች መጋለጡ የመውለድ ችሎታውን ብቻ ሳይሆን የልጆቹን የወደፊት ጤንነትም ይነካል።” የቀረቡት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ወንዶች “ሚስቶቻቸው እንዲያስወርዳቸው ወይም አካለ ስንኩል ልጆች እንዲወልዱ፣ ለካንሰር በሽታዎችና ለልጆቻቸው እድገት መጓትት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ከዚህ በፊት ይታወቅ ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ታውቋል።” በአሁኑ ጊዜ አደንዛዥ ዕጾችንና ሌሎች መድኃኒቶችን መውሰድ (ማጨስ የሚያስከትላቸው ውጤቶችም ጭምር) እንዲሁም ቪታሚን ሲ የያዙ ቅጠላ ቅጠሎችንና ፍራፍሬዎችን በብዛት አለመመገብ የወንዱን ዘር የሚጎዳ መሆኑ የታወቀ ይመስላል። ዴቭራ ሊ ዴቪስ የተባሉ ቶክሲኮሎጅስት (መርዝነት ስላላቸው ነገሮችና ስለሚያስከትሏቸው ውጤቶች የሚያጠኑ ሰው ናቸው) እንዲህ አሉ:- “ለረጅም ጊዜያት በእናቶች ላይ ብቻ ስናተኩር ቆይተናል። ጤነኛ ልጅ ለመውለድ አባትየው የሚያበረክተው ድርሻ አነስተኛ ግምት ሲሰጠው ኖሯል።”

የሕፃናትን ሕይወት የሚቀጥፉ በሽታዎች

በታዳጊው ዓለም በየዓመቱ ከሚሞቱት 13 ሚልዮን ሕፃናት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑትን የሚገድሉት ሦስት በሽታዎች እንደሆኑ ሌሶቶ ቱዴይ የተባለ በአፍሪካ የሚታተም አንድ ጋዜጣ አስታወቀ። እነዚህ በሽታዎች ኒሞኒያ (የሳንባ ምች)፣ ተቅማጥና ኩፍኝ ናቸው። እንዲህ ያሉትን በሽታዎች በአካባቢው በሚገኙና በጣም ውድ ባልሆኑ መድኃኒቶች መከላከል ወይም ማከም ይቻል እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ገልጿል። ለምሳሌ በየዓመቱ ለ3. 5 ሚልዮን ሕፃናት መሞት ምክንያት የሆነው ታላቁ ገዳይ በሽታ የሳንባ ምች ነው። በአብዛኛው ለዚህ በሽታ ምክንያት የሚሆኑት ባክቴሪያ የሚባሉ ረቂቅ ተሕዋስያን ናቸው። ይህም 1 ብር ከ50 ሣንቲም የሚያወጡ ፀረ ተሕዋስያን የሆኑ መድኃኒቶችን ለአምስት ቀናት ያህል በተከታታይ በመውሰድ በሽታውን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይቻላል። ተቅማጥ በየዓመቱ የሦስት ሚልዮን ሕፃናትን ሕይወት ይቀጥፋል። ወላጆች በአካባቢው በቀላሉ የሚገኝ በተቅማጥ የወጣውን የሰውነት ፈሳሽ የሚተካ ፈሳሽ ቢያጠጧቸው ኖሮ ወደ ግማሽ የሚጠጉትን ሕፃናት ሕይወት ማዳን ይቻል ነበር። በየዓመቱ 800,000 ሕፃናት በኩፍኝ ይሞታሉ። ሪፖርቱ ሕፃናቱን በማስከተብ ኩፍኝን መከላከል ይቻል እንደነበር ገልጿል። አንድን ልጅ የኩፍኝ ክትባት ለማስከተብ የሚወጣው ወጪ ከ3 ብር ያነሰ ነው።

“በዓለም ብዙ የግድያ ወንጀል የሚፈጸምባት ዋና ከተማ”

