የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 10/8 ገጽ 3-6
  • የብቸኝነት ስሜት ስውሩ ሥቃይ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የብቸኝነት ስሜት ስውሩ ሥቃይ
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ብቸኝነት የሚሰማቸው ሴቶች
  • ብቸኝነት የሚሰማቸው ወንዶች
  • ብቸኝነት የሚሰማቸው ወጣቶች
  • ራስህን ማሻሻል ያስፈልግሃል
  • የቅርብ ጓደኛ አስፈላጊነት
  • የብቸኝነት ስሜት ሕይወትህን እንዲያጨልመው አትፍቀድለት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ጓደኛ የሌለኝ ለምንድን ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2004
  • የብቸኝነት ስሜት እንዲለቀኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1993
g93 10/8 ገጽ 3-6

የብቸኝነት ስሜት ስውሩ ሥቃይ

ከሕዝብ መሐል ለይተህ ልታውቃቸው ትችላለህን? ፊታቸው ላይ ይነበባልን? ሰላም ሲሉህ ፈገግታቸው ይሸፍንላቸዋልን? በአካሄዳቸውና በአቋቋማቸው ልታውቅባቸው ትችላለህን? በመናፈሻ ውስጥ ባለ አግዳሚ ላይ ብቻቸውን የተቀመጡ አዛውንት ወይም ብቻዋን ሆና የሥዕል ሙዚየም የምትጎበኝ አንድ ወጣት ተመልከት። እነዚህ ሰዎች በብቸኝነት እየተሠቃዩ ይሆን? ሦስት ትውልድ የሚወክሉት እናት ልጅና የልጅ ልጅ ሆነው በመንገድ ዳር በእግራቸው ሲንሸራሸሩ ልብ ብለህ እያቸው። ደስተኞች ይመስላሉ፤ ደስተኛ ለመሆናቸው ግን ምን ያህል እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ? የሥራ ባልደረቦችህን ተመልከታቸው። የሚያስቡላቸው ቤተሰቦች እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ ሊያኖራቸው የሚችል ገቢ ያላቸው ደስተኛ ሰዎች እንደሆኑ አድርገህ ትመለከታቸው ይሆናል። ሆኖም ከመካከላቸው አንዱ ከልቡ “ብቸኛ ነኝ” ይል ይሆን? እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ደስተኛና ንቁ የሆነ ወጣት በብቸኝነት ስሜት ለመጠቃት ያሉት አጋጣሚዎች ምን ያህል ናቸው?

ዌብስተርስ ኒው ኮሊጄት ዲክሽነሪ “የብቸኝነት ስሜት” የሚል ትርጉም ያለውን “ሎንሊነስ” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ሲተረጉመው “የመከፋትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያሳድር” ይለዋል። አንድ ነገር እንደጎደለህ የሚያሳይ ውስጣዊ የባዶነት ስሜት ነው። ይህ ስሜት በግለሰቡ ውጪያዊ መልክ ላይ ሁልጊዜ ላይታይ ይችላል። አንድ ተመራማሪ “በኅብረተሰባችን ውስጥ ብቸኝነት ደብቀን የምንይዘው ምሥጢር ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከራሳችንም እንደብቀዋለን። ብቸኝነት አንድ መጥፎ ስም ተሰጥቶታል። ብቸኛ የሆንከው በራስህ ጥፋት ነው የሚል ግምት አለ። ያንተው ጥፋት ባይሆን ኖሮ ብዙ ጓደኞች ይኖሩህ አልነበረም?” ብለዋል። በተለይ ከሌሎች ብዙ የምንጠብቅ ወይም የምንፈልግ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ይህ እውነት ሊሆን ይችላል።

