የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከኤድስ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
“ይህ እንዲደርስብኝ መፍቀዴ አናዶኛል” በማለት ኬይ ተናገረች። “ያደረኳቸው ምርጫዎች ወደፊት ሊኖሩኝ ይችሉ የነበሩትን አማራጮች አሳጥተውኛል።” (ኒውስዊክ መጽሔት፣ ነሐሴ 3, 1992) ኬይ በ18 ዓመቷ በኤድስ ቫይረስ ተለከፈች።
ኬይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ቀሳፊ በሆነው በኤች አይ ቪ (ሂውማን ኢሚዩኖዴፊሸንሲ ቫይረስ) ከተያዙት ከአንድ ሚልዮን በላይ ከሚሆኑ ሰዎች መካከል አንዷ ብቻ ናት። ዶክተሮች ቫይረሱ አስፈሪውን የኤድስ በሽታ ያስከትላል ይላሉ።a ምን ያህል ወጣቶች በዚህ በሽታ እንደተያዙ በትክክል የሚያውቅ የለም፤ ይሁን እንጂ ነገሩ በይበልጥ ወጣቶችን አሳስቧቸዋል። የብሪታንያ ወጣቶች በጣም የተጨነቁበት ነገር ቢኖር ኤድስ መሆኑን አንድ ጥናት አመልክቷል። ወጣቶች ስለ በሽታው ይህን ያህል ቢጨነቁም የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳለው “ብዙ ጎልማሶች ራሳቸውን ለኤች አይ ቪ የሚያጋልጥ ድርጊት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።”
ኤድስ ምንጊዜም ገዳይ ነው፤ በዓለም ዙሪያም በከፍተኛ መጠን እየተዛመተ ይገኛል። ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ስለ ኤድስ የሚነዛውን የሐሰት ወሬ ከእውነታው መለየት
በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተዘጋጀ አንድ ቡክሌት “በኤች አይ ቪ ‘በድንገት’ አትለከፍም። እንደ ጉንፋን ወይም እንደ ኢንፍሉዌንዛ በቀላሉ ‘ሊይዝህ’ አይችልም” በማለት ይገልጻል። ስለዚህ ኤድስ ከያዛቸው ሰዎች ጋር የዕለት ተዕለት ግንኙነት ማድረግ አደገኛ ሊሆን አይችልም። ኤድስ ከያዘው ወይም ከያዛት የክፍል ጓደኛህ አጠገብ ስለተቀመጥክ ብቻ ኤድስ ይይዘኛል ብለህ ልትጨነቅ አይገባም። ኤች አይ ቪ በአየር የሚዛመት ቫይረስ ስላልሆነ አንድ ኤድስ የያዘው ሰው ቢስል ወይም ቢያስነጥስ ስጋት ሊያድርብህ አይገባም። እንዲያውም በቤተሰባቸው ውስጥ በኤድስ የተያዘ ሰው እያለ ፎጣዎችን፣ የመመገቢያ እቃዎችን አልፎ ተርፎም የጥርስ ብሩሾችን በጋራ ተጠቅመው ቫይረሱ ግን ያልተላለፈባቸው ሰዎች አሉ።b
ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ይህ ቀሳፊ ቫይረስ የሚኖረው በሰው ደም ውስጥ፣ ከወንዱ አባላዘር ወይም ከሴቷ የጾታ ብልት በሚወጣው ፈሳሽ ውስጥ በመሆኑ ነው። ስለዚህ በአብዛኛው ኤድስ የሚተላለፈው በጾታ ግንኙነት ማለትም በግብረሰዶም ወይም በወንድና በሴት መካከል በሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ነው።c በተጨማሪም የዚህ በሽታ ሰለባ የሆኑ ብዙ ሰዎች በኤች አይ ቪ ከተያዘ ሰው ጋር መርፌዎችን ወይም ሲሪንጆችን በጋራ በመጠቀማቸው በበሽታው ሊያዙ ችለዋል። ይህም የሚሆነው ብዙውን ጊዜ አደንዛዥ መድኃኒቶችን አላግባብ ሲወስዱ ነው።d ምንም እንኳን ዶክተሮች ከፍተኛ ምርመራ ስለሚደረግበት ችግሩን “ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ተችሏል” ቢሉም ኤድስ ደም በመውሰድም ሊተላለፍ ይችላል።
ስለዚህ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የሚፈጽም ወይም በሕግ የታገዱ አደንዛዥ መድኃኒቶችን በመርፌ የሚወስድ ማንኛውም ሰው በኤድስ በሽታ የመያዙ አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። እውነት ነው፣ ለጾታ ጓደኝነት የታሰበው ሰው በበሽታው የተያዘ ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ቮለንታሪ ኤች አይ ቪ ካውንስሊንግ ኤንድ ቴስቲንግ:- ፋክትስ፣ ኢሹስ ኤንድ አንሰርስ (ስለ ኤች አይ ቪ የሚሰጥ ምክርና ምርመራ:- እውነታዎቹ፣ አከራካሪዎቹ ጉዳዮችና መልሶቻቸው) የተባለው ቡክሌት እንዲህ ሲል ያሳስበናል:- “አንድን ሰው በማየት በኤች አይ ቪ ተይዟል ወይም አልተያዘም ማለት አትችልም። አንድ ሰው በቫይረሱ ተይዞም እያለ ፍጹም ጤንነት ሊሰማውና ጤናማ ሊመስል ይችላል። በዚህም ምክንያት በኤች አይ ቪ የተለከፉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው አያውቁም።”
“የማያሰጋ የጾታ ግንኙነት”?