“በዓለም ካሉት ዋና ከተሞች ጆሃንስበርግ ብዙ የግድያ ወንጀል የሚፈጸምባት ከተማ መሆኗ አያጠራጥርም ሲል” ዘ ስታር የተባለ አንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ አስታወቀ። “በፖሊሶች አኅዛዊ መረጃ መሠረት በ1992 በጆሃንስ በርግና በሶዌቶ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በድምሩ 3,402 ነበር። ይህም በአንድ ቀን ውስጥ 9. 3 ወይም በየ2 ሰዓት ተኩል ጊዜ ውስጥ አንድ ሰው ይገደላል ማለት ነው።” ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም በአንደኛ ደረጃ “ብዙ የግድያ ወንጀል ይፈጸምባት” የነበረችውን ሪዮ ዲ ዤኔሮን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ አድርጓታል። ሪዮ ባለፉት አሥረተ ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ 8,722 የግድያ ወንጀሎች ይፈጸሙባት ነበር። ይሁን እንጂ በሪዮ የሚኖረው ሕዝብ ብዛት 10 ሚልዮን ሲሆን በጆሃንስ በርግና በሶዌቶ ግን 2. 2 ሚልዮን እንደሆነ ይነገራል። ከጆሃንስ በርግ ጋር ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛት ባላት በፓሪስ በየዓመቱ በአማካይ የሚፈጸመው የግድያ ወንጀል 153 ነው። በጆሃንስ በርግ ከ647 ሰዎች 1፣ በሪዮ ዲ ዤኔሮ ከ1,158 ሰዎች 1፣ በሎስ አንጀለስ ከ3,196 ሰዎች 1፣ በኒው ዮርክ ከ4,303 ሰዎች 1፣ በማያሚ ከ6,272 ሰዎች 1፣ በሞስኮ ከ10,120 ሰዎች 1፣ በፓሪስ ደግሞ ከ14,065 ሰዎች 1 ሰው በሌሎች የሚገድልበት አጋጣሚ እንዳለ ተገልጿል።

ሌላ የፍሉ ወረርሽኝ?

“በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ከተከሰተ ከፍተኛ መቅሰፍት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም ለማለት ይቻላል” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት ገልጿል። እንደ ሳይንቲስቶቹ አባባል ከ20 እስከ 40 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከፈጀው በ1918 ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ሊከሰት የሚችልበት ጊዜ ደርሷል። በሜሪላንድ ክፍለሃገር በቤቴስዳ ከተማ ውስጥ በብሔራዊ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል የተላላፊ በሽታዎች ጉዳይ ዋና ኃላፊ የሆኑት ጆን አር ላ ሞንቴኝ “በሽታው ከአሁን በፊት አንድ ጊዜ ተከስቶ ስለነበረ እንደገና ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ከባድ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ሊያስነሣ የሚችለው የቫይረስ መለወጥ እምብዛም የማይከሰት ነው። በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የተከሰተው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። እነሱም:- በ1918 የተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚጠራው፣ በ1957 የተከሰተው ኤዥያን ፍሉ የሚባለውና በ1968 የነበረው ሆንግኮንግ ፍሉ የሚባሉት ናቸው። መጨረሻ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ከመጀመሪያው ጋር ሲወዳደሩ እምብዛም ኃይለኞች አልነበሩም። የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ቶሎ ቶሎና ሳይታሰብ የሚለዋወጥ ስለሆነ ገና ትክክለኛ የመከላከያ ክትባት ከመፈልሰፉ በፊት ገዳይ የሆነ ወረርሽኝ ሊነሣ ይችላል። ጽሑፉ ሲደመድም “በታሪክ ውስጥ በተከሰቱት ነገሮች የምንመራ ከሆነ የያዝነው መቶ ዘመን ከመገባደዱ በፊት አንቲጅን የሚባሉት በሰውነታችን ውስጥ መከላከያ የሚፈጥሩ ንጥረ ነገሮች ከፍተኛ ለውጥ ሊያደርጉና ከባድ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ዓለምን ሊያጥለቀልቅ ይችላል ብለን መጠበቅ እንችላለን።”

የሙዚቃ መዘዝ

“ሙዚቃውን ቀንሰው!” በማለት የተበሳጩ ወላጆች መጮኻቸው የተለመደ ነገር ነው። ብዙ ወጣቶች ድም ድም የሚለው የሙዚቃው ምት ካልተሰማ በስተቀር የዘፈኑ ጣዕም አይታወቀንም ይላሉ። ብዙውን ጊዜ ሙዚቃን እያስጮኹ መስማት የጆሮ መደንቆርን ያመጣል ሲባል የቆየ ቢሆንም በቅርቡ ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል በተባለው በቶሮንቶ ካናዳ የሚታተም መጽሔት ላይ የወጣ ዘገባ እንዳብራራው ይህ ልማድ የጆሮ መጮኽን ችግር ጭምር ይፈጥራል። ይህም ጆሮ ውስጥ የሚሰማ ጩኸት “አንድን ሙዚቃ ከሰሙ በኋላ በጭንቅላት ውስጥ የሚሰማው የሚደውል፣ የሚንጫጫ፣ ጥዝ የሚል፣ የሚንኳኳ ወይም የሚያፏጭ ድምፅ ነው። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ድምፅ በሁለቱም ጆሮዎች ውስጥ ይሰማል። ሆኖም ይህ [ገለጻ] የድምፁን መዘዝ በበቂ ሁኔታ አይገልጽም” በማለት ጋዜጣው ያትታል። የጆሮ መጮህ በሽተኞች ማኅበር አስተባባሪ የሆኑት ኤሊዛቤት ኤይርስ፣ ይህ እክል አንዴ ከጀመረህ “[ከዚያ ወዲያ] በጭራሽ ሙሉ ሰላምና ፀጥታ አታገኝም” ብለዋል። ይህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጠቃቸው ለራስ ብቻ ማዳመጥ በሚቻልበት የመስሚያ መሣሪያ (ሄድ ፎን) የሚጠቀሙና ድምፁን ሌላ ሰው ሊሰማው እስከሚችል ድረስ በጣም ከፍ አድርገው በማስጮህ የሚሰሙ ሰዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ወደፊት ሙዚቃንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ድምፅ ሰምተው ለመደሰት ያላቸው ችሎታ ይኰላሽባቸዋል።