ብቸኝነት የሚሰማቸው ሴቶች

ከወንዶች ይልቅ በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች በተለይ ባለ ትዳር ከሆኑ የተመቻቸ ኑሮ ለማግኘት ይፈልጋሉ በሚለው ሐሳብ ጠበብት የሚስማሙበት ይመስላል። ባሎቻቸው የሞቱባቸው፣ ከባሎቻቸው የተፋቱ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ነጠላ ሴቶች አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። ቤተሰብ ያላቸውና ደስተኞች የሚመስሉ ባለትዳር ሴቶችስ? ለምሳሌ 40 ዓመት የሆናት አንዲት መምህር በምሬት የተናገረችውን ተመልከት:– “ከጓደኞቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ የለም። በዚህም ምክንያት በጣም አዝናለሁ። እንዲህ ብሎ መናገሩ ራሱ ደግሞ ያሳፍረኛል። የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል ብዬ እንዴት ላማርር እችላለሁ . . .? በጣም ጥሩ ትዳር፣ ጎበዝ ልጆች፣ የሚያምር ቤት፣ የምወደው ሥራ አለኝ። እስካሁን በፈጸምኳቸው ነገሮች እኮራለሁ። ብቻ አንድ ነገር ይጎድለኛል።”

ምንም እንኳን ሴቶች ባሎቻቸውን ከልባቸው ቢወዱና ለባሎቻቸው ታማኝ ቢሆኑ፣ ባሎቻቸውም ለሚስቶቻቸው ይህንኑ ዓይነት ጠባይ ቢያሳዩም ይህ ዓይነቱ ፍቅር የሚያስፈልጋቸውን ጓደኝነት ሙሉ በሙሉ ሊያሟላላቸው ይችላል ማለት አይደለም። ከላይ የተጠቀሰችው መምህር እንዲህ በማለት አብራርታለች:– “ምንም እንኳን ባለቤቴ ከማንም የበለጠ የቅርብ ጓደኛዬ ቢሆንም ይህ ጥሩ የሴት ጓደኛ እንዳላፈራ አያደርገኝም። ወንዶች ይሰማሉ፤ ሴቶች ግን ያዳምጣሉ። ባለቤቴ በነገሩ ምን ያህል ተረብሼበት እንደነበረ ማወቅ አይፈልግም። ዘሎ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር በመሄድ ችግሩን ለመፍታት ይፈልጋል። ሴቶች ጓደኞቼ ግን ስለጉዳዩ ሳወራ ዝም ብለው ያዳምጡኛል። አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ማውራት ብቻ ሊሆን ይችላል።”

አንዲት ሴት የምትወደው ሰው ሲሞትባት ወይም ከባሏ ስትፋታ በጣም ትሸበር ይሆናል። ብቸኝነት ይይዛታል። በዚህ ጊዜ ባሏ የሞተባት ወይም ከባሏ የተፋታች ሴት ድጋፍ ለማግኘት ወደ ቤተሰቧና ወደ ጓደኞቿ ትሄዳለች። ይሁን እንጂ ራሷን ከአዲሱ እውነታ ጋር ለማለማመድ የራሷን ጥንካሬም መለስ ብላ ማየት ይኖርባታል። ምንም እንኳን ባሏን ማጣቷን ልትረሳው ባትችልም ለቀሪው ሕይወቷ እንቅፋት እንዲሆንባት ልትፈቅድለት እንደማይገባ መገንዘብ አለባት። ጠንካራ ባሕርያት ያሏቸው ሴቶች እነዚህ ባሕርያት ከሌሏቸው ሴቶች ይልቅ የብቸኝነት ስሜታቸውን ቶሎ ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ባለሞያዎች ደርሰውበታል።

ይበልጥ የተጎዳችው የትኛዋ ናት? ባሏ የሞተባት ወይስ የተፋታችው? በሚለው ላይ የሐሳብ ልዩነት አለ። 50 ፕላስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ከባሎቻቸው የተፋቱትን ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸው የሞቱባቸውን ወደምንረዳባቸው ቡድኖች በጠራናቸው ቁጥር ከሁለታችን ይበልጥ የተጎዳው ማን ነው? ብለው ይከራከራሉ። ባሏ የሞተባት ‘ቢያንስ ቢያንስ የትዳር ጓደኛሽ በሕይወት አለ’ ስትል ከባሏ የተፋታችው ደግሞ ‘አንቺ መች እንደኔ አልፈልግሽም ተባልሽ! አንቺ’ኮ አልሆነልኝም የሚል ስሜት አይሰማሽም’ ትላታለች።”