በዚህ የተነሣ ብዙ የጤና ባለሙያዎችና አስተማሪዎች በኮንደም መጠቀምን እያበረታቱ ነው።e የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች፣ የንግድ ማስታወቂያዎችና በትምህርት ቤት የሚሰጡ ትምህርቶች በዚህ የወሊድ መከላከያ መሣሪያ መጠቀም “ያለ ስጋት” ወይም ቢያንስ ቢያንስ “ብዙም ሳይሰጉ” የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ያስችላል የሚል ሐሳብ እያሰራጩ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ኮንደም አድለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ይህን በመሰሉ ፕሮፓጋንዳዎች በመቀስቀስ በኮንደም በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ “የማያሰጋ የጾታ ግንኙነት” የተባለው ነገር ምን ያህል አስተማማኝ ነው? በአሜሪካ ቀይ መስቀል የተዘጋጀ አንድ ብሮሹር “ኮንዶም በበሽታው ለመያዝ ያለህን አጋጣሚ ሊቀንሰው ይችላል” ይላል። ምንጊዜም ገዳይ በሆነው በሽታ ‘ለመያዝ ያለህን አጋጣሚ ሊቀንሰው’ ስለቻለ ብቻ አስተማማኝ እንደሆነ ይሰማሃልን? የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዲህ በማለት በጉዳዩ መስማማቱን ገልጿል:- “ኮንዶም ኤች አይ ቪንና በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዳ መሆኑ ታይቷል። . . . ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የሚያስተማምን አይደለም።” እውነት ነው፤ ኮንዶም በጾታ ግንኙነት ወቅት ሊቀደድ ወይም ሊወልቅ ይችላል። ታይም መጽሔት እንደሚለው ከሆነ ኮንዶሞች “ከ10 እስከ 15 በመቶ ስኬታማ ላይሆኑ ይችላሉ”! ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሕይወትህን አሳልፈህ ትሰጣለህን? በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የጾታ ግንኙነት ከሚፈጽሙት ወጣቶች መካከል በኮንዶም የሚጠቀሙት ከግማሽ የሚያንሱ መሆናቸውም ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል።
እንግዲያው “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” የሚለው በምሳሌ 22:3 ላይ የሚገኛው ምክር ከዚህ ነጥብ ጋር የሚስማማ ነው። ኤድስን ለመከላከል ከሚያስችሉት በጣም የተሻሉ መንገዶች አንዱ አደንዛዥ ዕፅን አላግባብ ከመጠቀምና የጾታ ብልግናን ከመፈጸም ሙሉ በሙሉ መታቀብ ነው። ይህን ከማድረግ መናገሩ ይቀላልን? በተለይ ወጣቶች የተደቀኑባቸውን አያሌ ግፊቶች ሲመለከቱ ብዙዎች እንዲህ ይሰማቸዋል።
ግፊቶቹ
‘በወጣትነት’ ወቅት የጾታ ፍላጎት በጣም ያይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:36 አዓት) በዚህ ላይ ቴሌቪዥንና ፊልሞች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ጨምርበት። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚሉት ከሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜዎች የሚገኙ ወጣቶች በየቀኑ ከአምስት ሰዓት በላይ ቴሌቪዥን በመመልከት ያሳልፋሉ። ከፕሮግራሞቹ መካከል አብዛኞቹ የጾታ ብልግናን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ይሁን እንጂ ቴሌቪዥን በስፋት በተሰራጨባቸው የዓለም ክፍሎች የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምንም ችግር አያመጣም የሚል የሐሰት ወሬ ይነዛል። አንድ ጥናት በአሜሪካ ቴሌቪዥን በሚታዩ ፊልሞች ላይ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል:- “ያልተጋቡ ፍቅረኞች ከባልና ሚስቶች ከአራት እስከ ስምንት ጊዜ የበለጠ ተደጋጋሚ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። የወሊድ መከላከያዎችን የሚያስባቸው የለም፤ ወይም አይጠቀሙባቸውም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሴቶች የሚያረግዙት ከስንት አንዴ ነው። ወንዶቹም ሆነ ሴቶቹ ዝሙት አዳሪዎች ወይም ግብረሰዶም የሚፈጽሙ ካልሆኑ በስተቀር በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች እምብዛም አይያዙም።”—ሴንተር ፎር ፖፑሌሽን ኦፕሽንስ።
እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞችን በብዛት መከታተል በጠባይህ ላይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላልን? አዎን፣ በገላትያ 6:7, 8 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በሚለው መሠረት:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና”። በ400 ወጣቶች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት “በጾታ ብልግና የተሞላ የቴሌቭዥን ፕሮግራም በብዛት የተመለከቱ ወጣቶች ፕሮግራሙን እምብዛም ካልተከታተሉት ጋር ሲነጻጸሩ የጾታ ግንኙነት የመፈጸማቸው አጋጣሚ ልቆ” አግኝቶታል።
ሌላው ኃይለኛ ተጽዕኖ የዕድሜ እኩዮች ግፊት ነው። ዴቪድ የተባለ አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ወጣት “የሚስማሙኝ ጓደኞች ለማግኘት ፈለግሁ፤ ማግኘቱ ግን አስቸጋሪ ነበር” በማለት ስህተት መፈጸሙን በማመን ይናገራል። “ብዙ ጊዜ በመጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ ወድቄያለሁ። . . . በኤድስ ተለከፍኩ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ወጣቶችም እንደዚሁ ብዙውን ጊዜ ለዕድሜ እኩዮች ግፊት ይጋለጡ ነበር። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል? “ልጄ ሆይ” ይላል የምሳሌ ጸሐፊ፣ “ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል።”—ምሳሌ 1:10
እምቢ ማለት
“የማያሰጋ የጾታ ግንኙነት” መፈጸምን የሚያበረታቱት ሰዎች የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም መታቀብ ሊሆን የማይችል ነገር ነው በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ የጾታ ብልግና ተቀባይነት አግኝቶ እንዲቀጥል መፍቀድ ወደፊት የሚያስገኘው ጥቅም ይኖራልን? አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ወጣት ይህ ጉዳይ ወጣቶችን ግራ የሚያጋባ መሆኑን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም ታቀቡ በማለት ይነግሩናል። ይህ ጤናማና ንጹሕ ለመሆን ስለሚረዳ እንዲህ ማለታቸው ጥሩ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ [ኮንዶም] ያድሉንና ምንም ችግር ሳይደርስብን እንዴት የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንደምንችል ይነግሩናል።”
የእንዲህ ዓይነቱ የሥነ ምግባር ውጥንቅጥ ሰለባ አትሁን። መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን ጊዜ ያለፈበት መስሎ ሊታይ ቢችልም ለኤድስ በሽታ ሊያጋልጥህ ከሚችል ጠባይ እንድትርቅ አበክሮ ይመክርሃል። ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ ካከበርክ ደም በመውሰድ ኤድስ ሊይዝህ አይችልም። (ሥራ 15:29) ‘ዕፅ ከመውሰድ’ መታቀብ እንደሚገባ የሚያዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተከተል። እንዲህ ካደረግህ በተበከለ የዕፅ መውሰጃ መርፌ ሳቢያ በበሽታ እንዳትለከፍ የምትፈራበት ምክንያት አይኖርም። (ገላትያ 5:20፤ ራእይ 21:8፤ ዘ ኪንግደም ኢንተርሊንየር ) በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ሥነ ምግባር ሕግ ከዚህ ይጠብቅሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ሲል ያዛል። “ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” (1 ቆሮንቶስ 6:18) ኤድስ ያስከተለው ቀውስ እነዚህ ቃላት ጥበብ የተሞሉ መሆናቸውን ጎላ አድርጎ ያሳያል።