መንስዔው ካፌን ነው ተባለ

ከፍተኛ የቡና ሱስ ያለባቸው ሰዎች ይህን ልማዳቸውን ባንድ ጊዜ ሲተዉ ራስ ምታት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ድካም፣ ሥጋት፣ እንዲሁም የጡንቻ ሕመም፣ ማቅለሽለሽና ትውከት ጭምር አጋጠመን ሲሉ አዘውትረው ይናገራሉ። በቀን አንድ ወይም ሁለት ሲኒ ቡና ወይም ሻይ ወይም ካፌን ያላቸው ሁለት ጠርሙስ ለስላሳ መጠጦች ይጠጡ የነበሩ ሰዎች ለሁለት ቀናት እነዚህን ሳይወስዱ ቢቀሩ እነዚህ የበሽታ ምልክቶች ሊታዩባቸው እንደሚችሉ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ይህን ልማዳቸውን ሲያቆሙ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በጣም ከባድ ከመሆናቸው የተነሣ ሰዎቹ ሒኪም ቤት መሄድ እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ይህ ዓይነቱ ችግር የሚያጋጥማቸው ቅዳሜና እሁድ ቢሮ ስለማይሄዱ ከቡና ማሽኑ ርቀው የሚቆዩ ሰዎች፣ ካፌን ያላቸውን ትተው ካፌን የሌላቸው መጠጦች መውሰድ የጀመሩ ሰዎች ወይም ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው በመጀመሪያ ምንም ምግብ እንዳይወስዱ የሚደረጉ ሰዎች ናቸው። ሐኪሞች ራስ ምታት የያዛቸው ወይም ካፌን መውሰድ ባቆሙ ሰዎች ላይ የሚታዩ ሌሎች የበሽታ ምልክቶች የሚታዩባቸው በሽተኞች ሲያጋጥሟቸው ሰዎቹ ከዚህ በፊት ካፌን ይወስዱ ወይም አይወስዱ እንደሆነ እንዲያጣሩ ተመክረዋል። ካፌን የሚወስዱ ሰዎች ካፌን መውሰዳቸውን ለማቆም ከፈለጉ ቀስ በቀስ ቢያቆሙ እንደሚሻላቸው ተመክረዋል። በዚህ ላይ የተደረገው ጥናት ካፌን፣ ቡናም ጭምር ማለት ነው፣ ሱስ ከሚያስይዙ አደንዛዥ ዕጾች መሐል ሊመደብ ይችል ይሆን? የሚል ጥያቄም አስነስቷል።

በመጨረሻ ይቅርታ ተደረገለት

ጋሊሊዮ “ትልቅ ይቅርታ” ተደርጎለታል ሲሉ ዳግማዊ ፖፕ ጆን ተናገሩ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዝነኛው የፊዝክስ አዋቂ ጋሊሊዮ መሬት በፀሐይ ዙርያ ትዞራለች በሚለው አቋሙ ድርቅ በማለቱ በ1633 “በቅዱስ ኢንኩዜሽን ቅጣት ከተፈጸመባቸው” አንዱ አድርጋ እስከ ዛሬ ድረስ ስትመለከተው ቆይታለች። ዛሬ ከ360 ዓመታት በኋላ ጳጳሱ በጵጵስና የሳይንስ አካዳሚው ፊት ባደረጉት ከፍተኛ ንግግር ለዚህ አከራካሪ ጉዳይ ማብራሪያ በመስጠት ጉዳዩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊዘጉት ሞክረዋል። ሆኖም ከሪየር ዴላ ሴራ የተባለው ጣሊያን አገር የሚታተም ጋዜጣ ባቀረበው ዘገባ መሠረት ጋሊሊዮ ሌላው ቢቀር በአንድ ነጥብ ላይ ተሳስቶ እንደነበረ ጳጳሱ አሁንም ደጋግመው ከመናገር ወደኋላ አላሉም። የፊዝክስ ምሁሩ የደረሰበት ውሳኔ “አስተማማኝ ማስረጃ” እስኪገኝለት ድረስ ግምታዊ ሐሳብ መሆኑን እንዲናገር የቀረበለትን “ምክር” አልቀበልም ብሎ የነበረ ይመ ስላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