ብቸኝነት የሚሰማቸው ወንዶች

ብቸኝነትን በተመለከተ ወንዶች እኛ ከሴቶች እንሻላለን ብለው ጉራቸውን ሊነዙ አይችሉም። ጡረታ በወጡ አሜሪካውያን ማኅበር (አሜሪካን አሶሴሽን ኦቭ ሪታየርድ ፐርሰንስ) ውስጥ የትዳር ጓደኞቻቸው ለሞቱባቸው ሰዎች አገልግሎት የሚሰጠው ክፍል የፕሮግራም ስፔሻሊስት የሆኑት አን ስቱድነር “ወንዶች የሚገጥማቸውን ችግር ከስሜታዊ መንገድ ይበልጥ በአካላዊ መንገድ ይወጡታል። ሴቶች ስለ ጉዳዩ 10 ትሪልየን ጊዜ ደጋግመው ያወራሉ። ወንዶች ግን በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ የሞተችባቸውን ሚስት በሌላ ሴት ለመተካት ይሞክራሉ” ብለው ነበር። ወንድ አማካሪዎች ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ወንዶች የተሰማቸውን ስሜት ቀስ በቀስ መናገር እንዲጀምሩ ለማድረግ ረጅም ጊዜ ይፈጅባቸዋል።

ወንዶች ምሥጢራቸውን ለወንዶች ከሚነግሩ ይልቅ ለሴቶች ቢነግሩ እንደሚሻላቸው ባለሞያዎች ደርሰውበታል። ሴቶች ግን እንደዚያ አይደሉም። በሮቸስተር ዩኒቨርሲቲ ስለ ብቸኝነት ስሜት የሚያጠኑ ዶክተር ላድ ዊለር የተባሉ ባለሞያ፣ ወንዶች ከወንዶች ጋር ጥልቀት ባለው ስሜት ልብ ለልብ እንደማይቀራረቡ ገልጠዋል። “ሚስቶቻቸው ከሞቱባቸው በኋላ ከሚውጣቸው የብቸኝነት ስሜት ለመላቀቅና ከሴት ጓደኛ ጋር ለመግባባት የሚፈልጉ መሆናቸው ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የትዳር ጓደኞቻቸው በሞት ከተለዩአቸው ወይም ከተፋቱ በኋላ በቶሎ የሚያገቡበትን ምክንያት ለማስረዳትም ይረዳል።”​—50 ፕላስ የተባለው መጽሔት

ብቸኝነት የሚሰማቸው ወጣቶች

ልጆችና ጎልማሶች የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። እነዚህ ምክንያቶች ብዙውን ጊዜ ትልልቅ ሰዎች የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ከሚያደርጉት ምክንያቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ብቸኝነት እንዲሰማቸው አስተዋፅዖ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ጓደኞቻቸውን ትተው ወደ አዲስ አካባቢ መሄድ፣ በአዲሱ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ አብረዋቸው በሚማሩ ልጆች መጠላት፣ ባላቸው ሃይማኖትና በጎሳቸው የተነሣ የሚያጋጥማቸው ጥላቻ፣ በቤት ውስጥ ፍቺ ሲያጋጥማቸው፣ በወላጆች እንዳልተወደዱ ሆኖ ሲሰማቸውና በተቃራኒ ፆታ ዘንድ ተቀባይነት ማጣታቸው ጎላ ብለው የሚታዩት ናቸው።

ትንንሽ ልጆች አብሯቸው የሚጫወት ሰው ይፈልጋሉ። አይዟችሁ የሚላቸውና ችግራቸውን የሚረዳላቸው ሰው ይፈልጋሉ። እንዲወደዱና የሚፈለጉ ለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ሌሎች በታማኝነት ከጎናቸው የሚቆሙና እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ማወቅ አለባቸው። ሲወደዱ ስጋታቸው ይወገዳል፤ እንዲሁም ሌሎችን መውደድን ይማራሉ። እነዚህ ማኅበራዊ ድጋፎች ከተለያዩ ምንጮች ማለትም ከቤተሰብ፣ ከእኩዮቻቸው ሌላው ቀርቶ ከሚያሳድጓቸው እንስሳት ጭምር ሊመጡ ይችላሉ።