አንድ ወጣት ከጾታ ብልግና ‘መሸሽ’ የሚችለው እንዴት ነው? ለብዙ ዓመታት “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በተባለው ርዕስ ላይ በርካታ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮች ተሰጥተዋል። ከነዚህም ውስጥ በቡድን ሆኖ እንደመቀጣጠር፣ (ከተቃራኒ ጾታ ጋር ብቻ በአንድ ክፍል ውስጥ ወይም በቤት ውስጥ አለዚያም በቆመ መኪና ውስጥ ለብቻ መሆንን የመሰሉ) አሳፋሪ የብልግና ድርጊት ለመፈጸም የሚዳርጉ ሁኔታዎችን ማስወገድ፣ ለፍቅር መግለጫዎች ገደብ ማበጀት፣ (ብዙውን ጊዜ ማመዛዘን እንዳይቻል የሚያደርግ ስለሆነ) አልኮልን ከመጠቀም መታቀብና የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን ላለመፈጸም ቆራጥ አቋም መውሰድ ይገኙበታል።f በማንኛውም ሁኔታ ሥር ማንም ሰው ለአካላዊ ጉዳት ወደሚያጋልጥ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትንም ሊያበላሽ ወደሚችል ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ ግፊት እንዲያደርግብህ አትፍቀድለት። (ምሳሌ 5:9–14) በአንድ ኒውስዊክ ላይ በወጣ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰች አሚ የተባለች ወጣት “ሕይወታችሁ በሌላ ሰው እጅ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ ትፈልጋላችሁን?” በማለት ጠይቃለች። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከመጨረሷ በፊት ከወንድ ጓደኛዋ ኤች አይ ቪ ተላለፈባት። “ያ ልጅ ወይም ያቺ ልጅ ልትሞቱለት(ላት) የሚገባው(ት) ናቸውን? አይመስለኝም” በማለት ግልጽ የሆነ ጥያቄ አቅርባለች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ነሐሴ 22, 1993 በታተመው የእንግሊዝኛ ንቁ! እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ለኤድስ ተጋልጫለሁን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዶክተር ሲ ኤቨረት ኩፕ በዚህ ረገድ ጥርጣሬ ላላቸው ሰዎች እንዲህ በማለት መልስ ሰጥተዋል:- “በዚህ አገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤድስ መከሰቱ የተነገረው በ1981 ነው። ኤድስ ምንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ሳይፈጸም እንዲሁ በአጋጣሚ የሚተላለፍ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን እናውቅ ነበር።”
c ይህ በአፍና በፊንጢጣ በኩል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነትንም ይጨምራል።
d የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “ጆሮአችሁን ለመበሳት ከፈለጋችሁ . . . በአዲስ ወይም ንጹህና ከጀርሞች ነጻ በሆነ መሣሪያ ወደሚጠቀምና በቂ ችሎታ ወዳለው ሰው ሂዱ። ስለ መሣሪያው ለመጠየቅ አትፈሩ።”
e ኤፍ ዲ ኤ ኮንሲውመር የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ያብራራል:- “ኮንዶም የወንድን የጾታ ብልት ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ልባስ ነው። ከወንዱ አባላዘር የሚወጣው ፈሳሽ፣ ደምና ከሴቷ የጾታ ብልት የሚወጣ ፈሳሽ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው እንዳይተላለፍ እንደ አጥር ወይም ግድግዳ ሆኖ በማገልገል በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ይከላከላል።”
f ለምሳሌ በሚያዝያ 22, 1986፣ በሚያዝያ 22, 1989 እና በሚያዝያ 22, 1992 የእንግሊዝኛ ንቁ! እትሞች ላይ የወጡትን “የወጣቶች ጥያቄ . . .” ርዕሶች ተመልከት።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጾታ ጥያቄ እጅ መስጠት ወደ ኤድስ ሊመራ ይችላል