ከዝቅተኛ ክፍል አንሥቶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ በሆነ መጠን የብቸኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ብዙውን ጊዜ ብቸኝነት የሚሰማቸው በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ሳይኖራቸው ሲቀር ነው። አንዲት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ “ብቻዬን ስለሆንኩና ከማንም ጋር ስለማላወራ ይከፋኛል። አስተማሪውን አዳምጣለሁ፣ የተሰጠኝን ሥራ እሠራለሁ፣ በቃ። ነፃ ጊዜ ሲኖር እዚያው ተቀምጬ ስዕል እስላለሁ ወይም ሌላ ነገር አደርጋለሁ። ሁሉም እርስ በርሳቸው ያወራሉ፤ እኔን ግን የሚያናግረኝ የለም። . . . ለዘላለም ተደብቄ ልኖር እንደማልችል አውቃለሁ። አሁን ግን ያለሁበት ሁኔታ ይህን ይመስላል።”

ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ሌሎች ሰዎች ያገልሉኛል ወይም ይንቁኛል ብሎ ማሳበብ ትክክል አይደለም። አንድ ሰው የጠባይ ወይም ተግባብቶ የመኖር ችግር ይኖርበት ይሆናል። ለምሳሌ በጣም ዓይን አፋር፣ ግልፍተኛ፣ ችኩል አለዚያም ከእኩዮቹ ወይም ከእኩዮቿ ጋር የመግባባት ችግር ያለበት ወይም ያለባት ሊሆኑ ይችላሉ። አካለ ስንኩል መሆንም በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ጠንካሮችና ተግባቢዎች ካልሆኑ በስተቀር ብቸኝነት እንዲሰማቸው በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትልባቸዋል።

ራስህን ማሻሻል ያስፈልግሃል

በካሊፎርኒያ ግዛት በፉሌርቶን ከተማ የሚገኙ ዶሎርስ ዴልኮማ የተባሉ ስለ ጤና አጠባበቅ የሚያስተምሩ ሴት አንድ ሰው ብቸኝነትን እንዴት ሊቋቋመው እንደሚችል ሐሳብ ባቀረቡበት ጊዜ አንድ ቁልፍ ሐቅ ጠቁመዋል:- “ጥረቱ ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባዋል። ቀስ በቀስ ያለበትን ችግር መገንዘብ አለበት። ምክንያቱም ብቸኝነት የሚሰማውን ሰው ለመርዳት ሌሎች ሰዎች የቱንም ያህል ቢጥሩ የብቸኝነትን ቅርፊት ሰብሮ ለመውጣት የሚችለው ግለሰቡ ራሱ ነው።”

ለራሳቸው ማስተካከያዎች የማያደርጉትን ሰዎች ዶክተር ዋረን ጆንስ ወደ ብቸኝነት የሚያዘነብል ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይሏቸዋል። “እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሳይታወቃቸው ሌሎችን እንዳይቀርቡ የሚያግዷቸውን ነገሮች ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ ማዳመጥ አያውቁም። እኔ ብቻ ልናገር ይላሉ። ሌሎችን መተቸትና ራሳቸውን መውቀስ ይቀናቸዋል። ብዙ ጥያቄ አይጠይቁም፤ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ አስከፊ ወይም የሚያስቀይሙ ነገሮችን በመናገር ጓደኝነታቸው እንዲቋረጥ ያደርጋሉ።”

ለራሳቸው አክብሮት ከሚጎድላቸው ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች በተጨማሪ የመግባባት ችሎታ የሌላቸውም አሉ። አቭሊን ሞሼታ የተባሉ ሐኪም እንደነዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች አስመልክተው እንዲህ ይላሉ:- “የብቸኝነት ስሜት ያለባቸው ሰዎች ስለራሳቸው ጥሩ አመለካከት የላቸውም። ሰዎች ላይፈልጉኝ ይችላሉ በሚል ፍራቻ ከሌሎች ጋር ለመግባባት አይሞክሩም።”

ብዙ ሰዎች ካላቸው ግምት በተቃራኒ በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ይልቅ ወጣቶች በብቸኝነት ስሜት እንደሚሠቃዩ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ለምን እንደሆነ ግን እርግጠኞች አይደሉም። አረጋውያን በብቸኝነት ስሜት የሚሠቃዩት ዘመድ በማጣት ሳይሆን ጓደኛ በማጣት እንደሆነም ደርሰውበታል። “ይህ ማለት ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ዘመድ አይፈልጉም ማለት አይደለም። ከቤተሰቦቻቸው እርዳታ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። የሚረዳቸው ብዙ ዘመድ ኖሯቸው ጓደኞች ግን ባይኖራቸው የብቸኝነት ስሜት ይበልጥ ሊሰማቸው ይችላል።”

የቅርብ ጓደኛ አስፈላጊነት

በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ሊያሟሉላቸው የማይችሉትን አስፈላጊ ነገር የቅርብ ጓደኛቸው ያሟላላቸዋል። ሰዎች እንጎዳለን የሚል ፍርሃት ሳያድርባቸው ምሥጢራቸውን ወይም ማንነታቸውን ሁሉ ግልጽ አድርገው ሊነግሩት የሚችሉት ጓደኛ፣ ማለትም የቅርብ ጓደኛ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ከሌላቸው የብቸኝነት ስሜታቸው ሊያይል ይችላል። አሜሪካዊው ደራሲ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ‘አንድን ሰው ጓደኛዬ ነው የምለው እፊቱ ጮክ ብዬ ማሰብ የምችል ከሆነ ነው’ በማለት የጻፉት ስለ እንዲህ ዓይነቱ ጓደኛ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰው ምሥጢሬን ይዘከዝክብኛል ብለህ ሳትፈራ ወይም ምሥጢሬን ሰምቶ ይወቅሰኛል ወይም ለሌሎች ነገሮ ያስቅብኛል ብለህ ሳትሰጋ ማንነትህን ግልጥልጥ አድርገህ የምትነግረውና የምትተማመንበት ሰው ነው። ታማኝ ጓደኞቼ ናቸው ብለህ ትተማመንባቸው የነበሩ አንዳንዶች ሁልጊዜ እንደጠበቅሃቸው ሆነው ላይገኙ ቢችሉም ‘ምሥጢርን ለሌላ ሰው የማይገልጥ’ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋ” ‘ወዳጅም’ አለ።​—ምሳሌ 18:24፤ 25:9

ጠንካሮችና የማንም እርዳታ የማያስፈልጋቸው መስለው መታየት የሚወዱ ሰዎች አሉ። በራሳችን የምንመራና ራሳችንን የቻልን ነን ይላሉ። ይሁን እንጂ ጉልበተኞች ነን ከሚሉ ሰዎች ጋር ቡድን ይፈጥራሉ። ልጆች የራሳቸው ክበብ ያቋቁማሉ፤ አንድ ላይ የሚሰባሰቡበትም ቤት ይኖራቸዋል፤ ዱርዬዎች አንድ ላይ ይገጥማሉ። በዕድሜ ከፍ ያሉት ወጣቶች ደግሞ በሞተር ብስክሌት የሚንቀሳቀስ የዱርዬዎች ቡድን ያቋቁማሉ። ወንጀለኞች እነሱን የማይነቅፉ ጓደኞች ያበጃሉ። የመጠጥ ሱስ ያለባቸው የጠጪዎች ቡድን አባላት ይሆናሉ። ብዙ የመብላት ችግር ያለባቸው ደግሞ የክብደት መጠናቸውን የሚቆጣጠሩ ሰዎች ቡድን አባላት ይሆናሉ። ሰዎች አብረው መሆን ይወድዳሉ፤ ለመደጋገፍ ሲሉ በቡድን መልክ ይደራጃሉ። በችግራቸው ጊዜም ሰው አብሯቸው ቢሆን ይወዳሉ። በአጠቃላይ ሁሉም ሰው ብቸኛ መሆን አይወድም። ታዲያ ከብቸኝነት ስሜት ለመላቀቅ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ብቸኝነት የሚያጠቃቸው ሰዎች ስለ ራሳቸው ጥሩ አመለካከት የላቸውም”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